Saturday, 23 August 2014 11:04

መምህራንን መሸለም ልባምነት ነው

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(6 votes)

            መርካቶ የሚገኘው አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ በሥነ ግጥም የሚሳተፉበት ውድድር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ግጥም እንዲጽፉበት የተሰጣቸው ርዕስ “መምህር” የሚል ነበር። አሸናፊዎቹ በተሸለሙበት መድረክ 20 ያህል ተማሪዎች ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ የዳኞችን ብቻ ሳይሆን የታዳሚዎችንም ቀልብ ስቦ በአንደኛነት የተሸለመው ተማሪ ግጥም፤ የአስተማሪን ታላቅ ሰውነት የገለፀው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማነፃፀር ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተንቀሳቀሰባቸው 33 ዓመታት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን፣ ቅንነትን፣ በጎነትን፣ ትህትናን፣ መልካምነትን … አስተምሮ ያለፈ ታላቅ ሰው ቢሆንም በዓለም ታላላቅ የሹመት ስሞች በአንዱም አልተጠራም የሚል መልእክት አንፀባርቋል ግጥሙ፡፡ ክርስቶስ በዘመኑ ብዙዎችን ከደዌያቸው ቢፈውስም ሐኪም አልተባለም፡፡ በባህር ላይ ብዙ ተአምራትን ቢፈፅምም ካፒቴን ተብሎ አልተሰየመም፡፡

ለብዙ ውስብስብና ፈታኝ ጥያቄዎች አጥጋቢና አስገራሚ ምላሾችን ቢሰጥም ፈላስፋ የሚል ማዕረግ አላገኘም፡፡ በኃይልና በጉልበት የመጡበትን ሰዎች በብልሐት ድል ቢነሳም ጄነራል የሚል ማዕረግ አላገኘም፡፡ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ ቢለውጥም የሳይንቲስትነት ክብር አልጠየቀም፡፡ የአገር መሪነት አላጓጓውም፡፡ ንጉስነት አልናፈቀውም… በግጥሙ እንዲህ ዓይነት ሃሳቦች ያካተተው ተሸላሚው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በተከታዮቹና ደቀ መዛሙርቱ ዘንድ ይጠራ የነበረው “መምህር” በሚለው ቃል እንደነበር አመልክቶ የአስተማሪነት ሙያ፤ ለሰው ክብርና ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች የሚሰማሩበት፤ ሰውን እንደ ብረት ቀጥቅጠው፣ እንደ እንጨት ልገው፣ እንደ ድንጋይ ጠርበው .. የሚቀርፁና ይህንንም ክቡር ተግባር ለመፈፀም ወደውና ፈቅደው የሚገቡ ልዩ ሰዎች እንደሆኑ በግጥሙ ጠቁሟል፡፡ እንዲህ ዓይነት የግጥም ውድድሮች የመምህርነት ሙያን ለማክበርና ዕውቅና ለመስጠት የሚዘጋጁ ነበሩ፡፡ ጅምሩ አልቀጠለም እንጂ፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ለመምህራንና ሙያቸው ትኩረት መስጠት የተጀመረ ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ 284 ተማሪዎቹን በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት አስተማሪና የማስተማር ሙያ ልዩ ክብር እንዲሰጠው ያለመ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት በአገራችን የትምህርትን ተደራሽነት ለማስፋት ብዙ ሥራ ቢሰራም ጥራቱን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች እነደሚነሱ ይታወቃል። በመምህርነት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡትን መሸለም የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል በሚል ዓላማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ መምህራንን እያወዳደረ መሸለም ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የትምህርት ጥራት ውድቀትን በተመለከተ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንን፣ እነሱ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንን፣ እነዚህም ወደ ታች እያዩ በመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ያለውን አሰራር እንደሚከስሱ በተጠቆመበት ያለፈው ሳምንት የሽልማት ፕሮግራም፤ መካሰስና መወነጃጀል ለችግሩ መፍትሔ እንደማይሆን፣ ለመማር ማስተማሩ ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረውና ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅም በራሱ ተቋማት ያሉ መምህራንን ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ዘጠኝ ክልሎች ተመርጠው የመጡለትን መሸለም የጀመረው ለለውጡ የድርሻውን ለመወጣት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የአስተማሪነት ሙያ ታላቅ መሆኑን ለማሳየት፣ መምህራንን ለማመስገንና ለመምህራን ውለታ ዕውቅና ለመስጠት በዚሁ ዓመት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያከናወነው አንድ ተግባር አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ባከበረበት ባለፈው ሰኔ ወር “የስልሳ ገጾች ወግ” በሚል ርዕስ ታትሞ የተሰራጨው መጽሐፍ፤ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ያስተዋውቃል፡፡ በጋዜጠኛ አብርሃም ዘሪሁን የተዘጋጀው 338 ገፆች ያሉት ዳጎስ ያለ መፅሃፍ፤ የመጀመሪያ ክፍል ከጎንደር ከተማ ታሪክ ባሻገር፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከየት ተነስቶ ለዛሬ እንደደረሰ፤ በዩኒቨርሲቲ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ምን እንደሚመስል፤ የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች እንቅስቃሴ፤ ስለ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ስራዎችና ለህብረተሰቡ ስለሚሰጠው አገልግሎቶች በስፋት ይገልፃል፡፡ “መውለድና መኖር” በሚል ንዑስ ርዕስ የቀረበው የመፅሐፉን ግማሽ የያዘው ሁለተኛ ክፍል ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩና በማስተማር ላይ የሚገኙ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው አስር መምህራንን ታሪክ ያስነብባል፡፡

የመጽሐፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብርሃም ዘሪሁን፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ማስተዋወቅ ከመጀመሩ በፊት ስለመምህራንና ሙያው ታላቅነት እንዲህ ይላል፡- “መውለድ በራሱ የህይወት ግብ አይደለም። መውለድ ከሚባለው ተፈጥሯዊ ምስጢር በኋላ ብዙ እውነታዎች አሉ፡፡ መውለድ በራሱ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ገፀ በረከት አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የሰው ልጆች ውልደት ከማንምና ከምንም በላይ ራሱን የቻለ ትርጉም አለው፡፡ ያለ ምክንያትና ትርጉም የተፈጠረ ማንም የለም፡፡ በተለይ የሰው ልጅ የሚወለደው (የሚፈጠረው) በምክንያትና በትርጉም ነው፡፡ እርግጥ ነው የሁላችንንም ውልደት ምክንያት አንድ አይነት አድርጎ መመልከቱ ሚዛናዊ አይሆንም፡፡ የጋራ የሆኑ የውልደታችን ትርጉሞች ግን የትየለሌ ናቸው፡፡ “እኔ ላወራችሁ የምሻው ግን ተወልደው በመኖራቸው … ኖረውም ትርጉም ያለው ነገር በመስራታቸው፤ ትርጉሙም ከራሳቸው አልፎ ለአብዛኛው ህብረተሰብ ስላንፀባረቀው እንቁዎች ነው፡፡ እነዚህ እንቁዎች ከራስ በላይ ለሆነ ትርጉም መፈጠራቸውን፤ ሲያስቡት በሚቀለው፣ ሲሞክሩት ግን በሚከብደው ዓለም ላይ በተግባር አሳይተዋል፡፡ “በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስልሳ (60) ዓመት ጉዞ ውስጥ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ሃውልት ላቆም ተነስቻለሁ፡፡ ይህንን ሃውልት ለማቆም ሳስብ ግን ታሪካቸውን የማወራላቸው እንቁዎች ሁሉም በህይወት እያሉ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በእርግጥም በህይወት ያሉ እንቁዎቻችንን የማድነቅ ባህላችንን ማሳደጉ ሳይጠቅመን አይቀርም” በማለት ባለታሪኮቹን ያስተዋውቃል፡፡

የትምህርት፣ የሥራና የቤተሰብ ታሪካቸው የቀረበው አሥሩ ፕሮፌሰሮች፡- የቆዬ አበበ፣ ያሬድ ወንድምኩን፣ ተፈራ አቡላ፣ ይግዛው ከበደ፣ መልኬ እድሪስ፣ ሞገስ ጥሩነህ፣ መንገሻ፣ አድማሱ፣ ጌጡ ደጉ፣ አፈወርቅ ካሱ፣ ራምስ ዋሚ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ራምስ ህንዳዊ ናቸው፡፡ አስተማሪነትና የማስተማር ሙያን የሚያወድሱ ንግግሮች፣ ግጥሞች፣ የአድናቂ ምስክርነቶች … በተለያዩ ጊዜያት ቀርበዋል፡፡ ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ተቋማት ሙያውንና ባለሙያውን ለማክበር የጀመሩት ጥረት የሚደነቅ ነው። ተጠናክሮም ሊቀጥል እንደሚገባው ይታመናል። መምህራን ትውልዱን የሚያንፁ የሀገር መሰረት መሆናቸውን ተገንዝቦ መሸለምና ዕውቅና መስጠት ልባምነት ነው፡፡

Read 5165 times