Saturday, 16 August 2014 10:14

አርቲስትና ጋዜጠኛ ፌቨን ከፈለኝ አረፈች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

     ከሳምንት በፊት አምባሳደር አካባቢ የመኪና አደጋ ደርሶባት በህክምና ላይ የነበረችው ጋዜጠኛ፣ ተዋናይትና መምህርት ፌቨን ከፈለኝ በተወለደች በ23 ዓመቷ አረፈች፡፡ በ97.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ የሚተላለፈው የ “ሄሎ ሌዲስ” ፕሮግራም ረዳት አዘጋጅ በመሆን የሰራችው የ23 ዓመቷ ወጣት ፌቨን፤ ከ8-9 ሰዓት የሚተላለፈውን የዕለቱን የሬዲዮ ፕሮግራም ስራዋን አጠናቃ ለነበራት የፊልም ስራ ቀጠሮ ወደ አምባሳደር ሲኒማ በመሄድ ላይ እያለች በሚኒባስ ታክሲ ተገጭታ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምና ስትረዳ ብትቆይም ከትላንት በስቲያ አመሻሽ ላይ ህይወቷ አልፏል፡፡
በአደጋው በደረሰባት ጉዳት ደም ወደ ጭንቅላቷ ውስጥ መፍሰሱን የህክምና ባለሙያዎች ገልፀው የህክምና እርዳታ ቢደረግላትም ጉዳቷ የከፋ በመሆኑ ልትተርፍ አለመቻሏን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደችው ወጣት ፌቨን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህቷን በየካ ተራራ ት/ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮከበ ፅባህ ት/ቤት፣ የከፍተኛ ትምህርቷን በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተከታትላ በኬምስትሪቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን፣ በFA አካዳሚና በስኩል ኦፍ ቱሞሮው ት/ቤቶች በመምህርነት ማገልገሏም ተነግሯል፡፡ ወጣቷ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ መድረኮችን በመምራት የምትታወቅ ሲሆን “የቴዎድሮስ ራዕይ” በተባለው ተውኔት ላይ በመተወን እውቅናና አድናቆትን ለማግኘት በቅታለች፡፡ “ፍቅር በአማርኛ”፣ “እፍርታም”፣ “ከፍቅር በታች”ና ሌሎችም ፊልሞች ላይ የተወነች ሲሆን ገና ለእይታ ያልበቁ “ፍቅርን ፈራሁ”፣ “ባየሽኝ” እና “አማሪያ” በተባሉ ፊልሞች ላይ መሳተፏ ታውቋል፡፡

Read 6879 times