Saturday, 16 August 2014 11:09

ሐማስ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

          ሰሞኑን በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል በተቀሰቀሰውና በተፋፋመው ውጊያ 1ሺ800 ፍልስጤማውያንና 67 አይሁዳውያን ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ አጭር ጽሑፍ አላማ ስለዚህ አስከፊና ጋዛን የድንጋይ ክምር እያደረገ ስላለ ጦርነት ትንተና ለመስጠት አይደለም፡፡ ይልቁንም የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት ስለሆነው ሐማስ አንዳንድ ነጥቦችን ለማስጨበጥ ነው፡፡ ሐማስ የአረብኛ ምህፃረ ቃል ሲሆን harkat muqawamah Islamya ወይም ደግሞ በእንግሊዝኛ Islamic resistance movement የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
ሐማስ የፍልስጤም ሱኒ ኢስላማዊ ድርጅት ሲሆን የተደራጀ ወታደራዊ ክንፍ አለው፡፡ ይህ ወታደራዊ ክንፍ izzad al quassam በመባል ይታወቃል፡፡ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አብዛኛውን የፍልስጤም ፓርላማ መቀመጫዎችን ካሸነፈ በኋላ ጋዛን ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡
ሀማስ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ ህብረት፣ በግብጽና ዮርዳኖስ በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት ሲሆን በአንፃሩ በኢራን፣ በሩሲያ፣ በቱርክ፣ በቻይናና በሌሎች በርካታ አረብ አገራት እንደአሸባሪ ድርጅት አይታይም፡፡ ሐማስ የተመሰረተው ፍልስጤምን ከእስራኤል ይዞታ ነፃ አውጥቶ እስላማዊ መንግስት በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ ለመመስረት ነው። ዋና ከተማውንም ምስራቅ እየሩሳሌም ለማድረግ አላማው አድርጐ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራቾች ሼክ አህመድ ያሲን አብደላ ዓዘዚ እና መሐመድ ዘሐር ሲሆኑ የተመሰረተው በ1987 ዓ.ም ነው፡፡ ዋና መቀመጫውም በፍልስጤም እና በደሃ ኳታር ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ኢስላማዊ መንግስት በፍልስጤም ከመመስረት ባሻገር የፍልስጤም ስደተኞችን ወደ እስራኤል መመለስና የ1967ትን ስምምነት መሰረት ያደረገ የድንበር ማካለልን አላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡
የሐማስ ወታደራዊ አንጃ ከመሳሪያ ግዢና አቅርቦት ጀምሮ እስከ ወታደራዊ ጥቃት የመፈፀም ተግባራትን ይፈፀማል፡፡ እንደ እስራኤል የስለላ ድርጅት መረጃ መሰረት፤ ሀማስ አባላቱን የሚያሰለጥነው በኢራንና በሶሪያ ውስጥ ነው፡፡ ሐማስ በዚህ አንጃው አማካኝነት በርካታ የአጥፍቶ መጥፋት ፍንዳታዎች እንዲሁም የሞርታርና የሮኬት ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ አድርሷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ፡- አፕሪል 9 ቀን 1996 በካፋር የአውቶብስ አጥፍቶ መጥፋት ፍንዳታ 8 ሰዎች ሲሞቱ፣ ሃላፊነቱን ሐማስ ወስዷል፡፡
ፌብሯሪ 25 ቀን 1996 በኢየሩሳሌም የአውቶብስ ላይ ጥቃት 26 ሰዎች ሲሞቱ፣ አሁንም ሃላፊነቱን ሀማስ ወስዷል፡፡
ማርች 3 ቀን 1996 ዓ.ም አሁንም በኢየሩሳሌም ባደረገው የአጥፍቶ ማጥፋት ፍንዳታ 19 ሰዎች ሲሞቱ፣ እስራኤል ከሐማስ ራስ አልወረደችም፡፡
ማርች 4 ቀን 1996 በዲዝ ንግፍ ሴንተር በደረሰው ፍንዳታ 13 ሰዎች ሲሞቱ፣ ሐማስና ኢስላማዊ ጀሃድ ዋናዎቹ ተጠያቂዎች ነበሩ፡፡
ይህ እንግዲህ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ያደረሰው ጥቃት ሲሆን ከ1996-2014 ያደረሰው ጥቃት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
በ2007 በተካሄደው ጥናት መሰረት፤ እስራኤል ላይ ከተደረጉት የአጥፍቶ መጥፋት የቦንብ ፍንዳታዎች 39.9 ፐርሰንቶቹ በሐማስ የተደረጉ ሲሆን 26.4 በፋታህ፣ 25.7 በኢስላሚክ ጀሀድ፣ 5.4 በፍልስጤም ነፃ አውጭ ግንባር (PFLP) 2.7 ደግሞ በሌሎች ድርጅቶች የተደረጉ ናቸው፡፡ IZZad al quassam” በመባል የሚታወቀው የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
መጅሊስ አል ሹራ ወይም የምክር ቤቱ መቀመጫ በሐማስ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያለው አካል ሲሆን ስብስቡም ከዌስት ባንክ፣ ከጋዛ፣ ከእስራኤል እስር ቤትና ከፖለቲካ ቢሮ በተውጣጡ አባላት የተዋቀረ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እስከ ወታደራዊ ጥቃት ያሉትን እንቅስቃሴዎች ይወስናል። ከፍተኛው ውሳኔ ሰጪ አካል ግን የፖለቲካው ቢሮ ነው፡፡
በ2014 የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል ሊቀመንበር ሙሳ አህመድ አቡ መዝሩቅ፤  “ሐማስ እስራኤልን እንደ ሐገር እውቅና አይሰጥም” ብለው ነበር፡፡ ይህ የማይሻገሩት ቀይ መስመር ነው፡፡

Read 3858 times