Saturday, 02 August 2014 10:48

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 3 ተጨማሪ የስልጠና አውሮፕላኖችን አስገባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአብራሪዎች የሚሰጠውን ስልጠና ለማሳደግ ሴስና ከተባለው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የገዛቸውን ‘ሴስና 172’ የተሰኙ ሶስት ተጨማሪ የስልጠና አውሮፕላኖች ባለፈው ሳምንት ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን ገለጸ፡፡ አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፤ በቅርቡ ዲያመንድ ከተሰኘው የኦስትሪያ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ 12 አውሮፕላኖችን ገዝቶ ማስገባቱን ጠቁሞ፣ ከሰሞኑ ያስገባቸው አዳዲስ አውሮፕላኖችም አራት መቀመጫዎች ያሏቸውና ባለ አንድ ሞተር እንደሆኑና በአሜሪካና በአውሮፓ ከአስር አመታት በፊት የጥራት ማረጋገጫ አግኝተው በተለያዩ አገራት ለስልጠና አገልግሎት በመዋል ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ የአየር መንገዱን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በመግለጫው ላይ እንዳሉት፣ አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2025 እደርስበታለሁ ብሎ ባስቀመጠውና በመተግበር ላይ በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ ለሰው ሃይል ልማት ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ አውሮፕላኖቹም አየር መንገዱ የሚሰጠውን የአብራሪዎች ስልጠና ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡

በስትራቴጂክ ዕቅዱ የመጨረሻ አመት በአፍሪካ መሪ የሆነ የአቪየሽን ስልጠና ማዕከል ባለቤት የመሆን ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ የሚገኘው አየር መንገዱ፣ አውሮፕላኖቹ በዘርፉ የሚሰጠውን የስልጠና አቅም እንደሚያሳድጉለት ገልጿል፡፡ አየር መንገዱ ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ አካዳሚውን የማስፋፋት ፕሮጀክት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው መግለጫው፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪየሽን አካዳሚ በአፍሪካ ትልቁ የአቪየሽን ስልጠና ማዕከል መሆኑና በያዝነው የፈረንጆች አመት፣ በአፍሪካ የአየር መንገድ ማህበር ‘የአመቱ አገልግሎት ሰጪ የአቪየሽን አካዳሚ’ ተብሎ መሰየሙንም አስታውሷል፡፡ የስልጠና አካዳሚው ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ባለፉት አራት አመታት ከፍተኛ እድገት ማሳየቱንና በአሁኑ ሰአትም አመታዊ የመቀበል አቅሙ ከ1ሺህ በላይ መድረሱን ገልጿል፡፡ በዕቅድ አመቱ መጨረሻ ይህን ቁጥር ከ4ሺህ በላይ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

Read 1151 times