Saturday, 16 August 2014 11:12

ታዋቂው ኮሜዲያንና የፊልም ተዋናይ ሮቢን ዊሊያምስ ራሱን ገደለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በከፍተኛ ድብርትና በመንፈስ ጭንቀት ሲሰቃይ ነበር
ታዋቂው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይና ኮሜዲያን አሜሪካዊው ሮቢን ዊሊያምስ በተወለደ በ63 አመቱ ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ ከሳን ፍራንሲስኮ በስተሰሜን ቲቡሮን አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መኝታ ቤት ውስጥ ራሱን በቀበቶ በማነቅ እንዳጠፋ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
‘ጉድሞርኒንግ ቬትናም’ና ‘ዴድ ፖየትስ ሶሳይቲ’ን በመሳሰሉ በርካታ ተወዳጅ ፊልሞቹ የሚታወቀውና የኦስካር ተሸላሚው ተዋናይ ሮቢን ዊሊያምስ፣ ለረጅም ጊዜያት በከፍተኛ ድብርትና በመንፈስ ጭንቀት ይሰቃይ እንደነበርና በቅርቡም ወደ አእምሮ ህክምና መስጫና ማገገሚያ ማዕከል አምርቶ ከዚህ ቀደም አቋርጦት የነበረውን ህክምና መከታተልና እንክብካቤ ማግኘት ጀምሮ እንደነበር ፖሊስን ጠቅሶ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ተዋናዩ የአልኮል መጠጥ ሱስ ተጠቂ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚህ ሱስ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል በኮሜዲ ስራዎቹ ውስጥ በግልጽ ይናገር እንደነበር ገልጧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተዋናዩን ሞት አስመልክተው ለቤተሰቦቹ በላኩት የሃዘን መግለጫ መልዕክት፣ “ሮቢን ዊሊያምስ ውስጣችንን ኮርኩሮ ሲያስቀን፣ ልባችንን ሰርስሮ ሲያስለቅሰን ኖሮ ያለፈ ልዩ ሰው ነው፡፡ እሱ በሰው አገር ከሚገኙ ወታደሮቻችን፣ በገዛ አገራችን ጎዳናዎች ላይ ተገልለው እስከሚገኙ ዜጎች በሁሉም ልብ ውስጥ አሻራውን ማስቀመጥ የቻለ ድንቅ ሰው ነው” ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1951 ኤሊኖይስ ውስጥ የተወለደው ሮቢን ዊሊያምስ በተለያዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ለረጅም አመታት የስታንዳፕ ኮሜዲ ስራዎቹን ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ1998 በምርጥ ረዳት ተዋናይነት የኦስካር ተሸላሚ ያደረገውን ‘ጉድ ዊል ሃንቲንግ’ ጨምሮ በበርካታ ተወዳጅ ፊልሞች ላይ በመስራት የትወና ብቃቱን ያስመሰከረ ተዋናይ ነበር፡፡ በርካታ የሆሊውድ ተዋንያንና አለማቀፍ አርቲስቶች የሃዘን መግለጫቸውን እየሰጡለትና ድንቅ የትወና ችሎታውን በተለያዩ የዓለማችን ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን እየመሰከሩ የሚገኙለት ሮቢን ዊሊያምስ፣ ከቀድሞ ትዳሩ ያፈራቸው የሶስት ልጆች አባት መሆኑን ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 3683 times