Wednesday, 30 July 2014 07:45

ተመልካቾች የድራማውን አጨራረስ አልወደዱትም

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

የ“ሰው ለሰው” አጨራረስ ይህችን ምድር ገነት አስመሰላት”
የሰው ለሰው አጨራረስ የምንኖርባትን አለም “ገነት” አስመሰላት፡፡ የአስናቀ መሞት ወይም ከፎቅ ላይ መወርወር ሲያንሰው ነው፡፡ ግን የሌሎቹ ገፀባህሪያት ጅምር ታሪክ በደስታ መጠናቀቁ አስገርሞኛል፡፡
እናቶች በወሊድ በሚሞቱባት አገር መዲ ብትወልድ ልትሞት እንደምትችል እየተነገራት፣ የፍሬዘር ሚስት የጤና ችግር እያለባት፣ አዱኛ ያ ሁሉ መጭበርበር ደርሶበት… ሁሉም ድንገት መልክ መልክ ይዞ ሳይ፣ ሌላ ፕላኔት ላይ እንጂ  በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ ያለ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ አልመስልህ ብሎኛል፡፡ ወይ መዲ አሊያም የፍሬ ሚስት መሞት ነበረባቸው ባይ ነኝ፡፡
“አብነት” በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የቴአትሪካል አርት ተማሪ

የ“ሰው ለሰው” አጨራረስ የፍትህ ስርዓታችን የደከመ መሆኑን አሳይቶኛል”
አስናቀ ለሰራው ግፍና በደል ተይዞ ፍርድ ቤት ተገትሮ የሞት ፍርድ ቢፈረድበትና ያ ተፈፃሚ ሲሆን ብንመለከት ብዙ ትምህርት እናገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን አጨራረሱ በዚህች አገር ላይ ያለው የፍትህ ስርዓት ደካማ መሆኑን ነው ከአጨራረሱ የተረዳሁት። ምክንያቱም የገደለችው በአስናቀ ግፍና በደል ስትለበለብ የነበረችው ወ/ሮ ማህሌት ናት፡፡ ሰዎች በአገራቸው የፍትህ ስርዓት ሳይተማመኑ ሲቀሩ ፍትህን በራሳቸው ለማግኘት ሲማስኑ ይታያል፡፡ የአስናቀና የማህሌት ገዳይና ሟችነትም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ እኔ ደስ ይለኝ የነበረው አንድ ሌላ ሰው ሞቶ፣ አስናቀ በህይወት ቢያዝና በፍ/ቤት የእጁን ቢያገኝ ነበር፡፡
(አምባው) ጋዜጠኛ
“ያስደሰተኝ አስናቀ ከፎቅ የተወረወረበት ሲን አኒሜሽንና የመስፍን ከዊልቼር ላይ መነሳት ነው”
 “ሰው ለሰው”ን በጥሩ ሁኔታ ተከታትየዋለሁ። ቀደም ብሎ ማለቅ ነበረበት፤ በኋላ እየተንዛዛ መጥቷል፡፡ የአስናቀ አሟሟት ልጁ ባለበት መሆኑ አሳዝኖኛል፡፡ በዚህ መልኩ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡  ከሰራው ግፍና በደል አንፃር ጥፍሩ እየተነቀለ፣ እንደ ዶሮ ብልት 12 አይደለም መቶ ቦታ ቢገነጣጠል አይበቃውም፡፡ ግን ፍትህ ባለበት አገር ፖሊስ ሊይዘው አጠገቡ እያለ በሌላ ሰው መገደሉ አላሳመነኝም፡፡ ከድራማው “ሰርፕራይዝ” ያደረገኝና ያልታሰበ የሆነብኝ የመስፍን ከዊልቸር ላይ ተስፈንጥሮ መነሳትና ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ማየት ሲሆን፤ ከትዕይንቱ ደስ ያለኝ ደግሞ አስናቀ በሽጉጥ ተመትቶ ከፎቅ ወደ ምድር የተወረወረበት አኒሜሽን ነው፡፡ ይሄ ጥሩ ሙከራ ነው፤ ቀረፃው የተሳካ ነበር፡፡ በተረፈ ያን ያህል የሚያስደንቅ አጨራረስ አልነበረውም፡፡
ቅዱስ ከካዛንቺስ

“አጨራረሱ ብቻ ሳይሆን ድራማው ራሱ ደስ አይለኝም ነበር”
ድራማውን የተጀመረ ሰሞን እመለከተው ነበር በኋላ እየደበረኝ መጣ ለምን ብትይ ብዙ የማያሳምኑኝ ነገሮች ተበራከቱ፡፡ አንደኛ አሳማኝነት አጣሁበት ሁለተኛው እኔ ቀድሜ ያሰብኩት ነው የሚሆነው ድራማው በአጠቃላይ የዚህ አገር ፊልሞች አይነት ባህሪ አለው፡፡ ገና ሲጀመር መጨረሻውን የምታውቂው አይነት፡፡
አንድ መጽሔት ላይ ኢቴቪ ድራማውን በቶሎ ማጠናቀቅ ስላለባችሁ ሲኖብሲስ አስገቡ ተብለው አዘጋጆቹ አስናቀን በሽጉጥ እንገድለዋለን ብለው እንደነበርና የአስናቀን በሽጉጥ መሞት ኢቴቪ አልቀበልም ማለቱን ሰምቼ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም በሽጉጥ ነው የገደሉት፡፡ በጭራሽ መሆን አልነበረበትም፤ ለፍርድ መቅረብ ነበረበት። ድራማው ባልሆነ መልኩ እንደሚጠናቀቅ ስሜቴ ይነግረኝ ነበር፡፡
ነቢያት ምትኩ (ተዋናይት)
“የአስናቀ አሟሟት በፍፁም ተገቢ አይደለም”
ሞት ለክፉም ለደጉም አይቀርም፡፡ በደግነታቸው፣ በአገር አመራር ብቃታቸው በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጭነታቸው የተመሰገኑና ብቁ የሆኑ ሰዎች፣ በአልባሌ ሰዎች በሽጉጥ ተገድለዋል፡፡ እንደ ሃየሎም አርአያ አይነት ጀግኖች ባልሆኑ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ አስናቀም ከእነዚህ እኩል እንደተገደለ ነው የማምነው፡፡ ያንን ሁሉ በደልና ግፍ ሰርቶ፣ ቤተሰብ በትኖ ለፍርድ መቅረብ ነበረበት፡፡ የሞት ፍርድ ተበይግበት ሲሞት አሊያም እድሜ ልክ እስራት ተበይኖበት እንደማንኛውም ወንጀለኛ ወህኒ ቢወርድ፣ እንደሱ ያሉ ክፉ ሰዎች ይማሩበት ነበር፡፡ ህዝቡም ፍትህ መኖሩን አምኖ ይቀበል ነበር በአጠቃላይ አጨራረሱ ችግር አለበት፡፡ ብዙ ነገሮች አልተቋጩም፡፡
ሐይማኖት ግርማ ነርስ እና
የሶሲዎሎጂ ተማሪ

“ድራማው ከሁለት ዓመት በፊት መጠናቀቅ ነበረበት”
አጨራረሱ አብዛኞቻችን አላረካንም፡፡ የአስናቀ አሟሟትም በዚህ መልኩ ይሆናል ብለን አላሰብንም። ድራማው በአብዛኛው የተጓዘው የስነ-ጥበብንና የስነ-ፅሁፍን መህ ተከትሎ አይደለም። ገቢ መሰብሰብ ላይ ስላተኮሩ እንኳን በባለሙያ ሙያውን በማያውቁትም  ሁሉ ተተችተዋል፡፡
አስናቀ በዚህ ክፋቱ ቀደም ብሎ መሞት ነበረበት። በአስናቀ ግፍ ስንት መከራና በደል የደረሰባትን ማህሌትን ወንጀለኛ አድርገው፣ ህይወቷን ሌላ ዝብርቅርቅ ውስጥ ከሚከትቱት አስናቀ በህይወት ተይዞ ለፍርድ ማቅረብ ተገቢ ነበር፡፡ አስናቀ አልሸነፍ ባይ ስለሆነ፣ ሌላ አደጋ ሳያደርስ ይገደል ቢባል እንኳን በፖሊሱ ቢገደል መልካም ነበር፡፡
በአጠቃላይ አጨራረሱ የይድረስ ይድረስ ሆነ እንጂ ከህግና ከፍትህ አንፃር ቢቋጭ ኖሮ አስተማሪነቱን የጎላ ያደርገው ነበር፡፡ የኢቴቪ ኃላፊዎችም ከፍትህና ከህግ አንፃር መቃኘትና  አስተማሪነቱ ማመዘን አለበት ብለዋቸው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
ነገር ግን አዘጋጆቹ፤ “በእኛ ስራ ማንም ጣልቃ አይገባም፤ ነፃነት አለን” ብለው ያንን ነፃነታቸውን ለማሳየት ሲሉ በዚህ መልኩ መቋጨታቸውን ሁላችንም አልወደድነውም፡፡ እኛ በአጨራረሱና በአስናቀ ላይ አተኮርን እንጂ ድራማው ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡
ማለቅ የነበረበት ከሁለት ዓመት በፊት ነው ያልኩበት ምክንያት አላስፈላጊ ታሪኮች ተካትተዋል፣ ተደጋጋሚና አሰልቺ ታሪኮች ነበሩት። መቀጠል የነበረባቸው ታሪኮች በተጠበቀው መልኩ አልቀጠሉም፡፡ ጥሩ ታሪክ ይዘው ተነስተው በምን ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ ውሃ የበላቸው ገፀባህሪያት አሉ፡፡ አሁን  ረስተናቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ ስትመለከቺ ብዙ ችግሮች ያስተናገደ፣ እስካሁን መቀጠል ያልነበረበትና ገቢ መሰብሰብን ማዕከል አድርጎ፣ የስነ-ፅሁፍ ስነ-ምግባርን ያልተከተለ ነው ብዬ በድፍረት ለመናገር እችላለሁ፡፡ ለዚህ ነው ባለሙያዎች ብቻ ሳንሆን በሙያው ውስጥ እንኳን ያልሆኑ ተመልካቾች ትችት የሰነዘሩት፡፡
ታጠቅ ነጋሽ (የቴአትር ባለሙያ)

“የሞተ የሚነሳበት ድራማ መሆኑ አናዶኛል”
“ሰው ለሰው” ድራማ ህዝብ እንደማያውቅ፣ ምንም ማገናዘብ እንደማይችል ተደርጐ የተቆጠረበትና የተናቀበት ከመሆኑም በላይ የሞተ የሚነሳበት ድራማ መሆኑ አናዶኛል፡፡
መዲ፤ እናቷ እንድታስወርድ የሰጠቻት መድሃኒት፣ ደሟን አንጠፍጥፎ ዶክተሩም ሞተች ብሎ ጥሏት ከሄደ በኋላ ነፍስ ዘራች፡፡ ደራሲዎቹ እንደ ፈጣሪም ያደርጋቸዋል እንዴ? ድራማውን ለማራዘምና ገቢ ለመሰብሰብ ሲባል የማያሳምን ነገር መዘብዘብ፣ ህዝብን መናቅና አላዋቂ ማድረግ ነው፡፡ አጨራረሱም ቢሆን ዝብርቅርቁ የወጣና ብዙ ታሪኮች ያልተቋጩበት ነው፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ማህሌት፣ የመዲን ወንድም አስከሬን በመኪና ወስዳ የጣለችበት ታሪክ ተድበስብሷል፡፡ ኧረ ምኑ ቅጡ! ተጫውተውብናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የስነ ጽሑፍና የቴአትር ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስተያየት ሰጥተውበት ወደፊት ለሚቀርቡ ድራማዎችም መማርያ መሆን አለበት፡፡ ታሪኩ በየጊዜው እየፃፈ የሚቀጥልና በደራሲዎቹ በጐ ፈቃድ የሚራዘም ሳይሆን ተሰርተው ተጠናቀው፣ ተገምግመውና ለህዝብ አዕምሮ የሚመጥኑ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የአስናቀ አሟሟት መንግስት በዚህች አገር ላይ እንደሌለ የሚያመላክት በመሆኑ አዝኛለሁ፡፡
መሰረት - ከካዛንቺስ

Read 4683 times