Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 December 2011 09:55

ኢህአዴግ “የሥልጣን ጥማት የለብኝም” ብሎ ይማልልን!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አልጋ ይዤም ቢሆን ሥልጣን አለቅም - ሙጋቤ
አላህ ከፈቀደልኝ ቢሊዮን ዓመት ብገዛስ? - የጋምቢያ ፕሬዚዳንት

በርከት ያሉ ትላልቅ ፖለቲከኞች ናቸው - የኢትዮጵያ ሳይሆን የአሜሪካ፡፡ አንድ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሚካሄድ የልማት እንቅስቃሴ ለመጐብኘት በትልቅ አውቶብስ ይጓዛሉ፡፡ የሚበዛውን ርቀት አገባደው ወደ ስፍራው ለመድረስ ትንሽ ሲቀራቸው ሹፌሩ ምን እንደነካው አይታወቅም መንገዱን ስቶ ጉድባ ውስጥ ይገባና መኪናው ይገለበጣል - እነዚያን ሁሉ ፖለቲከኞች እንደጫነ፡፡ የግዛቱ ፖሊስ ሲደርስ ለምስክርነት ቆሞ የተገኘው አንድ የአካባቢው ገበሬ ብቻ ነበር፡፡ አውቶብሱ እንደተገለበጠ ቢሆንም አንድም ፖለቲከኛ (የሞተም የቆሰለም) በአካባቢው አልተገኘም፡፡ አውቶብሱም ባዶውን ነው፡፡ ፖሊሱ ግራ ተጋብቶ ገበሬውን ጠየቀ:-

“ሰዎቹስ… ፖለቲከኞቹስ… የት ገቡ?”

“እያየኸው!” አለ ገበሬው - ጐማዎቹን ሰቅሎ ወደተገለበጠው አውቶብስ እየጠቆመው

“እሱንማ አየሁት” አለ ፖሊስ፤ ገበሬውን በጥርጣሬ እየተመለከተ

“ያው እዛ ቀብሬአቸዋለሁ” ገበሬው ቁልል አፈር እያሳየ መለሰ፡፡

“አንድም የተረፈ የለም?” ፖሊሱ ደንግጦ ጠየቀ

“ጥቂቶቹ እያቃሰቱ ነበር”

“እና … የት ወሰድካቸው?” እየተቅበጠበጠ ጠየቀ - ፖሊስ

“ያው የፖለቲከኞችን ዋሾነት ታውቀው የለ … ሲያብሉ ነው እንጂ ሞተዋል ብዬ አብሬ ቀበርኳቸው” አለ ገበሬው ዘና ብሎ፡፡

ፖሊሱ ከዚህ በኋላ ምንም  መናገር አልቻለም፡በእርግጥ ፖለቲከኞች (የእኛ ሳይሆን የአሜሪካ) ዋሾ መሆናቸውን አንክድም፡፡ ሆኖም ግን “ኧረ አልሞትንም” እያሉ እንደለመዱት ሲዋሹ ነው ብሎ ከሞቱት ጋር መቅበር በዓለምአቀፉ ፍ/ቤት የሚያስከስስ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከ40 ዓመት በላይ ህዝባቸውን ሲረግጡ፣ ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የከረሙት የሊቢያው ጋዳፊ የግድያ ጉዳይ እንኳን በዓለምአቀፉ ፍ/ቤት የሚያስጠይቅ እንደሆነ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ ምነው ቢባል… በ21ኛው ክ/ዘመን “ዓይን ያወጣ ዓይኑ ይውጣ” የሚለው የጥንት ህግ አይሰራማ! (ሰልጥነን የለ እንዴ?) እንግዲህ እስከዛሬ ለፖለቲካ ችግሮች ፕሮፖዛል እያቀረብን ነበር፡፡ አንዳንድ አንባቢያን ግን የሃሜት ትውፊታችን እንዳይጠፋ የሚል ስጋት ስላሳደረባቸውና እኔም ሃሳባቸውን ስለምጋራ ለዛሬ ፕሮፖዛል ሳይሆን የፖለቲካ ሃሜት እንድናማ ፈቅጄአለሁ፡፡ በአንባቢ ምርጫ ወይም ጥያቄ ማለት ነው (እንደ ኢቴቪ) ሃሜቱን የምንጧጡፈው ያለ ያለ ቡና በመሆኑ ግን ትልቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ሃሜታችን ከዚምባቡዌ ነው የሚነሳው፡፡

በፕሮስቴት ካንሰር ታመው ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙት የ87 ዓመቱ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ የጤናቸው ነገር አስተማማኝ ባይሆንም አልጋ ይዤም ቢሆን አገሬን እመራለሁ እንጂ ስልጣን ብሞት አለቅም ብለዋል (ፅናታቸው ይደነቃል!) እናም በሚቀጥለው ዓመት በአገራቸው ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከወዲሁ ዝግጅቱን አጣጡፈዋል - አዛውንቱ ሙጋቤ፡፡ እርጅና የተጫጫናቸው ሙጋቤ በቀጣዩ ምርጫ ያተኮሩት ወጣቶች ላይ ነው ይባላል፡፡ ግን የወጣቱን ትውልድ ህይወት ለማሻሻል ምናምን እንዳይመስላችሁ … እሳቸው እንዲህ ያለ ዋዛ ፈዛዛ አያውቁም፡፡ የእሳቸው ዓላማ የወጣቱን ትኩረት በመሳብ ድምፅ እንዲሰጣቸውና እንዳለሙት ከዘራ ይዘው ወይም ከሆስፒታል አልጋ ላይም ቢሆን ዚምባቡዌን ለመግዛት እንዲችሉ  ነው፡፡ (በድዴም ቢሆን እገዛለሁ ብለዋላ!) እናም ምስላቸውንና ፊርማቸውን በተለያዩ ልብሶች ላይ እያተመ ለሽያጭ የሚያቀርብ አዲስ ፋብሪካ ተቋቁሟል፡ አልባሳቱ ዘመናዊና ምቾት ያላቸው ሲሆኑ የዚምባቡዌ ወጣቶችን (ወንዱንም ሴቱንም) የሚማርኩ ተደርገው የተፈበረኩ ናቸው ተብሏል፡፡ ቲ-ሸርቶች፣ ኮፍያዎችና  የሴቶች አልባሳት የሙጋቤ ምስልና ፊርማ እየታተመባቸው በሃረሬ እየተሸጡ ሲሆን ገበያ እንደደራላቸውም ተዘግቧል፡ ራሳቸው ሙጋቤም የእሳቸው ምስል ያለባቸው ሸሚዞችና ባርኔጣዎች ጥሩ ገበያ ይኖራቸዋል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አልባሳት ወጣቶችን ያለሙ እንደመሆናቸው መጠን ገበያው ደራላቸው ማለት ሙጋቤ በቀጣዩ ምርጫ በወጣቶች የመመረጣቸውን ዕድል የላቀ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ እናም እንደ ቅድመ-ምርጫ ግምት መሰብሰቢያ (Opinion poll) ሊቆጠሩም ይችላሉ፡፡

እስቲ እንደው እስከዛሬ የምታውቋቸውን አምባገነን መሪዎች ባህሪ ለአፍታ መርምሩት፡፡ አብዛኛዎቹ አንድ የጋራ ባህሪይ ያላቸው ይመስላሉ - ካልደረሰብን አናምን ዓይነት፡ እንግዲህ በአንድ ዓመት ውስጥ ከዚህችው አህጉር ሦስት አምባገነኖች በህዝብ ትዕዛዝ ከቤተመንግስት ተገፍትረው ወጥተዋል፡፡ መቼም ይሄን ያየ መሪ (የፈለገውን ያህል አምባገነን ቢሆን) ምርጫ ያጭበረብራል ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባት ህዝቡን ይለማመጥ ይሆናል እንጂ - “ጥቂት የስልጣን ዘመን በፈቃዳችሁ ጨምሩልኝ” በማለት፡፡

ግን በቅርቡ በሁለት የአፍሪካ አገራት የተደረጉ ምርጫዎች በገዢ ፓርቲዎች መጭበርበራቸው ተደምጧል - በጋምቢያና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ፡፡

እንግሊዝ በ400 ዓመት የቅኝ ግዛት ዘመንዋ ለአገሪቱ ያልሰራቻቸውን ልማቶች እኔ በ17 ዓመት አከናውኛለሁ የሚሉት የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ፤ “ዓላህ ከፈቀደ ቢሊዮን ዓመት ብገዛስ” ሲሉ ተፈጥመዋል፡ አያችሁልኝ … እንዲህ ናቸው የአፍሪካ አምባገነኖች - ካልደረሰብን ፈፅሞ አናምን የሚሉ!! አምና በምዕራብ አፍሪካ አገራት የታዩት ህዝባዊ አመፆች (ሱናሜዎች) እነሙጋቤ ቤት የሚደርስ አይመስላቸውም፡፡ አልገባቸውም እንጂ ሱናሜው አንዴ ከተነሳ ማቆምያም የለው! (ይኸው ለሶርያና ለየመን ተርፎ የለ!)

ይሄን ያህል የአፍሪካ አገራትን ካማን ይበቃናል፡፡ ወደገዛ ጓዳችን ገብተን ደግሞ እርስ በርስ ትንሽ እንተማማ፡፡

ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ የፊት ሽፋን ላይ የወጡት የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ መሪ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የሰጡትን ቃለ ምልልስ በጥሞና አነበብኩት፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከሆነ ታዲያ ኢህአዴግ ከ20 እስከ 30 ዓመት ሥልጣን ላይ የመቆየት ዕቅድ አለው፡፡ የኢህአዴግን የሥልጣን ፍላጐት ከሌሎቹ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች የሚለየው አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ “የነጋሶ መንገድ” በሚለው መፅሃፍ ላይ በዝርዝር እንደነገሩን፤ ኢህአዴግ 30 ዓመት ያለተቀናቃኝ እቺን አገር መግዛት የሚመኘው የሥልጣን ጥሙ ስላልቆረጠለት አይደለም፡፡ ትልቅ አገራዊ ራዕይ ስላለው ብቻ ነው፡፡ ምንድነው ይሄ አገራዊ ራዕይ ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ማሰለፍ፡፡ ይሄን ህልሙን እውን ለማድረግ ደግሞ ከኢህአዴግ ከራሱ ውጭ አቅሙም ችሎታውም ያለው ፓርቲ የለም! (እኔ ሳልሆን ኢህአዴግ ነው ያለው!) ስለዚህ ፓርቲው ጥሮ ግሮ አገሪቱን እዛ ደረጃ ካደረሰ በኋላ ሥልጣኑን ለባለተረኞች ይለቃል ማለት ነው (ይሄ እንኳን የኔ ግምት ነው) ለምን መሰላችሁ? የኢህአዴግ ህልም ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ መሟዘዝ ሳይሆን አገሪቱን ለቁም ነገር ማብቃት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ኮትኩቶ፣ አሳድጐና አስተምሮ ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ይድራታል - ያኔ የአባትነት ሚናው ያበቃል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ለ30 ዓመት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ምክንያት በጥርጣሬ ቢመለከቱት ልንፈርድባቸዉ አንችልም፡፡ ለምን ቢባል … አንዳንድ ካድሬዎች “17 ዓመት የታገልነው ለተቃዋሚዎች ስልጣን ለመስጠት አይደለም!” ብለው ሲነጫነጩ ሰምተው ሊሆን ይችላል፡፡ እንደኔ እምነት ግን ኢህአዴግ አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ካሰለፈልን በኋላ “አገሪቷን በኢኮኖሚ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ 30 ዓመት የታገልኩት (የኢኮኖሚ ትግል) ለተቃዋሚዎች ስልጣን ለመስጠት አይደለም” ብሎ ሙጭጭ የሚል አይመስለኝም፡ አያድርገውና ሙጭጭ ቢልስ? … ምን ይደረጋል? እንባችንን ወደ ላይ ረጭተን ከማዘን በቀር!! ህዝብ ያዘነበት ፓርቲ ደሞ ምን እንደሚሆን በዓይናችን በብሌኑ አይተናል፡ አይወድቁ አወዳደቅ ይወድቃል፡፡

እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… ይሄን በጀብደኝነት የተሞላ የሚመስል የኢህአዴግ ምኞት (የሥልጣኑን ማለቴ ነው) ብዙም አልጠላውም፡፡ ትንሽ የማይመቸኝ …  እቺ አገር ያለ እኔ ትፈራርሳለች … (ኢትዮጵያ ያለ ኢህአዴግም ኖራለች እኮ!) እቺን አገር መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ተርታ እስከማሰልፍ ዓይኔ ተቃዋሚዎችን እንዳያይ! ዓይነት አካሄዱ ብቻ ነው፡፡ ለሌላ አይደለም፤ ሳያውቀው የአምባገነኖች ሃዲድ ላይ እንዳይወጣ ስለምሰጋ ነው፡፡

የቀድሞው የኢህአዴግ አባልና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደ እጃቸው መዳፍ አብጠርጥረው የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ ከ40 ዓመት ያላነሰ በፖለቲካውም ውስጥ ኖረውበታል - ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኢህአዴግን እስካስበረገገው የቅንጅት አብዮት፡፡ “የነጋሶ መንገድ” በሚለው አስደማሚ መፅሃፋቸው ውስጥ እንደሚነግሩን ግን ኢህአዴግ 10 ዓመት ሙሉ አታሎዋቸዋል - እሳቸው ሶሻሊዝም ነው ብለው ሲከተሉት ነጭ ካፒታሊዝም ተከታይ ሆኖ አግኝተውታል፡፡

ነጋሶ በዚህ ተቀይመው ከወጡ በኋላ ግን “ብልጦ” ኢህአዴግ በክፉ ጊዜ መሳቢያ ውስጥ ደብቄዋለሁ ያለውን ሶሻሊዝምን ጐትቶ አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ ጉብ አድርጐታል፡ ፕሬዚዳንቱን ለሁለተኛ ጊዜ አልሸወዳቸውም ትላላችሁ? ግን ደሞ እሳቸው የተሻለ አግኝቻለሁ ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ቃለ ምልልስ ላይ በኢህአዴግ ሳሉ ከነበራቸው የአገር ፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ይልቅ አሁን ያላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ሥልጣን እንደሚመርጡ ተናግረዋል (ኢህአዴግ እንዴት ይበሽቅ!)

እቺ 30 ዓመት ሥልጣን ላይ የመቆየት የኢህአዴግ ዕቅድን በተመለከተ ብዙ ሃሳቦችን ሳወጣ ሳወርድ ቆየሁና ከሃሜት ወጣ ብዬ አንድ ፕሮፖዛል የማርቀቅ ሃሳብ መጣልኝ፡፡ እውነት ኢህአዴግ ሥልጣኑን የሚፈልገው አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ብቻ ከሆነና ልዩ የሥልጣን ጥማት ከሌለበት (በፖለቲካ ሃኪሞች ተመርምሮ መረጋገጥ አለበት) ህዝቡ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ቢፈቅድለትስ? የምትል ናት - ፕሮፖዛሏ፡፡ ግን ደግሞ በኋላ ላይ እንደ ዶ/ር ነጋሶ “ተሸወድን” ብለን እንዳንፀፀት ቅድመ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ቅድመ ጥንቃቄው ምን መሰላችሁ? መሃላ! አዎ ኢህአዴግ የሥልጣን ጥም የለብኝም ብሎ ይማልልን፡፡ መሃላውን ካደረገ በኋላ የምንጠራጠረው ነገር አይኖርም፡፡

ይህችን የፕሮፖዛል ሃሳብ ያጫወትኩት “ፖለቲካ አዋቂ ነኝ” ባይ ወዳጄ ግን እንዲህ አለኝ:- “በ30 ዓመት ውስጥ አገሪቱ የተባለው የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ባትደርስስ?” ወዳጄ አናደደኝና “ጨለምተኛ!” አልኩት፡፡ ኢህአዴግን ለመፎተት ሳይሆን ከምሬ ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ እንኳን ኢህአዴግ ሰይጣንም የኢኮኖሚ ዕድገት አመጣለሁ ካለ በጭፍን የመቃወም አዝማሚያ የለኝም፡፡ በ2002 አገራዊ ምርጫ ወቅት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ከኢህአዴግ ጋር ተፈራርመው “ታሪካዊ” የመጨባበጥ ሥነ ስርዓት ባካሄዱ ጊዜ ከየአቅጣጫው ለተሰነዘረባቸው ነቀፌታ “እኛ ለሰላም እስከሆነ ድረስ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እንጨባበጣለን” ያሉ ይመስለኛል (ካልተሳሳትኩ) እኔም ለዚህ ነው ሰይጣንም እንኳ ቢሆን የኢኮኖሚ ዕድገት አመጣለሁ ካለ አልቃወመውም የሚል አቋም ይዤ ወዳጄን የተቃወምኩት፡፡ ወዳጄ ግን ለጊዜውም ቢሆን የማይረታበት መከራከርያ ነጥብ አመጣብኝ፡፡

“ኢህአዴግን በምንድነው የምታስምለው?” ሲል ጠየቀኝ

“እንዴት? አልገባኝም!” አልኩት - ከምርም ስላልገባኝ ነበር፡፡

“ኢህአዴግ እኮ ኮሙኒስት ነበር … አሁንም ቢሆን አለየለትም” ሲል መለሰልኝ፡፡ አሁን በዝምታ ተውጬ ቀረሁኝ፡፡ እውነት ኢህአዴግ ግን ምንድነው? ራሱስ ያውቀው ይሆን?  ምን ገረመኝ መሰላችሁ… የኢኮኖሚ ዕድገት እስከሆነ ድረስ ከሰይጣንም እንኳ ቢመጣ አልቃወምም ያልኩት ሰውዬ ኮሙኒስት ስባል ጭጭ አልኩ፡፡ ኮሙኒስት ከሰይጣን ይብሳል ማለት ነው? እኔጃ!!!

 

 

 

Read 3940 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 10:01