Wednesday, 30 July 2014 07:38

“ባዝኦፍ፤ ወባን የመከላከል ውጤታማነቱ 90 በመቶ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሌሊት አጎበር ስላለ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን አዘዋውራለች
(አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ የባዝኦፍ አምራች ኩባንያ መስራችና ዳይሬክተር)
በሙያቸው አካውንታንት የሆኑት አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ በ1964 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ተቀጥረው በሙያቸው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ በውሃና ፍሳሽ፣ በኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ድርጅትና በብረታ ብረት ኮርፖሬሽን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን በ1981 ዓ.ም ወደ ኬኒያ በማምራት የኢምፖርት ኤክስፖርት ስራ ላይ ከመሰማራታቸውም በተጨማሪ ባርና ሬስቶራንት በመክፈት ለረጅም አመታት መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡ አንበሳ ባንክና ኢንሹራንስን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ገዛኢ፤ ከ10 ዓመት በፊት ከውጭ ተመልሰው በአገራቸው መኖር ሲጀምሩ፣ ወባ በአገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት መመልከታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ወባ በአፍሪካ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ ጥናት ሰርተውም ለአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ IFF በመስጠት ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ በለገጣፎ አካባቢ “ባዝኦፍ” የተሰኘ የወባ ትንኝ ማባረሪያ መድኀኒት በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በመድኀኒቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ገዛኢ አምባዬ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡


“ባዝኦፍ” የተባለውን የወባ ማባረሪያ ቅባት እንዴት ሊያመርቱ ተነሱ?
እኔ በ1981 ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ ሄጄ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወይንና አምቦ ውሃ እየወሰድኩ ለኬኒያ፣ ለሩዋንዳ ለኡጋንዳና ብሩንዲ አከፋፍል ነበር። ኬኒያም ውስጥ “ግሪን” የተባለ ባርና ሬስቶራንት ነበረኝ፡፡ እዚያ እየሰራሁ እያለ IFF (International Flavors and Fragrance) የተባለ የአሜሪካኖች ትልቅ ኩባንያ ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ ማጣፈጫዎችንና መዓዛማ ዘይቶችን ያመርታል፡፡ እነ ኮካ ኮላ፣ ለነ ፔፕሲና ሌሎችም ትልልቅ ኩባንዎች የሚያከፋፍል ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት የዚህ ትልቅ ኩባንያ ወኪል ሆኜ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። ሁኔታዎችን በማመቻቸት ስመላለስና እዚህ ቢሮ ስከፍት ግን 15 ዓመት ሆኖኛል፡፡ እናም እነሱ ጋር  በነበረኝ ግንኙነት ቸኮሌት፣ ከረሜላና መሰል ጣፋጮችን የሚያመርት ኩባንያ ለራሴ መክፈት አስቤ ስንቀሳቀስ፣ በወቅቱ ወባ በተለይ በአማራና በሌሎች ክልሎች የአገሪቱ ፈተና ሆኖ አየሁት፡፡ መነሻዬ ይሄ ነው፡፡
ከዚያ ምን አደረጉ?
በወቅቱ ወባ ህዝቡን እየፈጀች መሆኑን ከተለያዩ ሚዲያዎች አንብቤ ነው በጣም ያዘንኩት፡፡ ምን ይሻላል ምንስ ቢደረግ ህዝቡን መታደግ ይቻላል በሚል ራሴ በራሴ ትግል ውስጥ ገባሁ፡፡ አንድ ጥናት አጠናሁና “IFF” ላልኩሽ ኩባንያ አቀረብኩኝ፡፡ አፍሪካ የኮስሞቲክስም የሽቶም ችግር እንደሌለባት፣ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቧ በወባ እያለቀ ስለመሆኑ፣ አምራች ኃይሉ በወባ ጥቃት እያለቀ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ጥናቱ። ጥናቱን ተቀብለው ካዩት በኋላ “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ” አገሩም ወባማ ስለሆነ ቀድመው አጥንተው ነበር፡፡ ጥናቱን ያጠኑበትን ዋና መነሻ ሲነግሩኝም፤ “The Boston Tea Revolution” በነበረ ጊዜ የአሜሪካ ሰራዊት ያለቀው በወባ ነው፡፡ ያኔ ግን ወባ ነው ተብሎ በሽታው ተለይቶ አልታወቀም ነበር። የሆነ ሆኖ ጥናቱን ተቀበሉት፡፡ ከዚያ “ኢሴንሻል ኦይሉን” እንዲልኩልኝ አደረግሁኝ።
ኦይሉ ከተላከ በኋላ መጀመሪያ ጥናቱን የትኛው የአፍሪካ አገር አደረጉ?
መጀመሪያ ጥናቱ እንዲጠና የወሰንኩት ኬኒያ ነው፡፡ ምክንያቱም ኬኒያ ውስጥ “ኢሲፕ” የተባለ የዓለም ሳይንቲስቶች በሙሉ ስለ “ትሮፒካል ዲዚዝ” ጥናት የሚያደርጉበት ማዕከል ስላለ ነው። ከእነሱ ጋር ስምምነት በማድረግ፣ ከአሜሪካ የተላከው “ኢሴንሻል ኦይል” ከፔትሮሊየም ጄሊ (በተለምዶ ባዝሊን የምንለው) ጋር ተቀላቅሎ ቢሰራ በእርግጥ የወባ ትንኝን ያባርራል ወይ? የሚለውን እንዲያረጋግጡልኝ ነው ያደረግሁት። ብዙ ዶላር ካስከፈሉኝ በኋላ ጥናቱን ሰሩልኝ። ብዙ ዶላር የከፈልኩት ጥናቱ ሰፊ ስለሆነ ነው። አንደኛ የላብራቶሪ ሙከራ ያደርጋሉ፣ ሁለተኛ ወባ በተነሳ ጊዜ ገጠር ገብተው ካምፕ ሰርተው፣ ህዝብን አስተባብረው፣ ደም ምርመራ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ጥናቱን የሚያካሂዱት በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መስፈርት መሰረት ስለሆነ ነው። ጥናቱ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ወስዶ፣ በመጨረሻ ምርምሩን አድርገን፣ሰ ቅባቱ “ባዝኦፍ” ከ 8 ሰዓት በላይ የወባ ትንኝ ያባርራል ሲሉ የምስክር ወረቀት ሰጥተውኛል፡፡ ይህ ከሆነ ወደ ስምንት ዓመት ገደማ ይሆነዋል፡፡
መድኀኒቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና አግኝቷል?
በሚገባ! እኔ ሰርተፍኬቱ ከተሰጠኝ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሳመጣው፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በጣም ተደስተው ነበር፡፡ እኔ ባዝኦፍን ወደ ኢትዮጵያ ባስገባሁበት ወቅት ሰዎች የሚጠቀሙት አጎበር በኬሚካል ያልተነከረ ስለነበር ብዙም ውጤታማ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጤና ጥበቃችሁ “ይህ መድኀኒት አማራጭ ስለሚሆነን አገር ውስጥ ያሉ የምርምር ተቋማት ለምን ጥናት አያደርጉበትም? ፓስተር ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢመራመሩበት ጥሩ ነው” አሉኝ፡፡
ምርምሩ ተካሄደ?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያጠኑት እንደገና ስምምነት አደረግን፡፡ “አክሊሉ ለማ የምርምር ማዕከል” የትሮፒካል ዲዚዝና የወባ ምርምር ማዕከል ነው፡፡ በዚህ መሰረት የላብራቶሪ ሙከራ ተደረገበት። ቆቃ አካባቢ ወባ ተነስቶ ስለነበር ዶክተሮቹ እዚያ ድረስ ሄደው ምርምርና ጥናት አድርገው፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ውጤቱ አመርቂ ነው በሚል ማረጋገጫ ሰጡኝ፡፡
ባዝ ኦፍ የሚመረትበት ፋብሪካ የት አካባቢ ይገኛል? በዓመት ምን ያህል ያመርታል?
ፋብሪካው ለገጣፎ ይገኛል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እያመረትን ነው፡፡ አንደኛ ለፋርማሲዎች እናከፋፍላለን፤ ዋና የባዝኦፍ ተጠቃሚ ግን መከላከያ ሰራዊታችን ነው፡፡ ሰራዊቱ በፊት ከውጭ እያስመጣ ይጠቀም ነበር፡፡ እኛ ማምረት ከጀመርን በኋላ ከውጭ ማስገባታቸውን አቁመዋል፡፡ የተሻለ ጠቀሜታ አግኝተንበታል በማለት፣ በጀታቸው ውስጥ አስገብተው በየአመቱ ይወስዳሉ፡፡ ፌደራል ፖሊስም እንዲሁ እየወሰደ ነው፡፡ ሌሎች ተቋማትም መውሰድ ጀምረዋል፡፡ መንግስትም ይህንን በማየት ከወርልድ ባንክ ባገኘው ድጋፍ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ወደ 103 ሺህ ዶላር ገደማ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ ይህ እርዳታ የተሻለ ምርምርና ጥናት ለማካሄድ እንዲሁም ኤክስፖርት ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡
እስካሁን ወደ ውጭ መላክ አልጀመራችሁም?
ጀምረናል፤ ወደ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን ሱማሌላንድና ሞቃድሾ ልከናል፡፡ሰ በአሁኑ ሰዓት ሌሎች የወባ ችግር ያለባቸው አገሮችም ምርቱን ለመውሰድ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡
“ኢሴንሻል ኦይሉ” ከአሜሪካ IFF እያስመጣችሁ ነው የምትጠቀሙት? ሌላስ ማቴሪያል ምንድን ነው የሚያስፈልጋችሁ?
ቤዙ እንዳልኩሽ ባዝሊን ነው፡፡ ባዝሊን ከውጭ ይመጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከአንዳንድ ሳይንቲስቶች ጋር “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት በምክክር ላይ ነን፡፡ አገራችን በርካታ ለመድኀኒትነት የሚያገለግሉ ሁሉም አይነት ዕፅዋት ስላላት ምቹ ናት፡፡ መድኀኒቱ ከእፅዋት ነው የሚሰራው፡፡ እነሱ የሰሩት ፎርሙላ ስላለን “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት ዶክተሮቹን አጋር አድርገን ፋብሪካውን በማቋቋም ላይ ነን፡፡
ከረሜላና ቸኮሌት የሚያመርት ኩባንያም እንዳለዎት ሰምቻለሁ፡፡ ከባዝኦፍ ማምረቻው ጋር አንድ ላይ ነው ያሉት?
ቅርብ ለቅርብ ነበሩ፡፡ አሁን መለያየት ስላለባቸው እየለየናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ኩባንያዎች ውስጥ አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ በሽርክና ለመስራት መጥቷል፡፡ አሁን ከፍተኛ እንቅስቃሴ አለ፡፡ “ባዝኦፍን” ስናመርት በዚያውም ሽቶና መሰል መዓዛ ያላቸውን ምርቶችም እዚህ ለማምረት እያስመዘገብን ነው፡፡ አላማችን ከውጭ የሚመጡ የቼኮሌት፣ ከረሜላ፣ የወባ መድኅኒቶችና ሌሎችንም አስቀርተን አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ነው። እዚህ አምርተንና እሴት ጨምረን ኤክስፖርት ማድረግ ከኢኮኖሚም አኳያ አገሪቱን ይጠቅማታል፡፡
ባዝኦፍ ከስምንት ሰዓት በላይ የወባ ትንኝን እንደሚያባርር ተገልጿል፡፡ የመከላከል አቅሙ በመቶኛ ሲሰላ ምን ያህል ነው?
የዓለም የጤና ድርጅት አንድ መድኀኒት ከ60 እስከ 68 በመቶ መከላከል ከቻለ ውጤታማ ነው ይላል፡፡ ባዝኦፍ ግን 90 በመቶ አመርቂ ነው፡፡ ከስምንት ሰዓት በላይ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይሰራል። እየቆየ ኃይሉ እየደከመ እየደከመ ስለሚሄድ ግን በአማካኝ ከስምንት ሰዓት በላይ ይሰራል፤ በሚል እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
አሁን አሁን በወባማ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በኬሚካል የተነከረ አጎበር እየተጠቀሙ ነው፡፡ የባዝኦፍ ተጨማሪ ነው ወይስ እንዴት ነው?
አሁን ጥሩ ጥያቄ አመጣሽ፡፡ ሁሉም የተነከረ አጎበር ስለሚጠቀም፣ ሌሊት ትንኟ የሰዎችን ደም ማግኘት አልቻለችም፡፡ ስለዚህ የምትናከስበትን ሰዓት ቀይራለች፡፡ ለመኖርና እድሜዋን ለማራዘም ንክሻዋን ወደ ቀን አዘዋውራለች፡፡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶችም ጥናት የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ይህን በተመለከተ ሳይንቲስቶች በ6300 ሰዎች ላይ ጥናት ሲያደርጉ ለመጀመሪያው ቡድን አጎበር ብቻ ሰጡ፣ ለሁለተኛው ደግሞ መከላከያ ቅባቱንም አጎበሩንም ሰጡ፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ መሰለሽ? አጎበሩንም መከላከያ ቅባቱንም የተጠቀሙ ሙሉ በሙሉ ከወባ በሽታ ነፃ ሲሆኑ አጎበሩን ብቻ ከተጠቀሙት መካከልብዙዎቹ በቀን እየተነከሱ የወባ ተጠቂ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
አሁን ባዝኦፍን ተፈላጊ ያደረገው አንዱም ጉዳይ የወባ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን ማዛወሯ ነው፡፡ ቀን ቀን አጎበር ተሸክመሽ አትንቀሳቀሺም፤ ስለዚህ የግድ በወባማ አካባቢና በወባ ነሻ ወቅት ቀንም ባዝኦፍ መቀባት ግድ ነው፡፡
አሁን ክረምት እንደመሆኑ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀሰቀስበት ወቅት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምርታችሁ ተፈላጊነት ምን ይመስላል?
እንደነገርኩሽ በቋሚነት የሚወስዱ እንደ መከላከያ ሰራዊት ያሉ ተቋማት አሉ፡፡ ምርቱ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ አሁን ሁለቱም ፋብሪካዎች በ6500 ካ.ሜ ላይ ነው ያሉት፡፡ 15 ሺህ ካሬ ለባዝኦፍ ማስፋፊያ ጠይቀን እየጠበቅን ነው፡፡ ጉዳዩ አንገብጋቢና መንግስትን የሚያግዝ በመሆኑ ማስፋፊያው ሲፈቀድ፣ በስፋትና በጥራት ለማምረት ዝግጁ ሆነናል፡፡ አጋሮቻችን ብሩን ልከዋል፤ የገበያውን አዋጭነት፣ ላለፉት ዓመታት ሁለቱም ኩባንያዎቻችን የነበራቸውን ጉዳዮች መሰል ታሪኮች አስጠንተው ካመኑበት በኋላ ነው ገንዘቡን የላኩት፡፡
በመጨረሻ የሚሉኝ ካለ?
ያው ባዝኦፍ በዚህ መልኩ እየተመረተ ነው፡፡ ለወባ በሽታ በአማራጭነት በመቅረቡ መንግስትም ደስተኛ ነው፡፡ኤክስፖርት እየተደረገ የውጭ ምንዛሬም እያመጣ ነው፡፡ መከላከያው ትልቅ ፋይዳ ያለው ስለሆነ፣ ወደፊት የወባን በሽታ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በምንችልበት አቅም ላይ እንድንደርስ በምርምሩም ሆነ በሁሉም ረገድ በርትተን እንሰራለን፡፡

Read 3046 times