Saturday, 16 August 2014 10:44

የ11 ዓመቷ ዝነኛ ጋዜጠኛ ብዙ ህልሞች አሏት!

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(3 votes)

“ህልም የሚሸጥ ቢሆን ኖሮ ምን ትገዙ ነበር?”

    ዙሬል ኦዱዎሌ የአስራ አንድ አመት ታዳጊ ናት፡፡ ከናይጄሪያዊ አባቷና ከሞሪታኒያዊት እናቷ  እንዲሁም ከሶስት ታላላቅ  እህቶቿ ጋር በአሜሪካን አገር በካሊፎርኒያ ግዛት ትኖራለች፡፡ በአፍሪካ በፖለቲካ ጋዜጠኝነቷ እየታወቀች የመጣችው ዙሬል፤ በዚህ ዕድሜዋ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት  መሪዎች ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ ብዙ ሰዎች አፍሪካን የሚያዩት እንደ ረሀብ፣ ሙስናና ጦርነት ባሉ  አሉታዊ ጎኖች  ብቻ ነው፤ እኔ ግን በዜና ላይ የማይታዩ በርካታ አዎንታዊ ነገሮችን አይቻለሁ የምትለው ታዳጊዋ፤ ለአለም ማሳየት የምትፈልገውም አፍሪካ ያሏትን ድንቅ ነገሮች እንደሆነ ትናገራለች፡፡
ዙሬል ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረት ያገኘችው ከሁለት አመት በፊት  በትምህርት ቤቷ ለተካሄደ የዶክመንተሪ ውድድር  እንዲያግዛት ስለ ጋና የ1979 አብዮት  ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የጋናን የቀድሞ ፕሬዚደንት ጄሪ ሮውሊንግስን በደብዳቤ በጠየቀችበት ወቅት ነው፡፡ ጄሪ ሮውሊንግስ ለቃለምልልሱ ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲያሳውቋት ተደናግጣ የነበረ ቢሆንም ከወላጆቿ ጋር ጋና በመሄድ የቀድሞውን ፕሬዚደንት አስደምማቸዋለች፡፡  ለ15 ደቂቃ ተይዞ የነበረው የቃለምልልስ ፕሮግራምም ለዘጠና ደቂቃ የተራዘመ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ከዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ ምሳ አዘው ተመግበዋል፡፡
ይሄን ተከትሎ የታዳጊዋ ጋዜጠኛ ታሪክ በመላው አፍሪካ ሲሆን ከበርካታ አገራት ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋርም ቃለመጠይቆችን ማድረግ ችላለች፡፡ ዙሬል ቃለመጠይቅ ካደረገችላቸው መሪዎች መካከል የኬኒያ፣ የላይቤሪያ፣ የደቡብ ሱዳንና የጃማይካ መሪዎች ይገኙበታል፡፡
በፎርብስ አፍሪካ መፅሄት የተጠቀሰ ውስጥ በእድሜ ትንሿ ታዳጊ ለመሆን የበቃችው ዙሬል፤ በቢዝነስ ኢንሳይደር መጽሔት የዓለማችን 100 ተፅዕኖ አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥም ለመካተት በቅታለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በአል ላይ የክብር እንግዳ የነበረችው ታዳጊዋ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ “ግሎባል ብራንድ” አምባሳደር ስትሆን የናይጀሪያው ሄሪቴጅ ባንክ “ፋይናንሻል ሊትረሲ” አምባሳደር ተብላም ተሰይማለች፡፡
ታዳጊዋ ስለ ራሷ ያላት ግምት ምን እንደሆነ ተጠይቃ ስትመልስ፤ “ራሴን እንደ ዙሬል ነው የማየው፤ ብዙ ስራዎች የሚጠብቋት የ11 ዓመት ልጅ፤ ነገር ግን ለብዙ አፍሪካውያንና በአለም ላይ ላሉ ህፃናት እንደ መንፈስ አነቃቂ የምትቆጠር” በማለት ገልፃለች፡፡
የዙሬል ግቦች በአንድ ሰው አማካይ የህይወት ዘመን የሚሳኩ አይመስሉም፡፡ በዘጠኝ አመቷ አሀዱ ብላ ከጀመረችው የጋዜጠኝነት ስራ ከስምንት ዓመት በኋላ በ19 ዓመቷ ተሰናብታ የልጆች መፅሀፍ  ደራሲ ለመሆን ትፈልጋለች፡፡ ፕሮፌሽናል አትሌት በመሆንም በመቶ ሜትር ሩጫ የመወዳደር ዕቅድ አላት፡፡  እኒህ ብቻ ግን አይደሉም፡፡ ኢንጂነርና ሃኪም ለመሆንም ትሻለች፡፡
እነዚህን ህልሞቿን ለማሳካት ደግሞ በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑ ሶስት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ገብታ መማር እንደምትፈልግ ዙሬል ትናገራለች፡፡ እነሱም የአሜሪካዎቹ ሀርቫርድ፣ ዬል እና ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ ዙሬል ሌላም ህልም አላት። “በዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እንድችል  የአሜሪካ ፕሬዚደንት መሆን እፈልጋለሁ” ትላለች፡፡
ዙሬልና እህቶቿ በአሁኑ ሰዓት ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በኢንተርኔት ኦንላይን ሲሆን ታዳጊዋ የዕድሜ ዕኩዮቿን በሦስት ክፍል በመብለጥ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ “ሌሎች ትምህርት ቤቶች የተመደበልህን ትምህርት ከጨረስክ ሌለ ትምህርት የለም፤  በኦን ላይን ፕሮግራም ግን ሌሎች ነገሮችንም እንሰራለን”፡፡ ብላለች - የኢንተርኔት ትምህርት ያለውን ጠቀሜታ ስታስረዳ፡፡
ዙሬልን ለማነፅ ሙሉ ጊዜያቸውን የሰጡት አባቷ፤ “ልጆችህ እንደተለመደው ሆነው እንዲያድጉ ከተውካቸው እንደዚያው ሆነው ያድጋሉ፡፡ እኛ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ብቻ ሳይሆን የተለዩ እንዲሆኑም ብዙ ሰርተናል” ብለዋል፡፡  
ልጆቹ ትምህርታቸውን ቤት ውስጥ ሆነው በኢንተርኔት መማራቸው ተጨማሪ ጊዜ እንደሰጣቸው የሚናገሩት የታዳጊዋ እናት ፓትሪሽያ፤ በተገኘው ትርፍ ጊዜ ቤተሰቡ በርካታ የዓለም ክፍሎችን መጐብኘት እንደቻለ ገልፀዋል፡፡ የዙሬል ቤተሰብ ከአሜሪካ በተጨማሪ በፓሪስና ሆንግኮንግ ይኖሩ እንደነበር ፓትሪሽያ ተናግረዋል፡፡
ዙሬልና ሁለቱ እህቶቿ ከትምህርታቸው ጐን ለጐን ከቻይና ዋና ዋና ቋንቋዎች አንዱ የሆነውን የማንዳሪን ቋንቋ እየተማሩ እንደሆነ እናትየው ገልፀዋል፡፡ “ሁሉም ልጅ የራሱ ተሰጥኦ አለው፤ የወላጆች  ትልቁ የቤት ስራ ተሰጥኦዋቸውን በመለየት ማነፅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ህፃን እድሉ ከተሰጠው የላቀ ውጤት ማምጣቱ አይቀርም” ሲሉም አስረድተዋል - ፓትሪሽያ፡፡
በአፍሪካ ጉዞዎቿ ብዙ ሴት ልጆች በመንገድ ላይ የተለያዩ ነገሮችን ሲሸጡና በርከት ያሉ ወንዶች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ማየቷን የምትናገረው ዙሬል፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከናይጄሪያ ሌጎስ ቢዝነስ ስኩልና ከዩኤስ ኮንሶሌት ጋር በመተባበር “አልሙ፣ ተናገሩ ፣በራሳችሁ ቁሙ” በሚል ፕሮግራም ላይ እየሰራች እንደሆነ ተናግራለች። በአፍሪካ አገራት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመሄድም ታዳጊ ተማሪዎችን በትምህርት ዙሪያ የሚያነቃቃና የሚያንፅ ንግግሮችን እንደምታደርግ ገልፃለች፡፡ “ልጆች ሁልጊዜ ትልቅ እንዲያስቡና ማንም ከህልማቸው እንዲያስተጓጉላቸው መፍቀድ እንደሌለባቸው እንዲያምኑ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ የምነግራቸውም ይህንኑ ነው” ትላለች ዙሬል፡፡
በታንዛኒያ ብዙ ተማሪዎች በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ ባደረገችው ንግግር፤ “ህልም የሚሸጥ ቢሆን ኖሮ ምን ትገዙ ነበር?” ስትል የጠየቀችው ታዳጊዋ፤ “ህልማችሁ ከጥረታችሁ ጋር ተዳምሮ መፃኢ ማንነታችሁን ይወስነዋል፤ ህልማችሁ ትልቅ በሆነ ቁጥር የብዙዎችን የወደፊት እጣ የሚወስን ይሆናል” ስትል ትልቅ ማለም ስላለው ፋይዳ አስረድታለች፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ኔልሰን ማንዴላ አርአያዬ ናቸው የምትለው ዙሬል፤ ምክንያቷን ስትናገርም “በልቡ ውስጥ ምንም ዓይነት ጥላቻ የሌለበት ሰው ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ የአገሩ መሪ ነበር” ብላለች፡፡
ከአብዛኞቹ የዕድሜ ዕኩዮቿ በተለየ “የማልወጣው ፈተና የለም” ብላ የምታምነው የ11 ዓመቷ ጋዜጠኛ፤ በቅርቡ ከአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ጋር ቃለምልልስ ማድረግና ወደ  ኢትዮጵያ መጥታ  ልጆችን የሚያነቃቃ ንግግር ማድረግ እንደምትፈልግ ገልፃለች፡፡

Read 2624 times