Wednesday, 30 July 2014 07:54

ብረር ብረር አለኝ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

       ናፍቆት ደጋግማ ስትመጣ ደጋግሜ የለም አስባልኩ፡፡ ጋሎይስን ለሦስተኛ ጊዜ ማንበቤ ነው። አንዳንዴ መንገዱ መንገዴ ይመስለኛል፡፡ ሌላ ጊዜ በእልሁ ከእኔ ይልቅ አሰፋ ጢሪሪን ወይም ንዳዴን መስሎ ይታየኛል፡፡
መኝታ ክፍሌ ተዘግቶ ማንበብ ስለሰለቸኝ ወጥቼ ካክስቴ ቤት ሥር የቱሪማንቱሪ ቅጠል አንጥፌ ተቀመጥኩ፡፡ መጽሐፉ የተዘጋጀው ለመኝታ ቤት ውስጥ ይመስላል፡፡ ሌላ ቦታ ለማንበብ አይመችም። በደረት አልጋ ላይ ተንበልብሎ በግራ በኩል መጽሐፉን፣ በቀኝ በኩል መዝገበ ቃላቱን አድርጐ በብዙ ማስታወሻ ወረቀቶች ተከብቦ ሲነበብ የበለጠ ይገባል፡፡ ግን ሰለቸኝ፡፡
ልዑል መውደቂያ ዘወትር ጭር እንዳለች ነው። አሁን ግን አንድ ናዝሬት ሚሽን የሚማር ልጅ ለክረምት ዕረፍት ወላጆቹ ጋ መጥቶ ይረብሻታል። ግራር ላይ ወይም የቱሪማንቱሪ ጫፍ ላይ ወጥቶ የተለያዩ ዘፈኖችን በረጅሙ ይለቅቃል፡፡ አሁንም አለ። የት እንደሆነ ግን ላየው አልቻልኩም፡፡ ዘፈኑ ብቻ እየመጣ ከጆሮዬ ጋር ይላጋል፡፡
“ልቤ ቢቀርበት ምነው
ልቤ ቢቀርበት ምነው
ምኞት እኮ ህልም ነው፡፡”
አባቴ በልጅነቱ ይኼን ልጅ ሳይሆን አይቀርም ስል አሰብኩ፡፡ ዘፈኑን ማስታወስ ከማልፈልገው አባቴ መንጭቄ የምጥልበት ስፈልግ ጋሽ በረደድ ትዝ አሉኝ። አክስቴ ላይ ያላቸው ምኞት ህልም እንደሆነ ከዚህ ዘፈን ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ መኖሪያቸው ከአክስቴ ቤት መደዳ ጫፍ ላይ ነው፡፡ ቤታቸው በእኛ ቤት ላይ ምኞት ያለው ይመስል ከሰልፉ አፈንግጦ በመቆልመም በአንድ ዓይኑ ወደዚህ ይመለከታል፡፡ የጋሽ በረደድ ሚስት አጐንብሰው ወጥተው አጐንብሰው ይገባሉ፡፡ ኅይለኛ ናቸው፡፡ የባላቸው ማጋጣነት ወሬ ሲደርሳቸው፣ ወይም ደስ የማይል አዝማሚያ ባላቸው ላይ ሲመለከቱ ቱግ ይላሉ፡፡ ቱግታቸው ፈር የለቀቀ አይደለም፡፡ የባላቸውን አንቱታን አይዘነጉም፤ ግን ይሳደባሉ፡፡
“አንቱ ሸርሙጣ” ይላሉ በእጃቸው ጭብጥ ጀርባቸውን እየደቁ፡፡ “አንቱ ሸርሙጣ፣ አንቱ ሸርሙጣ፣ አንቱ ሸርሙጣ….”
እኔ ጋሽ በረደድ ላይ እስቃለሁ፡፡ ጋሽ በረደድ አይናደዱም፡፡ ለኔ ምላሽ የሰጡ ሳያስመስሉ፤
“አጤ ቴዎድሮስም የተቸነፉ በሚስታቸው ነው፡፡ ለሚስት መቸነፍ የጀግና ወጉ ነው…ምናምን” ይላሉ፡፡
የልዑል መውደቂያ አባወራዎች ጥቂት ናቸው። ግማሽ ክብ ቅርጽ ላይ በድጋሚ የሚጠመጠምባት ሌላ የቤት መቀነት አለ፡፡ እያንዳንዱ ቤት ፀሐይ እንዳይገባበት ደጃፉ ላይ ቱሪማንቱሪ ዛፍ ተተክሏል፡፡ የጋሽ ጥበቡ ቤት እነዚህ መደዳ ጫፍ ላይ ከጋሽ በረደድ ቤት አጠገብ ይገኛል፡፡ የጋሽ ጥበቡ ሚስት ሲበዛ ተፀያፊ ናቸው፡፡ ጋሽ ጥበቡ ከዓይጥ አደን ሲመለሱ፤
“እዛው፣ እዛው….” እያሉ ያንቋሽሿቸዋል፡፡ የአይጥ ማስገሪያቸውን ማዶ አስጥለው ሳሙናና ውኃ ያመጡላቸዋል፡፡ እየተነጫነጩ ዕቃ ሳያስነኩ እራሳቸው ያስታጥቧቸዋል፡፡ ይህን ስመለከት ምናልባትም ባልና ሚስቱ አብረው ማዕድ ከቆረሱ ብዙ ዓመታቸው ሳይሆን አይቀርም እላለሁ፡፡
“በኑሮ ላይ ተቸግሮ ሰው ሲጐዳ፣
መልኩን ጥሎት ገሸሽ ይላል እንደባዳ”
ልጁን እንደ ጥንብ አንሳ ከተንሿጠጠ እራሱ ጋር ግራሩ ላይ አየሁት፡፡ ሹል አፉን እየከፈተ ሲታይ የሚዘፍን ሳይሆን የሚያንቋርር ይመስላል፡፡
በዚህ መካከል ከየት እንደመጣች ያላየኋት ናፍቆት ፊቴ ተገተረች፡፡ ያለወትሮው እግሯ ንፁህ ሆኖ አየሁት፡፡ በስሱ ቅባት የተባበሰሰ ቢሆንም የሞዶ እንኩሮአማ አቧራ አላንዣበበበትም፡፡ በአየር ላይ ተንሳፋ ካልመጣች በቀር እንዲህ ንፁህ ሊሆን እንደማይችል የታመነ ነው፡፡ የእግሯ ጣቶች በሽብር ዓይንን እንዲያፈገፍግ ያስገድዳሉ፡፡  
(ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ
“የብርሃን ፈለጐች” የተቀነጨበ

Read 8844 times