Print this page
Saturday, 19 July 2014 12:55

ከአሜሪካ ተፅእኖ ለመላቀቅ ያለመው ጉባኤ!

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(0 votes)

የBRICS አገራት አዲስ የልማት ባንክ ሊያቋቁሙ ነው

 እንኳ ብዙ የጓጉለትን ዋንጫ ብሔራዊ ቡድናቸው በደረሰበት አሳፋሪ ሽንፈት የተነሳ ማግኘት ባይችሉም ምርጥ የዓለም ዋንጫ እንዳዘጋጁ የተነገረላቸው የብራዚሏ ፕሬዚዳንት ዴልማ ሩሴፍ ከዓለም ዋንጫው መጠናቀቅ በኋላም ማረፍ አልቻሉም፡፡
ያለፈውን ሳምንት ያሳለፉት ባለፈው ሰኞ የተካሄደውን የBRICS ሀገራት የመሪዎች ጉባኤንና ረቡዕ እለት የተካሄደውን የBRICS የላቲን አሜሪካ ሀገራት የመሪዎች ጉባኤን ለማዘጋጀት ከላይ ታች በመባተል ነበር፡፡
በሰሜናዊ ምስራቅ ብራዚል የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነችው በፎርታሊዛ ከተማ ሰኞ እለት በተካሄደው የBRICS ሀገራት ራሺያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሪዎቹ ከተወያዩባቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱና ዋነኛው “በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ መድረክ ከአሜሪካና በምዕራባውያን ከሚመሩ አለም አቀፋዊ የገንዘብ ተቋማት ተፅእኖ እንዴት መላቀቅ እንችላለን?” የሚለው ነበር፡፡
የአምስቱ ሀገራት መሪዎች በጉዳዩ ላይ ለረዥም ሰዓት ከተወያዩ በኋላ የራሳቸው የሆነ የልማት ባንክና የችግር ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ ለማቋቋም ተስማምተዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስምምነቱን በማስመልከት ሲናገሩ፤ “እነዚህን ሁለት የገንዘብ ተቋማት ማቋቋም ከቻልን አሜሪካና የአውሮፓ ተባባሪዎቿ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን በመጠቀም የሚያደርጉትን ተጽዕኖና እጅ ጥምዘዛ በደንብ መቋቋም እንችላለን።” ብለዋል፡፡
አምስቱ የBRICS ሀገራት መሪዎች ከአርጀንቲና፣ ከቺሊ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከኢኳዶር፣ ከቬንዙዌላና ከሌሎች የላቲን ሀገራት መሪዎች ጋር ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ጉባኤም ዋነኛው የውይይት አጀንዳ፤ አሜሪካ በላቲን አሜሪካ ያላትን ከፍተኛ ተፅእኖ መቋቋም የሚቻልበት ዘዴ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በብራዚል ዋና ከተማ ለአንድ ቀን የተካሄደውን ይህን ጉባኤ የተካፈሉ የሀገራት መሪዎች የስብሰባውን ጠቀሜታ የገለፁት ከየሀገሮቻቸው ጥቅምና አመለካከት በመነሳት ነው፡፡
የስብሰባው አዘጋጅና አስተናጋጅዋ የብራዚል ፕሬዚዳንት ዴልማ ሩሴፍ፤ “ጉባኤው ብራዚል ስለ BRICS ሀገራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለ ላቲን አሜሪካ ሀገራት ትስስርም ጭምር እንደምታስብ ለመሪዎቹ በትክክል ለማስረዳት መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላታል፡፡”
በማለት ሲናገሩ፤ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው፤ “ይህ ጉባኤ እንደ አሜሪካ የግል ጓሮ ተደርጎ በሚቆጠረው የላቲን አሜሪካ አህጉር ላይ ቻይና የራሷን ቦታ ለማግኘት ያደረገችውን አዲስ ጥረት በሚገባ ያመላከተ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ይሄው ጉባኤ አዲስ ለተመረጡት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፤ ራሳቸውን ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ አሪፍ መድረክ ሆኖላቸዋል፡፡ የኡክሬን ግዛት የነበረውን የክረሚያን አካባቢ ወደ ራሺያ ግዛት እንዲቀላቀል በማድረጋቸው ከዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ተገልለው ለቆዩት የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉባኤው ወደ መድረኩ ብቅ እንዲሉና ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር እንዲቀላቀሉ እድር ፈጥሮላቸዋል፡፡
የላቲን አሜሪካ ሀገራት መሪዎች ደግሞ ከBRICS ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠራቸው እነዚሁ ሀገራት ከሚያቋቁሙት አዲሱ የልማት ባንክ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን የሚል አዲስ ተስፋ መሰነቅ አስችሏቸዋል፡፡
የBRICS ሀገራት የሚያቋቁሙት አዲሱ የልማት ባንክ የሚመሰረተው በ50 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ሲሆን ይሄው ካፒታል ወደ 100 ቢሊዮን ዲላር ከፍ እንዲል ይደረጋል ተብሏል፡፡ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ ካፒታል ደግሞ 100 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል። የዚህ ባንክ ዋና ጽህፈት ቤትም በቻይናዋ ሻንሀይ ከተማ እንደሚሆን ታውቋል፡፡ 

Read 1785 times