Saturday, 23 August 2014 11:15

ለ“ማር” ማምረቻ የዋለው ባዕድ ነገር ምንነት እየተጣራ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ዋንኞቹ የወንጀል ፈጻሚዎች እስከአሁን አልተያዙም
ህገወጡ “ማር” በመርካቶና በድፍን አዲስ አበባ ሲከፋፈል ነበር
ስኳርን ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ ከሆኑ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀልና በማቅለጥ ማር አስመስለው እያመረቱ ለገበያ ሲያቀርቡ እጅ ከፍንጅ የተያዙት ተጠርጣሪዎች፣ እያንዳንዳቸው በአንድ ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት የሰጠው ትእዛዝ በይግባኝ ተሻረ፡፡ የወንጀሉን ዋና ፈፃሚዎች ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑን  አስታውቋል፡፡
የፌደራል ንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ዐቃቤ ህግ፤ በእነ እንየው አንተነህ መዝገብ በ10 ሰዎች ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ እንደሚያመለክተው፤ ተከሳሾቹ ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛና ጎጂ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን ከስኳር ጋር በመቀላቀልና በማቅለጥ ማር አስመስለው እያመረቱ በመርካቶና በድፍን አዲስ አበባ ሲያከፋፍሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ በክሱ ላይ እንደተገለጸው፤ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ነሐሴ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 9፡30 ላይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 3 በተለምዶ ግራር አካባቢ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተከሳሾቹ ለጊዜው ምንነቱ ያልተረጋገጠ ባዕድ ነገር ከስኳር ጋር በመቀላቀል እያቀለጡ ማር አስመስለው ሲያመርቱ እጅ ከፍንጅ ይዟቸዋል፡፡ በሁለት ሚኒባሶች ላይ የተጫነ 40 ኩንታል ስኳር በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን አሁን ክስ የተመሰረተባቸው 10 ተጠርጣሪዎች በሶስት ትላልቅ ጐላ ላይ ስኳር እያቀለጡ ነው ፖሊስ የደረሰባቸው፡፡
ሶስቱ የወንጀሉ ዋና ፈፃሚዎች እስከአሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ይህንኑ ማር መሰል ነገር የሚያመርቱባቸው ቤቶች በዚሁ በአዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎች እነዳሏቸው የጠቆመው ዐቃቤ ህግ፤ ለማር ማምረት ስራው ከምስራቅ ጎጃም የተለያዩ ወረዳዎች ግለሰቦቹን በመመልመል አምጥተው እንደሚሰሩ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ማር መሰሉን ምርት ለማምረት የሚጠቀሙበትን ባዕድ ነገር ምንነት ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የገለፀው ዐቃቤ ህግ፤ ወንጀሉ ከሰው ጤናና ደህንነት አንጻር እጅግ አስከፊ ነው ብሏል፡፡
የፌደራል ንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ዐቃቤ ህግ፤ ሶስቱን ዋንኛ የወንጀል ፈጻሚዎች ለመያዝና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አቤቱታ ጋር ተያይዞ የቀረበውና በአንደኛ ዋንኛ ወንጀል ፈፃሚነት በፖሊስ በሚፈለገው አታላይ አስራት ስም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በአቃቂ ክ/ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ፅ/ቤት ማህተም ነሐሴ 6 ቀን 2006 ዓ.ም የወጣው የንግድ ፍቃድ እንደሚያመለክተው፤ ግለሰቡ በማኑፋክቸሪንግ የንግድ ሥራ ዘርፍ፣ በማርና የማር ውጤቶችን መፈብረክ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ይገልፃል፡፡ የንግድ ፈቃዱ የወጣበት ቀን ፖሊስ  ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለበት ቀን እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት በቁጥጥር ሥር የዋሉት 10 ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በአንድ ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የሰጠው ውሳኔ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጐ፣ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ዋንኛ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ለመያዝ የሚደረገው ክትትል ቀጥሏል፡፡


Read 2345 times