Saturday, 16 August 2014 11:10

ከ900 በላይ ደራሲያን ህልውናችን አደጋ ውስጥ ነው አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ900 በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ታዋቂ ደራሲያን ከመጽሃፍት ሽያጭ ጋር በተያያዘ በደል ፈጽመህብናል፤ አንተ በሚሊዮኖች ዶላር እያፈስክ እኛ ግን ማግኘት የሚገባንን ያህል ገንዘብ እያገኘን አይደለም፤  ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል፤ የምትከተለውን የመጽሃፍት ሽያጭ አሰራር በአፋጣኝ አስተካክል ሲሉ አማዞን ለተሰኘው የድረገጽ ሽያጭ ኩባንያ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከአለማችን ታላላቅ አሳታሚ ኩባንያዎች አንዱ በሆነው ‘ሃቼቴ’ አማካይነት መጽሃፍቶቻቸውን እያሳተሙ ለንባብ ሲያበቁ የቆዩት እነዚህ ታዋቂ ደራሲያን፣ ከአሳታሚው መጽሃፍቱን እየተረከበ ለገበያ የሚያቀርበው አማዞን እየተከተለው የሚገኘው የሽያጭ ስርዓት ከመጽሃፍቶቻችን ሽያጭ ተገቢውን ገንዘብ እንዳናገኝ የሚያደርግ ነው በማለት ነው አቤቱታቸውን ያቀረቡት፡፡
ደራሲያኑ ለአማዞን በላኩትና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ለንባብ በበቃው በዚህ ማመልከቻ እንዳሉት፣ አማዞን መጽሃፍትን በወቅቱ ለደንበኞቹ አለማድረሱ፣ የቅድመ ክፍያ ትዕዛዞችን መቀበል ማቆሙና ጄኪ ሮውሊንግና ስቴፋኒ ሜየርን በመሳሰሉ አንዳንድ የኣለማችን ታዋቂ ደራሲያን መጽሃፍት ላይ የነበረውን ዋጋ ቅናሽ ማቆሙ የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ አድርጎናል ብለዋል፡፡
አማዞን ከመጽሃፍት ባለፈ ማንኛውንም የሸቀጥ አይነት ለገበያ የሚያቀርብ ከአለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች አንዱ የመሆን ህልሙን ለማሳካት በጀመረው ጉዞ ውስጥ የኛ ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ደራሲያኑ፣ ኩባንያው የደራሲያኑን ስራዎች ሲሸጥ በቆየባቸው አመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማፍራቱን አስታውሰዋል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን አማዞን ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የጀመረው አዲስ የሽያጭ አሰራር፣ ብዙ ሃብት ያካበተባቸውን ደራሲያን የሚጎዳና ህልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ አሰራሩን በአፋጣኝ እንዲያስተካክል ለመጠየቅ መገደዳቸውን በጋራ ባስገቡት ማመልከቻ እንደገለጹ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሃቼቴ በተባለው አሳታሚ ኩባንያ አማካይነት ስራቸውን ለአንባቢ ከሚያደርሱትና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ማልኮም ግላድዌል፣ ጄምስ ፓተርሰንና ዶና ታርትን የመሳሰሉ ደራሲያን በተጨማሪም፣ በሌሎች አሳታሚዎች የሚያሳትሙ ጆን ግሪሻምና ሴተፈን ኪንግን የመሳሰሉ ሌሎች የአለማችን ዝነኛ ደራሲያንም የአማዞንን ድርጊት በመቃወም በማመልከቻው ላይ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል፡፡  አማዞን ከአሳታሚው ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት የደራሲያኑን መጽሃፍት በድረገጽ አማካይነት ሲሸጥ ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሽያጩ ላይ ያልተገባ ድርጊት ይፈጸማል በሚል በመካከላቸው አለመስማማት ተፈጥሯል፡፡
አማዞን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በድረገጽ አማካይነት ለሽያጭ የሚበቁ ኤሌክትሮኒክ መጽሃፍት አብዛኞቹ በ9.99 ዶላር መሸጥ ሲገባቸው በ14.99 ዶላር እየተሸጡ እንደሚገኙና ዋጋቸው ያለአግባብ ውድ መሆኑን በመጥቀስ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግሮ ነበር፡፡
ዋጋን በመቀነስ ብዙ መጽሃፍትን መሸጥና ከብዛት ትርፍን ማሳደግና ከሚገኘው ትርፍም ለአሳታሚው ኩባንያም ሆነ ለደራሲያኑም የተወሰነ ገንዘብ መስጠት እንደሚቻል በገለጸበት ወቅት፣ ከ 7 ሺህ በላይ ደራሲያን ጉዳዩን በመደገፍ ከአማዞን ጋር ለመስራት መፈራረማቸውንም ዘገባው አስታውሷል።

Read 1862 times