Saturday, 02 August 2014 11:47

ችላ የተባለው የወንዶች ግርዛት!

Written by  ሣሙኤል ልጅዓለም ሐሰን
Rate this item
(14 votes)

የኤችአይቪን ሥርጭት ለመግታት አንዱ መላ የወንዶች ግርዛት ሆኗል
የወንዶች ግርዛት በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደና እንደ ባህልም - እንደ ግዴታም የሚወሰድ ጉዳይ ነው፡፡ ያልተገረዘ ወንድ ልጅ በጓደኞቹም ሆነ በሌሎች የሕብረተሰቡ አባላት የ“መተረብና” አንዳንዴም የመንቋሸሽ ዕጣ ያጋጥመዋል - ቅጽል ስምም ይወጣለታል፡፡ በዚህ ምክንያት “ህመም አይሰማቸውም፤ ቁስሉም አይፀናባቸውም፤ ከእናቶቻቸው ጋር በአንድነት ይታረሣሉ” በሚል አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊ ወላጆች ወንድ ልጆቻቸውን በተወለዱ በሰባት ቀናቸው ያስገርዛሉ፡፡ ይሄ እሰየው የሚያሰኝ ከብዙ ሌሎች አገሮች የተለየ ልምድና ባህላችን ነው፡፡ ይህ በብዙ አገሮች የማይታይ ልምድና ባሕላችን በተለይ በዚህ የኤድስ ዘመን ለየት ያለ ፋይዳ ነው ያለው፡፡
ይሁንና፣ አሁን አሁን (ከኤድስ ክስተት በኋላ) አንዳንዴ ሰዎች እየፈሩ ወንዶች ልጆቻቸውን በዘመናዊ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ውስጥ እንኳን ማስገረዝን ችላ ማለት ጀምረዋል፣ አንዳንዶች እንዲያውም ልጆቻቸውን ጨርሶውንም አያስገርዙም፡፡
ወንድ ልጆችን ያለማስገረዙ ውሣኔ/አዝማሚያ አብዛኛው ህዝብ በሚኖርበትና አብዛኛው የሕክምናም ሆነ የግርዛት ስራ በባህላዊ ሀኪሞች በሚከናወንበት የገጠር አካባቢ ነዋሪ ወላጆችም ዘንድ እጅግ ተጠናክሮ እንደሚገኝ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ - ይህ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሕይወት ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ታላቅ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ከኤድስ ፍራቻ በተጨማሪ፣ በተለይም በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች፣ ወንዶች ልጆቻቸውን እንዳያስገርዙ የሚያደርጉ አንዳንድ ሁኔታዎችም ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች አንዱ በመላው አለም በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ዘመናዊነት ነው፡፡
 ዘመናዊነት፣
1ኛ/ ልጆች (ጓደኛሞች ተሰባስበው በአንድነት የሚፀዳዱበትን ሁኔታ አስቀርቷል፣ ብዙ ሰዎች በተናጠል ሽንት ቤት ውስጥ ለየብቻ መፀዳዳት በመጀመራቸው አንዱ ሌላውን ይገረዝ አይገረዝ የሚያውቅበት መንገድ ጠቧል፡፡
2ኛ/ ከዚህም የተነሣ ባልተገረዙ ወንዶች ላይ ይደርስ የነበረው መገለልና መድሎ (ስቲግማ ኤንድ ዲስክሪሚኔሽን) እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የተባበሩት መንግሥታት የኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት (UNAIDS)፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በአሁኑ ወቅት የኤችአይቪን ሥርጭት ለመግታት መላ ተገኘ በሚል የጦፈ ዘመቻ ከተያያዙበት አዲስ መፍትሔ መካከል  አንዱና ዋነኛው የወንዶች ግርዛት ሆኖአል።
እንደ ድርጅቶቹ እምነት፣ ወንዶች ከተገረዙ በኤች-አይ-ቪ የመያዛቸው አጋጣሚ በ60% ከመቶ ይቀንሳል፡፡
ይህ የሚሆንበት ዋንኛ ምክንያት፣
1ኛ/ ባልተገረዙ ወንዶች ብልት ጫፍ ላይ የሚንጠለጠለው ትርፍ ቆዳ የውስጠኛው ክፍል ስስና ርጥበታማ እንዲሁም በርካታ ሴሎች የተከማቹበት ከመሆኑ የተነሳ በኤችአይቪ በቀላሉ ሊጠቃ የሚችል በመሆኑ፣
2ኛ/ ይኸው ባልተገረዙ ወንዶች ብልት ጫፍ ላይ የሚንጠለጠለው ትርፍ ቆዳ የውስጠኛው ክፍል በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወቅት ሊያጋጥመው የሚችለውን ኤችአይቪ የያዘ ፈሳሽ ለብዙ ደቂቃዎች በውስጡ አቅፎ (አፍኖ) ስለሚቆይና በዚህም ቆይታ ወቅት ቫይረሱ ስስ ቆዳውን አልፎ ወደ ደም ውስጥ የሚገባበት ሰፊ ጊዜ እንዲያገኝ ስለሚረዳ ነው፡፡
የተገረዘ ብልት ግን ከላይ ከተጠቀሱት ለበሽታ የመጋለጥ አደጋዎች የተጠበቀ ነው፡፡
የወንዶች ግርዛት ወንዶች ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን በተለያየ ሁኔታና አጋጣሚ በወሲብ የሚጣመሯቸውን ሴት ጓደኞቻቸውን ሁሉ ከኤችአይቪ ጥፋት ይጠብቃል፡፡ የወንዶች ግርዛት ከዚህም ሰፋ ተደርጎ ሲታይ በመላው አገሪቱ የሚታየውን ፈጣን የኤችአይቪ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ነው፡፡ ስለዚህም ለረዥም ዘመናት የባህልና ልምዳችን አንዱ ክፍል ሆኖ የኖረው የወንዶች ግርዛት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ።
ቸር እንክረም!  

Read 13448 times