Saturday, 30 August 2014 10:15

የወር አበባ ሕመም ማህበራዊ ተጽእኖ አለው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(34 votes)

           25% የሚሆኑ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው የወር አበባ ሕመምን ያስተናግዳሉ፡፡ በአስራዎቹ እና ሀያዎች የእድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች ከ65-95 % የሚሆኑት የወር አበባ ሕመም ሊኖራቸው ይችላል፡ የወር አበባ ሕመም በእነማን ላይ ወይንም በየትኛው የእድሜ ክልል ይከሰታል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎችን መፈተሸ ይጠቅማል፡፡ የወር አበባ ሕመም መከሰት ከጠቅላላው እድሜ ጋር ሲፈተሸ ወደ 25 % ወይንም 1/4ኛ የሚሆኑ ሴቶች በሕይወታቸው የወር አበባ ሕመምን ያስተናግዳሉ፡፡ በተለይም በወጣትነት እድሜ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ማለትም በአስራዎቹ እና ሀያዎች የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉት ሴቶች ከ65-95% የሚሆኑት የወር አበባ ሕመም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ጉዳቱንም ስንመለከት ከሕመሙ ውጭ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫናው አስከፊ ነው፡፡ የወር አበባ ሕመም እንዴት? በምን ምክንያት ይከሰታል? መፍትሔውስ ምንድነው? ለሚለው ዶ/ር ሙሁዲ አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህር የሰጡን ማብራሪያ ለንባባ ቀርቦአል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም ማለት ምን ማለት ነው? መ/ የወር አበባ ሕመም ሲባል የወር አበባ ሊመጣ ሁለት ወይንም ሶስት ቀን ሲቀረው ጀምሮ በፍሰቱ ወቅት የሚሰማ ሕመም ነው፡፡ የወር አበባ ሕመም ስሜቱ ስለአለ ብቻ የወር አበባ ሕመም የሚያሰኘው አይደለም፡፡ 

ነገር ግን ሕመሙ የእለት ተእለት ተግባራት ወይንም ትምህርትን እስከማደናቅፍ ሲደርስ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ሕመም ሊባል ይችላል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ህመም ሲባል ደረጃ አለውን? መ/ የወር አበባ ሕመም ደረጃው ሁለት ነው፡፡ (Primary & secondary) ቀዳሚ እና ተከታይ በሚል ሊገለጽ ይችላል፡፡ ቀዳሚ የሚባለው (Primary dysmenorrheal) አብዛኛውን ጊዜ ከማህጸን ጋር ተያያዥነት ያለው በሽታ ወይንም ችግር በሌለበት ሁኔታ የሚከሰት ሲሆን ይህም ችግር የሚገኘው በተለይም በመጀመሪያዎቹ አስሮቹ ወይንም ሀያዎቹ በሚባሉት የእድሜ ክልል ውስጥ ነው፡፡ እንዲሁም መውለድም ሆነ እርግዝና ሞክሮአቸው በማያውቁ እና ገና በትኩስ እድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይ የመጀመሪያው አይነት የወር አበባ ሕመም ይከሰታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው የማህጸን በር መጥበብ ወይንም መዘጋት ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው (secondary dysmenorrheal) የሚባለው ከማህጸን ጋር ተያይዞ በሚመጣ ችግር የሚከሰት የወር አበባ ሕመም ነው፡፡ ለምሳሌም... የማህጸን እጢ የሚባለው (ማዮማ) ፣ እንዲሁም የወር አበባ ኡደት ተዛብቶ ወደሌላ የሰውነት ክፍል ሲሄድ፣ የማህጸን ኢንፌክሽን፣ በማህጸን በር ወይንም ግድግዳው ላይ የሚከሰቱ የእጢ የመለጠፍ አይነቶች፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ በዚህ ደረጃ ሴቶች የሚታመሙት እድሜያቸው በአብዛኛው በሰላ ሳዎቹና በአርባዎቹ ክልል ሲደርስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወር አበባ ሕመም መጀመሪያ ሳይሰማቸው ቆይቶ እነዚህ ችግሮች በመከሰታቸው ምክንያት የሚፈጠር ሕመም ሊሆንም ይችላል፡፡

ጥ/ ሕመሙን ሊያመጡ የሚችሉ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ? መ/ ሕመሙን ሊያመጡ ይችላሉ ከሚባሉት ምክንያቶች መካከል በተለይም በወጣትት እድሜ ክልል ያሉት ሴቶች ለሕመሙም አነስተኛ ግንዛቤ ያለቸው ወይንም ደግሞ በአእምሮአቸው ተጨናቂ ከሆኑ እንዲሁም ለሕመሙ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው እና ደረጃውንም ሳይጠብቁ መጨነቅ ሲያበዙ ሕመሙ የሚከሰትበትን እድል ያሰፉታል፡፡ በሁለተኛም ደረጃ ማህጸን በተፈጥሮው በየወሩ የወር አበባ ኡደት ውስጥ የሚሄድባቸው ለውጦች አሉ፡፡ የወር አበባ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እራሱን ያዘጋጅና ከዚያ በሁዋላ ከኦቩሌሽን ቀጥሎ የወር አበባ ወይንም እርግዝና እንዲከሰት ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በዛ ዝግጅት እርግዝና ሳይከሰት ሲቀር ወደመጨረሻዎቹ ሳምንታት የማህጸን ግድግዳ የመድማት ሂደትን ያስተናግዳል፡፡ እነዚያ የመድማት ክስተቶች በአንዴ የሚከ ሰቱ ሳይሆን ወቅታቸውን ጠብቀው በተወሰኑ ጊዜያቶች የንጥረነገሮችን ኡደታቸውን ለማካሄድ የተለያየ መጠን ደርሰው ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ የማህጸን የመኮማተር ወይንም ደግሞ ይህ መኮማተር ሕመም እንዲፈጥር ወይንም እንዲያሳይ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ ፡፡ የወር አበባ ተከስቶ ደም በሚፈስበት ጊዜ ያንን የተዘጋጀውን ደም በበቂ ሁኔታ እንዲፈስ የማህጸን በር የሚባለው ክፍት ሆኖ የወር አበባው ቆሻሻ መውጣት ሳይችል ሲቀር በሚፈጠረው ተፈጥሮአዊ ሂደት የማህጸን በር እንዲኮማተር የደም ዝውውሩ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ ይህ የደም ዝውውር በመቆሙ ወይንም ማህጸን በመኮማተሩ ምክንያት ህመም አምጪ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች እንዲፈልቁ ያደርጋል፡፡ በዛም ምክንያት ተደጋጋሚ መኮማተር ስለሚያጋጥም ሕመሙ ያጋጥማል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከማህጸን ችግር ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሕመም ችግሩ ሲወገድ አብሮ የሚወገድ ነው፡፡ ጥ/ በሽታው የሚገለጽበት ሁኔታ ምን ይመስላል? መ/ በሽታው ብዙውን ጊዜ ከእምብርት በታች ወይንም ሽንት መሽኛ እና የሽንት ፊኛ አካባቢ የተለያየ የህመም ስሜት አለው፡፡

ሴቶቹ ሲገልጹት አንዳንድ ጊዜ እጅግ የሚያም ቁርጠት አይነት ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ወደታች የመግፋት ስሜት ያለው ...ነገር ግን ለመግለጽ የሚያስቸግር ሕመም ነው ይሉታል፡፡ ሕመሙ ወደታችኛው የሰውነት ክፍል ማለትም ወደእግር ታፋ ወይንም ጭን አካባቢ ሁሉ የሚደርስ ስሜት አለው፡፡ ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስበት ጊዜ የማቅለሽለሽ ፣የእራስ ምታት፣ ተውከት ፣ድብርት ፣ ቁርጥማት ፣ተቅማጥ ፣ድርቀት በመሳሰሉት ሁሉ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይህ የወር አበባ ሕመም በማህጸን አካባቢ ብቻ የሚከሰት ሳይሆን ጠቅላላ ሰውነት ላይም ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም የሚያስከትለው ማህበራዊ ችግር ምንድነው? መ/ የወር አበባ ሕመም በሴትየዋ ከሚከሰተው የሕመም ስሜት እና የአእምሮ ስቃይ በተለየ ማህበራዊ ችግር ያስከትላል፡፡ የተማሪዎችን ሁኔታ ስንመለከት ከ15-20 ኀ የሚሆኑት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ከሚቀሩባቸው ምክንያቶች ዋነኛው የወር አበባ ሕመም ነው፡፡ በስራ ላይ ያሉ ሴቶች በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ጊዜ ከስራ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁበት ምክንያት የወር አበባ ሕመም ነው፡፡

ስለዚህም ይህ ሕመም ከሚያ ደርሰው ስቃይ በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊው እና ማህበራዊው ችግር ብዙ ሴቶች ሲጎዱ ይታያሉ፡፡ ሕብረተሰቡ ባለው ግንዛቤ ምክንያትም ሴቶቹ ሕመም ሲደርስባቸው አለመ ረዳት እና ከትምህርትም ሆነ ከስራ በሚቀርበት ጊዜ በቂ ምክንያት እና በቂ መረጃ እያቀረቡ ትብብርን ያለማሳየት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ሕመም ከሕክምናውም ባሻገር አእምሮአዊ እረፍት እና መረጋጋትን እንደሚፈልግ ህብረተሰቡ ቢረዳው እና በቂ ግንዛቤ ኖሮት እርዳታ ቢያደርግላቸው ተገቢ ነው፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም በጋብቻ እና ልጅ በመውለድ ምክንያት ይቀንሳልን? መ/ አንዲት ሴት ጋብቻ በመፈጸሙዋ ምክንያት ከወንድ ጋር በምታደርገው ግንኙነት ሳቢያ የወር አበባ ሕመም ሊተዋት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የወር አበባ ሕመም መንስኤው ከላይ እንደተገለጸው አንድም ከማህጸን ጋር በተያያዘ ችግር ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ነው፡፡ ከመውለድ ወይንም ከእርግዝና ጋር በተገናኘ በመጀ መሪያ ደረጃ የሚከሰተው ሕመም ሊወገድ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በእርግዝናው ወይንም በወሊድ ጊዜ የማህጸን በር በተወሰነ ደረጃ የሚከፈት በመሆኑ ሕመሙ ሊጠፋ ወይንም ደግሞ ሊታገስ ይችላል፡፡ ጥ/ ሕክምናው ምን ይመስላል? መ/ የወር አበባ ሕመም ላላቸው ሴቶች በቅድሚያ የሚሰጠው ሕክምና ማስታገሻ ነው፡፡

የማስታገሻው መድሀኒት ታማሚዎቹን የሚሰማቸውን ሕመም መጠኑን በጣም ሊቀንስላቸው እና ከስቃይ እረፍት እንዲያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በማስታገሸ መድሀኒቶች ሕመሙ የማይታገስ ከሆነ በመቀጠል የሚደረገው ሁለት አይነት ሕክምና አለ፡፡ አንደኛው በሕክምና የሚረዳ ሲሆን ሕመሙ በጣም የከፋ ከሆነ ደግሞ ሰርጂካል የሚባል ሕክምና ይሰጣል፡፡ በእርግጥ እንደዚህ ካሉ ሕክምናዎች ደረጃ ሲደረስ ሴትየዋ በቀጣይ ያላትን ዝግጅት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወደፊቱ ጊዜዋ እርግዝናን ታስ ባለች ወይንስ ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እርግዝና የምትፈልግ ከሆነ በሕመም ማስታገሻው ትእግስት አድርጎ እርግዝናው እንዲከሰት ማድረጉ ለወደፊቱም ሕመሙን የሚያስታግስ ስለሆነ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እርግዝናን የማታስብ ከሆነ ግን የእር ግዝና መቆጣጠሪያን ጨምሮ የህመም ማስታገሻዎቹን በሐኪም ትእዛዝ መሰረት በመውሰድ ሁኔታውን ማየት ይቻላል፡፡ በመድሀኒቶቹ ወይንም በማስታገሻዎቹ የማይታገስ ከሆነ እና ችግሩ ከማህጸን ችግሮች ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን በምርመራ በማረጋገጥ ምክንያቱ የማህጸን በር መዘጋት ከሆነ የማህጸን በርን በህክምና እንዲከፈት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

Read 39465 times