Saturday, 09 August 2014 11:51

ሳኡዲ የሌሎች አገራት ሴቶችን ለሚያገቡ ዜጎቿ ጥብቅ መመሪያ አወጣች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ትዳር መመስረት የፈለጉ ወንዶች ለመንግሰት ፕሮፖዛል ማቅረብ አለባቸው
የአገሪቱ ወንዶች ከ4 አገራት ሴቶች ጋር መጋባት አይችሉም

ሳኡዲ አረቢያ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት ለሚፈልጉ ዜጎቿ ጥብቅ የሆነ የትዳር መመሪያ ማውጣቷንና የአገሪቱ ወንዶች ከአራት አገራት ሴቶች ጋር እንዳይጋቡ መከልከሏን ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የሳኡዲ መንግስት ያወጣውን የትዳር መመሪያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት የሚፈልጉ ዜጎች፣ የትዳር ፕሮፖዛልና የሚኖሩበት ከተማ ከንቲባ ፊርማ ያረፈበት የነዋሪነት መታወቂያ ለአገሪቱ ፖሊስ ማቅረብና ማስገምገም ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመካ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት አሳፍ አልቁሪሽ እንዳሉት፣ መንግስት ትዳር ፈላጊዎች የሚያቀርቡለትን ፕሮፖዛል ገምግሞ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ አዲሱ መመሪያ እንደሚለው፤ ትዳር ፈላጊው ዕድሜው ከ25 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ትዳር የነበረውና የተፋታ ከሆነ ደግሞ፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው፣ ፍቺው ከተፈጸመ ከከ6 ወራት ጊዜ በኋላ ነው፡፡
“ዘ መካ” የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደገለጸው፣ ትዳር ፈላጊው የቀድሞ ትዳሩን በህጋዊ ፍቺ ያላፈረሰ ከሆነ፣ አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው በመንግስት ከሚተዳደር ሆስፒታል የቀድሞ ሚስቱ በጸና መታመሟን ወይም መሃን መሆኗን የሚያረጋግጥ አልያም የቀድሞ ሚስቱ አዲስ ትዳር ቢመሰርት እንደማትቃወም የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርብ ነው፡፡ አዲሱ የሳኡዲ አረቢያ መንግሰት ለአገሪቱ ትዳር ፈላጊ ወንዶች ያወጣው የጋብቻ መመሪያ፣ ወንዶቹ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ተቀጥረው ከሚሰሩ የፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ እና በርማ ሴቶች ጋር በፍጹም ትዳር መመስረት እንደማይችሉ ጥብቅ እገዳ የሚጥል መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፣ ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚደርሱት ከእነዚህ የውጭ አገራት ሰራተኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ወይም 500 ሺህ ያህሉ የትዳር እገዳ ከተጣለባቸው አራቱ አገራት የመጡ ሴቶች መሆናቸውን ጨምሮ ገልጧል፡፡

Read 9138 times