Saturday, 23 August 2014 11:47

የጉዲፈቻ አጀማመር አጭር ታሪክ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ጉዲፈቻ የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ ሲሆን ፍቺውም ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ገዛ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው፡፡
ጉዲፈቻ ለሚለው ቃል የእንግሊዝኛ አቻው “adoption” ሲሆን አመጣጡም ‘ad-optare’ ከሚል የላቲን ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም “መምረጥ” የሚል ነው፡፡ ይህም ጉዲፈቻ በጉዲፈቻ አድራጊው ምርጫ ብቻ የሚከናወን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊው በነጻ ፈቃዱ ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ለማሳደግና ለመጠበቅ እንዲሁም ለእድገቱ አስፈላጊ የሆኑትን ማናቸውም እንክብካቤዎች ለማድረግ ወስኖ የሚወስደው እርምጃ ሲሆን ይሄም ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊውን ቤተሰብ ስም፣ ንብረትና ህይወት እንዲካፈል የሚያደርግ መብት ያጐናጽፈዋል፡፡ ከአብራኩ ክፋይ የተገኘው ልጅ ያለው ማንኛውም መብት ይኖረዋል፡፡
በአጠቃላይ ጉዲፈቻ አንድ ሰው ቀደም ሲል የነበረውን ቤተሰባዊ የደም ትስስር በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ቤተሰባዊ ትስስር የሚተካ ወይም የሚለውጥ ማህበራዊ ተቋም ነው ሊባል ይችላል፡፡
ጉዲፈቻ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ማህበረሰቦች ዘንድ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲከናወን የቆየ ሥርዓት ነው፡፡ ለዚህም በአይሁድና በክርስትና ሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሰው የነቢዩ ሙሴ ጉዲፈቻ እንደ አብነት ሊነሳ ይችላል፡፡ በህንድ፣ በግብፅና በሮማውያን ዘንድ የዘር ግንዳቸው መቀጠል ባልቻለበት ሁኔታ የቤተሰብ ስም እንዲቀጥል ጉዲፈቻን እንደመሳሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በእስልምና ህግ የሚተዳደሩ አገሮች የሚጠቀሙበት “የጉዲፈቻ” ሥርዓት ከዚህ በመጠኑ ለየት ይላል፡፡ ካፍላህ በመባል የሚታወቀው ይሄ የጉዲፈቻ ሥርዓት ከኢንዶኔዥያና ቱኒዚያ በስተቀር በእስልምና ሃይማኖት ተከታይ አገራት በሙሉ  በስፋት ይተገበራል፡፡ ካፍላህ የተፈጥሮ ወላጆቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ሊያሳድጓቸው ላልቻሉ ልጆች የተፈጠረ አማራጭ የእንክብካቤ መንገድ ሲሆን በህጉ መሰረት ካፍላህ አድራጊዎች ልጆቹን ለዘለቄታው ወስደው እንደራሳቸው ልጆች የማሳደግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሆኖም ልጆቹ ማንነታቸውን ይዘው ማደግ አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን የካፍላህ አድራጊዎችን የቤተሰብ ስም እንዲጠቀሙ የማይፈቀድ ሲሆን ንብረት የመውረስ መብትም የላቸውም፡፡
በጥንቱ ዘመን ጉዲፈቻ የልጆችን ሳይሆን የጉዲፈቻ አድራጊዎችን ጥቅም መሰረት በማድረግ ነበር የሚከናወነው፡፡ ጉዲፈቻ የዘር ሀረግን በቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ በወንድ ጉዲፈቻ ተደራጊ ልጅ አማካይነት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እንዲሁም በገበሬዎች አካባቢ ተጨማሪ አጋዥ ሐይል ለማግኘት ጭምር ሲተገበር ቆይቷል፡፡ የጉዲፈቻ ተደራጊዎች የእድሜ ክልልም በአብዛኛው ከ10 ዓመት በላይ ነበር፡፡
በአብዛኛው የዓለም ክፍል ሲተገበር የቆየው የጉዲፈቻ ሥርዓት በመካከለኛው ዘመን ላይ በተለይ በአውሮፓ አገራት ወደ መጥፋት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ከክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የቤተሰብ ተቋም የደም ትስስር መለያ ባህሪ ስለተሰጠው ነው፡፡
ጉዲፈቻ ዳግም እንደ ሥርዓት ያንሰራራው በፈረንሳይ ቡርዥዋ አብዮት ማግስት በነገሰው ነፃ አስተሳሰብና ዘመናዊ ፍልስፍና ተፅዕኖ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1804 በወጣው የፈረንሳይ ፍትሀብሔር ህግ ላይ ጉዲፈቻ በተወሰኑ ሁኔታዎች እንዲደረግ ተፈቅዶ ነበር፡፡
ይህን የፈረንሳይ ተሞክሮ ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ጉዲፈቻ በአውሮፓ አገራት እንደ አዲስ የህግ ማዕቀፍ እውቅና አግኝቷል፡፡ በእንግሊዝ ጉዲፈቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊ ማዕቀፍ ያገኘው እ.ኤ.አ በ1926 “Children Act of 1926” (የ1926 የህፃናት ድንጋጌ) በሚል ሕግ ሲሆን በአሜሪካ በማሳቹስቴት ግዛት ደግሞ “The Massachusetts Adoption of Children Act” (የማሳቹሴትስ የህፃናት ጉዲፈቻ ድንጋጌ) በሚል በወጣው የጉዲፈቻ ህግ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ በወቅቱ ህግ ጉዲፈቻ ተደራጊው ከሁለቱም ቤተሰቡ ማለትም ከቀድሞ ቤተሰቡና ከጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ዝምድናውን ይዞ የሚቆይ ሲሆን ከሁለቱም የመውረስ መብት ነበረው፡፡ እነዚህ በአሜሪካና በእንግሊዝ የወጡት የጉዲፈቻ ድንጋጌዎች የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ የጉዲፈቻ ህጎች ተብለው ይታወቃሉ፡፡
የአሜሪካው የማሳቹሴትስ የጉዲፈቻ ድንጋጌ፣ ለቀጣዩ የጉዲፈቻ ህግ መበልጸግ የማእዘን ድንጋይ የጣለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ህጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉዲፈቻ ውል በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ የደነገገ ሲሆን ፍ/ቤቱም ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ለጉዲፈቻው ፈቃድ መስጠታቸውንና ውሳኔው የልጁን ደህንነት የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ ፍ/ቤቱ ጉዲፈቻ  አድራጊዎቹ ለህፃኑ ተስማሚ መሆናቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ እንዳለበትም ህጉ ያስቀምጣል፡፡
በሃያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ከአዳዲስ የጉዲፈቻ ህጐች መውጣት ጋር ተያይዞ የጉዲፈቻ አላማና ግብ ከጉዲፈቻ አድራጊው ጥቅሞች ተላቅቆ የህፃናትን ደህንነትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እየሆነ መጣ፡፡ ጉዲፈቻ መንግስታት የተጣሉ፣ ቤተሰብ የሌላቸው/የማይንከባከባቸው ወይም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆችን የሚንከባከቡበትና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁበት ተቋም ለመሆንም በቃ። ይሄን ተከትሎም የጉዲፈቻ ተቋም የሚያስከትለው ህጋዊ ውጤትም ተቀይሯል፡፡ በፊት ጉዲፈቻ ተደራጊው ከቀድሞ ቤተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ የማያቋርጥ ሲሆን ይህም ከፊል ጉዲፈቻ /weak or simple adoption/ በመባል ይታወቃል፡፡ አሁን በተሻሻለው የጉዲፈቻ ህጋዊ ሥርዓት ግን ጉዲፈቻ ተደራጊው ከቀድሞ ቤተሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ያቋርጣል፡፡ ይህም ሙሉ ጉዲፈቻ / ‘strong’ or ‘full’ adoption/ በሚል የሚታወቅ ሲሆን የህፃናትን ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በአውሮፓና በአሜሪካ የጉዲፈቻ መርህ “የህፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ ነው” የሚለው አስተሳሰብ እየጠነከረ የመጣው ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በርካታ ልጆች ያለቤተሰብና አሳዳጊ በመቅረታቸውና ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ልጆች በመበራከታቸው ነበር፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊዎች በአብዛኛው ባለትዳር ጥንዶች ቢሆኑም በርካታ ያላገቡ (ወንደላጤ ወይም ሴተላጤ) ግለሰቦችም ልጆችን በጉዲፈቻ ወስደው ያሳድጋሉ፡፡
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የጉዲፈቻ ልጅ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ብዙዎች የአብራካቸውን ክፋይ ማግኘት ባለመቻላቸው (የማይወልዱ በመሆናቸው) የጉዲፈቻ ልጅ ሲያሳድጉ፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ አባል ቤተሰባቸው ውስጥ ለመጨመር ሲሉ የጉዲፈቻ ልጅ ይወስዳሉ፡፡ አሳዳጊ ለሌለው ልጅ መኖሪያ ቤት ለመስጠትና ቤተሰብ እንዲኖረው ለማድረግም የጉዲፈቻ ልጅ የሚወስዱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
ህፃናቱም በተለያዩ ምክንያቶች በጉዲፈቻ የሚያሳድጓቸው ቤተሰቦች የሚፈልጉበት ሁኔታ አለ። አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን በሞት በማጣታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ወላጆች ቢኖሩም በህመም ወይም በሌላ የግል ችግር ማሳደግ አቅቷቸው በጉዲፈቻ የሚሰጡበት ሁኔታም አለ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተፈጥሯዊ ወላጆቻቸው ጥለዋቸው በጉዲፈቻ የሚሳድጋቸው ቤተሰብ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡
ፍላጐት ሳይኖራቸው የወለዱ ወላጆችን ማንነትን የሚያጋልጥ አለመሆኑ እንዲሁም የልጆችን ደህንነት የሚያስጠብቅ መሆኑ በህፃናት ሥነልቦናና ዕድገት ላይ በተደረጉ ጥናቶች መደገፉ ለጉዲፈቻ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ምክንያት ሆኗል፡፡
በአሜሪካ “የጉዲፈቻና አስተማማኝ ቤተሰቦች ድንጋጌ” (Adoption and Safe Families Act 1997) መውጣት ጋር ተያይዞ የህፃናትን ጥቅም ይበልጥ ሊያስጠብቅ የሚችለው ዘላቂ የሆነ አያያዝ ነው የሚለው ይበልጥ እየታመነበት መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል ልጆችን በተቻለ መጠን “ከቤተሰብ ጋር መቀላቀል” የሚለው መርህ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የቆየ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ልጆች ለረዥም ጊዜ በማሳደጊያ (ፎስተር ኬር) ውስጥ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር - አሳዳጊ ቤተሰብ እስኪመጣ፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ ልጆችን ከቤተሰብ ለመቀላቀል የሚደረገው ሙከራ በአብዛኛው እንደማይሳካ ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ልጆችን ከቤተሰብ ጋር መቀላቀል የሚለው መፍትሄ ቅድምያ የሚሰጠው ቢሆንም ህፃናት በማሳደጊያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየታቸው በደህንነታቸው ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ጥናቶች ይጠቆማሉ፡፡
የአሜሪካ የጉዲፈቻ ህግ ይሄን ለማስታረቅ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ልጁ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ከቤተሰቡ ጋር መቀላቀል ካልቻለ የወላጅነት መብት እንዲቋረጥ በቤተሰብ ላይ ክስ ተመስርቶ፣ ልጁ በጉዲፈቻ ሊመደብ እንደሚችል ህጉ ይደነግጋል፡፡ አሁን በአሜሪካ ተመራጩ የህፃናት እንክብካቤ መንገድ ጉዲፈቻ ሲሆን ለልጆች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ አማራጭ የእንክብካቤ መንገድ መሆኑ ይበልጥ እየታመነበት መጥቷል፡፡    
በኢትዮጵያ ጉዲፈቻ በትክክል መቼ እንደተጀመረ የሚጠቁም ጥናት ባይገኝም ከ1800 ክፍለ ዘመን መጀመርያ አንስቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በባህላዊ መንገድ ይካሄድ እንደነበር ይገመታል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዘንድ ይተገበር እንደነበርም ይነገራል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የህግ ማዕቀፍ የተበጀለት በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሄር ህግ ሲሆን በዚህ ህግ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ፣ በፍትሐብሄር ህግ ውስጥ ያለውን የቤተሰብ ህግ ክፍል ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ጋር አጣጥሞ ማሻሻል አስፈልጓል፡፡ በዚህም መሰረት የተሻሻለ የቤተሰብ ህግ በአዋጅ ቁ፣ 213/92 ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ፀንቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡   
ምንጭ - የጉዲፈቻ አሠራር በኢትዮጵያ
በወ/ሮ ረሂላ አባስ

Read 6009 times