Saturday, 09 August 2014 11:19

የአዲስ አበባ መንግስት ሆይ የት ነው ያለኸው?

Written by  በዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(4 votes)

ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የእውነቱን እናውራ

በየት እንለፍ?
የአዲስ አበባ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች መንግስት ህገ-ወጥ በሚላቸው የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ተጥለቅልቀዋል። እነዚህን ህገ-ወጦች በመንግስት የሚደራጀው ጥቃቅንና አነስተኛ ሊደርሳቸው አልቻለም፡፡ ጎዳናው ላይ ተዘርግቶ የማይሸጥ ነገር የለም፡፡ ልብስ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ጫማ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ሰዓት፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ መፅሃፍ፣ ቆሎ፣ ቄጤማ… ወዘተ…
ጎዳናው ቁመታቸው ተመሳሳይ በሆኑና አብዛኞቹ ከሌሎች ክልሎች በመጡ ወጣት ነጋዴዎች ተሞልቶአል። መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ ሜክሲኮ፣ ስድስት ኪሎ ወዘተ….በከተማዋ ከሸማቹ የበለጠ ሻጩ የሚበልጥ በሚመስል መልኩ፣ እዚህም እዚያም ህገ-ወጥ ንግዱ ደርቶአል። አስፋልቱም፣ የእግረኛ መንገዱም ንግድ ብቻ ሆነ፡፡ በድንገት የአንዱን ነጋዴ የላስቲክ ማዳበሪያ ለሽያጭ የቀረበ ዕቃ  የደፋ ወይም ረግጦ ያበላሸ መንገደኛ፣ ከጎረምሳው ጋር አንገት ላንገት ይተናነቃል። ክፈል አልከፍልም ይባባላል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ቡጢ ይሰናዘራል፡፡ በገዛ መንገዱ ይህንን ስህተት ላለመስራት ሲጠነቀቅና ሲሸሽ ደግሞ ዋናውን መንገድ ትቶ ወደ አስፋልቱ ዘልቆ ይገባል፡፡….ይሄን ጊዜ ደግሞ “ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት!” በሚለው ሪፖርት ስር አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን የሚዘገበው  የትራፊክ አደጋ ይከሰታል፡፡….በየት እንለፍ?
ትዝብቱ የህገ-ወጥ ነጋዴዎቹ ብቻ አይደለም፤ የሸማቹም ጭምር እንጂ፡፡ በዕቅድ የመገበያየት ልምዱ እምብዛም የሌለው የከተማዋ ነዋሪ፤ ቅዳሜና እሁድን ጠብቆ አስፋልት እየተዘጋ በሚካሄደው ግብይት ብዙ ተሳታፊ አይደለም፡፡ እግረመንገዱን ወደ ስራው ሲሄድ አልያም ከስራው ሲመለስ መንገድ ላይ “በቅናሽ” ሲባል የሚሰማውን ሁሉ ሊያግበሰብስ ሲጋደል እታዘበዋለሁ፡፡ “ሶስቱን ሰርቪስ ትሪ መቶ-መቶ ብር” ሲባል መሸመት፣ “ሻርፕ በ50 በ50 ብር” ሲባል መጋደል፣” “ሰዓት በ75 ብር ሲባል …..”
ከእዚህ አሰቃቂ ትርዒት እልፍ ሲሉ ደግሞ ወኔን ቁርጥ የሚያደርግ፣ ሃሞትን ፍስስ የሚያደርግ የታክሲ፣ የሃይገር ባስና የአውቶብስ ጠባቂዎች ወረፋ መንገዱን ዘግቶት ይታያል፡፡ በየት እንለፍ?....የሚገነቡ ህንፃዎች ፓርኪንግ ስለሌላቸው መኪኖች የእግረኛ መንገድ ላይና አስፋልት ዳር መኪና ያቆማሉ፡፡ ከዚያ እንደምንም ተሽሎክሉኮ ሲታለፍ ደግሞ የኔ-ቢጤዎች ልጆቻቸውን ይዘውና ምንጣፋቸውን ዘርግተው “እያያችሁ አትለፉን!” ይላሉ። ሳንቲም ዘርዛሪ ወጣቶች መሬት ላይ ሳንቲማቸውን ደርድረው ግዛታቸውን ሲያስጠብቁ ይታያል፡፡ በእጅ በሚገፉ ጋሪዎች የሚሸጡ ነገሮች ተሞልተው አጠገብ ላጠገብ ተቀጣጥለው “ማለፍ ክልክል ነው!” ይሉናል፡፡
የተቆፋፈሩ መንገዶች እስካሁንም ቁፋሮአቸው አልተጠናቀቀም፡፡ ሰውም፣ መኪናም፣ እንስሳትም ጉድጓድ ውስጥ ገብተው አደጋ ሲደርስባቸው አይተናል፣ ሰምተናል፡፡ መንገዶች እየተዘጉ ተለዋጭ መንገዶች ግን በአግባቡ ሳይዘጋጁ እየቀሩ፣ ዛሬ ዛሬ መንገድ በራሱ ብርቅ ሊሆንብን እኮ ነው፡፡ መንገድማ ድሮ ቀረ ብለን ልንተርትም ደርሰናል፡፡ በከተማዋ አውራ መንገዶች የእግር ጉዞ/ዎክ ማድረግ ሩቅ እየሆነ ነው፡፡ ብስክሌት/ሳይክል መንዳት የማይታሰብ እየመሰለ ነው፡፡ በየት እንለፍ?
የደንብ ማስከበር ስራዎችን የሚሰሩ የየቀበሌዎቹ ምድቦች (ራሳቸው ተክለ ሰውነታቸው ድቅቅ ያሉ ነገሮች) ህገ-ወጦችን ማባረር ካቅማቸው በላይ የሆነባቸው ይመስላል፡፡ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉት ፖሊሶችም ነገሩ ሳያታክታቸው አልቀረም፡፡ እያዩ እንዳላዩ መሆን ጀምረዋል፡፡ አዲስ አበባ መንግስት ያላትም አትመስልም፡፡ መንግስት ካለም ትኩረቱ ለህንፃ ግንባታዎች ብቻ የሆነም ያስመስልበታል፡፡
በገዛ ብራችን!
በየመኖሪያ ቤታችን መብራትና ውሃ አለመኖሩን መቼስ ተላምደነዋል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን አንስተን መደወል አልያም ካርድ ለመሙላት ስንፈልግ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መታገስ መቻልም ተዋህዶናል፡፡ ነገር ግን የገዛ ብራችንን፣ ለባንክ በአደራ መልክ “አስቀምጥልን” ብለን የሰጠነውን ገንዘባችንን ለማውጣትስ እንዴት “በኔትዎርክ የለም” ይሳበባል?...ብር ከባንክ የሚወጣበትን ምክኒያት ቤቱ ይቁጠረው! ………ስንት ነገር አለ፡፡ የባንክ አስተዳደሮች ግን ለዚህ ብዙም ግድ የሰጣቸው አይመስልም፡፡ ሱፍ በለበሱ ሰራተኞቻቸው አማካኝነት “ኔትዎርክ የለም!” ያስብሉናል፡፡ ሃላፊነቱን ወደ ቴሌ ያላክካሉ፡፡ ሌላ መፍትሄ ሲፈልጉ አይታዩም። በ“እኔ ምን ላድርጋችሁ?” ዓይን እኛኑ ላይ መልሰው ያፈጡብናል። የገዛ ብራችንን ለማውጣት፣ የገዛ ደሞዛችንን (በባንክ ለሚከፈላቸው) ለመውሰድ እንዴት መከራ ማየት ይገባናል?
ጡረታ መቀበል፣ ኮንዶሚኒየም መክፈል፣ ከውጪ የተላከ ብርን መውሰድ፣ ወደ ተለያዩ ክልሎች ለተማሪዎች የሚላኩ ተቆራጮችን መላክ ወዘተ አልተቻለም፡፡ “እዛኛው ቅርንጫፍ ሞክሩ” እንባላለን፡፡ እዚያ ስንሄድ ደግሞ “እዚያኛው ብትሞክሩስ!” እየተባለ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ በመባከን ላይ ነው፡፡ “ታገሱን” ይባላል፡፡ እስከመቼ እንደሆነ ግን የቁርጥ ቀኑ አይነገረንም፡፡
ዝም ብሎ “እስኪ አንተ ታውቃለህ!.... እንዳደረክ አድርገኝ” ከሚል ፀሎት አልፎ “እንዴት? ለምን?” የሚል ሁሉ የሚጠብቀው ሌላ ነገር ስለሆነ፣ የሆዱን በሆዱ ይዞ በገና ለገና “ኔትዎርኩ ሊመጣ ይችላል” ጉጉት የባንኩን የእንግዳ መቀመጫ ወንበር ሲያሞቅ ውሎ ያመሻል፡፡
በገዛ ገንዘቡ…
ደሞዝ ሳይጨመርልን ዋጋ ተጨመረብን!
መንግስት “ደሞዝ ጨመረ” የተባለው ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ አይደለም፡፡ ጭራሹኑም ስራ የሌለውም ሞልቶ ተትረፍርፎአል፡፡ ገቢው አነስተኛው፣ ምንም ገቢ የሌለው፣ ለማኙና ሌላውም ሁሉ የዚህች ከተማ ነዋሪ የመንግስትን ደሞዝ ጭማሪ ምክኒያት በማድረግም ባለማድረግም በሁለቱም ወቅቶች ህገ-ወጥ ነጋዴዎች የሚከምሩትን የዋጋ ጭማሪ እንዴት ለመቋቋም ይቻለዋል?
ዛሬ ዛሬ የቀድሞ ዋጋዎች ሁለትና ሶስት እጥፍ ቢያሻቅቡ ህዝቡ “ተመስገን” ይላል፡፡ ምክኒያቱም ዋጋዎች እየናሩ ያሉት በመቶና በሁለት መቶ እጥፍ ነውና፡፡ የጤፍ፣ የበርበሬ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት ወዘተ ዋጋዎችን ልብ ይሏል! የሸማቾች ህብረቶችና አለ በጅምላ በየዕለቱ እንደጉድ እየናረ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ሊያስታግሱት አልተቻላቸውም፡፡ ነጋዴዎች የመንግስትን ማስፈራሪያ እየሰሙ ያሉ አይመስልም፡፡ ደሞዝ ያልተጨመረለት፣ ወይንም ጭራሹኑም ደሞዝ የሌለው ሰው፣ ደሞዝ የተጨመረለት ሰራተኛም ቢሆን በአንድነት የኑሮ ውድነቱን እየጎመዘዘው በመጎንጨት ላይ ይገኛል፡፡
ጉጉት…ተስፋ….ምኞት……ብቻ!
ኮንዶሚኒየም ይደርሰናል ብለን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው፡፡ የከተማዋ መንግስት ግን “እኔ ብቻ ነኝ እውነተኛው አማራጭ!” የሚል በሚያስመስልበት ሁኔታ የከተማዋን ነዋሪ የቤት ፍላጎት ሊያሟላ ይባክናል። የተመዘገበውና በጉጉት ዕጣ የሚጠብቀው ቁጥር የከተማዋ መንግስት በዓመት ከሚገነባቸው ውስን ቁጥር ያላቸው ቤቶች አንፃር ሲመዘን ጭራሹኑ የማይመጣጠን ነው፡፡ የአዲስ አበባ መንግስት እስካሁንም በ1997 ዓ.ም ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የተመዘገቡትን ነዋሪዎች ፍላጎት ሳያሙዋላ 10 ዓመታት ተቆጠሩ። በ10 ዓመታት ውስጥ ደግሞ እልፍ አዕላፋት ቤት ፈላጊዎች ተፈለፈሉ፡፡ ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
መንግስት ለሌሎች አማራጮች እስካሁንም በሩን አልከፈተም፡፡ “ለቱርክ፣ ለቻይና፣ ለአሜሪካ ወዘተ ኢንቨስተሮች አማራጭ ልንሰጥ ነው!” ይባላል፣ እስካሁን ድረስ ግን በተግባር ጠብ ሲል አላየንም፡፡ መንግስት ለራሱ የሚያደርገውን ድጋፍና ማበረታቻ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ብቻ እንኳን ቢያደርግ (ከሊዝ ነፃ መሬት፣ ከታክስ ነፃ ቁሳቁሶችና አቅርቦቶች፣ የረጅም ጊዜ ብድር ወዘተ) የመኖሪያ ቤቱ እጥረት በስንት እጥፍ በተቃለለ! ግን ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
በየዓመቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ነገር የአዲስ አበባን መንግስት እየተገዳደረው እንደሆነ ይታወቀኛል፡፡ መንግስት ለሁሉም ተመራቂያን ያዘጋጀው ጎጆ አንድ ብቻ ይመስል “በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀት፣ ስራን ሳይንቁ መስራት…ኮብል ስቶን…ከብት ማርባትና ማደለብ” ወዘተ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ተሰማርተው የፈጠራ ስራ ለሚሰሩ ወጣቶች የተመቻቸ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ የቴአትር ተመራቂዎች ፊልም ለመስራት ቢፈልጉና ለፊልማቸው የሚሆናቸውን ወጪ ለመሸፈን የአምስት መቶ ሺህ ብር ብድር ቢጠይቁ የትኛው ባንክ…የትኛው የቁጠባ ተቋም ነው ሊያበድራቸው የሚችለው?....ሲያምራቸው ይቀራል እንጂ!...ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
የትራንስፖርቱ ሁኔታ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ እየባሰበት እየሄደ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ዝርጋታ በታሰበው ፍጥነት እየሄደ ነው የሚል ዕምነቱ የለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ ባቡሩ ጉጉታችን፣ ተስፋና ምኞታችን ነው፡፡
ሆኖም ግን አሁን በሚታየው መልኩ በከተማዋ የነዋሪው ቁጥር እንዲህ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እየመጣ ባለበት ሁኔታ ዕውን የባቡር ዝርጋታው መጠናቀቅ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ሊፈታላት ይችላል የሚለው ትልቅ ጥያቄ የሚፈጥር ነው፡፡ ለዚህም ጠዋትና በስራ መውጫ ሰዓት ላይ የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት ፍላጎትን ብቻ በማየት ነገሩን ለመገመት ይቻላል፡፡
ጎን ለጎን ሌሎች መፍትሄዎች በአስቸኳይ የማይታሰቡ ከሆነና ባቡሩን ብቻ የችግሩ ፈቺ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማሰቡ፤ ለእኔ  ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ ነው የሚሆንብኝ፡፡
እነሆ የአዲስ አበባ መንግስት የት ነው ያለኸው?
እስቲ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የዕውነቱን እንነጋገር፡፡ አዲስ አበባ በብዙ ነገሮች ቅጥ እያጣች በመምጣት ላይ አይደለችምን?....የከተማዋ አመራር ከከንቲባ እስከ ደንምብ ማስከበር አዲስ አበባ ያቃተቻቸው አይመስልምን?..ህገ-ወጦች እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አዲስ አበባ ለመኖሪያነት እያስቸገረችን አይደለምን?...
መጤ ድርጊቶች ከተማዋን እንደጉድ ወረዋት አዲስ አበባ በጭንቀት ተወጥራለች፡፡ ከጫት እስከ ሺሻ…ከእስቲም እስከ ልቅ ማሳጅ፣ ከሴተኛ አዳሪነት እስከ ግብረሰዶማዊነት፣ ከስራ አጥነት እስከ ማጅራት መቺነት፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የመኪና ዕቃዎች ስርቆት፣ ማታለልና ማጭበርበር ወዘተ የዕለት ተዕለት ዜናዎች ሆነው እየሰማንም እያየንም ነው፡፡
በራሱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገንዘብ ድጋፍ በከተማዋ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በተካሄደው ሰፊ ጥናት፤ አዲስ አበባ በመጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተዋጠች ነው፡፡ በባህልና በማህበራዊ ስልጣኔዋ አዲስ አበባ ቁልቁል እየገሰገሰች ትገኛለች። ጥናቱ እያንዳንዱን ነዋሪ በሚያስደነግጥ መልኩ ዕውነታዎችን ፍንትው አድርጎ ሲያሳይ ማንም ልቡ ይሰበራል፡፡ ማንም ወይ አዲስ አበባ እያለ በሃዘን አንገቱን መድፋቱ፣ ደረቱን መደለቁ፣ ፀጉሩን መንጨቱ አይቀሬ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ያለእንከን ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የማየው ፎቅ ብቻ ነው፡፡ ፎቆቹ የማናቸው የሚል ጥያቄ አሁን አላነሳም፡፡ የማንም ይሁኑ የከተማችን ድምቀቶች ናቸው።
ነገር ግን የአንድ ከተማ ስራ፣ ህንፃ መገንባት ብቻ አይደለም፡፡ በነዋሪው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ባህላዊና የጤና ጉዳዮች ዙሪያ ወዘተ እኩል መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ለልጆች መጫወቻና ለአረጋውያን ማረፊያ የሚሆኑ ክፍት ቦታዎች እያጣን ባለንበት በዚህ ወቅት፣ ከተማዋን በዓለም ካሉ 10 የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱዋ የማድረግ ህልም ሊሰምር አይቻለውም፡፡
የአዲስ አበባ መንግስት ካለህበት ሆነህ ድምፅህን አሰማ! እነሆ የት ነው ያለኸው?
መልሱ “ኮንዶሚኒየም እያስገነባን፣ ቀላል ባቡር እየዘረጋን፣ ከተማዋን በህንፃ እያስዋብን፣” ወዘተ በሚል ሰበባ ሰበብ ሊድበሰበስ አይገባውም፡፡ እስቲ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የእውነቱን እንነጋገር፡፡………የአዲስ አበባ መንግስት ካለህበት ሆነህ ድምፅህን አሰማ! እነሆ የት ነው ያለኸው?
ሰላም ቅዳሜ!

Read 4948 times