Tuesday, 29 July 2014 14:35

የፀረ-ሽብር ህጉ አሁንም ማወዛገቡን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ተቃዋሚዎች በአተገባበሩ ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ይላሉ
የፀረ-ሽብር ህጉ የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ መውጣቱን ተከትሎ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና  ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ተከሰው መታሰራቸው በህጉ ላይ የከረረ ተቃውሞ የሚሰነዝሩ ወገኖች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አንድነት ፓርቲ መቃወም ብቻም ሳይሆን ህጉ ከእነአካቴው እንዲሰረዝ “የሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት” በሚል ባደረገው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ያቀደውን ያህል ድምፅ ማግኘቱን ጠቁሞ  ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው መግለፁ አይዘነጋም፡፡
የፀረ-ሽብር ህጉ አወዛጋቢነት በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤የፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች መታሰርን በመቃወም መንግስት ህጉን፣ተቺዎቹን ለማጥቂያነት እየተጠቀመበት ነው በማለት ይኮንናሉ፡፡   
 የግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የመን ላይ ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግስት መተላለፋቸውን ተከትሎ አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ተይዘው መታሰራቸው (በሽብርተኝነት የተከሰሱትን  ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ጨምሮ) በብዙዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል፡፡ ፓርቲዎቹም የፖለቲከኞቹን መታሰር  በመቃወም መግለጫዎች አውጥተዋል፡፡ ለመሆኑ በሽብር ወንጀል እየተጠረጠሩ የሚታሰሩ ዜጐች መበራከት በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ምን አንደምታ ይኖረው ይሆን? በቀጣይስ ሀገሪቷን ወዴት ይመራታል? በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲ አመራሮችና የህግ ባለሙያዎች የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


“በኢትዮጵያ ሽብርተኛ ማለት ነፃነትን መሻት፣ እውነትን መፈለግ ነው”
(ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ሽብርና ሽብርተኝነት አሁን በኢትዮጵያ ባለው ግንዛቤ፤ እውነት ለሚናገሩ፣ለህብረተሰቡ መብት መከበር ለሚቆሙ፣ መንግስትን አምርረው ለሚተቹ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው፡፡ በየጊዜው ሽብርተኛ እየተባሉ የሚታሠሩት የማህበረሰብ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሽብርተኛ ማለት  ነፃነትን መሻት፣ እውነትን መፈለግና  መንግስትን መተቸት ሆኗል፡፡
መንግስት ሰዎችን በብዛት ማሰሩ አቅመቢስ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል፡፡ የህዝብ ጥያቄ እያሸነፈ መንግስት  ተቀባይነት እያጣ ሲመጣ ነው ሁሉን ነገር በጉልበት ለማድረግ የሚፈልገው፡፡ በአንፃሩ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች በታሰሩ ቁጥር የነፃነት ትግሉ እየተፋፋመ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ በዚህ ረገድ እኔ ብሩህ ተስፋ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም ለእውነት ብለው ለመታሰር የሚደፍሩ ሰዎች (እነ አንዷለም ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ) እየበዙ ነው፡፡ ለመታሰር ዝግጁ የሆኑ ሰዎች በዙ ማለት ወደ ለውጥ መቅረባችንን ያመለክተናል፡፡


አዋጁ በአግባቡ እየተተረጐመ አይደለም”
ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የኢዴፓ ሊቀመንበር)


በአጠቃላይ መንግስት እየተከተለ ያለው አካሄድ ለዲሞክራሲ ግንባታው በጣም እንቅፋት እየፈጠረ ነው፡፡ በተለይ የፀረ ሽብር አዋጅን በተመለከተ የአተረጓጐም ስህተት እየተከተለ ነው የሚል ግንዛቤ አለን፡፡
የፀረ ሽብር ህግ ቢያስፈልገንም አተረጓጐሙ ግን በአግባቡ መሄድ አለበት፡፡ መንግስት የራሱን ጥቅም ለማስከበርና የገዥውን ፓርቲ እድሜ ለማራዘም ብቻ የተናገረውንም፣ ጦር ይዤ እታገላለሁ የሚለውንም፣ የሚጽፍበትንም--- በአጠቃላይ ገዥውን ፓርቲ የማይደግፈውን  ሁሉ በሽብር ስም ማሠሩ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡
ይሄ አጠቃላይ የዲሞክራሲ ሂደቱን የሚያስተጓጉል ሲሆን የህብረተሰቡንም መብት የሚጫን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹንም አካሄድ ሊያበላሽ የሚችል፤ ወደ ኋላ እየመለሰን ያለ አካሄድ እንደሆነ ኢዴፓ ያምናል፡፡
ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታ ምንም አይነት ቁርጠኝነት እያሳየ አለመሆኑን እንዲሁም  የስርአት ለውጥ በተጨባጭ ከምርጫ ሳጥን እንዳይገኝ፣ መጪውን ምርጫ ለማበላሸት እየተከተለው ያለው መንገድ ነው ብለን እናምናለን፡፡
የኛ ፓርቲ ብሔራዊ መግባባትን እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ መንግስት ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ሲባል “የተጣላ ሰው የለም፤ማንን ከማን ለማግባባት ነው” የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ቆም ብሎ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለበት፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች መንግስትን ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የምንጠይቅበትን አካሄድ በጋራ መፈለግ ይገባናል። አለበለዚያ ለህዝባችን ምንም ነገር ሳንሰራ፣ የቆምንለትን አላማ ሳናሳካ እንዲሁ ዝም ብለን ጊዜ መፍጀት ይሆናል፡፡
በፀረ ሽብር ህጉም ላይ ቢሆን የጋራ ግንዛቤና መግባባት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ህጉ በጣም አስፈላጊ ነው፤ በአተረጓጐሙ ዙሪያ ግን የጋራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሲረቀቅ ጀምረን እስካሁን በአተረጓጐሙ ላይ ተቃውሟችንን ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ በህጉ አተረጓጐም ላይ የጋራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተቃራኒ ሃሳብን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ቁጭ ብለን መግባባት ይኖርብናል፡፡


 “ሽብርተኛ ስለመሆናቸው መንግስት ተጨባጭ ማስረጃ አያቀርብም”

(አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ የመድረክ አመራር)


በሠላማዊ ትግሉና ሠላማዊ ታጋዮች ላይ በሽብርተኝነት ስም የሚወሰዱት እርምጃዎች፣ሽብርተኝነት የሚለውን ስያሜ በአግባቡ እንዳንረዳ እያደረገን ነው ያለው፡፡ ሽብርተኝነት ሲባል በአለማቀፍ ደረጃ የታወቁ ነገሮች አሉ፡፡ አሸባሪዎች በሃይል አስፈራርተው የራሳቸውን ፖሊሲና አማራጭ ሌላው እንዲከተል በማድረግ፣ “ይሄን ባታደርግ እንዲህ አደርጋለሁ” የሚሉ ናቸው፡፡ መድረክም ይህን መሰሉን ድርጊት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ አሁን በኛ ሀገር እነዚህ አሸባሪ ተብለው የሚወነጀሉ ሰዎች ይሄንን አድርገዋል ወይ? ማንን ነው ያስገደዱት? ማንን ነው ያስፈራሩት? በማን ላይ ነው እርምጃ የወሰዱት? በሚለው ላይ መንግስት በተጨባጭ ማስረጃ አያቀርብም፡፡ በዚህም ሳቢያ እኛም አሸባሪ ስለመሆናቸው ምንም ልንገነዘብ አልቻልንም፡፡ ጭራሽ አሸባሪ በሚለው ጉዳይ ላይ ግራ እንድንጋባ እየሆንን ነው፡፡ ሽብርተኝነት የሚለው በራሱ ግልጽነት ይጐድለዋል፡፡
መንግስት የሽብርተኝነትን ትርጓሜ ጥርት አድርጐ ባለማስቀመጡ፣ ህጉን ሠላማዊ ሰዎችን ለማስፈራሪያነት እየተጠቀመበት ነው የሚል ስጋት አለን፡፡ የሽብር ክሶችና እስራት እየተጠናከረ መቀጠሉ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ፤ ለማሸማቀቅና የፍርሃት ድባብን ህዝብ ላይ ለመጫን ነው፡፡ ህዝብ በፍርሃትና በመሸማቀቅ የተሣተፈበት ምርጫ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ሰው ተደፋፍሮ ከውስጡ መሸማቀቅና ፍራቻን እንዲያስወግድ ከተፈለገ፣ አሸባሪን ከሰላማዊ ትግል የሚለይ ነገር መቀመጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ አሁን የተያዘው የሽብርተኝነት ግንዛቤ በምርጫም ሆነ በፖለቲካ ሠላማዊ ትግል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ግንዛቤውን ለማጥራትም ሆነ ችግሩን ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል። ሽብርተኝነት ምንድን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሽብርተኝነትን እንዴት በጋራ እንታገል በሚለው ላይም በተመሳሳይ የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ ብሔራዊ መግባባት ካለ የሽብር አደጋዎችን ሁሉ መከላከል እንችላለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የውይይት በሮችን ሁሉ መዝጋቱን ትቶ፣ ተቃዋሚዎችን እንደጠላት መመልከቱን አቁሞ፣ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን የውይይት መድረክ ሊያመቻች  ይገባዋል፡፡

===========
“አዋጁ የምርጫ 97 ውጤት ነው”
(ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ የአንድነት ሊቀመንበር)

ፓርቲዬ አንድነት የፀረ - ሽብር አዋጁ፤ የዲሞክራሲ ሂደቱን የማፈን ጥረት ውጤት ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ መሠረት በ“የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት” ላይ በዋናነት የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ጠይቀናል፡፡ ህጉ ከየት መጣ ብለን ከጠየቅን፣የምርጫ 97 ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኢህአዴግ በነፃ ምርጫ ማሸነፍ እንደማይችል ሲረዳ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን የማፈን እንቅስቃሴ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ሚዲያዎችን፣ ፓርቲዎችን፣ሲቪል ማህበራትን ማፈን የሚለውን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ስለፈለገ፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ አዋጅ አውጥቶበታል፡፡ ስለዚህ የፀረ ሽብር ህጉም የዲሞክራሲ ስርአቱን ሙሉ ለሙሉ ለማዳፈን የወጣ ነው ብለን እናምናለን፡፡
እኛ የፀረ ሽብር ህጉ መሠረዝ አለበት ስንል፣ ሽብርተኝነትን እንደግፋለን ማለት አይደለም፡፡ ከማንም በላይ ሽብር ለሃገራችን አስጊ ነው በሚል እምነት፣ ፓርቲዬም ሆነ እኔ ከመንግስት ጐን ተሠልፈን የምንዋጋው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን  ያለው አዋጅ እየተተረጐመበት ባለው አግባብ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ አለን፡፡
ሚዲያው አካባቢ ሲኬድ በከፍተኛ ሁኔታ ራሱን በራሱ የሚገድብ (Self censorship) ሆኗል። ሲቪል ሶሳይቲውም የኢህአዴግን ቡራኬ ካላገኘ መኖር አይችልም፡፡ ይሄ ዲሞክራሲውን በእጅጉ ይጐዳል፡፡
ኢህአዴግ ኳሱ በእጁ ነው፡፡ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ የሆነ ቦታ መቆማቸውም አይቀርም፡፡
ስለዚህ ዲሞክራሲው እንዳይቀጭጭ፣ እንዳይጐዳ ኳሱን በእጁ የያዘው ኢህአዴግ ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ የዲሞክራሲ ሂደቱ በሚፈቅደው መጠንም ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ መድረኩንም መፍጠር አለበት፡፡ እኛ በዚህ አዋጅ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፍትህና በዲሞክራሲያዊ ስርአቱ ላይ ከብሔራዊ መግባባት የሚያደርስ ውይይት እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ብሔራዊ መግባባት መኖር አለበት፡፡   


“ህጉ ለኛ አስፈላጊ ነው ወይ?”

(አቶ ተማም አባቡልጉ፤ ጠበቃና የህግ አማካሪ)

ብዙ ሰው ህጉ በአግባቡ መተርጐም አለበት በሚለው ላይ ነው ጥያቄ የሚያነሳው፡፡ እኔ ደግሞ ህጉ ለኛ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለውን ነው የምጠይቀው፡፡ ህጉ ላይ የተጠቀሱት ነገሮች እኮ በወንጀለኛ ህጉ ላይ አሉ፡፡ እንደገና በሌላ መልክ መምጣታቸው አግባብ አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚከሰሱ ሰዎችን ስንመለከት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር “ህጉ ለማጥቂያነት አልዋለምን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የሽብር አዋጅ በየትኛው ዓለም ቢሆን በአገር ላይ የሚደርስን ጥቃት  የሚከላከል እንጂ ፓርቲን፣ ጋዜጣንና ሃሳብን በነፃነት መግለጽን አይደለም መገደብ ያለበት፡፡ ለምሣሌ ሩዋንዳ በህጓ ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን በተመለከተ፣ ቀጥታ የጅምላ ጭፍጨፋን የሚያነሳሱ ሃሳቦችን ለይታ ነው ገደብ ያበጀችው፡፡ የኛ ግን ጥቅል ነው፡፡ ይሄን አይመለከትም ተብሎ ተለይቶ መቀመጥ አለበት። በእንግሊዝ ሀገር ህጉ ሲወጣ ፖለቲከኞች “አንዴ ስልጣን ላይ የወጣው መንግስት ስልጣን እንዳይለቅ የማድረጊያ መንገድ ሆኗል” ብለው ነው ህጉን ኋላ ላይ ያስቀሩት፡፡ ስለዚህ በኛም ሃገር ህጉ ለፖለቲካ ማጥቂያ አይውልም ተብሎ አይታሰብም፡፡

Read 5618 times