Saturday, 16 August 2014 10:34

ኧረ ተው ኢህአዴግ ተረጋጋ!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“ዴዣ ቩ” - በአምስት አመቱ የተደገመ ታሪክ የጋዜጠኞችን ማሰርና ማሳደድ፤ ንግድ ቤቶችን ማሸግና ማዋከብ

የ2001 ዓ.ም ዘመቻ - ለ2002 ምርጫ?
ዘመቻው የተጀመረው በአዲስ ዘመን ላይ በወጡ ፅሁፎች ነበር። “የውጭ ሃይሎች በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነው” በሚል ውግዘት ዩኤስአይዲ ላይ ጣት ከመቀሰር ቢነሳም፤ ብዙም ሳይቆይ ነው ነፃ የግል ጋዜጦች ላይ በማነጣጠር ዘመቻ የተካሄደው። ከዚያ ኢቴቪ “ጥናታዊ ዘገባ” ሰርቻለሁ ብሎ በወቅቱ ሲታተሙ የነበሩ ጋዜጦችን የኩነኔ መዓት አወረደባቸው - በአብዛኛው ከሕትመት የወጡ የድሮ ጋዜጦችን እያሳየ። ብዙም ሳይቆይ ወከባና እስር መጣ። የቪኦኤ ጋዜጠኛ ለበርካታ ቀናት እንደታሰረና የኤፒ ጋዜጠኛ እንዳይታሰር በመስጋት ከአገር እንደወጣ የሚያስታውሱ የሙያ ባልደረቦች እንደሚሉት፤ ወከባው የበረታው ግን በግል ጋዜጦች ላይ እንደነበር ይገልፃሉ - የአዲስ ነገር ጋዜጣ መዘጋትንና የጋዜጠኞቹ መሰደድን በመጥቀስ።
ከመነሻው ዩኤስአይዲ ላይ የተጀመረው ውግዘት ብዙ ባይዘልቅም፣ ወደ ሌሎች አለማቀፍ ድርጅቶች ተሸጋገረ እንጂ አልከሰመም። ውግዘቱ ብዙ አለማቀፍ ድርጅቶችን ቢያዳርስም፤ ዋናው ኢላማ ግን ሂዩማን ራይት ዎች ነበር። የኋላ ኋላም በአለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፤ በሂዩማን ራይት ዎች ላይ ሰለማዊ ሰልፍ እስከመውጣት ተደርሷል።
የመንግስት ዘመቻ በፖለቲካ መስክ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም - በኢኮኖሚ መስክም ጭምር እንጂ። ከልክ ባለፈ የብር ህትመት ሳቢያ በመንግስት የተፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ በወቅቱ ከተከሰተው የዝናብ እጥረት ጋር ተዳምሮ በጣም አሳሳቢ ሆኖ ነበር። አሳዛኙ ነገር፤ ሁሉም ችግር በነጋዴዎች ላይ ተሳበበ። እናም፤ ነጋዴዎች አበሳቸውን እስኪያዩ ድረስ ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል።
እነዚህ የ2001 ዓ.ም ዘመቻዎች ተገቢ ባይሆኑም፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ቢበዛም፤ “ምንም መነሻ አልነበራቸውም” ማለት አይደለም። አንደኛ፣ የ97 የምርጫ ቀውስ ገና መንፈሱ አልደበዘዘም ነበር። በዚያ ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር መንግስት ላይ ቀላል የማይባሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫናዎች ወይም ፈተናዎች ተጋርጠው እንደነበር አይካድም። ከአገር ውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፈተናዎች በተጨማሪ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘመቻ ራሱ ቀላል አልነበርም - በተለይ የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ አክራሪዎችን ለመዋጋት ከተሰማራ በኋላ።
የኢትዮጵያ ጦር ስምሪት ከአሜሪካ ድጋፍ አግኝቷል የሚለው ስሜት ለኢህአዴግ እንዲያ ፈታኝ ይሆንበታል ብሎ ማን ገመተ? ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሚተባበር አገር ላይ ክፉኛ ጥርሳቸውን የሚነክሱት ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ኒው ዮርክ ታይምስ ናቸው፤ ኢህአዴግን ከግራና ከቀኝ ወጥረው የያዙት። በዚያው ልክ፤ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ጫናም የሚናቅ አልነበረም። ከዳያስፖራ ፖለቲካው ጋር በአገር ውስጥ የ”መድረክ” ተቀናቃኝነት፣ የዋጋ ንረት፣ የረሃብ አደጋ ... ኢህአዴግ፤ በእነዚህ ተደራራቢ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፈተናዎች ምክንያት ስለተጨናነቀ ሊሆን ይችላል ወደ አላስፈላጊ ዘመቻ ያመራው።
አሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ? የያኔዎቹ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፈተናዎች ዛሬ ቢደበዝዙም፣ ልክ እንደያኔው፣ በነፃ ፕሬስ ላይ የእስር እና የስደት፤ እንዲሁም በቢዝነስ መስክ የእሸጋና የወከባ ታሪክ ዛሬም እየተደገመ ነው።

የ2006 ዓ.ም ዘመቻ - ለ2007 ምርጫ?
አለማቀፉን የፕሬስ ነፃነት ተቋም (አርቲክል 19ን) በማውገዝ የተለኮሰው የዘንድሮ ዘመቻ፤ አዲስ ዘመን የግል መፅሔቶችን በመወንጀል ባሰራጨው “ጥናታዊ ሪፖርት” ነው ጎልቶ የወጣው። በኢቴቪ የተሰራጩትንም ዘገባዎች ተመልክታችኋል። ዘጠኝ ፀሐፊዎችና ጋዜጠኞች ሲታሰሩም ታዝበናል። ሰሞኑን ደግሞ ጋዜጠኞች ሲሰደዱና ሕትመቶች ሲቋረጡ እያየን ነው።
ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ያኔ በ2001 ኢህአዴግ ብርድ ብርድ ቢለው አይገርምም። የ97ቱ ትዝታ ገና አልደበዘዘም። 2001 ላይ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ግጭት ነበር። የጎዳና ላይ አመፅ፣ በወቅቱ ገና ፋሽኑ አላለፈበትም። በአገር ውስጥ ቅጥ ባጣ የብር ህትመት ከተፈጠረው የዋጋ ንረት በተጨማሪ፣ የረሃብ አደጋው ታክሎበት፤ በዚያ ላይ አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ተደምሮበት፤ የአገሬው ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነበር።
ዘንድሮ ግን ያን ያህልም የሚያሰጋ የዋጋ ንረት አልተከሰተም። የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ስለተደረገ የዋጋ ንረት ይከሰታል በሚል ሰፊ የፕሮፓጋንዳና የማስፈራሪያ ዘመቻ ቢካሄድም፤ እንደተለመደው የቢዝነስ ስራን በማውገዝ የንግድ ቤቶችን በገፍ የማሸግ ዘመቻ ቢካሄድም፤ ለዚህ መነሻ የሚሆን ሰበብ እንኳ የለም። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ የሐምሌ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ከሰኔ ወር የሚያንስ እንጂ የሚበልጥ የዋጋ ንረት አልተፈጠረም። ደግሞም አይገርምም። መንግስት አለቅጥ የብር ኖት ከማተም እስከተቆጠበ ድረስ፤ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊከሰት አይችልም።
ዘንድሮ ከ2001 ዓ.ም የሚለየው፣ አስደንጋጭ የዋጋ ንረት ባለመፈጠሩ ብቻ አይደለም። ትልቅ የረሃብ አደጋም አልተፈጠረም። በእርግጥ የኑሮ ችግር እንደያኔው ዛሬም አለ። ሰባት ሚሊዮን ገደማ የሴፍቲ ኔት ተረጂዎችና ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። እንደምንም ብለው ኑሯቸውን የሚገፉ ችግረኞችም ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። ነገር ግን፤ የዘንድሮው ረሃብ፣ ችግርና ድህነት ካለፉት አመታት ይሻል እንደሆነ እንጂ አይብስም።

የፖለቲካ ጫና እና ፈተናስ - ድሮና ዘንድሮ
በ2001 ዓ.ም፤ ምንም እንኳ ከምርጫ 97 ፉክክር ጋር የሚስተካከል ባይሆንም፤ በስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረተው “መድረክ”፤ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያካሂድ ነበር። ከመድረክ በተጨማሪ፤ የዜጎችን ትኩረት ለመሳብ የሚጣጣሩ አዳዲስ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ይሉ ነበር። ከያኔው ጋር ሲነፃፀር፤ ዘንድሮ ኢህአዴግን ክፉኛ የሚቀናቀን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም። አዳዲስ ፓርቲዎችንም እያየን አይደለም።
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ነፃ ማህበራትና ነፃ ጋዜጦች ለመንግስት እንደ ፈተና የሚቆጠሩ ከሆነም፤ ከ2001 ወዲህ ቁጥራቸው በእጅጉ ቀንሷል፤ ህልውናቸውን ያላጡትም ተዳክመዋል። በአጭሩ፤ በአገር ውስጥ ኢህአዴግን ለስጋት የሚዳርግ ከባድ የፖለቲካ ጫና ወይም ፈተና አይታይም።
ከአገር ውጭም  ያን ያህል የጎላ ስጋት የለም። በሶማሊያ በኩል የነበረው የአልሸባብ ስጋት ረግቧል። በኤርትራ በኩል፤ ብዙም እንቅስቃሴ አይስተዋልም። በእርግጥ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ የዳያስፖራ ፖለቲካው የተለወጠና የተጠናከረ ይመስላል። ግን ብዙም አልተለወጠም። በ1996 ዓ.ም “ህብረት” ለመፍጠር ሲሰባሰቡ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛትና እንቅስቃሴ ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ማስታወስ እንችላለን። የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ፣ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በውጭ አገራት ያካሄዱት እንቅስቃሴም ከፍተኛ ነበር። የዳያስፖራ ፖለቲካ እንደወትሮው፣ ለገዢው ፓርቲ የሚመች ባይሆንም፣ ዛሬ ከድሮው የባሰ ፈታኝ ሆኗል የሚባልለት አይደለም።
የውጭ መንግስታትና አለማቀፍ ተቋማትማ፤ በአብዛኛው ድምፃቸው ጠፍቷል ማለት ይቻላል። አንዳንዶቹ ድምፃቸውን ለማሰማት ቢሞክሩም ያን ያህልም ብዙ ጆሮ እያገኙ አይደለም። በ2001 ዓ.ም ላይ ታች እያሉ ድምፃቸውን አጉልተው ሲያሰሙ የነበሩ አለማቀፍ ተቋማትን በጥቂቱ እናስታውሳቸው።

የውጭ መንግስታትና አለማቀፍ ተቋማት - ድሮና ዘንድሮ
“በሶማሌ ክልል መንግስት ጭፍጨፋ አካሂዷል” ከሚለው የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ጀምሮ፤ የኒውዮርክ ታይምስ ተከታታይ የትችት ዘገባዎችን ጨምሮ በ2001 ዓ.ም የውጭ መንግስታትና የአለማቀፍ ተቋማት ጫና ለኢህአዴግ እጅግ ከባድ ሆኖበት ነበር።
“መንግስት የአገሬውን ረሃብ ደብቋል” የሚሉ የረድኤት ድርጅቶች የሚያሰራጩት ተከታታይ መግለጫ ታክሎበት፤ “ገዢው ፓርቲ በ77ቱ ረሃብ ለእርዳታ የመጣ ገንዘብ ለመሳሪያ መግዣ አውሎታል” የሚል የቢቢሲ ሰፊ ዘገባ፣ “በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተስፋ ጨልሟል” የሚል የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት፣ ከዚያም “የሰብአዊ መብት ረገጣ ተባብሷል” የሚል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ሪፖርት... የያኔው ጫና ቀላል አልነበረም። የአሜሪካ ኮንግረስ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያወጣውና በእንጥልጥል የነበረው  ኤች.አር 2003 የተሰኘው ህግም ለኢህአዴግ እጅግ ፈታኝ መሆኑ አልቀረም።
የዚያ ሁሉ ርብርብ መነሻ፤ “ለውጥ ማምጣት እንችላለን” የሚል ተስፋ ነው። “መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር ወይም ተቃውሞ በማበረታታት፤  ገዢው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በድርድር ተቻችሎ እንዲሰራ መገፋፋትና ለውጥ ማምጣት ይቻላል” የሚል አስተሳሰብ በስፋት ይታይ ነበር - በውጭ መንግስታትና በአለማቀፍ ተቋማት ዘንድ።
ይህ አስተሳሰብ ግን፤ ባለፉት አምስት አመታት ተሸርሽሯል። አንደኛ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አገራት ላይ ጫና የማሳደር ፍላጎት የላቸውም። ሁለተኛ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት በኢኮኖሚ ቀውስ ስለተመቱ፣ አብዛኞቹ መንግስታት በራሳቸው ውስብስብ ችግር ውስጥ ተጠምደዋል። በመጨረሻ ደግሞ፣ በኪሳራ የተደመደመው የአረብ አገራት አብዮት መጣ።
በእርግጥ፤ “በአረብ አገራት ውስጥ የነፃነት ለውጥ ማምጣት ይቻላል” የሚለው የምዕራብ መንግስታት አስተሳሰብ እየተሸረሸረ የመጣው፣ በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ ጦርነት ማግስት ነው። በአፍጋኒስታን የአክራሪው የታሊባን አገዛዝ ቢወገድም፤ በኢራቅ የሳዳም ሁሴን አምባገነንነት ቢወገድም፣ የነፃነት መንፈስ አልሰፈነም። በሃይማኖት ወይም በጎሳ እየተቧደኑ ስልጣን ለመያዝ ሲጨፋጨፉ፣ በአንዳች አጋጣሚ ስልጣን ላይ የወጣ ቡድን አምባገነንነትንና ግጭትን ለማስፈን ሲጣጣር ነው የታየው። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ማግስት፣ በጃፓን እና በምዕራብ ጀርመን ላይ የተፈጠረው የነፃነት ለውጥ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ አልተደገመም።
ምናልባት ጥሩ ለውጥ የሚመጣው፣ በውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት ሳይሆን፣ በፖላንድ እና በቼክ እንደታየው፣ የአገሬው ህዝብ በሚያካሂደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይሆን እንዴ? በግብፅ፣ በሊቢያ፣ በቱኒዚያ፣ በሶሪያ የተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ፣ “የፀደይ አብዮት” በሚል ስያሜ ተስፋ የተጣለበትም በዚህ ምክንያት ነበር - ለውጥ ያመጣል በሚል። ደግሞስ፣ እንደ ሙዓመር ጋዳፊ የመሳሰሉ አምባገነኖች ከስልጣን ሲወገዱ፣ ብዙዎች ቢደሰቱ የተስፋ ብርሃን ቢታያቸው ምን ይገርማል?
ነገር ግን በፓላንድ እና በቼክ እውን ለመሆን የበቃው የነፃነት ለውጥ፣ በእነ ግብፅ እና በእነ ሶሪያ አልተደገመም። ሊቢያና ሶሪያ፣ በደርዘን በሚቆጠሩ ታጣቂ ቡድኖችና ጎራዎች አማካኝነት የጦርነትና የግጭት ማጥ ውስጥ ገብተዋል። በቱኒዚያና በግብፅ፤ ለወጉ ያህል የፖለቲካ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ነገር ግን፤ “ለውጥ” እና “ምርጫ”፣ በቀጥታ “የነፃነት ለውጥ” እና “የነፃነት ምርጫ” ይሆናሉ ማለት አይደለም። በግብፅ፣ ምርጫውን ያሸነፉት የሃይማኖት አክራሪዎች ናቸው። የጦር ሃይል ኮሎኔል በነበሩት በሁስኒ ሙባረክ ከሚመራው መንግስት ይልቅ፤ በመሃመድ ሙርሲ የሚመራው የአክራሪዎች መንግስት፣ በአምባገነንነት የባሰ ሆኖ አረፈው። አሁን የመንግስት ስልጣን ወደ ጦር ሃይል ተመልሷል - በጄኔራል አልሲሲ።
በሊቢያም እንዲሁ፤ የነፃነት ተስፋ አይታይም። ተቀናቃኞቹ ቡድኖች፣ አንድም አክራሪዎች ናቸው፤ አልያም በቀድሞ የጦር ጄኔራል ስር የተሰለፉ የስልጣን ጥመኛ ቡድኖች ናቸው፤ ወይም ደግሞ በጎሳ የተቧደኑ ታጣቂዎች። የሶሪያም ተመሳሳይ ነው። የኢራቅም እንዲሁ። በአጭሩ፣ መልካም የነፃነት ለውጥ አልመጣም። በዚህም ምክንያት፤ “መልካም ለውጥ እንዲመጣ መገፋፋትና ጫና ማሳደር እንችላለን” የሚለው የምዕራብ መንግስታት የቀድሞ ዝንባሌ ዛሬ ተሸርሽሯል።
እናም፣ ጋዜጠኞች በገፍ ሲታሰሩ ወይም ሲሰደዱ፣ በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰዎች ሲገደሉ ወይም የፓርቲዎች ፉክክር የማይታይበት ምርጫ ሲካሄድ፣ አለማቀፍ ተቋማትና የምዕራብ መንግስታት ዛሬ ዛሬ፣ ብዙም ድምፃቸውን አያሰሙም። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ስለ ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች መታሰር ሲጠየቁ የሰጡትን ምላሽ ማየት ይቻላል።
እንደ ድሮ ቢሆን፤ ጆን ኬሪ እስኪጠየቁ ድረስ ባልጠበቁ ነበር። የጋዜጠኞችን እስር እንደሚያወግዙ በመግለፅ ከእስር እንዲለቀቁ ጥሪ ያቀርቡ ነበር። ዛሬ ግን እንደ ድሮ አይደለም። ጆን ኬሪ እዚሁ አገር መጥተው ስለ ጋዜጠኞች መታሰር አልተናገሩም። ትንፍሽ አላሉም። ጥያቄ ሲቀርብላቸውም፤ “የጋዜጠኞቹና የፀሐፊዎቹ መታሰር ያሳስበናል...” የሚል ምላሽ ነው የሰጡት። በቃ? “ያሳስበናል” በሚል ነው ጉዳዩን ያለፉት።
ከአገር ውጭ የሚመጣ ጫና ተመናምኗል። እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋማት፣ በየጊዜው እንደተለመደው መግለጫና ሪፖርት ማውጣት አቁመዋል ማለት አይደለም። ነገር ግን፤ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታትን ወደ እርምጃ የማነሳሳት አቅማቸው ተዳክሟል። ምናለፋችሁ? ከአሜሪካና ከአውሮፓ መንግስታት እንዲሁም ከአለማቀፍ ተቋማት ይሰነዘር የነበረው ግፊትና ጫና፣ ዛሬ ከሞላ ጎደል ከስሟል ማለት ይቻላል። “ያሳስበናል” ከሚል የአንድ ደቂቃ መግለጫ ያለፈ ጫና እየጠፋ መጥቷል።
በአጭሩ፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በ2001 ዓ.ም ኢህአዴግን ሲያስጨንቁ የነበሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፈተናዎች፣ ዛሬ በአብዛኛው ጠፍተዋል፤ ወይም ደብዝዘዋል። እና ለምድነው የያኔው የወከባ ታሪክ ዛሬ የሚደገመው? ኧረ ተው ኢህአዴግ ተረጋጋ!





Read 4067 times