Saturday, 02 August 2014 11:45

ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ክትባቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የህፃናትንና እናቶችን ህይወት ከበሽታ ለመከላከል የሚጠቅሙ ወሳኝ የበሽታ መከላከያ ዘርፍ ናቸው። ከክትባቶች ግኝት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክትባት መከላከል የምንችላቸው በሽታዎች ስርጭትና ስፋት እጅጉን ቀንሷል። ክትባት የሚሰጠው ጤነኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በክትባት መከላከል የምንችላቸውን በሽታዎች ለመከላከል ስለሆነ ጥራቱ እና ደህንነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ ክትባት በሚሰጥበት ወቅት ቀላል የሆኑ ክስተቶች ለምሳሌ ትኩሳት፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ የማበጥ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ባይሆንም ከፍተኛ የጐንዮሽ ጉዳት እንደ አለርጂ፣ እራስን የመሳት ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን መጠንና ጉዳት ለመቀነስ በክትባቶች ምክንያት ስለሚመጡት ጉዳቶች መገንዘብና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ማለት ማንኛውም ከክትባት በኋላ የሚከሰት የጤና ችግር፣ የሚያሰጋ እና በክትባት ምክንያት እንደተከሰተ የሚታመን ወይም የሚገመት የጤና ችግር ማለት ነው። ይህ ማለት እውነተኛ በክትባት ምክንያት የመጡ የክትባት ችግሮች ወይም በአጋጣሚ በዚያን ወቅት የሚከሰቱ ሌላ የጤና ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያመቸን ክስተቶቹን በመከፋፈል እናያቸዋለን፡፡
በክትባት ምክንያት የሚከሰቱ የጐንዮሽ ጉዳቶች
የክትባቶች ዋነኛ ጥቅም በሰውነት ውስጥ በሽታ የመከላከል አቅምን ማጐልበት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለሰውነት ባእድ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነት ስለሚገቡ ሰውነትም በአንፃሩ ለባእድ ነገሩ ምላሽ ወይም መከላከያ ለመስጠት በሚዘጋጅበት ወቅት የተለያዩ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች የክትባት መድኃኒቱ ተፈጥሮአዊ ይዘት፣ ተጨማሪ ንጥረ ነገር እና የክትባት መድኃኒት እንዳይበላሽ ወይም ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ የሚያደርጉት ኬሚካሎች የተነሳ የሚመጡ ናቸው። እነዚህም - ትኩሳት፣ እብጠት፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ መቅላት፣ መነጫነጭ፣ የምግብ ፍላጐት መቀነስ፣ ህመም እና ሌሎችም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የጐንዮሽ ጉዳቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰቱት ክትባቱ በተሰጠበት ቀንና በሁለተኛው ቀን ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እስከ ጥቂት ቀናት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
የፕሮግራም ስህተቶች
የፕሮግራም ስህተት የምንላቸው በክትባት አያያዝ፣ አቀማመጥ፣ ዝግጅትና አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ስህተቶችና አደጋዎች ናቸው። በፕሮግራም ስህተት የሚፈጠሩ ክስተቶች በብዛት በአንድ ቦታ ሊከሰት የሚችል ነው። ይህም በተወሰነ ባለሙያ፣ ጤና ተቋም ወይም የክትባት ብልቃጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። በፕሮግራም ስህተት ምክንያት ከሚፈጠሩ ክስተቶች መካከል ዋነኛው ብክለት (infection) ንፅህናው ባልተጠበቀ መርፌ ምክንያት የሚከሰት ነው። ይህም መግል የያዘ እብጠት፣ ለደም ብክለት (sepsis), በደም ንክኪ ምክንያት ለሚተላለፉ በሽታዎች (ኤችአይቪ እና የጉበት ቫይረሶች) የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡ እነዚህ ስህተቶች በሚከሰቱበት ወቅት በባክቴሪያ ብክለት ምክንያት ከሆነ ምልክቶቹ በሰዓታት ውስጥ የሚታዩ ሲሆኑ እነዚህም ምልክቶች፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ ሲነካ የህመም ስሜት፣ ትውከት፣ ተቅማጥና ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት ናቸው፡፡
በአጋጣሚ (ከክትባቱ ውጪ) የሚፈጠሩ ክስተቶች
እነዚህ ክስተቶች በጊዜ አጋጣሚ ከክትባቱ ጋር የሚከሰቱና በስህተት ከክትባት ጋር የሚያያዙ ናቸው። ይህም ማለት ክስተቱ በአጋጣሚ ክትባቱ በተሰጠበት ወቅት ይፈጠር እንጂ በክትባቱ ምክንያት የተከሰተ ስላልሆነ ክትባቱ ባይሰጥም መከሰቱ የማይቀር ነው። በዚህም ምክንያት የተለያዩ ክስተቶች ሞትንም ጨምሮ በክትባት ምክንያት እንደተፈጠረ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ክስተቱ በጊዜ አጋጣሚ የሚፈጠር በመሆኑ ጥልቅ ምርመራ ሊደረግበት ይገባል፡፡
መርፌ በመወጋት ምክንያት የሚፈጠሩ ክስተቶች
የተለያዩ ሰዎች ወይም ግለሰቦች መርፌ ለመወጋት ሲሉም ሆነ ከተወጉ በኋላ በፍርሃት ምክንያት የሚፈጠርባቸው ክስተቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ እራስን መሳት ነው፡፡ ይህ ክስተት ከክትባት ይዘቱ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይህም በብዛት የሚከሰተው ከአምስት አመት በላይ በሆኑ ህጻናት ላይ ነው፡፡    
ከክትባት በኋላ የሚያጋጥሙ ክስተቶች መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች
ሀ. በጤና ባለሙያዎች
ለክትባት መድኃኒቱ አለርጂ ያላቸውን ቀድመው መለየት፣
ለህፃናት ወላጆችና አሳዳጊዎች ስለ ክትባቱ ባህሪ ማስተማርና መምከር እንዲሁም የትኞቹ ምልክቶች ሲከሰቱ ወደ ጤና ተቋም መምጣት እንዳለባቸው ማስገንዘብ፣
በፕሮግራም ስህተት ምክንያት የሚፈጠሩ ክስተቶችን መለየትና ማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣
በክትባት ብልቃጥ ብክለት የተከሰተ ከሆነ ለባክቴሪያ ምርመራ ወደሚመለከታቸው አካላት መላክ፣
የሚበጠበጡ ክትባቶችን በአምራቹ ምርት ብቻ መበጥበጥ እንዲሁም ከተበጠበጡ ከስድስት ሰዓት በኋላ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ፣
ክትባቶች የሚቀመጡበት ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ ሌላ መድኃኒት አለማስቀመጥ፣
ለክትባት ተብለው የሚዘጋጁ መመሪያዎችን በደንብ መገንዘብና ተግባር ላይ ማዋል፣
ተገቢውን የክትባት ትምህርት እና ክህሎት ስልጠና መውሰድ፣
ከክትባት በኋላ የሚከሰቱ ክስተቶች ሲፈጠሩ ወዲያውኑ ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት ማድረግ እንዲሁም ምርመራ በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣
ለ. በህፃናት ወላጆችና አሳዳጊዎች
በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክርና ትምህርት መከታተልና መተግበር፣
ድንገተኛ እና ያልታሰበ ምልክት ሲያዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ፣
ለህፃናት የሚሰጠውን የክትባት ምንነት፣ የሚከላከለው የበሽታ አይነት፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችንና መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ከጤና ባለሙያዎች መጠየቅ፣
ምንጭ፡-
የዓለም ጤና ድርጅት ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶ ቅኝት መመሪያ
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ቅኝት መመሪያ በኢትዮጵያ
WHO-Vaccine Safety Basics Learning Manual

Read 7705 times