Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 31 December 2011 10:30

“አራዳ” ፓርቲና መንግስት እንፈልጋለን!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ፖለቲካዊ ወጌን በ “ፈገግታ” ለመጀመር በማሰብ ወደ ቁም ነገር ከማለፋችን በፊት ሁለት ቀልዶችን ጣል ላድርግላችሁ፡፡

ኩባ ውስጥ ነው አሉ፡፡ አገሪቷን ለግማሽ ክ/ዘመን (50 ዓመት ገደማ) አንቀጥቀጠው ከገዙ በኋላ ሥልጣናቸውን ለወንድማቸው ያወረሱት አምባገነኑ የቀድሞ የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ላይ ያነጣጠረ ፊልም ይሰራና ለህዝብ ይቀርባል - በየሲኒማ ቤቱ፡፡ ካስትሮ ህዝቡ ፊልሙን ሲመለከት ስላለው  ስሜት ማወቅ ፈለጉና ማንም ሳያውቃቸው (በድብቅ ማለት ነው) ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው ሲኒማ ቤት ገቡ - ፊልሙን ለማየት ሳይሆን ከህዝቡ የሚሰጠውን አድናቆት ተመልክተው ለመደመም፡፡

(ሌላ ፊልም ለማየት ልትሉት ትችላላችሁ!) እናም ኋላ ወንበር ጥጋቸውን ይዘው ተቀመጡ - ለብቻቸው፡፡ ወዲያው መብራት ጠፋና ፊልሙ ተጀመረ፡፡ ካስትሮ ብቅ አሉ - ስክሪኑ ላይ፡፡ ተመልካች ጭብጨባውን አቀለጠው፡፡ የተነሱም አልጠፉም፡፡ ካስትሮ በዚህ ተደንቀው ሳያበቁ አንድ የማያውቁት እጅ ትከሻቸው ላይ አረፈ፡፡ ካስትሮ ደንገጥ ብለው ዞር አሉ - በጨለማው ውስጥ፡፡ “አንተ አጨብጭብ እንጂ … ደህንነት ካየህ አንገትህን አንቆ ወህኒ ነው የሚወረውርህ!” አላቸው - ካስትሮ እንደሆኑ ያላወቀ ምስኪን ተመልካች፡፡ ለካስ ያ ሁሉ ጭብጨባ በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ነበር - ያላጨበጨበ አዳሩ ከርቸሌ ነዋ! የሚገርመው ግን አምባገነኖች የህዝብ አድናቆትና ጭብጨባ ከልብ ሳይሆን ከፍርሃት የመነጨ መሆኑንም እያወቁ ይፈልጉታል፡፡ የእውነት አድርገው በምናባቸው ይስሉታል፡፡ ለነገሩ እውነታቸውን ነው፡፡ ሳይደነቁና ሳይጨበጨብላቸው እንዴት መኖር ይችላሉ? ለእነሱ እኮ ኦክስጂን ማለት ነው - አድናቆት፣ ሙገሳና ጭብጨባ፡፡ እናም ሲሆን በፍቅር (በውዴታ) ያስጨበጭባሉ፤ ካልሆነ በማስፈራራት፡፡ (የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚለው ተረት ትዝ አለኝ)እንግዲህ “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይባል የለ (አባባሏ ለፖለቲከኞቻችን አስፈላጊ ናት!) እኔም ይኸው ቃሌን ጠብቄ ሁለተኛዋን ቀልድ እነሆ በረከት እላለሁ፡፡  እኔ የምለው ግን ፖለቲከኞቻችንና ባለስልጣናቶቻችን ለምንድነው እንደኔ ቃላቸውን የማይጠብቁት? (ተመክሮዬን ባካፍላቸው ደስ ይለኛል) ሁለተኛው ቀልዳችንም መቼቱ እዚያው ኩባ ነው፡፡ የታሪኩ ባለቤትም ራሳቸው ፊደል ካስትሮ ናቸው፡፡ ካስትሮ የእንቅልፍ እጦት (insomnia) ያሰቃያቸውና ወደ ግል ሃኪማቸው ጋ ይሄዳሉ፡፡ በፖለቲካ ዙሪያ ትንሽ ካወጉና አሜሪካን ከረገሙ በኋላ (ለሁለት) ችግራቸውን ያማክሩታል፡፡ ካስትሮ - “ዶክ… ባክህ እንቅልፍ እምቢ ብሎኛል! ተዓምር ቢመጣ ዓይኔ አይከደንም! ምን ባደርግ ይሻለኛል?…”

ዶክተር - “እስቲ አልጋህ ላይ ስትወጣ የራስህን ንግግር (Speech) ለማንበብ ሞክር…ያስተኛህ ይሆናል”

እንግዲህ የካስትሮ ስፒች ከመንዛዛቱ የተነሳ ታክቶአቸው ይተኛሉ በሚል ግምት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም መበቀሉ ሊሆን ይችላል - ለህዝቡ፡፡ በረዥም ንግግራቸው ህዝቡን እንዳታከቱት እራሳቸውም እንዲታክታቸው፡፡ ክፋቱ ደግሞ የሃኪም ምክር አልቀበልም አይባልም፡፡ ካስትሮ የራሳቸውን ንግግር አንብበውም እንቅልፍ እምቢ ካላቸው ግን ከባድ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ልብ አድርጉ! አምባገነኖች ከራሳቸው ንግግር በላይ የሚያስደስታቸው ወይም የሚጥማቸው ምንም ዓይነት ጽሑፍም ሆነ የጥበብ ሥራ እንደሌለ በ”ጥናት” ተረጋግጧል፡፡ በሌላ አነጋገር የዓለማችን አምባገነኖች (አፍሪካንም ይጨምራል) ራሳቸውን በማምለክ የሚወዳደራቸው የለም እንደማለት ነው፡፡ ፈርዶባቸው ከራሳቸው ጋር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡

አንድ ሌላ ቀልድ ልመርቅላችሁ፡፡ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ኒኮታ ክሩስቼቭ ሚስታቸውን ከጐናቸው ሸጉጠው ዓለምን ሲዞሩ ሚስት “የኔ ፍቅር፤ አሁን የት ነው ያለነው?” ስትል ትጠይቃቸዋለች፡፡

ክሩስቼቭም:- “አሜሪካ” ሲሉ መለሱ

“እንዴት አወቅህ?”

“ቲማቲም ተወረወረብኝ እኮ!”

ምንም አምባገነን ቢሆኑ የዲሞክራሲ በረከቶችን አሳምረው ያውቋቸዋል - ክሩስቼቭ፡፡ በእርግጥም የአፍና የጽሑፍ ተቃውሞ (ሲያስፈልግ ማለቴ ነው) ብቻ ሳይሆን በቲማቲምና በእንቁላል መመታትም ለዲሞክራት መሪዎች (መንግስታት) እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ባይሆን እንደ ጆርጅ ቡሽ ሽል ብሎ ራስን ከጫማ ውርወራ ማትረፍ ይቻላል፡፡  ለነገሩ ቦዲጋርዶችም ሥራቸው ይኸው ነው፡፡ የጥይት ተኩስን ብቻ ሳይሆን የቲማቲምና የእንቁላል ውርጅብኝንም በመመከት መሪውን ከጥቃት ይከላከላሉ - እንጀራቸው ነዋ! በእርግጥ ደመወዛቸውን የሚከፍላቸው ህዝብ ነው - የመሪዎቹንም የጠባቂዎቻቸውንም፡፡ የቀድሞ የማስታወቂያ ሚኒስትር፤ አሁን የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር የሆኑት የአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘ መጽሐፍ በተመረቀበት ምሽት ሼህ መሃመድ አላሙዲ በ97 ምርጫ “አሰደብከኝ” በሚል አቶ በረከትን ወቀሷቸው ልበል? ወቀሳው እንኳ ምንም ክፋት የለውም - በአደባባይ ሆነ እንጂ!፡፡ እኔ የምለው ግን የአቶ በረከት መጽሐፍ ይሄን ያህል ጊዜ ለምን ዘገየ? የ97 ምርጫ እንኳን 7 ዓመት አለፈው እኮ! ምርጫው ራሱ ከእነዝግጅቱ ቢበዛ አንድ ዓመት ነበር የፈጀው፡፡ መጽሐፉ ግን ድፍን 7 ዓመት! ልብወለድ ቢሆን እንኳ እሺ - 20 ዓመትም ሊፈጅ ይችላል፡፡ ሲታሽ ሲቀመም፡፡ ይሄ ግን ፖለቲካዊ ክስተት ነው፡፡ ለታሪክ ፀሃፊዎች እንደ መነሻ የሚያገለግል (የኢህአዴግ ዕይታ ወይም ምልከታ ብቻ ስለሆነ) አሁን ትዝ አለኝ - ለምን መፅሃፉ እንደዘገየ፡፡ ከምርጫው ቀውስ ጋር በተያያዘ የመጣውን ድንገተኛ “ናዳ” ለመግታት “አገራዊ ሩጫ” ላይ ነበርኩ ብለውናል፡፡ በእኔ በኩል አጥጋቢ ምክንያት ስለሆነ ጥያቄዬን አንስቼአለሁ፡፡ አቶ በረከት የ97ቱን “ናዳ” ከኢህአዴግ ጋር ገትተነዋል ቢሉም አሁን ደግሞ አዲሱ መጽሐፋቸው ሌላ ናዳ ይዞባቸው መጥቷል፡፡ ይሄኛው ግን የትችት ናዳ ስለሆነ አገራዊ ሩጫ አያስፈልገውም፡፡ በተባ ብዕር ብቻ ሊመክቱት ይችላሉ፡፡ የፓርቲያቸው ወይም የካድሬዎች እገዛም አይሹም፡፡ ለብቻቸው ይመክቱታል፡፡ (ይሄ የእኔ ግምት ነው) እርግጠኛ ነኝ እሳቸው መጽሐፉን ለማሳተም በገንዘብ እንደደገፏቸው ባለሃብት ተተቸሁ (ተሰደብኩ) ብለው አያማርሩም፡፡ በነገራችን ላይ ባለሃብቱ ኢህአዴግን በመደገፋቸው ብቻ መሰደብ አለባቸው ብዬ አላምንም - ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ነውና፡፡ አቶ በረከት በበኩላቸው፤ በ97ቱ ምርጫ የቴሌቪዥን መስኮት በርግደው በመክፈታቸው ይቆጫሉ ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ ከተቆጩማ የስንት ዓመት እልህ አስጨራሽ  ትግላቸውን ዋጋ አሳጡት ማለት ነው፡፡ (ለፍቶ መና ይሆናል!) በእርግጥ እንደ አልአሙዲ የ”ስድብ” ሰለባ የሆኑ አንዳንድ ወገኖች አይጠፉም፡፡ ይሄ ግን የዲሞክራሲ ሥርዓት “ጣጣ” ስለሆነ መታገስ የግድ ነው (ሲወዱ ከነ ምናምኑ ነው ይባል የለ!) የስድብና የትችት ውርጅብኝ ብቻ ሳይሆን የእንቁላልና የቲማቲም ውርጅብኝም እንዳለ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት ተሞክሮ መውሰድ (መኮረጅ) “አራድነት” ይመስለኛል (በጥናት ባይረጋገጥም!) እኔ የምለው ግን የአቶ በረከትን መጽሐፍ እንዴት አያችሁት? ልብ አድርጉ! እንዴት አያችሁት ነው እንጂ “አነበባችሁት ወይ?” አልወጣኝም፡፡ የመፅሃፉን ውድነት እያወቅኩኝ ይሄንንማ ልጠይቃችሁ አልችልም፡፡ እውነቴን እኮ ነው… የመጽሐፉ ዋጋ የኑሮ ውድነትን፣ የዋጋ መናርን፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውደቁን፣ ዓለማቀፉን የኢኮኖሚ ድቀት ወዘተ… ያገናዘበ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ኢህአዴግ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ አሰልፋችኋለሁ ያለው እኮ ከ20ና ከ30 ዓመት በኋላ እንጂ ዛሬውኑ አይደለም፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ጋ ስንደርስ የ90 ብር ሳይሆን የ200 ብር መጽሐፍ እንኳን ኮራ ብለን ልንገዛ እንችላለን፡፡ ያን ጊዜ ሌማታችንም - ኪሳችንም ሙሉ ነዋ! (ኢህአዴግ በሰጠን ተስፋ መሠረት) አሁን ግን እንኳን ለመጽሐፍ 90 ብር ልናወጣ ቀርቆ… ብቻ ይቅር! (ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል) እቺን ያነበቡ የኢህአዴግ ካድሬዎች ምን ሊሉ እንደሚችሉ አይጠፋኝም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ያወጡት መጽሐፍ እስከ 200 ብር ድረስ ሲሸጥ ትንፍሽ ሳይል  የኢህአዴግ አመራር ሲያወጡ… ተወደደ ምናምን ብሎ ይተቻል ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ይሄን ወቀሳ እቀበለዋለሁ፡፡ እውነት ነው፡፡ ምክንያት ግን አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ለድሀው የታገለ አሁንም የሚታገል የጭቁኖች ፓርቲ ነው ሲሉ ስለሰማሁ ነው ትችቴ ያየለው፡፡ በርግጥ አሁን “ጭቁን ፓርቲ” አይደለም - ኢህአዴግ!!የዛሬው ኢህአዴግማ ድልቅቅ ያለ ሃብታም ሆኗል - ሞጃ! የገንዘብ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የኢህአዴግ ሃብት ወይም ካፒታል ገንዘብ ሳይሆን ህዝብ ነው፡፡   የህዝብ ሃብታም ነው - ኢህአዴግ! እንዴ ብትሉ… 85 ሚ. ህዝብ እንዳሻው ይመራል (ግን አስፈቅዶ ነው ህዝቡን) ከ97 ምርጫ ወዲህ “ናዳን ለመግታት ባደረገው አገራዊ ሩጫ” ከ7 ሚሊዮን በላይ አባላትን አፍርቷል ይባላል፡፡ (ገቢያቸውን ሲጠየቁ ሃብታችን ህዝብ ነው የሚሉ የአገሬ ድምፃውያን ትዝ አሉኝ)   በነገራችን ላይ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የምትለዋ ርዕስ በጣም ተመችታኛለች፡፡ (አቅም ጠፋ እንጂ ርዕሷ ብቻ 90 ብር አይበዛባትም!) እውነቴን ነው የምላችሁ … ርዕሷን የመረጣት ሌላ ተራ ፀሐፊ ቢሆን  የአድናቆት መዓት ባዥጐደጉድኩለት ነበር፡፡ አቶ በረከት ግን ገጣሚ (ቃል አቀባይም ናቸው!) በመሆናቸው ብዙም አልገረመኝም፡፡ ገጣሚዎች የቃላት (ቋንቋ) ሃብታም ናቸው ይባል የለ! (ገቢያቸውን ሲጠየቁ ሃብታችን ቋንቋ ነው እንዳይሉ ብቻ!) በዚህች አጋጣሚ የሼህ ሙሃመድ አላሙዲንና የኢህአዴግን ወዳጅነት የምትተርክ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለኝና ርዕሷንም “የሁለት ወዳጃሞች ወግ” እንደምላት ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ (ማመልከቻ መሰለብኝ አይደል? ይምሰላ!) በነገራችን ላይ የአቶ በረከት መጽሐፍ በሸራተን አዲስ የተመረቀ ምሽት ሼህ አልአሙዲ በይፋ “ኢህአዴግን እወደዋለሁ! አራት ነጥብ!” ሲሉ መናገራቸው አንጀቴን አርሶኛል፡፡ እንዲህ የልቡን የሚናገር ሃቀኛ ባለሃብት ያስፈልገናል፡፡ ወዲያው ግን ሌላ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ - “ተቃዋሚዎችን እወዳቸዋለሁ! አራት ነጥብ!” ብሎ በአደባባይ መናገር የማያሸማቅቀው ባለሃብትም መፍጠር አለብን የሚል፡፡ (በግድ እንፍጠር ግን አልወጣኝም - ካለ ማለቴ ነው!) አዎ … የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት የፃፉትን መጽሐፍ ሳይሸማቀቅ በግልጽ የሚያሳትም ባለሃብት ማየት አለብን - እንደ አልአሙዲ፡፡ ያኔ ነው ሚዛናዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አለን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም… ለኢህአዴግ የተፈቀደ ነገር ሁሉ ለተቃዋሚዎችም መፈቀድ አለበት የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ይሄ እምነቴ ስህተት ከሆነ ለመታረም ዝግጁ ነኝ (በተለይ ከኢህአዴግ ከመጣ - እርማቱ!) ከሌላም ከመጣ ችግር የለም - እቀበላለሁ፡፡ ይታረማል ብላችሁ ግን እንዳትጠብቁ፡፡ ከዚህ በላይ ስለመፅሃፉ ብናገር “ፕሮሞሽን” ይመስልብኛልና ይብቃኝ፡፡አሁን እንግዲህ በቀጥታ ወደ ዛሬው አዲስ ፕሮፖዛል እንለፍ - የአየር ሰዓታችን ከመጠናቀቁ በፊት፡፡ ሰሞኑን ያረቀቅኩት ፕሮፖዛል “አራዳ ፓርቲና መንግስት እንፈልጋለን” ይላል፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ኢህአዴግ “ፋራ” ነው ልትል ፈልገህ ነው በማለት መረጃ የለሽ ክስ ሊመሰርቱብኝ ይችላሉ፡፡  ፕሮፖዛሌ እንደሚለው ግን ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች አራዳ ይሁኑ ፋራ እስካሁን የሚታወቅ ነገር ስለሌለ በዚህ ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል (ስፖንሰር ከተገኘ እኔም ላጠናው እችላለሁ)በፕሮፖዛሉ ላይ እንደሰፈረው “አራዳ” የሚለው ቃል ጮሌ፣ አሪፍ፣ የገባው፣ ተቆንጥጦ ያደገ፣ የሰለጠነ፣ አሪፍ ወይም “ስማርት” ፓርቲና መንግስት ለማለት እንጂ ዱርዬ፣ ተደባዳቢ፣ ወይም “ጉልቤ” ፓርቲና መንግስት ለማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ (በፓርቲያቸው ጽ/ቤት የሚደባደቡና የቢሮ ቁልፎች የሚደብቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ ልብ ይሏል) ለመሆኑ “አራዳ” እና “ፋራ” የሚሉት ስያሜዎች መመዘኛቸው ምንድነው? ፕሮፖዛሌ ምሳሌ እየጠቀሰ ያብራራል፡፡ ለምሳሌ ቲማቲምና እንቁላል እንዲወረወርበት የሚፈቅድና የሚታገስ ፓርቲ ወይም መንግስት የገባው ወይም አሪፍ (Smart) ይባላል፡፡ (አሪፍ አይቸኩልም ሲባል አልሰማችሁም?) በሌላ በኩል ለምን ቀና ብላችሁ አያችሁኝ ብሎ ዜጐቹን ፊት የሚነሳ፣ የሚሳደብ፣ የሚያስፈራራ፣ ለስደት የሚዳርግ ወይም እስር ቤት የሚወረውር ደግሞ “ፋራ” ፓርቲ ወይም መንግስት እንደሚባል አዲሱ ፕሮፖዛል ይጠቁማል፡፡ ተቃዋሚዎችን እንዳያንሰራሩ አድርጐ እግር ከወርች የሚያስር ፓርቲም ፋራ ነው፡፡ ገና ለገና የህዝብ አመጽ በመፍራት ኢንተርኔትን፣ አይፎንን፣ (እንደ ሶርያ መንግስት) ፌስቡክን ጠርቅሞ ዜጐችን ከቴክኖሎጂ ትሩፋቶች የሚያፋታ መንግስትና ፓርቲ እልም ያለ ፋራ ነው ይለዋል - ፕሮፖዛሌ፡፡ (በ97 ምርጫ ቴሌ የቴክስት አገልግሎት አቋርጦ እንደነበር ትዝ አለኝ) ምርጫ የሚያጭበረብሩትንም (እንደ ጋምቢያና ኮንጐ) ፋራ ፓርቲዎችና መንግስታት ይላቸዋል፡፡እኔ ብቻ ልግዛ የሚል “ራስ ወዳድ” ፓርቲም ከፋራዎቹ ጐራ ነው - ፕሮፖዛሉ እንደሚለው፡፡ እርስ በእርስ የሚጠላለፉና የሚወዛገቡ የፓርቲ አመራሮችም የፋራ ፓርቲ ውጤት ናቸው፡፡የፖለቲካ ምህዳርን የሚያጠብስ? እሱማ እልም ያለ ፋራ ነው፡፡ (እኔ ሳልሆን ፕሮፖዛሉ ነው ያለው) መንገድና ኮንዶሚኒየም በመስራት የዜጐችን ኑሮ የሚያቀል ደሞ ስማርት ፓርቲ ይባላል፡፡ ዜጐችን ከአቅም በላይ በሆነ ታክስ የሚያጨናንቅስ? እሱ በርግጥም ፋራ ነው ይላል - ፕሮፖዛሉ፡፡ ንብረትነቱ የህዝብ በሆነ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የእኔ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ይሰራጭ ብሎ ክችች የሚል ፓርቲና መንግስት ፈጽሞ ስማርት ሊባል አይችልም - የለየለት ፋራ ነው - እንደ ፕሮፖዛሉ መመዘኛ፡፡   ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በገፍ የሚያስርና የሚያንገላታ (እንደ ኤርትራ መንግስት) እሱም ዕጣ ክፍሉ ከፋራዎች ጐራ ነው፡፡ በማስፈራራት የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚሞክርም (እንደ አፍሪካ አምባገነኖች) ምድቡ ከፋራ ፓርቲዎች ነው፡፡ የሰው ነገር የማይሰማና ራሱን ብቻ የሚያዳምጥም የትም ሊመደብ አይችልም - ከፋራዎች ተርታ እንጂ፡፡ ተቃዋሚውን እያሳደደ የሚገድል መንግስትስ? እንዲህ ያለው ፋራም አራዳም አይደለም - “ንክ” ነው፡፡ እንዲህ ያለ መንግስት ሁነኛ ሆስፒታል መግባት አለበት -የአዕምሮ ሃኪም (ስፔሻሊስት) ነው ለዚህ መድሃኒቱ፡፡  በመጨረሻም ፕሮፖዛሉ ፋራና አራዳ ፓርቲዎችንና መንግስታትን በመለየት በየጐራቸው የሚመድብ ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ይጠቁምና ፓርቲዎች ለምርጫ ሲወዳደሩ አባላቶቻቸው “ስማርት” ወይም “ፋራ” የሚሉ ባጆችን ደረታቸው ላይ ማንጠልጠል  እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡ ለምሳሌ - “ኢህአዴግ - አራዳ ፓርቲ” ወይም “ኢህአዴግ ፋራ ፓርቲ” አሊያም “ኢዴፓ - አራዳ ፓርቲ” ወይም “ኢዴፓ - ፋራ ፓርቲ”  የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛስ? ከዛማ ቀላል ነው፡፡ ህዝብ የሚፈልገውን ይመርጣል - ከስማርትና ከፋራ ፓርቲዎች፡፡ ፕሮፖዛሌ እንደሚለው ፋራና አራዳ ፓርቲዎች የሚለዩበት ዋና ዓላማው፣ ዜጐች ድምጽ ሲሰጡ ፋራዎችን መርጠው እንዳይሸወዱ (እንዳይፀፀቱ) ለማድረግ ነው፡፡  በተግባር ያልተፈተኑ አዳዲስ ፓርቲዎችን ለመመዘን ደግሞ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን መገምገም እንደሚያስፈልግ ፕሮፖዛሌ ይመክራል፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን በማየት ብቻ ፋራ ይሁኑ አራዳ ማወቅ እንደሚቻል አንዳንድ “ጥናቶች” ይጠቁማሉ፡፡ በነገራችን ላይ ምርጫ ቦርድ ራሱም በስማርትና ፋራ ምድብ ውስጥ እንደሚካተት ፕሮፖዛሌ ይጠቁማል፡፡ እኔ የምለው ግን ያለፉትን አራት ብሔራዊ ምርጫዎች ያስተናበረው ብሔራዊ የምርጫ ቦርዳችን “ፋራ” ነው “አራዳ”? በነገራችን ላይ አቶ በረከት የ97ና የ2002ን ምርጫ የገለፁበት ቋንቋ ማርኮኛል፡፡ (ልብ አድርጉ ቋንቋው ነው የማረከኝ! ይዘቱ አልወጣኝም!) “የ97 ምርጫ - በሰላም ተጀምሮ በረብሻ የተጠናቀቀ” ሲሉት “የ2002 ምርጫ - በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ” ብለውታል፡፡ (ግጥም ሊመስል እኮ ትንሽ ነው የቀረው!)  ውድ አንባብያን - ፋራና ስማርት የምትሏቸውን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ዳያስፖራን አይመለከትም) በመለየት ለዲሞክራሲ ባህላችን መዳበር የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ተጋብዛችኋል፡፡ ስፖንሰርሺፕ ከባለሃብቶች እስኪገኝና ፕሮፖዛሉ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ብቸኛው አማራጭ “አራዳ” ፓርቲዎችን ያብዛልን እያልን መፀለይ ብቻ ነው፡፡ ሰናይ ሰንበት!!

 

 

 

Read 3821 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 10:35