Saturday, 09 August 2014 11:34

“አደገኛ አጥር” እና አደጋው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           በገጠር ገበሬው መኖርያ ቤቱን በእሾህ ያጥራል፡፡ በከተማ ደግሞ አጥር ከማጠር በተጨማሪ ቤት ጠባቂ ውሻ በማሳደግ፣ “ሃይለኛ ውሻ አለ” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፎ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ “አደገኛ አጥር” በሚል እየተተካ የመጣ ይመስላል፡፡ ቀድሞ በጥቂት ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም ኤምባሲዎች ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የኤሌክትሪክ አጥር አሁን በብዛት ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል፡፡
“ኔምቴክ”  መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገ፣ በ54 የተለያዩ የዓለም አገራት የኤሌክትሪክ አጥር በመስራት የሚታወቅ ዓለምአቀፍ ድርጅት ነው። ሚስተር ዲክ ኢራስመስ፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ በኤክስፐርቶች ማናጀርነት ይሰራሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ በኤሌክትሪክ አጥር አተካከልና አጠቃቀም ዙሪያ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ የኤሌክትሪክ አጥሮችን ወጪ በሚቆጥብና የላቀ ውጤት በሚያስገኝ ሁኔታ እንዴት መጠቀም  እንደሚቻል አሰልጥነዋል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በዘርፉ ሲሰራ የቆየው “ኔምቴክ”፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል። በነገራችን ላይ ድርጅቱ ከሚሰራባቸው የዓለም አካባቢዎች አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከወንጀሎች መበራከት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ዲክ ኢራስመስ ይናገራሉ፡፡
ኢራስመስ በኤሌክትሪክ አጥር አጠቃቀም ዙሪያ፣ ስለአደገኛነቱና በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አጥሮች አጠቃቀም
የኤሌክትሪክ አጥሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ በመጀመሪያ በደንብ መተከል አለባቸው። የኤሌክትሪክ አጥሮች የሚተከሉት ሰውን ለመግደል አይደለም፡፡ ሌሎች ጉዳቶችንም ማድረስ የለባቸውም፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአለም ላይ በርካታ ወንጀሎች ከሚፈፀምባቸው የአለማችን ክፍሎች አንዷ ናት። በአገሪቱ በሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች ብዙ ሰዎች ንብረታቸውንና ህይወታቸውን ያጣሉ። የተለያዩ ወገኖች በኤሌክትሪክ አጥር አስፈላጊነት ላይ ጥያቄዎችን ቢያነሱም በወንጀሎች መበራከት የተነሳ፣ የኤሌክትሪክ አጥር ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የኤሌክትሪክ አጥር፤ ዝርፊያን ለመከላከልና ደህንነትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ብቃት አለው፡፡ በወጪም አንፃር ቢሆን የተጋነነ አይደለም፡፡
የኤሌክትሪክ አጥርን እኔ “ስሪ ዲ” ነው የምለው። “ዲተር”፣ “ዲቴክት እና “ዲሌይ” ማድረግ ነው ስራው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰው አጥሩ ላይ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሲያይ ወደዚያ እንዳይጠጋ ምልክት ይሰጠዋል፡፡ ያን አልፎ የሰው አጥር መንካት ሲጀምር “ዲቴክት” በማድረግ ገፍትሮ ይጥለዋል፡፡ በዚህም ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሊፈፅሙ ያሰቡትን ወንጀል እንዳይፈፅሙ በማዘግየትና ድምፅ በማሰማት  ሰዎች በንብረታቸው ወይም በህይወታቸው ላይ ሊፈፀም ከታቀደ አደጋ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የኤሌክትሪክ አጥሮች በሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ማድረስ የለባቸውም፡፡
የማይሰሩ የኤሌክትሪክ አጥሮች
በመስክ ስልጠናው የታዘብኳቸው ስህተቶች አሉ፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ አጥሮቹ በትክክል አለመተከል ዋነኛው ነው፡፡ አጥሩን ያስተከሉ ሰዎች መስራት አለመስራቱን ስለማያረጋግጡ አጥሩ ቢኖርም ላይሰራ ይችላል፡፡ ዋናው ስህተት በሽቦውና በኤሌክትሪኩ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወንጀል ለሚፈፅሙ ሰዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡  እንዲህ ሲሆን ከኪሳራውም ባሻገር ሰዎች ለዘረፋና በህይወት ላይ ለሚቃጣ አደጋ ይጋለጣሉ፡፡
ሌላው አጥሩ ላይ ሌሎች ነገሮች ተሰቅለው የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ የሆኑ ብረቶች ተቀላቅለው ያየሁባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ዛፍና አትክልቶች ከአጥሩ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የኤሌክትሪክ አጥሩ በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ በስልጠናው ወቅት የኤሌክትሪክ አጥር የሚተክሉ ሰዎች በተገቢው መንገድ እንዲተክሉ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና ሰጥተናቸዋል፡፡ ከቤት ውበት ጋር በተያያዘም አተካከሉ ላይ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ተዳስሰዋል፡፡
አጥሩን ሊነካ የሚሞክር ሁሉ ወንጀለኛ ነው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ይህ አጥር በተተከለበት ቦታ ሁሉ በግልፅ ሥፍራ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ መለጠፍ ግዴታ ነው። ይሄ በደቡብ አፍሪካ በህግ ተደንግጐ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አጥር የሚተክሉ ሰዎች ተገቢ ስልጠና ያገኙ መሆን እንዳለባቸው ህጉ ይደነግጋል፡፡ ባለቤቱ ሰው የማይገድልና የጥራት ደረጃውን ያሟላ ምርት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ያላዩ ሰዎች አጥሩን ቢነኩ እንኳን ገፍትሮ ይጥላቸዋል እንጂ አይገድላቸውም፡፡  
በዚህ አጥር እንስሳትም ቢሆኑ መጐዳት የለባቸውም፡፡ በኤሌክትሪክ አጥሩ ጉዳት የሚደርስባቸው በማንኛውም ኤሌክትሪክ ሊጎዱ የሚችሉ እንደ  ሸረሪትና እባብ አይነት እንስሶች ብቻ ናቸው፡፡ ወፎች የሚቆሙት  ብረቶቹ ላይ ስለሆነ ጉዳት አይደርስባቸውም፡፡
አፍሪካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቦታዎች እንደ ስዊድን፣ አውስትራሊያና ኔዘርላንድስ ባሉ አገራትም የኤሌክትሪክ አጥሮች ብዙ ህይወቶችንና የንብረት ጉዳቶችን ታድገዋል፡፡
አጥሮቹ መብራት በሌለበት ጊዜ የባትሪ መጠባበቂያ ስላላቸው ስራቸውን አያቋርጡም፡፡ እኔ እንዳየሁትና ከሌሎች ቦታዎች ጋር እንዳነፃፀርኩት፣  አዲስ አበባ ያለው የመብራት ሀይል አቅርቦት እምብዛም የከፋ አይደለም፡፡
ኬኒያ፣ ናይጄሪያና፣ ጋና በመሳሰሉት አገራት የሀይል አቅርቦቱ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ተከታታይ የሀይል አቅርቦት በማይኖርባቸው ጊዜያት ወይም ቦታዎች ሶላር እንጠቀማለን፡፡
አዲሱ የ“ደህንነት” ኩባንያ
አቶ ሳምሶን ገብረስላሴ፤ የ“ሳሜክ ኢንጂነሪንግ” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በቅርቡ በ ደህንነት እና አደጋ መከላከል ስራ ላይ የተሰማራ አዲስ ድርጅት በአዲስ አበባ ከፍተዋል፡፡  “ሳሜክ ኢንጂነሪንግ ለንደን የሚገኘው የ “ሳሜክ” ኩባንያ እህት ድርጅት ነው፡፡ የደህንነት እና የአደጋ መከላከያ እቃዎችን ከውጪ በማስመጣት፣ በኢትዮጵያ በዚህ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ያቀርባል፡፡ እነዚህ ድርጅቶቹ መሳሪያዎቹን ከመግጠማቸው በፊት ስልጠናዎች በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ ሥራ እንዲሰሩ ያግዛል፡፡ የ“ኔምቴክ” ስልጠናም የዚሁ አካል ነው፡፡ የ“ሳሜክ ኢንጂነሪንግ” ባለቤት አቶ ሳምሶን ገ/ሥላሴ፤ በኢትዮጵያ ስላለው የኤሌክትሪክ አጥሮች ተሞክሮአቸውን እንዲህ ይገልፁታል፡፡
“እኛ አገር ያለው ችግር አጥሩ  በብዛት የሚተከለው በልምድ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የሚጠቀሙት ኤምባሲዎችና ትልልቅ መስሪያ ቤቶች ነበሩ፤ አሁን ግን ወንጀል እየተበራከተ ሲመጣ በመኖሪያ ቤቶች በስፋት እየተገጠመ ነው፡፡ አጥሩ መስራት አለመስራቱ የሚታወቀው ሌባ ያን አጥር ነክቶ ገፍትሮ ሲጥለው ነው፤ ተከላው በትክክል ስለማይከናወን ውጤታማነቱ አጠያያቂ ነበር። የሚገጥሙት ሠራተኞች መስራት አለመስራቱን ለማወቅ በቂ ስልጠናም ሆነ ማረጋገጫ መሳሪያዎች አልነበራቸውም፡፡
ከዚህ በፊት የተገጠሙትን ስናይ፤ መስመሩ የተላቀቀ፣ የተቆራረጠ፣ በቂ የኤሌክትሪክ ሀይል የሌለው ሁሉ አጋጥሞናል፡፡ ወደፊት ተከታታይ ስልጠናዎች ይኖራሉ፤ የሚተክሉት ሰዎች ብቃት ያላቸው እንዲሆኑና በአገራችን መንግስት የኤሌክትሪክ አጥር ህግ እንዲያወጣ ግፊት እናደርጋለን፡፡”
እስከዚያው ግን የኤሌክትሪክ አጥር ባለበት ሥፍራ ሁሉ ይሄንኑ የሚገልጽ ማስታወቂያ በግልፅ በሚታይ ቦታ ላይ መሰቀል እንዳለበት ባለሙያዎቹ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

Read 5475 times