Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 24 December 2011 10:40

“የሞትነውም እኛ፤ የነገስነውም እኛ” - በሰሜን ኮሪያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ትልቅዬው ኪም ሲሄድ፤ ትንሽዬው ኪም ተተካ

አብሮ ማልቀስ፤ አብሮ ማጨብጨብ - የዜጎች ግዴታ

አምባገነኖቹ ለፕሮፓጋንዳ የሚፈጥሩት ተረት

ትልቅዬው ኪም ሲወለዱ፤ “ወፎች ዘምረዋል፤ ሰማዩ በድርብ ቀስተደመና ተሞልቷል”

አሁን ሲሞቱ፤ “ተራራው ብርሃን አፈለቀ፤ የሃይቁ በረዶ ተተረተረ፤ ውሽንፍር ቆመ”

ትንሽዬው ኪም፤ “ሺ ጊዜ ተኩሶ አንዴም የማይስት አልሞ ተኳሽና ብልህ መሪ ነው”

የሰሜን ኮሪያን ወሬ እያያችሁ ነው? በእርግጥ ብዙ የሚታይ ነገር የለውም። ሁለት ነገር ብቻ ነው የሚታየው። ሰዎች ሁሉ በመሪያቸው ንግግር “ከልብ ተደስተው” ሲያጨበጭቡ፤ ወይም ሰዎች ሁሉ በመሪያቸው ሞት “ልባቸው ተሰብሮ” በሃዘን ሲጮሁ ... ይሄው ነው የሰሜን ኮሪያ ወሬ?

ሁሉም ሰው በ”ህዋስ” (አምስት አምስት እንደሚባለው አይነት) እንዲደራጅ በተደረገበት አገር ውስጥ፤ የበላይ ሃላፊ ሲናገር ሁሉም ያጨበጭባል። መቃወም ይቅርና ዝም ማለትም ጨርሶ አይታሰብም። እንዲያውም፤ ከሌሎች ቀድሞ ጭብጨባውን ማቆምና ማቋረጥም  ያስፈራል። በራሱ በበላይ ሃላፊው ትእዛዝ ነው፤ ጭብጨባው የሚቆመው። መሪ የታመመ ወይም የሞተ ጊዜ ደግሞ፤ ሁሉም ሰው፤ አባትና እናት የሞተበት ያህል ማልቀስ ይኖርበታል። ሌሎች አምርረው ደረት ሲመቱና ፀጉር ሲነጩ፤ መሬት ተደፍተው ለያዥ ለገላጋይ ሲያስቸግሩና በእሪታ ሲያለቅሱ፣ በለቅሶ በልጦ ለመታየት የሚፎካከር ይበዛል። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ፤ ተቀላቅሎ መመሳሰል ያስፈልጋል። በዝምታ ማለፍ ወይም ቆሞ ማየትማ፤ የካድሬ ጥርስ ውስጥ ገብቶ ህይወትን አደጋ ላይ መጣል ይሆናል። የአምባገነኖች አገር አሳዛኝ ድራማ ተመሳሳይ ነው - አብሮ ማጨብጨብና አብሮ ማልቀስ። ስታሊን ሲሞት እንደታየው ሁሉ፤ የሰሜን ኮሪያው አምባገነን ኪም ጆንግ ኢል ሲሞቱም፤ ይሄው እንዳያችሁት አገር ምድሩ በለቅሶና በእሪታ ተሞልቷል። እንዲያውም፤ ሳያለቅሱ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ እስከመሆን ደርሷል። አለበለዚያ “መጠቆር” ይመጣላ። አያትየው ኪም ኢል ሱንግ ከ40 አመት በላይ አገሪቱን ከገዙ በኋላ፤ ኪም ጆንግ ኢል፤ ተተኩ። ከ15 አመት በኋላ ደግሞ፤ ይሄውና የልጅ ልጅ መጥቷል - ኪም ጆንግ ኡ።አባት ሄዶ ልጅ በቦታው ቢተካም፤ የሰሜን ኮሪያ ህይወትና የካድሬዎች ፕሮፓጋንዳ አልተቀየረም። አባትዬውን ሲያወድሱ የነበሩ ካድሬዎችና ለአባትዮው ተገዢ የነበሩ ዜጎች፤ የልጅየው አወዳሽና ተገዢ ይሆናሉ። ኪም ጆንግ ኢልን አምላክ ለማሳከል በተፈጠሩትና በተሰራጩት ተረቶች ቦታ፤ ኪም ጆንግ ኡን ወደ አምላክ ዙፋን ለማድረስ  የሚፈለፈሉ የካድሬ ተረቶች መበራከት ጀምረዋል።ሟቹን ኪም ጆንግ ኢልን ከመለኮታዊ ሃይል ጋር ለማስተሳሰር ታስበው ከተፈበረኩት የስብከት ተረቶች አንዱ፤ የአንዲት እርግብ ታሪክ ይገኝበታል። ከአገሪቱ ህዝብ መካከል ሩብ ያህሉ፤ ማለትም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰሜን ኮሪያዊያን የሟቹን አስከሬን ለመሰናበትና ሃዘናቸውን ለማሳየት ወደ ዋና ከተማዋ እንደጎረፉ የአገሪቱ የመንግስት ቲቪና ሬድዮ ገልፀው የለ? ግን፤ በፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ ለተሰማራ ፓርቲ፤ እንዲህ አይነት ወሬዎች በቂ አይደሉም። የስብከት ተረቶችን ይፈጥራል። ... እናም፤ “በሟቹ መሪ፤ እጅግ ያዘኑትና ልባቸው የተሰበረባቸው ሰሜን ኮሪያዊያን ሰዎች ብቻ አይደሉም። ሰሜን ኮሪያዊያን አእዋፍና እርግቦችም አዝነዋል። አንዷ እርግብም፤ በሃዘን የሟቹን ሃውልት ስትዞር ነበር። ዞራ ዞራ በአቅራቢዋ የሚገኘው ዛፍ ላይ ሄዳ ተቀመጠች - በሃዘን አንገቷን ደፍታ”

እንዲህ አይነት ታሪኮችን የመፍጠር፣ የማሰራጨት፤ በአጠቃላይ የማስተዳደር ሃላፊነት  - የፕሮፌሰር ኪናም ነው። ያረጁበት ስራ ነው። የ82 አመቱ አዛውንት ፕሮፌሰር ዋነኛ ስራቸው፤ የሰሜን ኮሪያዊያንን አእምሮ በፕሮፓጋንዳ መሙላትና መጠፍጠፍ፤ መቅረፅና መሞረድ ነው። ዜጎች፤ ለመሪዎች፣ ለፓርቲና ለመንግስት ተገዢ እንዲሆኑ፤ መሪዎችንን እንዲያከብሩ ብቻ ሳይሆን እንዲያመልኩ ጭምር ለማድረግ፤ ተረቶች ይፈበረካሉ። የመሪዎች የገፅታ ግንባታ፤ የማያቋርጥ የዘወትር ስራ ነው።

ኪም ጆንግ ኢል የጣኦት ያህል እንዲከበሩ በማሰብ፤ በርካታ ተረቶችን እየፈጠረ፤ ያለፋታ ለአመታት ሲያሰራጭ የነበረው የፕሮፓንጋዳና የቅስቀሳ ሚኒስቴር፤ አሁንም በፕ/ር ኪናም አመራር ስር አዲስ ሃላፊነት ተጥሎበታል። ለአዲስ መሪ፤ አዲስ የገፅታ ግንባታ ያስፈልጋል። የአባቱ ወራሽ የሆነው ታናሽዬው ኪም ጆንግ ኡ፤ የአማልክት ያህል ልዩ ፍጡር እንደሆነ፤ ሰሜን ኮሪያዊያን አምነው እስኪቀበሉ ድረስ ወይም አምነው የተቀበሉ እስኪመስሉ ድረስ የሚዘልቅ፤ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጧጡፏል ይላል አሶሼትድ ፕሬስ።

በእርግጥ፤ ወጣቱን ጆንግ ኡ በገፅታ ግንባታ ለመሪነት የማዘጋጀት ፕሮጀክት የተጀመረው ከሶስት አመት በፊት ነው። ያኔ ነው፤ የ25ቱ አመት ኪም ጆንግ ኡ፤ ከየት መጣ ሳይባል የጄነራልነት ማእርግ የተሰጠው። ድንቡሽቡሽ ያለው ወጣት፤ በፓርቲ እና በጦር ሃይል ውስጥ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን እንዲይዝ ሲደረግ፤ ለተተኪ መሪነት በአባቱ እንደታጨ አጠራጣሪ አልነበረም። እናም በአባቱ ቦታ ተተክቶ መሪነቱን እስኪይዝ ድረስ፤ ቀስ በቀስ መለኮታዊ የሚመስል ታላቅ ዝና እንዲጎናፀፍ የሚያደርግ የፕሮፓንጋዳና የቅስቀሳ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ስራው እየተካሄ ቆይቷል - ለረዥም ጊዜ እንደሚቀጥል በማሰብ። አሁን አባትዬው በድንገት ሲሞቱ ግን፤ የገፅታ ግንባታ ፕሮፓጋንዳውን አፋጥኖ ውጤቱን ቶሎ ማድረስ የፕ/ር ኪናም ፈተና ሆኗል።

ቀላል ስራ ባይሆንም፤ አዛውንቱ ፕሮፌሰር የአመታት ልምድ አላቸው። ለአባትዬው፤ ለኪም ጆንግ ኢል የተካሄደው የገፅታ ግንባታ ፕሮፖጋንዳ፤ በፕ/ር ኪናም የተከናወነ ነው። ከፕሮፓጋንዳዎቹ መካከልም፤ የኪም ጆንግ ኢል ልደትን ከልዩ መለኮታዊ ሃይል ጋር ለማያያዝ የተፈጠሩ ተረቶች ይገኙበታል። ኪም ጆንግ ኢል የተወለዱ ቀን፤ ሰማዩ በመብረቅና በነጎድጓድ ሲታረስ ሲታመስ እንደነበር የሚተርኩት የፕሮፓጋንዳ ካድሬዎች፤ ድርብ ቀስተደመና ከአድማስ አድማስ ተዘርግቶ ነበር ይላሉ። አሟሟታቸውም ተአምራዊ ገፅታ እንዲላበስ ለማድረግ፤ ፕሮፓጋንዳው ቀጥሏል። የሰሜን ኮሪያ የዜና አገልግሎት ባሰራጨው “ዜና”፤ ኪም ጆንግ ኢል ሲሞቱ፤ ሰማዩ ደም እንደለበሰ ሸማ መቅላቱን፤ እንዲሁም የበረዶው ውሽንፍር ወዲያው ፀጥ ረጭ ማለቱን ለፍፏል።

ለገፅታ ግንባታ ተብሎ የሚካሄደው የተረት ፈጠራ፤ በሰሜን ኮሪያ ቁልፍ የመንግስት ስራ ነው ይላል አሶሼትድ ፕሬስ። “ኪም ጆን ኢል የተወለዱ እለት፤ ወፎች ዘምረዋል፤ ሰማዩ በድርብ ቀስተደመና ደምቋል” የሚለው የፕሮፓጋንዳ ተረት፤ ጥቂት ጊዜ በሬድዮና በቲቪ ተወርቶ የሚቀር አይደለም። በትምህርት ቤት መፃህፍትም አማካኝነት ይሰበካል። ከህፃንነት እድሜ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ወጣትነት እድሜ እስከ ዩኒቨሪሲቲ ድረስ፤ ስብከቱ አይቋረጥም።

ልጅዬው፤ ኪም ጆንግ ኡ፤ አሁን ስልጣን ላይ ሲቀመጥም፤ ፕሮፓጋንዳው፣ ተረቱና ስብከቱ ይቀጥላል። ለምሳሌ የአገሪቱ የዜና አገልግሎት ድርጅት፤ የኪም ጆንግ ኡ ብልህነት በአለማችን አቻየለሽ እንደሆነ ሲገልፅ ሰንብቷል።  “በብልሁ ኪም ጆንግ ኡ አመራር አማካኝነት ተግባራዊ የሚሆነውን ግስጋሴ የሚገታ አንዳችም ምድራዊ ሃይል የለም” ሲል ድርጅቱ አውጇል። የአገሪቱ ጋዜጣም፤ “ከማንም የላቀ፤ የፓርቲ፤ የጦር ሃይል እና የአገር መሪ” በማለት የ28 አመቱን ወጣት አወድሷል።

በእርግጥ፤ ጆንግ ኡ በጦርነት ተካፍሎ አያውቅም። የዩኒቨሪሲቲ ትምህርት ሲጨርስ ነው፤ የጄነራልነት ማእርግ የተሰጠው። እንዲያም ሆኖ፤ “ሺ ጊዜ ቢተኩስ፤ አንድም ጊዜ ሳይስት፤ የነጥብ መሃል ላይ አነጣጥሮ ኢላማ መምታት የሚችል አስደናቂ የጦር መሪ ጄነራል ነው” የሚል አድናቆት በጋዜጣ፣ በሬድዮና በቲቪ ይግለበለብለታል።

ለገፅታ ግንባታ የሚውል የተረት ፈጠራና ስብከት፤ በሰሜን ኮሪያ ቀልድ አይደለም። ራሱን የቻለ መስሪያ ቤት ተቋቁሞለት፤ በጀት ተመድቦለት፣ ካድሬዎችና ሰራተኞች የሚሰማሩበት ዋና ስራ ነው። ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሌሎች ስራዎችም አሉ። የገፅታ ግንባታ ዘመቻዎችን ያደናቅፋሉ፤ ወይም ለማደናቀፍ ያስባሉ ወይም ለማደናቀፍ ሊያስቡ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ባለስልጣናትን፤ ካድሬዎችንና ተራ ዜጎችን እየለቀመ ወይም እያፈሰ ወደ ግድያና እስር የሚወስድ ሌላ መስሪያቤትና ሌላ በጀት ይኖራል።

ለፕሮፓጋንዳና ለአፈና፤ ለሚሊዮን ጦር ሰራዊትና ለኒኩሌየር ቦምብ ግንባታ፤ ብዙ ገንዘብና ጊዜ የሚባክነው፤ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰሜን ኮርያዊያን በረሃብ እያለቁ በነበረበትም ጊዜ ጭምር ነው። በተለይ ከ15 አመታት ወዲህ፤ እንደማንኛውም ኮሙኒስት አገዛዝ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይበልጥ እየደቀቀ፤ ድህነትና ረሃብ እየከፋ መጥቷል። እዚያው አጠገባቸውኮ፤ ወንድሞቻቸው ደቡብ ኮሪያዊያን በብልፅግና ሲገሰግሱ አለም በአድናቆይ ያያቸዋል።

የአንድ አገር ልጆች የነበሩት ኮሪያዊያን፤ የዛሬ 60 አመት ገደማ በተቃራኒ ጎዳና መጓዝ ከጀመሩ ወዲህ የተፈጠረው ልዩነት ሲታይ፤ እውነትም የሰው “እጣ ፈንታ”፤ በዘር ወይም በቋንቋ፤ በመልክአምድር ወይም በተፈጥሮ ማእድን የሚወሰን እንዳልሆነ በግልፅ ይመሰክራል። የሰው ትልቁ ሃይል አእምሮው አይደል? አእምሮና የአእምሮ ስራ ነው ወሳኙ። የአስተሳሰብ ትክክልነትና ስህተትነት ነው የስኬትና የውድቀት ምንጩ።

“ለራስህ ጥቅም ሳይሆን፤ ለህዝብ፤ ለአገር፤ ለጭቁኖች መስዋእት መሆን አለብህ” በሚል ስብከት ላይ የተመሰረቱ፤  እንደኮሙኒዝምና ሶሻሊዝም የመሳሰሉ የክፉትና የስህተት አስተሳሰቦችን የተከተለ ማህበረሰብ፤ በእስርና በግድያ፤ በድህነትና በረሃብ ይሰቃያል፤ ያልቃል። በአፈና፤ አብሮ እያጨበጨበና አብሮ እያለቀሰ መከራውን ያያል።

ራሱን ለሌሎች ጥቅም እንዲሰዋ የማይገደድበት፤ ሌሎችንም ለራሱ ጥቅም መስዋእት እንዲሆኑ የማያስገድድበት፤ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ጥረት፤ የራሱን ህይወት ማሻሻል የሚችልበት፤ ሁሉንም ሰው እንደየስራው እየመዘነ በጋራ ፍቃደኝነት ላይ በተመሰረተ የንግድ ትብብርና የጓደኝነት ፍቅር ደስታ የሚያገኝበት ፍትሃዊው አስተሳሰብ ደግሞ፤ ወደ ብልፅግና ያደርሳል። ይሄው ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው የካፒታሊዝም  ስርአት ስረ መሰረት። የነፃነት ስርአት ልትሉት ትችላላችሁ - አስኳሉ የግለሰብ መብት (የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት) ነውና። በአመዛኙ የካፒታሊዝምን የብልፅግና መንገድ የተከተለችው ደቡብ ኮሪያን ተመልከቱ።

ሰሜን ኮሪያዊያን በረሃብና በአፈና ሲያልቁ፤ ደቡብ ኮሪያዊያን በሳይንስና በቴክኖሎጂ፤ በምርትና በቢዝነስ ግስጋሴያቸው ወደ ብልፅግና ተሸጋግረዋል። እንደ ኢትዮጵያና እንደ ሰሜን ኮሪያ ከድህነት ወለል በታች በነበረችው ደቡብ ኮሪያ ውስጥ፤ አማካይ የአንድ ሰው አመታዊ ገቢ፤ በ30 አመታት ውስጥ ከ10 እጥፍ በላይ በማደግ 17ሺ ዶላር ገደማ ደርሷል። ከቻይና ጋር ሲነፃፀር እንኳ በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

 

 

Read 4770 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:41

Latest from