Saturday, 30 August 2014 10:18

አይረሴው አትሌት ወርቁ ቢቂላ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“አትሌት የሆንኩት ባለማወቅ ካዳበርኩት አቅም ነው” አትሌት ወርቁ ቢቂላ ወርቁ ቢቂላ በጣም ታዋቂና አይረሴ የሚያሰኙ በርካታ የአትሌቲክስ ገጠመኞች ያሉት ታዋቂ አትሌት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከ1976 ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ 2002 ድረስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የአገሩን ባንዲራ በድል አውለብልቧል፡፡ ከጀግናው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ጋር በተለያዩ የአለም የሩጫ ትራኮች ላይ ጥሩ የቡድን ስራ በመስራት ለድል በቅተዋል፡፡ በአርሲ ክ/ሀገር ሰሬ ወረዳ አርብ ገበያ የተወለደው አትሌት ወርቁ ቢቂላ፣ የጐልደን ሊግ አሸናፊም ነበር፡፡ በጐልደን ሊግ ካስመዘገበው ስኬት በኋላ አዲዳስ ኩባንያ ጋር የማስታወቂያ ውል በመፈራረም ለሶስት አመታት ማስታወቂያ ሰርቷል፡፡ በግምት 48 ዓመት እንደሆነው የሚናገረው አትሌት ወርቁ በአሁኑ ሰዓት በዱከም ከተማ ትልቅ ሆቴልና ትልቅ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ት/ቤት ከፍቶ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቷል፡፡

ለህንፃ ግንባታ በዝግጅት ላይ እንደሆነም ተናግሯል፡፡ ከሩጫ አጀማመሩ፣ ከስኬቶቹ፣ ከቢዝነስ ስራውና ከግል ህይወቱ ጋር በተገናኘ ዱከም በሚገኘው ሆቴሉ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እስኪ ስለአስተዳደግህ አጫውተኝ… እኔ እንግዲህ ገጠር ነው የተወለድኩት፤ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፡፡ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ በእርሻ በከብት ጥበቃ ቤተሰቤን እያገለገልኩ፣ ከዚያው ጎን ለጎን ትምህርት እየተማርኩ ነው ያደግሁት፡፡ ያው ገጠር ውስጥ ስትኖሪ በግብርና ህይወት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እነዚያን ውጣ ውረዶች በፅናት ማለፌ አሁን ላለሁበት ህይወት መሰረት ጥሎልኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ስለአትሌቶች ሲነሳ አርሲ ትጠቀሳለች፡፡ ብዙዎቹ ሩጫ ለመድን የሚሉት የመኖሪያ ቤታቸውና ት/ቤታቸው ሩቅ በመሆኑ እየሮጡ ስለሚሄዱ ነው፡፡ የአንተ ሯጭነት መነሻው ከዚህ ይለያል? በእርግጥ እኔ የተማርኩበት ት/ቤት ከቤቴ ብዙ አይርቅም ነበር፡፡

ግፋ ቢል በእግር የ20 ደቂቃ መንገድ ነው፡፡ እሷን በሩጫ በአምስት ደቂቃ ፉት ነው የምላት፡፡ ከቤቴ ሲደወል ተነስቼ እንኳን ሮጬ እደርሳለሁ፡፡ ትልቁ እኔን ለሯጭነት ያበቃኝ ጉዳይ ከብት እረኝነት ላይ እያለሁ አንድ አመፀኛ ወይፈን ነበረኝ፡፡ ይህ ወይፈን አውድማ ላይ እህል ሲወቃ በጄ ብሎ አይወቃም፡፡ ጥጋበኛ ነው፡፡ ሳሩ ለምለም ነው፤ እንደልቡ ይበላል፡፡ ውቂያ ውስጥ ግባ ስትይው ይፈረጥጣል፡፡ በዚህን ጊዜ ጭራውን ይዤ አብረን እንሮጣለን፡፡ ይገርምሻል እኛ የምንኖርበት አካባቢ ሜዳማ ነው፤ ያንን ሁሉ ሜዳ ጭራውን ይዤ አብሬው እሮጣለሁ፡፡ ለምን አብረኸው ትሮጣለህ? አሃ! ወይፈኑ ሮጦ ሮጦ ሲደክምና ሲያለከልክ ይዤው እመለስና ወደ ውቂያው እከተዋለሁ፡፡ ይሄን በየጊዜው ስለማደርግ ለካ ሳላውቀው አቅም አዳብሬ ኖሯል፡፡ በሌላ በኩል እህል እነግድ ነበር፡፡ እህል ለመሸመት የምንሄድበት ገበያ የአራት ሰዓት መንገድ ሲሆን ስንመለስ አራት ሰዓት በድምሩ በቀን የስምንት ሰዓት መንገድ እጓዛለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ በዚህ የአካል ብቃቴ እየዳበረ መጣ፡፡ ይህ የሆነው ሳላውቀው ነው፡፡ ስራዬ ብለህ ሩጫ የጀመርከው እንዴትና መቼ ነበር? ሩጫ የጀመርኩት ት/ቤት እያለሁ ነው፡፡ በስፖርት ክፍለ ጊዜ እንሮጣለን፡፡ እንዳልኩሽ እኔ ከዚያ በሬ ጋር ስሮጥ፣ ገበያ በቀን ስምንት ሰዓት ስጓዝ፣ ሳላውቀው ሯጭ ሆኛለሁ፡፡ በማወቅና ባለማወቅ ነው ስፖርት የሚሰራው ብሏል ኃይልሻ (ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለማለት ነው) ከዚያ በስፖርት ክፍለ ጊዜ ሩጫ ስንወዳደር ማን ይቻለኝ! 1500 ሜትርና 800 ሜትር አንደኛ፣ ከት/ቤቶች ጋር ስወዳደር አንደኛ፤ በአርሲ ክ/ሃገር በ1500 እና 800 ሜትር አንደኛ እየሆንኩ ማንም ሊደርስብኝ አልቻለም፡፡

በዚያን ጊዜ የሙዚቃ ክፍለጊዜም ነበረን፤ ሙዚቃም ስፖርትም ማርክ ነበረው፡፡ ዘፈን በድምፄ ስለማልችል ማርክ ሊያመልጠኝ ሆነ፡፡ ዋሽንት መፈለግ አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፡፡ በሸምበቆ እሰራለሁ፤ እበሳለሁ፣ አልተሳካም፡፡ ብዙ ስቃይ አየሁ፡፡ የዋሽንት አሰራሩ ችግር ለካስ የራሴው ነው፡፡ በኋላ አንድ የብረት ዋሽንት በአንድ ብር ገዛሁ፡፡ ድምፅ ማውጣት ጀመረች፡፡ በእሷ ቀስ በቀስ ስለማመድ ዋሽንት መንፋት ቻልኩ፡፡ የሙዚቃ ማርኬን ማግኘት ቻልኩኝ ማለት ነው፡፡ በሁለቱም መስኮች ተሳትፎዬ አደገ፡፡ ያኔ ወረዳችን ስፌ ወረዳ ይባል ነበር፤ አሁን ጦሳ ወረዳ ተብሎ ተቀይሯል፡፡ ያኔ በወረዳችን መጥተው ሲያወዳድሩ አንደኛ እወጣ ጀመር፡፡ ልጁ በሙዚቃውም በስፖርቱም ጠንካራ ነው በማለት ካምፕ አስገቡኝ፡፡ መቼ ነው ይህ የሆነው? በ1976 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ካምፕ ከገባን በኋላ መማር፣ መሰልጠን ጀመርን፡፡ እዚያም ማሸነፍ ሆነ ስራዬ፡፡ መጨረሻ ላይ ፍስሃ የሚባል ሰው “ጐበዝ አትሌት ስለሆንክ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ ውብሸት ከሚባል አሰልጣኝ ጋር ላስተውዋቅህ” አለኝ፡፡ በትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም መሬት ሸልመውታል፡፡ በወቅቱ የወጣቶችና ስፖርት ክፍል ኃላፊ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ፈርቼ እምቢ አልኩኝ፡፡ በኋላ ትዕዛዙ ራሱ ተዋወቀኝና “ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀኝ “እኔ በህይወቴ መሆን የምመኘው ፖሊስ ነው፤ ፖሊሶችን በጣም እወዳለሁ” አልኩት፡፡ ለምን ነበር የምትወዳቸው? ይሄ ጃምቦ የሚመስል ትልቅ ኮፍያቸውን ሲያደርጉ በጣም ደስ ይሉኛል፡፡ እናም በወር 30 ብር ደሞዝ ላግኝ እንጂ ምንም አልፈልግም አልኩኝ፡፡

ለካስ ቤት ኪራይ አለ፣ ምግብ አለ፣ መታመም አለ፤ ያንን 30 ብር ምን ላደርገው ነበር እያልኩ አሁን ሳስብ ያስቀኛል፡፡ በቃ ትዕዛዙ “በቃ በርታ፤ ስፖርትህን አታቋርጥ፤ በደንብ ስራ” አለኝ፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በ1979 የሰራዊቱ የስፖርት በዓል በአዲስ አበባ ይካሄድ ነበር፡፡ ትዕዛዙ ያኔ ተመልምሎ አርሲ ሄዷል፡፡ እኔ ገና ሰሬ ወረዳ ውስጥ ነበርኩኝ፤ እድሜዬም ገና ነበር፤ በዚህ በአገር አቀፍ የስፖርት በዓል ላይ እሱ አርሲን ወክሎ ሄዶ ነበር፡፡ ስድስት ወር ያህል ቀድሞ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ በስፖርቱ ለመሳተፍ ግዳጃቸውን ፈፅመው የተመለሱ አንድ ሺህ ሰራዊት፣ እንደገና ከዚያው አካባቢ የተመለሱ ስድስት መቶ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ “ከ1600 ሰራዊት የሚበልጥ፣ ከእነሱ ሁሉ አንደኛ የሚወጣ ወርቁ ቢቂላ የሚባል አትሌት አመጣለሁ” አለ፡፡ “እንዲህ የምትለው ከስልጠና ለመሸሽ ነው፤ እሱ ከተሸነፈ አንተ ትባረራለህ” አሉት፡፡ “ግዴላችሁም ልባረር” አለና እኔ ጋ መምጫ ብር አጥቶ፣ ከጓደኞቹ አንድ አንድ ብር ለቃቅሞ በ10 ብር እኔ ጋ መጣ፡፡ ካምፕ መጥቶ “ወርቁን ፈልጉልኝ” አለ፤ ገና እንዳገኘሁት “በል ልብስህን ያዝና ተነሳ” አለኝ፤ “ለምን?” ስለው “ፖሊስ ላደርግህ ነው” አለኝ፡፡ ያኔ ምን እንደተሰማህ ታስታውሳለህ? በደንብ እንጂ! ቀላል አስታውሳለሁ! ማመን አቃተኝ፤ የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ ካምፕ ውስጥ መንግስት የሰጠኝን ልብስ በሙሉ ፀጋዬ ለሚባል ጓደኛዬ “ከመጣሁ መጣሁ፣ ካልመጣሁ የት እንደሄደ አላውቅም ብለህ ልብሱን ብቻ አስረክብልኝ” አልኩት፡፡

ተመልሰህ ወደ ካምፕ የመምጣት ሃሳብ ነበረህ እንዴ? አይ… ምናልባት በጤና ምርመራ ወይም ሌሎች መስፈርቶችን ላላሟላና ልመለስ እችላለሁ በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ ከዚያ ወደ አዲስ አበባ መምጫ ብር ከየት ይምጣ! በሌሊት ዶሮ ሲጮህ ተነሳንና እናቴ ቤት ጅማታ ሎዴ ጉዞ ጀመርን፡፡ ምክንያቱም 20 ብር ያስፈልገናል፡፡ መንገዱ አራት ሰዓት ያስኬዳል፤ ገደላገደል አለው፤ አስቸጋሪ መንገድ ነው፡፡ አንዲት ሸራ ጫማ ነበረችኝ፡፡ እሱ ደግሞ መንግስት የሰጠው ቆዳ ጫማ ነበረው፡፡ ያ ፖሊስ ቤት የተሰጠው ጫማ እንዳይቆሽሽና በአስቸጋሪ መንገድ እንዳይቀደድ አወለቀና የእኔን ሸራ ሰጥቼው፣ እኔ በእግሬ ሆኜ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ እሾሁ፣ ድንጋዩ እግሬን እየጋጠኝ፣ አይደረስ የለም ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ ደረስን፡፡ ብሩን አገኘህ? እህቴ በወቅቱ ቡና ትነግድ ነበር፡፡ ከእሷ ወሰድኩ፡፡ ትንሽ አረፍንና በሁሩታ በኢተያ አድርገን አዲስ አበባ ገባን፡፡ ከዚያ ማሰልጠኛ ገባሁ፤ ጥቂት እንደቆየን ማጣሪያ ውድድር ተባለ፡፡ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ እንደነገርኩሽ፣ ቀልጣፋና ተግባቢ በመሆኑ፣ ምልመላ ፖሊሶችም ሆኑ ኃላፊዎቹ ይወዱታል፡፡ ማጣሪያ ሲባል ተጠራጠረኝ፤ ምክንያቱም “እሱ ከተሸነፈ ትባረራለህ” ተብሏል፡፡ ያኔ ፖሊስ ቤት የመግባት እድል ጠባብና ከባድ ነበር፡፡ እኔ ላይ ጥርጣሬ ሲያድርበት ለማጣሪያ የሚወዳደሩትን ጠዋት ከባድ ልምምድ ሰጥቶ አደከማቸው፡፡ ከሰዓት ማጣሪያው ሆነ፡፡ ባለስልጣኑ ሁሉ ወጣ፣ ሰራዊቱ ተደረደረ፣ ሜዳዋ ጠባብ ስለነበረች ለ1500 ሜትር ስምንት ዙር ነው የምትሮጪው፡፡ ሲጀመር ፈትለክ ብዬ ወጣሁና ደርቤ ደርቤ አንደኛ ወጣሁ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፤ ያኔ ትዕዛዙን “ሼባው” ነው የሚሉት፣ “የሼባው ልጅ አንደኛ” እያሉ ጮሁ፡፡ አሸነፍኩ፡፡ የመጣንበት የትራንስፖርት ታስቦ ተሰጠን፡፡ ደስታ በደስታ ሆንን እልሻለሁ፡፡ አንተ ግን ያን ጊዜ ያሸነፍከው በሙስና ነው ማለት? እንዴት? ምክንያቱም ከሰዓት በኋላ ማጣሪያው እንደሚካሄድ ሲያውቅ ትዕዛዙ ስልጣኑን ተጠቅሞ ተፎካካሪዎችህን በልምምድ ስላደከማቸው ነው ያሸነፍከው (ሳ…ቅ) በእውነት እልሻለሁ፤ በልምምድ ባይደክሙም እምቅ ጉልበት ስለነበረኝ አሸንፋቸው ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ነው የምነግርሽ በዚያን ወቅት እንደ ንፋስ ነበር የምበረው፡፡ እሺ ከማጣሪያው በኋላ ምን ሆነ? ከዚያማ ኦሜድላ ስፖርት ገባን፡፡

የጤና ምርመራ አደረግን፡፡ በምርመራው ወቅት ሲያዩኝ “ስፖርተኛ ነህ አይደል?” አሉኝ፤ “አዎ” አልኳቸው፡፡ “በቃ አንተ የሰራዊታችንን ስም ታስጠራለህ፤ ሰራዊታችንን ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ትልቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በርታ ውጤት እንጠብቃለን” አሉኝ፡፡ በቃ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ መግባቴን አረጋገጥኩኝ፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጥክበትን መድረክ እስኪ አስታውሰኝ ከዚያ በፊት ልነግርሽ የምፈልገው ትዕዛዙ ቀድሞ ስድስት ወር ስልጠና ገብቶ ስለነበር ስልጠናውን ጨርሶ ወጣ፤ እኛ ገና ስድስት ወር ይቀረናል፡፡ ስለዚሀ አርሲ ሆኖ በመደወል “አትሌት ወርቁ ቢቂላ ጎበዝ እና ጠቃሚ በመሆኑ ወደ አርሲ እንዲዛወርልን” በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ወዲያው ስልጠናው እንደተጠናቀቀ ሃላፊው “ወደ አርሲ ይዛወር” ብለው ፈቀዱ፡፡ የዚያኔ የደርግ ዘመን ጦርነት ስለነበረ ወይ ወደ አንዱ ግንባር ዘምቼ ሞቼና ተረስቼ እቀር ነበር፤ አሊያም አካል ጉዳተኛም ሆኜ ልኖር እችል ነበር፡፡ በትዕዛዙ ምክንያት ወደ አርሲ ሄጄ የፖሊስ አትሌት ሆኜ ቀጠልኩኝ፡፡ የትምህርትህስ ጉዳይ? ትምህርት እስከ 8ኛ ነበር የተማርኩት፡፡ አርሲ ፖሊስ ስገባ ትዕዛዙ የማታ ተማር አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ “እንዴት አድርጌ እማራለሁ” አልኩት፤ ምክንያቱም ገና ከፖሊስ ስልጠና ስትወጪ ጥበቃ ነው የምትሰሪው፡፡ “ጥበቃ ሰርቼ፣ ሩጫ ሮጬ እንዴት ትምህርት ማታ እማራለሁ” አልኩት፡፡ “ጥበቃውን ከእኔ ጋር አንድ ሽፍት እናደርግና የአንተንም አደር እየጠበቅሁ እረዳሃለሁ፤ አንተ ብቻ ትምህርትህን ቀጥል” አለኝ፡፡ አሰላ ጭላሎ ት/ቤት እስከ 11ኛ ክፍል ትምህርቴን ተከታተልኩኝ፡፡ አግደው ወልዴ የሚባል የጥበቃ ኃላፊ ነበር “አይዞህ አንተን አሳድገን አንድ ነገር ላይ እናደርስሃለን ይለኝ” ነበር፡፡ ብቻ ድጋፋቸው በጣም አበረታታኝ፡፡ ትዕዛዙ ደግሞ አሰላ ቤተሰብ ስለነበረው ወንድሙ ቤት እንድቀመጥ አድርጐ ከምግብ ጀምሮ በእንክብካቤ ያኖረኝ ጀመር፡፡ ሁሉን ነገር ትቼ ሩጫዬ ላይ አተኮርኩኝ፤ ከዚያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕሮጀክት ስለነበረ፤ እዛ ገባሁ፡፡ እዚያ በሶስት ወር ሶስት መቶ ብር ይሰጡናል፡፡

የፖሊስ ደሞዝ ደግሞ 137 ብር ነበረ፡፡ በቃ ሃብታም ሆንን፡፡ ሶስት መቶ ብር ብዙ ነው ያን ጊዜ፡፡ እኔ፤ ሃይሌ ገ/ሥላሴና ሌሎች አትሌቶች ከዚህ ፕሮጀክት ነው የወጣነው፡፡ የፖሊስ አትሌቶችም ሆነን በአየር መንገድም ታቅፈን ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ስንሰለጥን ከቆየን በኋላ በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ገባ፡፡ በወቅቱ ስፖርቱም ሁሉም ብትንትኑ ወጣ፡፡ የለውጡ ሂደት ሲረጋጋ የስፖርቱ ሂደት መቀጠል አለበት ብለው ኢህአዴጎች ስፖርቱን መልሰው አቋቋሙት፡፡ ተበትናችሁ በነበረበት ሰዓት ምን እየሰራህ አሳለፍክ? ይገርምሻል፤ ተበትነንም እኔ ስፖርት መስራቴንና ሩጫ መሮጤን አላቆምኩም፡፡ እናቴም በሶና የተለያዩ ምግቦች እየላከችልኝ፣ ትእዛዙ ውብሸትም እየረዳኝ ልምምዴን ቀጥዬ ነበር፡፡ ከለውጡ በኋላ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ውድድሬን ያደረግሁት ሃዋሳ ላይ ነበር፡፡ ውድድሩ የ21 ኪ.ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ነበረ፡፡ በመሰረቱ የእኔ የሩጫ ዘርፍ አጭር ርቀት ነበር፤ 800፣1500 እና 5000 ሜትር ላይ ነው የምሮጠው፡፡ ሃዋሳ ላይ ስሄድ ትእዛዙ “ታሸንፋላችሁ አይዟችሁ” አለንና ተወዳደርን፡፡ ፊሽካ ተነፋ፡፡ እኔ 21 ኪ.ሜትር ርቀት ተወዳድሬ አላውቅም፤ ግን ሸክሽኬ ሸክሽኬ አፈትልኬ ስወጣ፣ ትዕዛዙ ሳይክል ተከራይቶ ይከተለን ነበር፡፡ በምልክት “አይዞህ” አልኩት፡፡ ይገርምሻል ትዕዛዙ ሰው ሲሞት እንኳን አያለቅስም፡፡ በቁም እያለ መርዳት ያለበትን ይረዳል፣ ያስታምማል፤ ያንን አልፎ ከሞተ “ምንም ማድረግ አይቻልም” ባይ ነው፡፡ “አይዞህ አሸንፋለሁ” የሚለውን ምልክት ስሰጠው አለቀሰ፡፡ አንደኛ ወጥቼ አሸነፍኩኝ፡፡ ከዚያ ፖሊስ ኦሜድላ መግባት አለብህ አለ፡፡ አሰላ ፖሊስ ደግሞ አንለቀውም አሉ፡፡ “ከኦሜድላ ሁለት ወታደር እንሰጣችኋለን፤ ወርቁን ስጡን” አሉ፤ ከዚያ በሁለት ፖሊስ ተቀይሬ ኦሜድላ ገባሁ እልሻለሁ፡፡ የኦሜድላ ፖሊስ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር? ኦሜድላ ደግሞ ሃይለኛ ሃይለኛ ልጆች ነበሩ፡፡ ያኔ ሃይልሻ (ኃይሌ ገ/ሥላሴ) ብሄራዊ ቡድን ገብቶ ነበር፡፡

“እባክህ ብቻዬን ሆኛለሁ፤ ቶሎ ወደ ብሄራዊ መጥተህ ተረዳድተን እንስራ” ይለኝ ነበር፡፡ ኦሜድላ እያለሁ ብሄራዊ ቡድን እንድገባ ትዕዛዙ በጎን ጥረት ጀመረ፡፡ እሱ ይጥራል፤ እኔ በውጤት እያሸነፍኩ እደግፈዋለሁ፡፡ ከዚያ ኢትዮጵያ ሻምፒዮን ውድድር ተደረገ፡፡ በአምስት ሺህ አንደኛ ወጣሁ፤ በ10 ሺህ ሁለተኛ ወጣሁ፡፡ 10ሺውን አሸንፌያለሁ ስል አንዱ አንገቱ ብቻ ቀድሞኝ ሁለተኛ አልወጣ መሰለሽ፡፡ ተበሳጭቼ ልሞት! እንደ ኃይሌና ፖልቴርጋት አገባብ ማለት ነው? ትክክል፡፡ እንደዚያ አይነት መሸነፍ ነው የተሸነፍኩት፡፡ ገርባ በትቻ የሚባል የአምቦ ውሃ ልጅ ነው ያሸነፈኝ፡፡ ከዚያ ብሄራዊ ቡድን ገባሁ፤ ይህ እንግዲህ በ1984 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጭ አገር የተወዳደርከው የት ነው? ውጤትህስ? ቦስተን የዓለም አገር አቋራጭ (Cross Country) ውድድር ላይ ተሳተፍኩና በጣም የሚያስቅ ውጤት አመጣሁ፡፡ 90ኛ ወጣሁ (በጣም እየሳቀ…) በረዶው እስከ ቅልጥምሽ ይደርሳል፡፡ እኔ በእንደዚህ አይነት አየር ላይ ተወዳድሬም እንዲህ አይነት የአየር ንብረት አይቼም አላውቅም፡፡ ሃይልሻም አልቀናውም፡፡ ወደኔው አካባቢ ነው ውጤቱ፡፡ ያኔጥሩ የነበረው ፊጣ ባይሳ ነው፡፡ ደራርቱም ጥሩ ነበረች፡፡ ሃይሌ ገ/ሥላሴ 100 ሺህ ብር እንደ ሸለመህ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን ነበር የሸለመህ? በፈረንጆቹ 1994 አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ከሃይልሻ ጋር አብረን ሮጠናል፤ ማናጀራችንም አንድ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ውድድር ሃይሌ ሪከርድ መስበር አላሰበም፡፡ እኔ አፌ ላይ መጣብኝና “ሃይልሻ አብሬህ ልሂድና ልወዳደር ሪከርድ እንሰብራከን አልኩት፡፡ ውድድሩ ሆላንድ ሄንግሎ ውስጥ ነበር፡፡

“ያንተ ውድድር ጣሊያን ሮም ውስጥ ነው፤ ሄንግሎ ውስጥ ሆቴልም የለህም አልተያዘልህም” አሉኝ፡፡ “እኔ ምንም አልፈልግም፤ ሆቴል ብቻ ያዙልኝ፤ ገንዘብም ምንም አልፈልግም፤ ግን ሪከርድ እንሰብራለን” አልኩት፡፡ ተሳካ ታዲያ? ሃይሌ ያኔ እንዳሁኑ ፈረንጅ አልሆነም፤ እንግሊዝኛ ትንሽ ትንሽ ይችል ነበር፤ ለማናጀሩ ሃሳቤን ነገረው፤ እኛ እንግሊዝኛ “Yes” እና “No” ብቻ ነበር የምንችለው፤ እርግጥ የሚናገሩት ይገባናል፤ መመለስ ላይ ነው ችግሩ (ሳ…ቅ) ሄድን ተወዳደርን፤ አሪፍ የቡድን ስራ ሰራን፤ ሪከርድ ሰበርን፡፡ ውድድሩ የ10 ሺህ ሜትር ነበር፤ ሃይሌ ሪከርድ ሰበረ፡፡ ብር የለም የተባልኩት ሰውዬ ማናጀሩ ተደስቶ 5ሺህ ዶላር ለቀቀብኝ፡፡ መቶ ሺህ ብር ተሰጠኝ ማለት ነው፡፡ የሚገርምሽ በሶስተኛው ቀን ሮም ላይ ውድድር አለኝ አላልኩሽም፡፡ ሮም ላይ እሱ ሆላንድ ሄንግሎ ያስመዘገበው ሪከርድ ተሰበረበት፤ ተናደድኩ፤ አበድኩ በቃ ምን ልበልሽ … ሪከርዱ ስለተሰበረ ነው? አዎ … እኔ ባለሁበት እንዴት ይሰበራል ብዬ ነዋ! እኔ ሶስተኛ ወጣሁ፤ የእኔ ውጤት በእለቱ በአምስት ሺህ ሜትር ከዓለም አራተኛ ሆኖ ተመዘገበ ሃይሌ በሩጫው አልተሳተፈም፡፡ እዚያው ሆላንድ ቀረ፤ ግን በቴሌቪዥን ውድድሩን ይመለከት ነበር፡፡ በጣም ተደሰተ፤ ሆላንድ ስገባ “ዝነኛ ሆንክ ኮንግራ” አለኝ፡፡ “በቃ ሌላ ጊዜ ሪከርዱን እንሰብራለን” አለኝ “እሺ እንሰብራለን” ተባብለን ወዲያው ስዊዘርላንድ ዙሪክ ላይ ሪከርድ ሰበርን፡፡ ተዓምር ሰራን፡፡ ከዚህ ሁሉ ድል በኋላ ነው ሃይልሽ 100ሺህ ብር የሰጠኝ፡፡ ጎልደን ሊግ ላይም ተወዳድረሃል ሲባል ሰምቻለሁ … በዚሁ በ1994 ዓ.ም ለአትላንታ ኦሎምፒክ ሚኒማ ለማምጣት ልሞክር ብዬ ነበር የገባሁት፡፡ እኔ፤ ዳንኤል ከመን፤ ፖልቱርጋርና ሌሎችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ትልቅ ደረጃ ላይ ያሉ ሯጮች ናቸው፤ በ10ሺህ ሜትር ነው፡፡

እኔ ለሚኒማ ነው የሮጥኩት፡፡ ሩጫው ተጀመረ፤ እጅብ ብለን እንሮጣለን፤ የሚመራውን እግር እግር ስከተል ስምንት መቶ ሜትር ላይ ስደርስ ተለይቼው ወጣሁ፡፡ ጎልደን ሊግ ትልቅ ውድድር ነው፤ ወርቅ ከሚያስገኙ ሰባት ውድድሮች አንዱ ጀርመን ስቱትጋርት ውስጥ አንዱን ማርቼሊስ ከሃይሌ ጋር የበላው እስማኤል ኩሪ የተባለ ሯጭም አለ፡፡ ዳንኤል ኮመንን ደረብኩት እና በዚህ ጎልደን ሊግ አንደኛ ወጣሁ፤ ጩኽት ቀጠለ… ምን ልበልሽ… በዚህ ውድድር አሸናፊነትህ የተነሳ በጥሩ ብር ከአዲዳስ ኩባንያም ጋር ለማስታወቂያ መፈራረምህን ሰምቻለሁ እውነት ነው? እውነት ነው፤ ከውድድሩም ከማናጀሬም ጥሩ ገንዘብ አግኝቼያለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር ለሶስት ዓመት ማስታወቂያ ተፈራርሜ ነበር፡፡ ጫማ ብትይ ልብስ እስካሁን የምለብሰው የአዲዳስን ምርቶች ነው፡፡ ምን ያህል ዶላር ነበር በዓመት የተፈራረምከው? እነሱ ምን ያህል እንክፈልህ አሉኝ፤ 25 ሺህ ዶላር በዓመት አልኳቸው፤ የኩባንያው ኃላፊ “Is it enough?” አለኝ “Yes it is enough” አልኩት በኋላ “It is no not enough” አለኝ “so how much” አልኩት “60 ሺህ ዶላር እንከፍላለን” አለኝ፡፡ “በሶስት ዓመት 180 ሺህ ዶላር ታገኛለህ፤ በዚህ ተስማምተህ ፈርም” አሉኝ፤ ፈረምኩ፡፡

ፈረንጅ አሪፍ ነው፤ ሌላው ቢሆን እኛ ምን አገባን ብለው በ25 ሺህ ያስፈርሙኝ ነበር፡፡ የሩጫ ጫማህን የሰቀልከው መቼ ነው? ማራቶን ፓሪስ ላይ ከሮጥኩ በኋላ 8ኛ ወጣሁ፡፡ በእርግጥ የመጀመሪዬ እንደመሆኑ በዚያው መቀጠል ነበረብኝ ግን ብዙ ዓመት ስለሮጥኩ ከአገር ቤት ጀምሮ ቆይ ትንሽ ልረፍ አልኩኝ፡፡ በቃ በዛው አቆምኩኝ፤ ወቅቱ በፈረንጅ 2002 ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ብዙ አትሌቶች እና ታዋቂ ሰዎች ስኬት ላይ ሲደርሱ ህንፃም ሆቴልም የሚሰሩት በትውልድ አካባቢያቸው ነው፡፡ አንተ ሆቴል የከፈትከው ዱከም ከተማ ነው እንዴት ነው? አንድ ጓደኛ አለኝ ብርሃኔ ሚደቅሳ ይባላል፤ የሆለታ ልጅ ነው፤ ብዙ ነገሮችን የሚያማክረኝ እሱ ነበር፤ ከውድድር ስመለስ ላዝናናህ አየር ቀይር ብሎኝ ዱከም ይዞኝ መጣ፡፡ ድሮም አካባቢውን እወደው ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ሃሳቤ አዲስ አበባ ውስጥ ክትፎ ቤት ለመክፈት ነበር፡፡ ብርሃኑ ያልኩሽ ጓደኛዬ ለምን እዚህ (ዱከም) ሆቴል አትከፍትም አለኝ፡፡ በል ቶሎ ደላላ ፈልግና ቦታ ይፈለግ አልኩት፤ መጀመሪያ ቤት ሂድና ከባለቤትህ ጋር ተማከር አለኝ፤ ግዴለም አሳውቃታለሁ ትስማማለች አልኩት፡፡ በኋላ አሁን ሆቴሉ ያረፈበትን ቦታ ገዛሁ፡፡ ለካ ያኔ በነፃ ሁሉ ማግኘት እችል ነበር፤ ቦታ እየገዛሁ እየገዛሁ አስፋፋሁ እስኪ ስለቤተሰብህ ንገረኝ? ጥሩ ትዳርና ቤተሰብ አለኝ፡፡ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ የመጀመሪያው ልጄ የ17 ዓመት ልጅና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ አንደኛው ወደ ስምንት አልፏል፤ ሴትም ልጅ አለችኝ፤ የመጨረሻው ህፃን የሁለት ዓመት ነው፤ ልጆቼ ጥሩና ጨዋ ናቸው፡፡

አሁን ጤናህ እንዴት ነው? ጤናዬ ጥሩ ነው፤ ደስተኛ ሆኜ ነው የምኖረው፡፡ ለስፖርት ፍቅር ላላቸው የአቅሜን እደጉማለሁ፡፡ መርዳት ያለብኝን እረዳለሁ፡፡ ቢዝነስ ላይ ነኝ፤ በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው የምኖረው፡፡ የእሬቻ በዓል ከደብረዘይት ቀጥሎ አንተ ሆቴል ውስጥ በድምቀት ይከበራል ይባላል፡፡ እውነት ነው? የእሬቻ በዓል ጊዜ መጥተሸ ብታይ ጉድ ነው የምትይው፡፡ አካባቢው በሰው ይሞላል፤ የሙዚቃ ባንድ አለ፤ የከተማው ሰው ይመጣል፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የገዳ ስርዓት መሪዎች ሳይቀሩ ይታደማሉ፡፡ በልዩ ድምቀት ይከበራል፡፡ በቀጣይም የመስቀል በዓል በዋለ በቀጣዩ እሁድ ይካሄዳል፤ በጣም አስደሳች በዓል ነው፡፡ አባ ገዳ ሆነህ ልትሾም ነው ሲባል ሰምቻለሁ ሰምተሽ ይሆናል፡፡ እሱን ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ከስርዓቱ መሪዎች ብትጠይቂ ይሻላል፡፡ አሁን እሱን ለመናገር ጊዜው አይደለም፤ የሚሆነውን አብረን እናየዋለን፡፡ በተረፈ በሁሉ ነገር ደግፎ አይዞህ ብሎ መንገዱን ምቹና ቀና ላደረገልኝ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ ውብሸት ታላቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፤ ዘመኑ ይባረክ እላለሁ፡፡ ሻለቃ ሃይሌ ገ/ሥላሴንም አመሰግናለሁ፤ ሃይልሻ ጠንካራና ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው፡፡ በተረፈ ለሁላችንም እድሜና ጤና ይስጠን፡፡ አገራችንን ከክፉ ይጠብቅልን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 4185 times