Saturday, 16 August 2014 10:24

“ሴቶች በአደባባይ መሳቅ የለባቸውም” ያሉት የቱርክ ምክትል ጠ/ሚ ክስ ተመሰረተባቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)
  • የአገሬ ሴቶች ሆይ!... እስከቻላችሁት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ሳቁ!”
  • የቱርክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ

    የቱርኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቡለንት አሪንክ ባለፈው ሳምንት ሴቶች በአደባባይ ድምጻቸውን ጎላ አድርገው መሳቅ የለባቸውም ብለው መናገራቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ክስ እንደተመሰረተባቸውና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረገጾች የሚሰነዘርባቸው ነቀፌታና ትችት እየተበራከተ መምጣቱን ሲ ኤን ኤን ዘገበ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት፣ “ሴቶች ሰው በተሰበሰበበት ጎላ አድርገው መሳቅ የለባቸውም፣ ነውር የሆነን ነገር ለይተው ሊያውቁና ‘አንገት ደፊ’ ሆነው ሊኖሩ ይገባል፣ ወንዶችም ‘ሴት አውል’ መሆን የለባቸውም!” በማለት ከሳምንት በፊት የተናገሩ ሲሆን፣ የጾታዊ መብቶች ተሟጋቾች የሴቶችን መብቶች ህጎች የሚጥስና የጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ የሚዳርግ ህገወጥ ተግባር ፈጽመዋል በሚል በምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ላይ ክስ መስርተዋል፡፡ በምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ንግግር የተበሳጩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ሴቶች በአደባባይ ሲስቁ የተነሷቸውን ፎቶግራፎችና ተቃውሟቸውን የሚገልጹ መልዕክቶቻቸውን በድረገጾች ላይ በስፋት ማሰራጨታቸውን እንደተያያዙትም ሲ ኤን ኤን በዘገባው ገልጧል።
በትዊተር ገጽ ላይ ጉዳዩን በተመለከተ ከ 160 ሺህ በላይ ምልልሶች መደረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ አብዛኞቹ አስተያየቶች የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር የሚተቹ እንደሆኑና ዜጎችም በባለስልጣኑ አባባል የተበሳጩ መሆናቸውን ገልጧል፡፡ በቱርክ ሴቶች ላይ የሚደረገው ጭቆና በአደባባይ አትሳቁ ከሚለው የባለስልጣኑ ንግግር የዘለለና እጅግ ስር የሰደደ ነው ያለው ሲ ኤን ኤን፣ 40 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ ሴቶች የአስከፊ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ሆነው ኑሯቸውን እንደሚገፉ ገልጧል፡፡ በዚህ ሳምንት በሚካሄደው የቱርክ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የአሁኑ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አንድ ተወዳዳሪ ሴቶች አትሳቁ የሚለውን የሰሞኑን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው ላይ ለአገራቸው ሴቶች ባስተላላፉት መልዕክት፣ “የአገሬ ሴቶች ሆይ!... እስከምትችሉት ድረስ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ሳቁ!” ብለዋል፡፡

Read 2386 times