Saturday, 30 August 2014 10:35

የአዲስ አበባን ጎርፍ ለመከላከል እየተጠና ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

          በዘንድሮ ክረምት የአዲስ አበባ ዋና ዋና የአስፓልት መንገዶች በከፍተኛ ጎርፍ መጥለቅለቃቸውን ተከትሎ ሲሆን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የችግሩን መንስኤና መፍትሄ እያጠና ሲሆን በመጪው ዓመት ክረምት መፍትሄ ይበጅለታል ብሏል፡፡
መንገዶቹን በበላይነት የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፍቃዱ ሃይሌ፤ በክረምቱ ወቅት እያጋጠመ ያለው የጎርፍ ችግር በአስፓልቱ ላይ የሚፈሰውን ውሃ ተቀብለው ወደ ቱቦ የሚያስገቡ ቀዳዳዎች (ማንሆሎች) ክፍተታቸው በትክክል ውሃውን ማስተናገድ የሚችል ሆኖ ባለመሰራቱ የተፈጠሩ እንደሆነ ተገንዝበናል፤ በተለይ ቁልቁለታማ መንገዶች ላይ ለፍሳሽ ማስገቢያው የተዘጋጁት ቀዳዳዎች ውሃውን በአግባቡ እየተቀበሉ አይደለም ብለዋል፡፡
ከተማዋ ተራራማ እንደመሆኗ ዳገታማ ከሆኑ ቦታዎች ወደ መንገዶች የሚፈሰውን ጎርፍ መንገዱ ላይ ከመድረሱ በፊት አቅጣጫ ሊያስለውጥ የሚችል ነገር ስለሌለ ቀጥታ አስፓልቱ ላይ መፍሰሱም ችግሩን በዋናነት አባብሶታል ያሉት ኢ/ር ፍቃዱ፤ በየመንገዱ የተቀበሩት ጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ግን በከተማዋ የሚዘንበውንና በአስፓልቱ ላይ የሚፈሰውን ውሃ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡
የክረምቱን የመንገድ ላይ ጎርፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንደመከረበት የጠቆሙት ኃላፊው ፤ዲዛይን ሲሰራ መንገዱ ላይ ያለውን ውሃ ብቻ ነው ወይንስ ከዳገታማ ቦታዎች የሚመጣውንም መቀበል የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን? በሚለው ላይ የሙያ አለመግባባት መኖሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ዲዛይን የተደረጉትን የጎርፍ መስመሮች እንደገና በመመልከት ማስተካከያ ለማድረግ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመጪው ዓመት በክረምት ጎርፍ ዙሪያ ሁለት ዋነኛ ተግባሮችን ለማከናወን ያቀደ ሲሆን አንደኛው በአማካሪ መሃንዲስ አማካኝነት አዲስ የፍሳሽ ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ነው ያሉት ኃላፊው፤ ሌላው የውሃዎቹ ተፋሰስ እንዴት መሆን አለበት የሚለው ን ማጥናት እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህ ተግባርም አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ፣ ጎርፍ የሚያይልባቸውን ቦታዎች የመለየት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በበጋ ወራትም በጥናቱ መሰረት የማስተካከያ ስራዎች እንደሚሰሩ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የመንገድ ላይ ውሃ መጥለቅለቅ በሌላውም ዓለም የተለመደ እንደሆነ የጠቀሱት ኢ/ር ፍቃደ፤ ልዩነቱ የተጥለቀለቀው ውሃ በምን ያህል ፍጥነት ከመንገዱ ላይ ይወገዳል የሚለው ላይ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮው ክረምት ቦሌን ጨምሮ አዳዲስ በተሰሩ የአስፋልት መንገዶች የጐርፍ መጥለቅለቅ መከሰቱ ይታወቃል፡፡  

Read 1485 times