Saturday, 09 August 2014 11:07

የጸጉር ጤና እንክብካቤና ፋሽን በአፍሪካ የቢሊዮኖች ዶላር ቢዝነስ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በደ/አፍሪካ ብቻ አምና ከ20 ቢ. ብር በላይ የሚያወጡ መዋቢያዎች ተሸጠዋል የአህጉሪቱ “የተፈጥሮ ጸጉር” አመታዊ ሽያጭ ከ120 ቢ. ብር በላይ ደርሷል

         የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በአፍሪካ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ንግድ እየሆነ መምጣቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡ በአህጉሪቷ እየተስፋፋ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ የህንድና የቻይናን ኩባንያዎች ከማሳተፍ ባለፈ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑትን “ሎሬል” እና “ዩኒሊቨር” የመሳሰሉ የፋሽንና የውበት ኩባንያዎች ወደ አህጉሪቷ እንዲገቡ ማድረጉን ነው ዘገባው የገለጸው፡፡ የአፍሪካ ሴቶች የጸጉራቸውን ጤንነት የመጠበቅና የዘመኑን አለማቀፍ የጸጉር ፋሽን የመከተል ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፣ በአህጉሪቱ የተለያዩ አገሮች በመስኩ የሚሰሩ አገር በቀል ድርጅቶች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን እነ “ኦግሎብ”ን የመሳሰሉ ታዋቂ አለማቀፍ ኩባንያዎችም በአህጉሪቱ በስፋት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡

ዩሮ ሞኒተር ኢንተርናሽናል የተባለ አለማቀፍ የገበያ ጥናት ተቋም ያወጣው የጥናት መረጃ እንደሚለው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት በደቡብ አፍሪካ ብቻ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጸጉር ውበት መጠበቂያና መዋቢያ ሻምፖዎች፣ ሎሽኖችና ማለስለሻዎች ለገበያ ቀርበው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡በናይጀሪያና በካሜሩን የፈሳሽ የጸጉር ቅባቶችና ውበት መጠበቂያዎች ገበያ ከአመት ወደ አመት እያደገ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በመላ አህጉሪቱ ያለው አመታዊ የተፈጥሮ ጸጉር ሽያጭም 6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል፡፡

ታዋቂዋ ናይጀሪያዊት ድምጻዊት ሙማ ጊ በቅርቡ ከ56 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ አንድ የተፈጥሮ ጸጉር ከነመዋቢያው እንደገዛች ብዙሃን በይፋ መናገሯን በዋቢነት የጠቀሰው ዘገባው፤ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ከ100 በላይ የተለያዩ አይነት የንግድ ምልክቶች ያሏቸው የተፈጥሮ ጸጉር አይነቶች በገበያ ላይ እንደሚገኙና አመታዊ ሽያጩም 600 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውሷል፡፡ በመላ አፍሪካ እያደገ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ሴቶች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠሩንና በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በናይጀሪያና በአንዳንድ አገራት የቤት ለቤት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር መጀመሩን ገልጧል፡፡

Read 3919 times