Saturday, 16 August 2014 10:26

የኡጋንዳ ፖሊስ 2 ኢትዮጵያውያንን በሽብርተኝነት ጠርጥሮ አሰረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ አስገብቷል በሚል ተከስሶ ጉዳዩ በፍ/ቤቱ እየታየ የነበረውን ባሻ አድነው የተባለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ከፍርድ እንዲያመልጥ አድርገዋል የተባሉት የማላዊ የአገር ውስጥ ጉዳዮችና የደህንነት ሚኒስትር ፖል ቺቢንጉና የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዋና ሃላፊ ሁድሰን ማንካዋላ መታሰራቸውን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘው ድረገፅ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያዊው ስደተኛ የክስ ሂደት ሳይጠናቀቅና ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ተከሳሹን በሙስና ወደ አገሩ እንዲያመልጥ በማድረግ ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል የተከሰሱትን ሁለት ባለስልጣናት ጉዳይ የሙዙዙ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እያጣራ ሲሆን ባለስልጣናቱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእስራት ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል፡፡ ከሁለቱ ባለስልጣናት ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሶስት የመንግስት ኃላፊዎችም ክስ እንደተመሰረተባቸው ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ግንቦት ከሌሎች ሁለት የማሊ ዜጎች ጋር በመተባበር ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ማሊያዊ እንዲገቡ አድርጓል በሚል የተከሰሰውን ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ባሻ አድነው ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤቱ፤ ባለፈው ማክሰኞ የእስር ትዕዛዝ ያስተላለፈበት ሲሆን ግለሰቡ ግን ባለስልጣናቱ ተሳትፈውበታል ተብሎ በተጠረጠረ ሙስና ከአገር እንዲወጣ መደረጉ ተረጋግጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክስ የመሰረተው በሚኒስትሩ፣ በሁለት የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ውስጥ ባዋለው የፖሊስ መኮንንና ወደ ፍርድ ቤት ሲያመላልሰው በነበረው የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ ላይ ሲሆን ተጠርጣሪዎች የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ታዝዟል፡፡
ባለስልጣናቱ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ስልጣን ከያዙ ወዲህ በሙስና የተያዙ የመጀመሪያዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ ጉዳዩ አዲሱ አስተዳደር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚያስተናግድ የሚፈተንበት ይሆናል ብሏል፡፡
የኡጋንዳ ፖሊስ ካባላጋላ በተባለች ከተማ ዙሪያ ባደረገው ለሁለት ቀናት የዘለቀ አሰሳ፤ ሁለት ኢትዮጵያውያንንና አንድ ኡጋንዳዊን በሽብርተኝነት ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኒው ቪዥን የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘገበ፡፡
አበበ መኮንንና አስፋው ወንድወሰን የተባሉትን ኢትዮጵያውያንና ጁማ ሲምዋንጋ የተባለውን ኡጋንዳዊ ከአስር ቀናት በፊት በሽብርተኝነት ጠርጥሮ ማሰሩን የገለጸው ዘገባው፤ ግለሰቦቹ ከተያዙ በኋላ ጉራንጉር ውስጥ በተከራዩት መኖሪያ ቤታቸው ፍተሻ መደረጉን አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ከየት አግኝቶ በቁጥጥር ውስጥ እንዳዋላቸው የገለጸው ነገር የለም፡፡

Read 3516 times