Saturday, 16 August 2014 10:46

የአልኮል ሱሰኝነትና መዘዙ

Written by  ከወንድወሰን ተሾመaltacounselingeth@yahoocom
Rate this item
(4 votes)

(የማህበራዊ ሳይንስና የስነ ልቦና ባለሙያ)
ከአልታ ምርምር ሥልጠናና ካውንስሊንግ

      በዚህ አጭር ፅሁፍ ሱሰኝነት ምንድነው? ከሚለው ጀምሮ አልኮልን አዘውትሮ መጠጣት የሚያመጣቸውን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ችግሮች እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ቤተሰባዊና ማህበራዊ ቀውሶችን፣ ከአልኮል ሱሰኝነት ነፃ ለመሆን የሚያስችሉ መንገዶችን ጭምር ለማየት አንሞክራለን፡፡
ከብዙ አመታት በፊት  በዩኒቨርሲቲ እያለን አንድ ጓደኛችን ሲሰክር መንገድ ዳር የተኛ ቁሻሻ ውስጥ “ዋና ላሳያችሁ” እያለ “ይዋኝ” ነበር፡፡ በመጠጥ ሃይል ሲሰክሩ አንዳንዶች ከሰዎች ጋር ይጋጫሉ፣ሌሎች ራሳቸውን ከግንብ ጋር ያጋጫሉ፡፡ እንዲሁም ሌሎች “ይጀግናሉ”- በሰፈር ያለ “ጠላታቸውን” ውጣና ይዋጣልን በማለት ጎረቤቶቻቸውን ይረብሻሉ። ሌሎች ደግሞ ሚስታቸውን ይደበድባሉ (ሰክራ ቤት ገብታ ባሏን የምትደበድብ ሴትም ትኖር ይሆናል)፤ እንዲሁም ሌሎች እኩለ ሌሊት ላይ ቤታቸው ገብተው ልጆቻቸውን ከተኙበት ቀስቅሰው በእጃቸው ያንጠለጠሉትን “ግማሽ ኪሎ ስጋ” ተጠብሶ  አንድ ሰው ሳይቀር ይብላ ይላሉ፤ አንዳንዶች ቱቦ ስር ያድራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሰው ፈንክተው ጣቢያ ይታሰራሉ፣ እንዲሁ ሌሎች “ለምን አየኸኝ” ብለው አንቧጓሮ ይፈጥራሉ፤ ሌሎች ደግሞ “ለምን ዘጋኸኝ” ይላሉ:: አንዳንዶች ያለቅሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ያስለቅሳሉ፡፡ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡

ሰው የአልኮል ሱሰኛ የሚባለው ምን ሲሆን ነው?
ሰው ሱሰኛ የሚባለው አልኮል መጠጣቱ ማህበራዊ፣ ቤተሰባዊና ህጋዊ ችግሮችን እያመጣበት መጠጣቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡

በአልኮል የተመረዘ ሰው በሚከተሉት ይታወቃል፡-
በቅርብ አልኮል መጎንጨቱ
አግባብ ያልሆኑ ባህሪያትን ማሳየት:- ለምሳሌ አግባብ ያልሆነ የወሲብ ባህሪ፤ ቁጡነት፤የ ስሜት መለዋወጥ፤የተዛባ ውሳኔ ሰጪነት፤ የስራና የማህበራዊ እንቅስቃሴ መገታት፤ ወዘተ ሆነው እነዚህም ባህሪያት መጠጥ በሚወስድበት ጊዜና መጠጡን በወሰደ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡
ቀጥሎ ከተዘረዘሩት አንድ እና ከዚያ በላይ ምልክቶች መታየት፡- የማይሰማ ድምፅ ማውጣት( Slurred speech)፤ የሰውነትን  እንቅስቃሴ በአግባቡ  አለመጠቀም (in coordination)፤የአይን ፈጣን በሆነ መልኩ መርገብገብ (nystagmus)፣ መንገዳገድ  (unsteady gait)፤ ትኩረትና የማስታወስ ችሎታ መገታት (impairment in attention or memory)፣  እና ራስን መሳት (Stupor or coma) ናቸው
በአልኮል መጠጥ ላይ መደገፍ (Alcohol Dependance) ምን ማለት ነው?
አልኮል የሚያመጣውን ከባድ ችግሮች እያወቁ መጠጣት መቀጠልን ያሳያል፡፡  ለመስራትም ሆነ ነቃ ብሎ ወዲያ ወዲህ ለማለት አልኮል መጎንጨትና ያለ አልኮል ለመስራትም ሆነ ማህበራዊ ግዴታዎችን ለመወጣት አለመቻል ነው፡፡ ይህም የፊዚዎሎጂ (physiological)፣ የአዕምሮና(cognitive) የባህሪ (behavioral) ችግሮችን ያካትታል፡፡
ይህም በተደጋጋሚ መጠጣትና ጥገኛ መሆን የሚከተሉት  ችግሮች  እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡-
መጠጡ የሚያመጣለትን የባለፈውን ውጤት ለማግኘት ከባለፈው ተጨማሪ መጠን ለመጠጣት መፈለግ (Alcohol tolerance) ወይም ተመሳሳይ የአልኮል መጠን በመውሰድ የመጀመሪያውን ያህል ውጤት እያደር ማጣት፡-
ለረዥም ጊዜ ሲደረግ የነበረን አልኮል መጠቀም ማቆም ወይም መጠኑን መቀነስ (Alcohol Withdrawal symptoms) የሚከተሉትን ምልክቶች ያሳያል  እነዚህም ፡-
ቅፅበታዊ መነሳሳት(ማላብ፤ የልብ ምት  ከተለመደው ይልቅ መጨመር)
የእጅ መንቀጥቀጥ
እንቅልፍ ማጣት
ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ
ጊዜያዊና ያልተለመደ ድምፅ በጆሮ መስማት፣ በአይን እንግዳ ነገር መመልከት(visual and auditory hallucinations or illusions)
ዓላማ የሌለው የሰውነት እንቅስቃሴ
ከጥቂት ሰኮንዶች እስከ 2 ደቂቃ የሚወስድ የሰውነት መራድና መውደቅ
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ሲከሰቱ በሰውየው የሥራ፣የማህበራዊና ሌሎች ጠቃሚ ድርጊቶች ላይ ችግርን ይፈጥራል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት  ምልክቶች ጠጪው አልኮል መውሰድ ካቆመበት ወይም ከቀነሰበት ጀምሮ እስከ 12 ሰዓታት ባለ ጊዜ ውስጥ መታየት የሚጀምሩ ናቸው፡፡ ከ እነዚህ ችግሮች ለመውጣት መልሶ አልኮል መጎንጨት ወይም ወደ ህክምና መሄድ ይጠበቅበታል፡፡
3. ተገድዶ መጠጣት (compulsive use):- ሱሰኛ
የሆነ ሰው “ጠጣ ጠጣ” የሚል የውስጥ ከፍተኛ
ፍላጎት (craving for alcohol) በመኖሩ እንኳን
ገንዘብ ኖሮት “ተበድሮም ተለቅቶም” ቢሆን
አልኮልን ተገድዶ ይጠጣል፣
4. ከፍተኛ ከሱስ የመላቅቅ ፍላጎት መፈጠርና
    ለተደጋጋሚ ጊዜ  ያልተሳካ (የሚቋረጥ) ሙከራ
    ማድረግ፣
5. ለመጠጥ ፍለጋ ፣ መጠጥ ለመጠጣት እና
   መጠጡ ከሚፈጥረው ጫና ለመላቀቅ የማይናቅ
    ጊዜ ማቃጠል/ማባከን፣
6. ጠቃሚ ማህበራዊ ጉዳዮችን፣የስራ እና የመዝናኛ
    ዕድሎችን መተው ወይም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣
7. አልኮሉ የሚያመጣውን ችግር እያወቁ መጠጣት
    መቀጠል፣

የአልኮል ሱሰኞች በተጨማሪም የሚከተሉትን ችግሮች ይፈጥራል፡-
በስራና በትምህርት ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል
ልጆችን ከማሳደግና የቤተሰብ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ችግር ይኖረዋል
ከስራ ወይም ከትምህርት ቤት መቅረትን ያመጣል
መኪና ከመንዳትና ማሽን ከማንቀሳቀስ  ጋር ተያይዞ ለአደጋ ያጋልጣል
ከሰዎች ጋር ሊኖር የሚገባውን ጤናማ ግንኙነት ያበላሻል
በህፃናት ላይ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ለመፈፀም ያበረታታል

ከአልኮል ሱሰኝነት ነፃ  እንዲሆኑ የሚረዱ  መንገዶች፡-
አስተሳሰብና  ባህሪ ለውጥ ላይ የሚሰራ ካውንስሊንግ (Cognitive Behavioral Therapy)፡- በዚህ የስነ ልቦና ሂደት ካውንስለሩ የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጦችን በክሊያንቱ ላይ እንዲመጣ በመርዳት በሂደት መጠጡን እየቀነሰ እንዲሄድና እንዲያቆም ይረዳዋል፡፡ ይህ በአጭር ጊዜ የሚሆን አይደለም፡፡ የአስተሳስብና የባህሪ ለውጦች ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡
ከክሊያንቱም ሙሉ ፈቃደኝነትና ትዕግስትን መጠየቃቸው እርግጥ ነው፡፡ በካውንስሊንግ የሚረዳ ክሊያንት ከካውንስለሩ ጋር በመሆን የህክምና ዕቅዱን በማውጣት (treatment plan) ተግባራዊ ያደርጋል ማለት ነው።  የካውንስሊንግ ህክምው ስለ አልኮል ማስተማርን (Alcohol education) እና ሌሎች የህክምና ስልቶችን(Therapies/interventions)  ሊያካትት ይችላል፡፡
አልኮል በማቆም ምክኒያት የተፈጠረውን ችግር (withdrawal symptoms) ለመቀነስ ሃኪምዎ መድሃኒት ሊሰጥዎ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይኸኛው የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጥን አያመጣም፡፡
ዓለም አቅፍ ከአልኮል ነፃ የሆኑ ሰዎች በመሰረቷቸው ድርጅቶች አባል በመሆን ተሞክሮዎችን በማግኘት ራስን መርዳት፡- ለምሳሌ  በዓለም አቀፍ ደረጃ የእንረዳዳ ድርጅት አለ፡፡
በርካታ የአልኮል ሱሰኞችን ከአልኮል ነፃ እንዲወጡ በመምከርና ተሞክሮን በማካፈል ውጤታማ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ይህ ድርጅት Alcoholics Anonymous (AA) ይባላል፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. በ 1935 በቢል ዊልሰንና በ ዶ/ር ቦብ ስሚዝ የተመሰረተው ድርጅት በመንፈሳዊና በባህሪ ለውጦች ላይ ያተኮረ መፍትሄ አለኝ ይላል፡፡
ቸር እንሰንብት

Read 5450 times