Saturday, 09 August 2014 11:07

ካውንስሊንግና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞቹ

Written by  ወንድወሰን ተሾመ (የማህበራዊ ሳይንስና የስነ ልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(2 votes)

 

         ማህሌት ስለ ስነ ልቦና ዕርዳታ (ካውንስሊንግ) ማወቅ በጣም ጓጉታለች፡፡ በተለይ ካውንስሊንግ ለማን ነው? የሚለው ጥያቄ ያብሰለስላት ነበር። መጪውን አዲስ ዓመት ማለትም 2007ን ውጤታማ ሆና ለመኖር ስለ ግብ መተለምና እቅድ ማውጣት እንዲሁም ግብ ላይ ለመድረስ መከተል ስላለባት መርህዎች ለማወቅ ጊዜ ወስዶ አቅጣጫ ሊያሳያት የሚችል ሰው ስትፈለግ ነበርና፣ ለመሆኑ ካውንስሊንግ የሚባለው የሙያ ዘርፍ ይሄ ይመለከተዋል ወይ? የሚል ጥያቄ አነሳች፡፡ “ካውንስሊንግ ምን ምን ያካትታል? ለማን ነው? ” የሚለው ጥያቄ የብዙ ሰዎች ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በመሆኑም በዚህ አጭር ፅሁፍ ካውንስሊንግ ምንድነው?የካውንስሊንግ ተጠቃሚ ማን ተብሎ ይጠራል? የካውንስሊንግና የምክር አገልግሎት ልዩነታቸው ምንድነው? የካውንስሊንግ ግብ ምንድነው? የካውንስሊንግ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ካውንስለሮችስ? ካውንስለሮች ከማን ጋር ይሰራሉ? በሚሉ አጫጭር ርዕሶች አብረን እንዘልቃለን፡፡

ካውንስሊንግ ምንድነው? ካውንስሊንግ ሰዎች ምርጫቸውን የሚወስኑበትና እንዲተገብሩት የሚያስችል በስነ ልቦና ባለሙያ ወይም በሙያው በሰለጠነ ሰው የሚደረግ እገዛ ሲሆን ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት ያስፈልገዋል፡- አገልግሎቱን የሚፈልግ ሰው(client) አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ፣የሰለጠነና(trained) አገልግሎቱን መስጠት የሚችል (capable) ባለሙያ፣ አገልግሎቱን ለመስጠትና ለመቀበል የሚያስችል ቦታ(setting) የካውንስሊንግ ተጠቃሚ ማን ተብሎ ይጠራል?፣ ደንበኛ? ህመምተኛ? ደንበኛ፡- በእኛ አገር ደንበኛ(Customer) ስንል አዘውትሮ አገልግሎታችንን የሚጠቀም ሰው ለማለት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አገልግሎት ሰጪውም “ደንበኛውን” በተቻለ መጠን ደጋግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በካውንስሊንግ ደግሞ ሰው ችግሩን እንዲፈታ ወይም የእውቀትና የክህሎት ባለቤት እንዲሆን እገዛ ተደርጎለት መፍትሄ አግኝቶ እንዲሄድ እንጂ ደጋግሞ እንዲመጣ አይፈለግም፡፡

ችግሩን ለመፍታት ወይም የሚፈልገውን አውቀትና ክህሎት ለማግኘት የሚስፈልገው የጊዜ መጠን በባለሙያው ተሰልቶና ቀርቦ፣ አገልግሎቱን በሚጠቀመው ሰው እና በባለሙያው መካከል በጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ የካውንስሊንጉ አገልግሎት ከሚወስደው የጊዜ መጠን ውጪ “ደንበኝነት” የለም፡፡ ስለዚህ ለካውንስሊንግ ተጠቃሚ “ደንበኛ” የሚለውን ቃል መጠቀም ለባለሙያዎች የሚከብድ ይመስላል፡፡

አንዳንዴ ግን ለአንባቢ ተጠቃሚውን ለመግለፅ በእንግሊዘኛው “client” የሚል ቃል የምንጠቀምበት ጊዜ አለ፡፡ ይህም ሰዉ እስኪለምደው ለጊዜያዊ ብቻ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ካውንስሊንግ ሰዎችን ደንበኛ የማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ካውንስሊንግ ሰዎች ሰለ ራሳቸው፣ ስለህይወት ወይም ስለ ሌሎች ሰዎች ያላቸውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በመስራት የተፈጠረባቸውን ስነልቦናዊ ክፍተት ወይም እውቀትና ክህሎት በማሟላት ያልተጠቀሙበትን አቅማቸውን (untapped potentials) እንዲያወጡ፣ ከሌሎች ጋር በአግባቡ እንዲኖሩ፣ስሜታቸውን፣ ሃሳባቸውንና ባህሪያቸውን በአግባቡ እንዲቆጣጠሩ በመርዳት ብቃትን ያጎናፅፋል እንጂ ጥገኛ(ደንበኛ) አያደርግም። ስለዚህ የካውንስሊንግ ተጠቃሚ ደንበኛ አይደለም። ህመምተኛ፡- የካውንስሊንግ ተጠቃሚ ህመምተኛ(patient) ተብሎ አይጠራም:: ህመምተኛ የሚለው ቃል የህክምና ሞዴል (medical model)ነው፡፡ ይህንን ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ይጠቀሙበታል፡፡ በካውንስሊንግ ይህንን መጠቀም አይቻልም። አገልግሎቱን ፈላጊ ሰው የስነ ልቦና ድጋፍ የሚፈልግ እንጂ ህመምተኛ አይደለም፡፡ በተለይ ህመምተኛ የሚለው ቃል አሉታዊ መልእክትም ስላለው የሰዎችን ስነልቦና አይገነባም፡፡ የመሰረታዊ ካውንስሊንግ ሥልጠና በምሰጥበት ጊዜ ከሰልጣኞች መካከል አንዲት እናት (ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂስት ናት) በአንድ ሆስፒታል የእርግዝና ክትትል ስታደርግ “patient’s Name” ተብሎ ስሟ ተፅፎ እንደተሰጣትና ይህም “እኔ እርጉዝ ነኝ እንጂ በሽተኛ አይደለሁም” የሚል ሃሳብ በአዕምሯ ውስጥ እንደፈጠረባት ነግራናለች፡፡ በተጨማሪም ካውንስሊንግ የሚሰጠው የስነልቦና ክፍተት ላለባቸውና ለሌለባቸው ነገር ግን ውጤታማ ህይወት ለመኖር ለሚፈልጉ ሰዎች ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ማህሌት ስለ ግብ ማስቀመጥና ዕቅድ ማውጣት (ለማወቅ፣ ወደ ካውንስሊንግ አገልግሎት ማዕከል ብትመጣ ህመምተኛ ልንላት እንችላለን? አንችልም -አይደለችምና ፡፡

ካውንስሊንግ ለሁሉም ሰው ሊያስፈልግ የሚችል አገልግሎት በመሆኑ የ ካውንስሊንግ አገልግሎት ተጠቃሚ በሽተኛ አይባልም፡፡ ክሊያንት፡- በዓለምአቀፍ ደረጃ የስነልቦና ባለሙያዎች የሚጠቀሙት ክሊያንት(Client) የሚለውን ቃል ነው፡፡ ይህም “ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎችንም ድርጅቶችንም ያካትታል፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት የካውንስሊንግ አገልግሎትን አንዴም ይሁን ከዚያ በላይ ቢጠቀም ክሊያንት እንለዋለን፡፡ በመሆኑም የካውንስሊንግ ተጠቃሚ ማን ተብሎ ይጠራል ለሚለው ጥያቄ መልሱ ክሊያንት ይባላል ነው፡፡ አማርኛ ትርጉም ብናገኝለት ደግሞ በጣም ይመረጣል፡፡ የካውንስሊንግና የምክር አገልግሎት ልዩነታቸው ምንድነው? ካውንስሊንግ መደበኛ ነው (Formal ነው)፣ በሰለጠነ ባለሙያ ይሰጣል፣ ቅድመ ሁኔታዎች አሉት፣ መርህዎችን ይከተላል፣ ቴክኒኮች አሉት፣ምቹ ስፍራና ሁኔታ ያስፈልገዋል፣ካውንስለሩ አማራጭ አቅራቢ(option giver) ነው እንጂ “አድርግ አታድርግ” በማለት ትዕዛዝ ሰጪ አይደለም(prescriber አይደለም)፡፡ ምክር መደበኛ(Formal) ወይም ኢ - መደበኛ(informal) ሊሆን ይችላል፤ በባለሙያ(professional) ወይም ባለ ሙያ ባልሆነ ሰው(non professional) ሊሰጥ ይችላል፣ ቅድመ ሁኔታ ላይከተል ይችላል፣ ቴክኒክ ላይኖረው ይችላል፤የትም ቦታ(ቦታ ሳይመርጥ) ሊሰጥ ይችለል። ስለዚህ የካውንስሊንግ አገልግሎትን የምክር አገልግሎት ብሎ መጥራት አግባብ አይደለም። ካውንስለሩንም “አማካሪ” ብሎ መጥራት የሚሰጠውን አገልግሎት አይገልፀውም። በነገራችን ላይ ካውንስሊንግና ምክር ከላይ ከተጠቀሱት ልዩነቶች ባለፈ ልዩነት አላቸው፡፡

የካውንስሊንግ ግብ ምንድነው? ካውንስሊንግ ሶስት ዋና ዋና ግቦች አሉት የመከላከል ግብ(Prevention):- ካውንስሊንግ የመከላከል ግብ አለው። ለምሳሌ አንዲት አዲስ አበባ ተውልዳ ያደገች ልጅ ዩኒቨርሲቲ እንድትገባ የሚያስችላትን ነጥብ አግኝታ፣ ክፍለ ሀገር በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ብትመደብ፣ በተመደበችበት ዩኒቨርሲቲ እንዴት መኖር እንደሚገባትና በትምህርቷ ውጤታማ ለመሆን ልትከተለው የሚገባትን የስሜት፣ የአስተሳሰብና የባህሪ ደረጃ በካውንስሊንግ ልታገኝ ትችላለች፡፡ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ:- ወደ አረብ አገራት ወይም ወደ ተለያዩ አገራት የሚሄዱ ዜጎች የቅድመ መከላከል ካውንስሊንግ (prevention counseling) በመውሰድ ስለሚሄዱበት አገር ካላቸው ስሌት(Expectation) ጀምሮ ሊከተሉት ስለሚገባ የስሜት፣የሃሳብና የባህሪ ደረጃ ክህሎቶችንና እውቀቶችን በካውንስሊነግ ሊያገኙና ህይወታቸውን የተሻለ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችል የስብዕና አቋም ማግኘት ይችላሉ። በልጆች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ወላጆችና ከልጆች ጋር የሚሰሩ ባለሙያዎች ካውንስሊንግ በመውሰድ፣ ልጆቻቸው ራሳቸውን የሚጠብቁበትን ዕውቀትና ክህሎት ሊያስታጥቋቸው ይችላሉ፡፡ ቤተሰብ በሰላም እንዲኖርና የቤተሰቡ አባላት ውጤታማ ህይወት እንዲኖሩ አግባብ ያልሆኑ ባህሪያትን (dysfunctional behaviors) የመከላከል ግብ ያለው ካውንስሊንግ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም አንዱ የካውንስሊንግ ግብ መከላከል ነው። የማሳደግ ግብ ( Developmental) አንዱ የካውንስሊንግ ግብ ክሊያንቱን ማሳደግ ነው፡፡

ክሊያንቱ ሰው ወይም ተቋም ሊሆን ይችላል። ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ የሚሰጥ የካውንስሊንግ አገልግሎት አለ፡፡ ለምሳሌ ማህሌትን እንውሰድ፡- ማህሌት ዘንድሮ በኖረችበት መልኩ የሚቀጥለውን ዓመት ለመኖር አልፈለገችም። “ሁልጊዜ የምትሰራውን ሥራ አሁንም የምትሰራ ከሆነ፣ ሁልጊዜ የምታገኘውን ውጤት አሁንም ታገኛለህ” የሚለውን አባባል በደንብ የተረዳች ትመስላለች-ማህሌት። ስለዚህ ስለ ግብ ማስቀመጥና ስለ ዕቅድ ማውጣት በካውንስሊንግ አገልግሎት በማግኘት ለእድገቷ ትጥራለች። ለምሳሌ ካውንስለሩ ፍላጎቷን፣ችሎታዋንና አካባቢዋን በደንብ እንድትረዳ በማድረግ፣ የአመቱን ግቧን እንድትለይ በመርዳት ለዚያ ደግሞ ውሱን(specific)፣የሚለካ (measurable)፣ ሊፈፀም የሚችል (achievable)፣ተአማኒነት ያለው (reliable)፣ እና በጊዜ የተገደበ (time bound) የሆነ ግብ እንዲሆን ክህሎትን በማስታጠቅ ማድረግ የሚገባትን በካውንስሊንግ አገልግሎት ታገኛለች። በመሆኑም የተለያዩ የክህሎት ክፍተት ያለባቸው ሰዎች ከካውንስሊንግ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡ የማስተካከል ግብ (Remedial)፡- ሶስተኛው የካውንስሊንግ ግብ የማስተካከል ግብ ነው፡፡ ይህም ማለት በሰዎች ላይ በተለያዩ ምክኒያቶች የስሜት፣ የሃሳብና የባህሪ ችግሮች በሚደርስበት ጊዜ ወደ ካውንስሊንግ አገልግሎት በመምጣት ክሊያንቱ ወደ ቀድሞው ህይወቱ እንዲመለስ የማድረግ ስራ ነው።

በአንድ ወቅት የ 8 ዓመት ልጅ ባጋጠመው ሁኔታ (event) ምክኒያት በወላጆቹ ለካውንስሊንግ አገልግሎት መጥቶ የቅበላ ቃለ መጠይቅ ካደረግሁለት በኋላ “ከዚህ የካውንስሊንግ አገልግሎት ምን ትጠብቃለህ?” በማለት የካውንስሊንጉን ግብ እንዲነግረኝ ጠየኩት። መልሱ አጭር ነበር “ ወደ ቀድሞው ሁኔታዬ መመለስ” ነበር ያለኝ፡፡ ምላሹን የሰጠበት ፍጥነትና የሃሳቡ ፍንትውታ አስገርሞኛል። በመጣበት ጊዜ ያለበት ሁኔታ ትምህርት ቤት መሄድ መፍራት፣ መጫወት መጥላት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትና መቃዠት ስለ ነበር፣ ከዚህ ወጥቶ እንደ ቀድሞው ትምህርት ቤት መሄድ መውደድ፣መጫወት፣ ምግብ ደስ ብሎት መብላትና እንቅልፉን በአግባቡ መተኛት ማለቱ ነው፡፡ በቤተሰብ አባላት ሞት፣በመኪና አደጋ፣በኑሮ ውጥረት፣ በሥራ ጫና፣ ከሌሎች ጋር ባለ ግንኙነት ወዘተ ስነልቦናዊ ችግር ሊገጥመን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ የስነ ልቦና ድጋፍ ለማግኘት ካውንስሊንግ አገልግሎትን በመጠቀም ስነ ልቦናዊ ጤንነትን መጎናጸፍ ይቻላል። የካውንስሊንግ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? የካውንስሊንግ ተጠቃሚዎች ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ቤተሰብ እና ተቋማት/ድርጅቶች/ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ካውንስለሮች እነማን ናቸው? ሰዎችን በማገዝ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን (helping professionals) በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ፕሮፌሽናልስና ፓራ ፕሮፌሽናልስ (professionals and para- professionals) ተብለው ይመደባሉ፡፡

ፕሮፌሽናልስ የምንላቸው በቋሚነት የካውንስሊንግ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን እነዚህም ሳይኮሎጂስቶች፣ሳይካትሪስቶች፣ ፕሮፌሽናል ካውንስለሮች፣የጋብቻና የቤተሰብ ካውንሰለሮች ሲሆኑ ፓራ ፕሮፌሽናልስ የሚባሉቱ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜና በተወሰነ መጠን የካውንስሊንግ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህም የሃይማኖት ሰዎች፣ዶክተሮች፣ነርሶች፣ የማህበራዊ ስራ ሰራተኞች እና መምህራንን የሚያካትት ሲሆን በሁለቱም ጎራዎች ያሉ ባለሙያዎች የካውንስሊንግ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ይጠበቃል። የሁለቱ ጎራዎች መገናኛ ድልድይ ሰዎችን የመርዳትና የማገዝ ፍላጎታቸው እና ዓላማቸው ነው፡፡ በዚህም መሰረት የካውንስሊንግ ዕውቀት፣ክህሎት፣መርህና ሙያው የሚጠይቀውን ሚስጥር ጠባቂነት በተገቢው ደረጃ የሰለጠኑና አቅም ያላቸው ባለሙያዎች የአገራቸውን ባህል፣ ህግና ደንብ ባገናዘበ መልኩ የካውንስሊንግ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። ካውንስለሮች ከማን ጋር ይሰራሉ? ከህክምና ተቋማት ጋር፡- የተለያዩ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ህክምና ተቋማት ይሄዳሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በመኪና አደጋና በሌሎች ምክኒያቶች አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች ጉዳታቸው ከአካላዊ ጉዳቱ ያልፍና ከደረሰባቸው ጉዳት(trauma) አንፃር ከፍተኛ የስነልቦና ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። በዚያን ጊዜ ሃኪሞች እነዚህን ሰዎች ወደ ካውንስለር ሊመሯቸው ይገባል። በካውንስሊንግ ያልተፈታውን ስነልቦናዊ ችግር ካውንስለሩ ወደ ሳይካትሪስቱ ይመራዋል። በተለይ ልጆች ወሲባዊ ጥቃት(Rape) ሲፈፀምባቸው ችግራቸውን ካውንስሊንግን ሳያካትት በህክምና ብቻ ለመፍታት መሞከር በልጆች ስነልቦናና ማህበራዊ ጤንነት ላይ ፋይዳ ያለው ውጤት አያመጣም። ከፖሊስና ፍትህ ተቋማት ጋር፡- ካውንስለሮች ከፖሊስና ከፍትህ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራሉ።

በተለይ በህፃናት ላይ ጥቃት ሲደርስና ሰዎች በህፃናት ላይ ግልፅ የጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ ካውንስለሮች ከነዚህ ተቋማት ጋር በጥምረት ይሰራሉ። ባለፈው ግንቦት ወር በአሜሪካ ሳይካሎጂካል አሶሴይሽን (APA) እና በአሜሪካ የጠበቆች ማህበር(American Bar Association) በጋራ ስፖንሰር በሆነ አንድ ኮንፍረንስ፤ የስነልቦና ባለሙያዎችና የህግ ባለሙያዎች ህፃናትን ከጥቃት የመከላከያ መንገዶች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ሳምንት በወጣው እና በአሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን በሚታተመው “Monitor on Psychology” መፅሄት ላይ እንደተገለፀው፤ በአሜሪካ በ የዓመቱ 676,000 ህፃናት አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም መገለል ይደርስባቸዋል። ከህፃናትና ከቤተሰብ ጋር ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር፡ ካውንስለሮች በስልጠናና በካውንስሊንግ አገልግሎት ከከእነዚህ ተቋማት ጋር የሚሰሩ ሲሆን በተለይ በእነዚህ ተቋማት የሚገኙ የማህበራዊ ሰራተኞች (social workers) እና ከልጆች ጋር የሚሰሩ ሌሎች ባለሙያዎች መሰረታዊ የካውንስሊንግ አገልግሎት ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግና የሱፐርቪዥን ስራ በማከናወን በጋራ ይሰራሉ።

ቀጥታም አገልግሎቱን በመስጠት ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ከትምህርት ቤቶች፣ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር፡- ትምህርት ቤቶች ትውልድን ከሚቀርፁና የዕውቀት፣ የክህሎትና የመልካም ስብዕና ባለቤት ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በየትምህርት ቤቱ በርካታ የባህሪና የስነልቦና ችግር ያለባቸው ህፃናትና ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ይህንን ግዙፍ ችግር ብቻቸውን መወጣት ያዳግታቸዋል፡፡ ስለዚህም ከካውንስሊንግ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመስራት ትውልድን የመቅረጹን ሂደት በጥራትና በባለሙያ እውቀት ላይ በተደገፈ መልኩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከወላጆች ጋር፡- ካውንስለሮች በጋብቻ ፣ በልጆች አስተዳደግና በቤተሰብ ግንኙነት ካውንስሊንግና ስልጠና ዙሪያ በርካታ ስራ ይሰራሉ፡፡ ለአገር እድገትም ሆነ ልማት መሰረቱ የሚመነጨው ከቤተሰብ ነው፡፡ ወላጆች በልጆቻቸው ህይወት ዙሪያ እንዴት ልጆቻቸው ለራሳቸው ያላቸውን አስተሳሰብ (self-esteem) እንደሚገነቡ፣የመወሰን ክሎት እንዲኖራቸው እንደሚረዷቸው፣ እድሜያቸውን ባገናዘበ መልኩ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ፣በልጆቻቸው ውስጥ እሴትን እንዴት እንደሚፈጥሩ ወዘተ በባለሙያ የታገዘ ስልጠና ካላገኙ፣ በዚህ ዘመን እንደ “ጥንቱ” ልጆችን ለማሳደግ መሞከር ከቤተሰብ ውጪ ያለውን ተፅእኖ በቅጡ ያለመረዳት ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ ምሁራኖችም፣ መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላትም ቤተሰብ ላይ ካልሰሩና ለቤተሰብ ትኩረት ካልሰጡ ልማቶች ዘላቂነት ሊኖራቸው ፈፅሞ አይችሉም።

የአንድ ትልቅ ማህበረሰብ መሰረቱ ቤተሰብ ነው፣ የአገር መሰረቱ ቤተሰብ ነው! ከንግድ ተቋማት እና ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር፡- በአገራችን የደንበኛ አገልግሎት ጥራት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አገልግሎት ሊሰፋ የሚችለው ወይም ገቢ ሊጨምር የሚችለው ደንበኞችን(customers) በአግባቡ በማስተናገድና ራስን በጥሩ ሁኔታ በማቅረብ በፈገግታ፣በታታሪነትና በቅልጥፍና ለደንበኞች አገልግሎትን በመስጠት ነው፡፡ ይህን ስብዕና ለመፍጠር በአብዛኛው መሰራት ያለበት በአመለካከት ወይም በሰራተኞቹ አስተሳሰብ ላይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ካውንስለሮች በሆቴል ሰራተኞች፣በመንግስት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በሌሎች የንግድ ድርጅቶች ዙሪያ የአገልግሎትን (customer service)ጥራት ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን መስራት ይችላሉ፡፡ ውድ አንባቢያን:- “ካ/wንስሊንግ ለሁሉም!” የሚል መፈክር በማሰማትና ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነችኝን ማህሌትን በማመስገን የዛሬ ፅሁፌን በዚሁ ላብቃ፡፡ ቸር እንሰንብት!!

Read 3146 times