Saturday, 30 August 2014 10:22

የእንግሊዙ ጠ/ሚ አገሬን በሞባይሌ ማስተዳደር እችላለሁ አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ አገሬን ብላክቤሪ በተባለው ዘመናዊ ስማርት ፎን የሞባይል ቀፎዬ ብቻ በወጉ ማስተዳደር እችላለሁ ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ ዴቪድ ካሜሩን ባሉበት ቦታ ሆነው አገሪቱን የማስተዳደር ስራቸውን በሞባይላቸው አማካይነት በአግባቡ ማከናወን እንደሚችሉ መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፤ በየትኛውም የአለም ጫፍ ላይ ብሆን ብላክቤሪ ሞባይሌን ከእጄ ስለማላወጣት፣ በእሷ አማካይነት ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ መስራት የሚገባኝን ነገር ሁሉ ሳላጓድል ማከናወን አያቅተኝም ማለታቸውን አስረድቷል፡፡ ብላክቤሪ ስማርት ፎን መረጃን በማስተላለፍ ረገድ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ የሞባይል ቀፎው የዴቪድ ካሜሩን ቀዳሚ ምርጫ መሆኑን የጠቆመው ዘ ጋርዲያን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብላክቤሪ የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጽዋል፡፡ “ካለፉት ጥቂት አመታት አንስቼ፣ የበአል ቀናትን በመሳሰሉ ስራ ላይ በማልገኝባቸው ጊዜያት አገር የማስተዳደር ስራዬን ሳከናውን የቆየሁት በዚህች ዘመናዊ ብላክቤሪ የሞባይል ቀፎዬ ነው” በማለት በግልጽ ተናግረዋል ብሏል ዘገባው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት አመታት በፊት በአፕል አይፓዶች ላይ በሚጫኑ አፕሊኬሽኖች በመጠቀም የአገሪቱን የኢኮኖሚ መረጃ ለማወቅ ሙከራ ማድረጋቸውንና በዚህም፣ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት፣ የባንኮችን የብድር አሰጣጥ አሰራር፣ የስራ ዕድሎችን፣ የንብረት ዋጋ ተመኖችን፣ የምርጫ ውጤቶችን የመሳሰሉ መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት እንደቻሉ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ቴክኖሎጂ ያለውን እገዛ ማጤናቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1835 times