Saturday, 23 August 2014 10:50

“...ሴቶች ሽንት የመቋጠር ችግር አራት ጊዜ እጥፍ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(12 votes)

                         በተለያዩ ጊዜያት ስለሽንት መቋጠር አለመቻልና የሴቶች የስነተዋልዶ አካላት ጤንነት ግንኙነት አላቸው? ወይንስ የላቸውም? የሚሉ ጥያቄዎች ደርሰውናል፡፡ በዚህ ርእስ ዙሪያ ከደረሱን ጥያቄዎች መካከል ሁለቱን ታነቡዋቸው ዘንድ መርጠናቸዋል፡፡ ሽንቴ አሁንም አሁንም ስለሚመጣብኝ መጸዳጃ ቤት ከሌለበት አካባቢ ጉዳይ ገጥሞኝ ስሔድ እጅግ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ብዙውን ጊዜም ባገኘሁበት ቦታ ዘወር ብዬ ከመንገድ ላይ ስለምሸና አለባበሴ ሁሉ እንደልቤ ቁጭ ብድግ ለማለት እንደሚመች ሆኖአል፡፡ ወደሐኪም ቤት ሄጄም ስለጤንነቴ እንዳላማክር ከዚህ ውጭ ሌላ የጤና ችግር አልገጠመኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር ከምን የሚመጣ ነው? ስሜን አትግለጹ አንድ ቀን በስራ አጋጣሚ ሽንቴን ከሙሉ ቀን በላይ ሳልሸና ውዬአለሁ፡፡ ከዚያም ወደ አስር ሰአት ገደማ ሲሆን ሽንቴ መጣ፡፡ ለመሽናት ስሞክር ግን ትንሽ ሽንት ብቻ ሸናሁ፡፡ ነገር ግን ሕመም ተሰማኝ፡፡

አሁንም ትንሸ ቆይቶ ሽንቴ መጣሁ ሲል ወደመታጠቢያ ቤት ሔድኩ፡፡ ነገር ግን ከሕመም እና ከማማጥ በስተቀር ሽንት የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ምልልሱ ፈጠን እያለ ሕመሙም እየበዛ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ቆየሁ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ትንሸ ሽንትና ደም ቅልቅል እየሆነ ህመሙ ተባባሰ፡፡ ወደ ሆስፒታል ስሄድ በየመንገዱ መቆም ነበረብኝ፡፡ ሆስፒታልም ሐኪምጋ እስክቀርብ ድረስ በዚሁ ሁኔታ ሕመሙ ቀጥሎ በጣም አደከመኝ። ሆኖም ግን ታክሜው ድኛለሁ፡፡ የእኔ ጥያቄ... ለመሆኑ ሽንትን በወቅቱ አለመሽናት ለእንደዚህ ያለ ሕመም ይጋብዛልን? ሀና ተፈሪ - ከሳሪስ ከሽንት መቋጠር አለመቻል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ሌሎች ተሳታፊዎችም አድርሰውናል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ...ከሴቶች የስነተዋልዶ አካላት ጋር ተያያዥነት አላቸውን? የሚል እና ሽንትን ቋጥሮ መያዝ ለሕመም ይዳርጋልን? የሚል በመሆኑ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል በማምራት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የሆስፒታሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ኃላፊን ዶ/ር ብርሀኑ ከበደን ማብራሪያ እንዲሰጡን ለዚህ አምድ ጋብዘናቸዋል፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ እንደገለጹት ሽንትን መቋጠር አለመቻል ሲባል ተገቢ እና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ መሽናት ሲቻል ነገር ግን ከዚያ ውጪ በማይቆጣጠሩት መንገድ ሽንት ከማምለጥ ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡

ጥ/ ሽንትን በተገቢው መንገድ የመያዝ ስርአቱ ምን ይመስላል? መ/ ሽንትን ለተገቢው ጊዜ ተቆጣጥሮ ይዞ አግባብነት ባለው እና ተቀባይነት ባለው መንገድ፣ በፈለጉት ጊዜ ማስወገድ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ስርአት የሚመራ ነው፡፡ ለምሳሌም ሽንት በተገቢው መንገድ የሚወገደው የታችኛው የሽንት ማለፊያ ቱቦ፣ የሽንት ቱቦውንና ሌሎችንም የመራቢያ አካላት ደግፎ የሚይዙ አካሎች እና በተወሳሰበው የነርቭ ስርአት ጥምረት በሚወሰነው መንገድ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እክል በሚገጥመው ጊዜ የችግሩ ምልክቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ጥ/ ሴቶች ከስነተዋልዶ አካላት ጋር በተያያዘ የሽንት መቋጠር ችግር ሊደርስባቸው ይችላልን? መ/ ሽንት የመቋጠር ችግር ከሁለት እስከ አራት እጥፍ በሚሆን መልኩ በሴቶች ላይ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። ይህም እንግዲህ የሴቶች የሽንት መሽኛ የውጭው አካል አጭር ከመሆኑ የተነሳና እንዲሁም በወሊድና በእርግዝና ጊዜ በስነተዋልዶ አካላት ላይ በሚደርስ ጫና ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሽንት መቋጠር ችግር ምክንያት ይሆናሉ ከሚባሉት ውስጥ እንደ ከፍተኛ ውፍረት፣ እርግዝና፣ ብዙ ልጅ መውለድ፣ ለረጅም ጊዜ ምጥ ማማጥ (ፌስቱላ) በመሳሰሉት ምክንያት በመራቢያ አካላት ላይ በሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች የተነሳ የችግሩ ተጋላጭነት ይጨምረዋል፡፡ ጥ/ እርግዝና ለችግሩ በምክንያትነት የሚጠቀሰው እንዴት ነው? መ/ በእርግዝና ጊዜ ከሚከሰቱት ፊዚዮሎጂካላዊ ለውጦች መካከል በሆድ አካባቢ የሚፈጠረውን ግፊት ይጨምረዋል፡፡ ይህም በታችኛው የፊኛ አካላት ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድር በቀጥተኛ መንገድ ሽንትን የመቆጣጠር ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡

በሁለተኛም ደረጃ ከመውለድ ስርአቱ ጋር በተያያዘ በተለይም ብዙ የወለዱ ሴቶች በምጥና በተለያየ አጋጣሚ ሰውነታቸው ሊጎዳ ስለሚል ችግሩን ይጨምረዋል። ጥ/ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት እብጠት ከሽንት ጋር የሚያያዝበት መንገድ አለ? መ/ በእርግዝና ጊዜ የሚታየው እብጠት 80% ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ይኄውም በእርግዝናው ጊዜ የሚከሰቱት ፊዚዮሎጂካላዊ ለውጦች የሚያመጡት ሲሆን ከደም ግፊት እና ከሌሎች ችግሮች ጋር ካልተያያዘ በስተቀር ብዙ ጊዜ እንደችግር አይታይም፡፡ አንዳንዴ ግን ከኩላሊት እና ከሌሎች የውስጥ አካላት ችግሮች ጋር ሲገናኝ እና እብጠቱ ከእግር አልፎ ወደእጅ እንዲሁም በፊት ላይ የሚታይ ከሆነ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በእርግዝና ጊዜ የሚታየው የሰውነት እብጠት ሽንትን ከመቋጠር ወይንም ካለመቆጣጠር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ጥ/ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳቢያ የሚደርሰው የጤንነት ችግር ምን ይመስላል? መ/ የታችኛው የሽንት ቧንቡዋ እና ሌሎች የመራቢያ አካላትን በማርገብ እንዲሁም ደግሞ የረጅም ጊዜ ምጥ በሚኖርበት ጊዜ በዚያ አካባቢ ያሉ አካላት የደም ዝውውር በማጣታቸው የተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ ቀዳዳ መፍጠር፣ በእድሜ ምክንያት የወር አበባ መቆም ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የኢስትሮጂን የተባለው ንጥረ ነገር እጥረት የተነሳ መሳሳቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በስነተዋልዶ አካላት አካባቢ የሚደረጉ ኦፕራሲዮኖች፣ የጨረር ሕክምናዎች ለሽንት መቋጠር ችግር ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ጥ/ ሽንትን የመቆጣጠር ችግር ምን ያህል አስከፊ ነው? መ/ ችግሮቹ ሲከሰቱ የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ እንደየሀገሮቹ የእድገት ደረጃ እና የአኑዋኑዋር ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም ከህክምናው ወይንም እንደበሽታ ከመታየቱ ውጪ በሰዎች የአኑዋኑዋር ዘይቤ ላይ ያለው አስተዋጽኦ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሰዎች በደረሰባቸው ችግር ይጨነቃሉ፣ ያፍራሉ፣ ድብርት ይገጥማቸዋል፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ስለዚህም ችግሩ ከገጠማቸው ሰዎች መካከል ወደሕክምና የሚመጡት ከግማሽ በታች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ የዚህም ምክንያት ችግሩን ለሰው ለማማከር ከማፈር ወይንም ደግሞ የህክምና እርዳታ አለው ብለው አለማሰባቸው ሊሆን ይችላል። ብዙዎች በቤታቸው ችግራቸውን አፍነው በመያዝ ቶሎ ቶሎ ሽንት ቤት በመሄድ ወይንም ከስራ በመቅረት እራሳቸውን ለማስታመም ስለሚሞክሩ ይህም በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ እንዲሁም በአገር ላይ ችግር ማስከተሉ ስለማይቀር ኪሳራ ያመጣል፡፡ ስለዚህም በአግባቡ የህክምና እርዳታ ሊያገኝ የሚገባው የጤና ችግር ነው፡፡ ጥ/ ሕክምናው ምን አይነት ነው? መ/ ከታመሙት መካከል ከግማሽ በታች የሆኑት ወደሕክምና ይመጣሉ ቢባልም የመጡትን በአግባቡ በህክምናው የመርዳት አሰራር አለ፡፡ የሽንት መቆጣጠር ችግር ሊከሰትባቸው የሚችሉ ምክንያቶችና በአካል ላይ የሚታየው ሕመም ከላይ ተገልጾአል፡፡ ስለሆነም የአካል መላላት ወይንም መርገብ የመሳሰሉት ችግሮች ሲከሰቱ በሳል ወይንም በሳቅ ጊዜ ሽንት ሊያመልጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም የሽንት አወራረድ ስርአቱን በማየት ሽንት ማምለጡ አልፎ አልፎ ነው ወይንስ በተከታታይ ነው የሚለውን ተገቢውን ጥያቄዎች በመጠየቅ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ እንዲሁም በተሸሻሉና ችግሩን ሊለዩ በሚችሉ የምርመራ መሳሪያዎች በመታገዝ እንደአስፈላጊነቱ አስፈላጊው ሕክምና ይሰጣል፡፡

ጥ/ የሽንት የመቆጣጠር ችግር የደረሰባቸው ሴቶች እራሳቸውን ሊረዱ የሚችሉበት እድል ይኖራል? መ/ የደረሰው የጤና ችግር ቀለል ያለ ከሆነ ለምሳሌም የታችኛው ሽንት መውረጃ አካላት አካባቢ ያለ የሰውነት ክፍል መርገብ የደረሰበት መሆኑ በሕክምና ሲረጋገጥ ከሕክምና ባለሙያው በሚሰጠው ምክር መሰረት የጡንቻ አካሎችን ለማጠንከር የሚሰሩ የሰውነት ማጠንከሪያዎች አሉ፡፡ ሰውነትን ጭምቅ አድርጎ እየያዙ በመልቀቅ ጊዜ ሰጥቶ በቀን ውስጥ ሶስት አራት በመስራት ሴቶቹ መጠነኛ የሆነ እርዳታን ለእራሳቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሆርሞን እጥረት ጋር የተያያዘ ከሆነ ኢስትሮጂን የተባለውን ሆርሞን በመቀባት ወይንም በኪኒን መልክ በመውሰድ ሰውነት ያጣውን ንጥረ ነገር በመተካት ችግሩን ማቃለል ይቻላል፡፡ ጥ/ ሽንትን ሳይሸኑ ቋጥሮ በመያዝ ምክንያት ሕመሙ ሊከሰት ይችላልን? መ/ ሽንት በሚቋጠርበት ጊዜ የሚደርሰው የፊኛ መወጠር በሁዋላ ላይ ለሚከሰተው ሽንትን በተገቢው መንገድ የማስወገድ ችግር እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ሽንትን ሳይሸኑ ለረጅም ጊዜ መያዝ ሽንት እንዲረጋ ስለሚያደርግ እና የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን ስለሚያስከትል በጊዜያዊ መልክም ቢሆን ለሽንት መቋጠር ችግር መንስኤ ይሆናል ሊባል ይችላል፡፡

Read 19551 times