Print this page
Saturday, 16 August 2014 10:51

በእንግሊዝ የአልኮል መጠጦች የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲጀመር ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእንግሊዝ የአልኮል መጠጦች በተጠቃሚዎች ላይ የሚያደርሷቸውን ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች ለመቅረፍ አምራቾች በመጠጦቹ ላይ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ጽፈው ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ህግ እንዲወጣ በፓርላማ አባላት ቡድን ለእንግሊዝ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአልኮል መጠጦች የሚያደርሱትን ችግር በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራውና ሁሉንም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ያቀፈው የፓርላማ ቡድን ለመንግስት ያቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚለው፣ አምራቾች የአልኮል መጠጦችን ጎጂነት የሚገልጹ ጽሁፎችን በምርቶቻቸው ላይ እንዲለጥፉ መገደድ ይኖርባቸዋል፡፡
በእንግሊዝ ከአልኮል መጠጦች ተጠቃሚነት ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለማቃለል ያግዛሉ ተብለው በቡድኑ የቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች 10 ሲሆኑ፣ ቡድኑ ለሃሳቦቹ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ቡድኑ ለመንግስት ባቀረበው የመፍትሄ ሃሳቦች ሰነድ፤ የጤና ማስጠንቀቂያዎች በሲጋራ ምርቶች ላይ መለጠፍ የተለመደ መሆኑን ጠቅሶ፣ በአልኮል መጠጦች ላይ ግን የመጠጡን ይዘትና በውስጡ የሚገኙትን ንጥረነገሮች ከመግለጽ ያለፉ ጽሁፎች እንደማይወጡ ገልጧል፡፡
በመሆኑም የአልኮል መጠጦች የሚያደርሷቸውን የጤና ችግሮች፣ ውስጣዊ ቅንብራቸውንና የንጥረ ነገር ይዞታቸውን ወዘተ ለተጠቃሚዎች የሚገልጹ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ይዘው ገበያ ላይ እንዲውሉ የሚያስገድድ ህግ ሊወጣ ይገባል ብሏል፤ ቡድኑ ለመንግስት ባቀረበው የመፍትሄ ሃሳቦች ሰነድ ውስጥ ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል፣ ጠጥቶ የማሽከርከር ገደብ እንዲሻሻል፣ በአልኮል ገበያ ላይ ጠበቅ ያለ የህግ እርምጃ እንዲወሰድ፣ አስገዳጅ የዋጋ ተመን እንዲወጣ የሚጠይቁ ይገኙባቸዋል፡፡
ከአልኮል ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ብሄራዊ ዘመቻ እንዲጀመር፣ ለማህበራዊ ሰራተኞች ሆነ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና የሚሰጥበት መንገድ እንዲፈጠር፣ ከአልኮል ሱሰኝነት ለመውጣት የሚያስችለውን ህክምና ሽፋን አሁን ካለበት 6 በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እንዲሰሩም ቡድኑ ጠይቋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ መንግስት ከመጠን በላይ የሆነ የአልኮል ተጠቃሚነትን ለመቀነስና ህብረተሰቡ የአልኮልን ጎጂነት በተመለከተ ግንዛቤ እንዲጨብጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው፣ ርካሽና አደገኛ የሆኑ የአልኮል መጠጥ አይነቶች ለገበያ እንዳይቀርቡ በህግ መከልከሉንም አስታውሰዋል፡፡ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባልና የቡድኑ ሊቀመንበር የሆኑት ትሬሲ ክሮች እንዳሉት፣ በእንግሊዝ በየአመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ከአልኮል ጋር ተያያዥነት ባላቸው በሽታዎች ተጠቅተው በህክምና ተቋማት ይረዳሉ፡፡ በጉበት በሽታ የሚጠቁ እድሜያቸው ከ30 አመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥርም ባለፉት 20 አመታት ከእጥፍ ላይ ጨምሯል፡፡
አልኮል በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ 21 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል ያሉት ክሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቡድኑ ላቀረባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ተፈጻሚነት ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው፣ የአልኮል መጠጦች በአገሪቱ ትልቅ የጤና ችግር መንስኤዎች ሆነው እንዳይቀጥሉ የሚያስችል በጎ ጅምር ይሆናል ሲሉም አክለዋል።
አልኮል ኮንሰርን የተባለው የአገሪቱ ተቋም ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃኪ ባላርድ በበኩላቸው፣ የአልኮል መጠጦችን በተመለከተ አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበት ገልጸው፣ የአልኮል መጠጦች 60 ያህል ከሚደርሱ የጤና ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ጨምረው አስረድተዋል፡፡

Read 3208 times
Administrator

Latest from Administrator