Saturday, 02 August 2014 11:04

መኢአድና አንድነት ለውህደት ማስፈፀሚያ የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

1ሚ. ብር ያስፈልጋል ተብሏል ፓርቲዎች ውሁዱን ፓርቲ እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ

         ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የቅድመ - ውህደት መግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የመጨረሻውን ውህደት ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ የመጨረሻ ውህደቱ በመጪው ሳምንት እንደሚፈፀምም የሁለቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ በመኢአድ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ “የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱን ለማስተናገድ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ገደማ ያስፈልጋል” ያሉት የአንድነት ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ የባንክ ሂሳብ ከፍተን ከአባላትና ውህደቱን ከሚፈልገው ህዝብ ገንዘብ ለማሰባሰብ የወሰንነው የውህደቱ ወጪ በአመታዊ የፓርቲዎቹ ወጪ ውስጥ ባለመካተቱና አዲስ የገንዘብ ምንጭ ስለሚያስፈልገው ነው ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ከ 97 ዓ.ም ወዲህ የፓርቲዎችን የፋይናንስ አቅም በማዳከም የትግሉን ሂደት ለማደናቀፍ እየተጋ ነው ያሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ፤ ለዚህም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲመሩበት የወጣው አዋጅ በቂ ማስረጃ ነው ብለዋል፡፡

ገንዘብ ለማሰባሰብ የተነሳችሁበት ጊዜና ውህደቱ የሚፈፀምበት ቀን ተቀራራቢ ከመሆኑ አንፃር የተፈለገው ገንዘብ ባይገኝ እንዴት ትሆናላችሁ? በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ የፓርቲዎቹ አመራሮች ሲመልሱ፤ “ምንም እንኳ የባንክ ሂሳቡን ዛሬ ይፋ ብናደርግም ቀደም ብለን በዚሁ ጉዳይ ላይ ስንሰራ ነበር፤ ህዝቡ መዋሃዳችንን ስለሚፈልገው ገንዘቡ አይገኝም የሚል ስጋት የለንም” ብለዋል፡፡ “ገንዘቡ ባይገኝ እንኳን እቅድ “ሀ”፣ እቅድ “ለ” ብለን የያዝናቸው ፕሮግራሞች ስላሉ፣ ውህደቱ በፍፁም አይቀርም በማለት አስረድተዋል፡፡ ለውህደቱ ሁለቱም ፓርቲዎች ቅዳሜ የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ከተወያዩ በኋላ በነጋታው እሁድ ከእያንዳንዳቸው 200 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በድምሩ 400 አባላት በተገኙበት ውህደቱ እንደሚፈፀምም ተናግረዋል፡፡

“ዲሞክራሲያዊ በሆነ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች በጀት የሚመደበው በመንግስት ነው” ያሉት አቶ አበባው መሃሪ፤ መንግስት ሰጠሁ ለማለት ብቻ ለመኢአድ 3,500 ብር ሰጥቶን በኦዲት 16 ሺህ ብር ተወስዶብናል ብለዋል፡፡ “ለደጋፊ ፓርቲዎችና ለተለጣፊዎች ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚሰጥ መረጃው አለን” ሲሉም ተናገረዋል፡፡ ውህደቱ እንዲፈፀም የታቀደው ሐምሌ 5 እና 6 ቀን 2006 ዓ.ም የነበረ ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ወደ ነሐሴ 3 እና 4 ለማራዘም መገደዳቸውን ፕሬዚዳንቶቹ ተናግረዋል ገልፀዋል፡፡ “ኢህአዴግ ውህደቱ እንዳይፈፀም የተለያየ ጫና እየፈጠረብን ነው” ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ በቅድመ ውህደቱ ፊርማ ጊዜ ሰርጎ ገቦችና የኢህአዴግ ካድሬዎች አባል በመምሰል ውህደቱን ሊያውኩ መሞከራቸውን በማየታችን የፀጥታ ኮሚቴ አቋቁመዋል ብለዋል፡፡

አሁንም ለውህደቱ እንደ ስጋት የሚያነሱት ጉዳይ እንዳለ የጠቆሙት ኢ/ሩ፤ “ምርጫ ቦርድ አነስተኛና ጥቃቅን ምክንያት እየፈጠረ ውህደቱን ሊያራዝምብን ይችላል፤ ለዚህም አንዳንድ ምልክቶች እያየን ነው” ብለዋል፡፡ ሆኖም ማናቸውንም ጫናዎችና እንቅፋቶች ተቋቁመን ውህደቱ ይፈፀማል ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ እኛ በመዋሃድ ስንጠናከር በዚህች አገር የፖለቲካ ምህዳር ላይ የምንፈጥረው ተፅዕኖ ኢህአዴግን ስለሚያስፈራው፣ በየአቅጣጫው የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ሳይበግረው ህዝቡ የገንዘብና የሞራል ድጋፉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ወደ 75 የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተመዘገቡ የጠቆሙት ኢ/ሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ በትክክል ስራ ላይ ያሉና የሚንቀሳቀሱት ከ10 አይበልጡም፤ ሌሎቹ ምን እየሰሩ እንደሆነ አይታወቅም ብለዋል፡፡ በዚህች አገር ላይ ትልቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር በተናጠል መሮጥ እንደሆነ የገለፁት የአንድነት ፕሬዚዳንት፤ ቢያንስ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ 10 ትክክለኛ ፓርቲዎች ውህዱን ፓርቲ እንዲቀላቀሉና በተጠናከረ ኃይል እንዲታገሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

Read 3136 times