Saturday, 30 August 2014 11:02

“ኪነጥበብ”- በአማርኛ ስነ ግጥም

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(30 votes)

ኪነጥበብ (Art) የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ ነው፡፡ ዲሲፕሊኑ እጅጉን ሰፊ የሆነና በውስጡም ብዙ ሙያዎችን (እንደ ሥዕል፣ ድርሰት፣ ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ቅርጻቅርጽ፣ ፎቶግራፍ፣ የፊልም ጥበብ…) የሚያቅፍ ሲሆን በርካታ ንድፈ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሙያዎች በመውሰድ ራሱን የሚያበለጽግ መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ መስኩ ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው፡፡ ኪነጥበብ በታሪክ፣ በርዕዮተ ዓለሞች መለዋወጥና በክስተቶች ውስጥ ትኩረቱና አገልግሎቱ ተለዋውጦአል፤ ይለዋወጥማል፡፡

           ዛሬ ስነ ጽሑፍን ማደሪያ አድርገን አቢይ ዘርፉ ስለሆነው ስነ ግጥም እንድናወራ ወደድኩ፡፡ የጽሑፌ ጉዳይ የአማርኛ ስነ ግጥም፣ ትኩረቱም ኪነጥበብን ጭብጣቸው (Theme) ያደረጉ “የታተሙ ግጥሞች” ናቸው፡፡ እናም መነሻዬን የ1950ዎቹ መግቢያ፣ መድረሻዬንም ያለንበትን አሰርት አድርጌ በየዘመኑ በተጻፉት ግጥሞች ላይ የኪነጥበብ ጭብጥ ምን ይመስላል? ገጣሚያኑስ ለኪነጥበብ የነበራቸው እይታ ምንድን ነው? የሚለውን እጅጉን ቁንጽል በሆነ ወፍ በረር ዳሰሳ ላስቃኝ፡፡ ጭብጥ (Theme) በአንድ ኪናዊ ሥራ ውስጥ አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ያለ ጭብጥ የተከየነ ጥበባዊ ሥራ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በግጥምም ውስጥ ጭብጥ ከግጥሙ ማዕከላዊ ሀሳብ (idea) ይሰርጻል፡፡ የአንድን ኪናዊ ሥራ ጭብጥ ማግኘት ብዙውን ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም የግጥሙን ማዕከላዊ/ገዢ ሀሳብ በመረዳት ጭብጡ ይሄ ነው ለማለት ጥልቅ ንባብ፣ የቋንቋና የቃላት እውቀት አለፍ ሲልም የሌሎች ሙያዎች መጠነኛ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ “የግጥም ሥራዎችን እንደሚያነሱት አቢይ ጭብጥ በልዩ ልዩ ጭብጣዊ ዘውጎች ማዋገን” ይቻላል፡፡ ይህም ጭብጥን በቅጡ ለመረዳት የተሻለ መንገድ እንደሆነ አጥኚዎች ይገልጻሉ፡፡

ኪነጥበብ (Art) የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ ነው፡፡ ዲሲፕሊኑ እጅጉን ሰፊ የሆነና በውስጡም ብዙ ሙያዎችን (እንደ ሥዕል፣ ድርሰት፣ ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ቅርጻቅርጽ፣ ፎቶግራፍ፣ የፊልም ጥበብ…) የሚያቅፍ ሲሆን በርካታ ንድፈ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሙያዎች በመውሰድ ራሱን የሚያበለጽግ መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ መስኩ ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው፡፡ ኪነጥበብ በታሪክ፣ በርዕዮተ ዓለሞች መለዋወጥና በክስተቶች ውስጥ ትኩረቱና አገልግሎቱ ተለዋውጦአል፤ ይለዋወጥማል፡፡ ከዚሁ ከኪነጥበብ የሚወለደው ስነ ጽሑፍም ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦችንና ንድፈ ሀሳቦችን ወስዶ በማልመድ የዳበረ ጥበብ ነው፡፡ የእሱ “ቀዳሚው ልጅ” የሆነው ስነ ግጥምም እንዲሁ፡፡ እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩት ጉዳዬ ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ ግጥሞች ናቸው፡፡ ትኩረቴም የኪነጥበብ አንጋፋ ልጅ የሆነው ስነ ግጥም፣ “አባቱን” ኪነጥበብን ጭብጡ ሲያደርገው ምን ይመስላል? የሚለው ላይ ነው፡፡ 1950ዎቹ በኢትዮጵያ በየመስኩ በርካታ አዳዲስ ነገሮች የተጀመሩበት፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዘመናዊነት እርምጃን የጀመረችበትና ነባሮቹ አስተሳሰቦች መዘመን የያዙበት አሰርት መሆኑን በርካታ የታሪክ ፀሐፊያን ይገልጻሉ፡፡ ይህም የለውጥ እንቅስቃሴ በኪነጥበቡም ላይ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡

ስነ ግጥምን ስናነሳ በዚህ አሰርት ራሱን ኪነጥበብን የግጥሞቻቸው አቢይ ጭብጥ ያደረጉ የአራት ገጣሚያንን አራት ግጥሞች እናገኛለን፡፡ ቀዳሚው ግጥም የገብረ ክርስቶስ ደስታ “ከበሮ” ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ጭብጥ አንዱ የኪነጥበብ ዘርፍ የሆነው ሙዚቃ ነው፡፡ ከሙዚቃም የከበሮ ድምጽ፡፡ የግጥሙ ተራኪ የከበሮ ድምጽ ኃያል የሆነ ግርማ እንዳለው በመግለጽ ያገዝፈዋል፡፡ በእሱም ላይ የሚያሳድርበትን ስሜት ይነግረናል፡፡ እንዲህ እያለ፡ …ይቀሰቅሰኛል ጩኸቱን ስሰማ በሰውነቴ ላይ ይፈጥራል መሸበር ያቅበዘብዘኛል… ሌላው የዚህ አሰርት ግጥም ጥበብን ሀሳቡ ያደረገው “ሊቅና ቧልተኛ” የተባለው የመንግስቱ ለማ ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ ገጣሚው ለኪነጥበብ ያለውን ክብር ያሳየበት ነው፡፡ የግጥሙ ማዕከላዊ ሀሳብ ጠቢብና አዋቂ መሆን እንዲሁም ለጥበብ መትጋት ነው፡፡ በዚህም መሀይም ሆኖ ከመከበርና ከመበልጸግ ይልቅ አዋቂና ጠቢብ ሆኖ መቸገርና መውደቅ እንደሚሻል ግጥሙ ያወሳል፡፡ በዚህ ዘመን የግጥሞቻቸውን አቢይ ጭብጥ ኪነጥበብ ካደረጉ ገጣሚያን መካከል ከበደ ሚካኤል በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከበደ “ለሁሉም ጊዜ አለው” በሚለው ግጥማቸው ይህንኑ ጉዳይ ጭብጥ አድርገዋል፡፡ የግጥሙ አቢይ ጉዳይ መጠየቅ ነው፡፡

ግጥሙ ታላቅ ጠቢብ የሚባለውን ሰሎሞንን ጊዜና ቦታ ሳይገታው “ሞት የሚሞትበት ግዜ መቼ ነው?” በማለት ይጠይቃል፡፡ በግጥሙ የሰው ልጅ ታላቅ “እዳ” የሆነው “ሞት” ራሱ የሚሞትበት ጊዜ ይጠየቃል፡፡ ጥያቄው የ“ነገረ ህላዌ” (የፍልስፍና) ጥያቄ ነው፡፡ የግጥሙ ሀሳብ በርካታ ፍቺዎችን ያዘምራል! እጅጉን “ተራማጅ” እንደነበረ የሚነገርለት ዮሐንስ አድማሱም ጭብጡን የግጥማቸው ጉዳይ ካደረጉ የዘመኑ ገጣሚያን አንዱ ነው፡፡ ዮሐንስ “ስንኞች” በሚል ርዕስ በጻፈው ግጥሙ በጊዜው የነበረውን ማህበረሰብ አስተሳሰብና አኗኗር ጠይቆአል፡፡ ግጥሙ ታላቅ ሀሳብን ያዘለ ጥያቄ ነው፡፡ የዘመኑ ማህበረሰብ ላይ የተሰነዘረ ጥያቄ፡፡ ግጥሙ የሚከተለውን በማለት ነው የሚቋጨው፡፡ …እራስን ረስቶ ከራስ ለማምለጡ ከራስ ለመብረር፣ ቁም ነገሩን ጥሎ፣ በከመ ፈቃድ ኑሮ እንጂ መስከር? በአሰርቱ ተገኝተው (ልብ በሉ “ተገኝተው” ነው ያልኩት) የተቃኙት እነዚህ አራት ግጥሞች ኪነጥበብን አቢይ ጭብጣቸው ያደረጉ ናቸው፡፡ ገጣሚያኑ ለጭብጦቹ የነበራቸውን አመለካከት የግጥሞቻቸው ሀሳብ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፡፡

በዚህም ለኪነጥበብ ያላቸውን ክብርና ቦታ በውብ አቀራረብ አሳይተዋል፡፡ “በ1950ዎቹ ላቅ ወዳለ ኪነጥበባዊ ደረጃ የተሸጋገረው የአማርኛ ስነ ግጥም፤ በ1960ዎቹ በመጡት ገጣሚያን የመጠንና ዓይነት ለውጥ” እንዳሳየ ብርሃኑ ዘሪሁን “የአማርኛ ስነግጥም፤ አንዳንድ ነጥቦች” (2001) በተባለው ጥናታቸው ይገልጻሉ፡፡ 1960ዎቹ በሀገራችን ታላላቅ ገጣሚያን የተነሱበትና እነዚህም አዳዲስ ቅርፅንና ጭብጥን ያስተዋወቁበት ዘመን ነው፡፡ በአሰርቱ ኪነጥበብን የግጥማቸው ጭብጥ ካደረጉ ገጣሚያን መካከል ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እና ደበበ ሰይፉ ይጠቀሳሉ፡፡ “ሙዚቃ” የተባለው የሰይፉ ግጥም ጭብጡ የኪነጥበብ ዘርፍ የሆነው ሙዚቃ ነው፡፡ ግጥሙ እጅጉን ሀሳባዊ ነው፡፡ ሙዚቃን “ሙዚቃ” ብሎ በሦስት ፊደል መግለጽ እንደማይቻል፣ ይልቁንም ሙዚቃ ከፊደልና ከቃል በላይ መሆኑን በማውሳት፣ ሊገልጹትና ሊወስኑት የማይችሉት ታላቅ ኃይል እንደሆነ ያስረግጣል፡፡ በግጥሙ “ሙዚቃ” ከልብ የሚፈልቅ ቋንቋ፣ ንግግርና እጅጉን ከፍ ያለ ሀሳብ ነው፡፡ ከፍታውም ከቃልና ከስሜት በላይ ነው! ሌላው ተወሺ ግጥም የደበበ ሰይፉ “ለአንዲት ቅጽበት ብቻ” ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ጉዳይ ሙዚቃና ቅኔ ናቸው፡፡ በግጥሙ የሙዚቃና ቅኔ ልዕልና ተንጸባርቆአል፡፡ ለግጥሙ ተራኪ ሙዚቃና ቅኔ ከህይወት ግሳንግስ መሸሸጊያ፣ ከማዕበል መከለያ ናቸው፡፡ “ህሊናዬን፣ ቀልቤን፣ አካሌን” ለአንዲት ቅጽበት ብሰጣችሁና ብታድሱኝ በማለት አግዝፏቸዋል፤ ከፍ ከፍም አድርጎአቸዋል! 1960ዎቹን ይወክላሉ ያልናቸውን ግጥሞች በመመልከት ለዘመኑ ገጣሚያን ኪነጥበብ እጅጉን ከፍ ያለ ክቡር ጉዳይ እንደነበር መገንዘብ እንችላለን፡፡

60ዎቹን ተሰናብተን ወደ 70ዎቹ እንቅዘፍ፡፡ እንደ ቀዳሚዎቹ አሰርት ሁሉ በ1970ዎቹም ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ በርካታ ግጥሞች ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በከበደች ተክለአብ የተጻፈው “ጣት ወዳጁን ሲያጣ” የተሰኘው ግጥም ተጠቃሽ ነው፡፡ በግጥሙ ብዕር ታላቅ የሰው ልጅ “ፍላተ ስሜት” (ሀዘንም ቢሉ ደስታ) መተንፈሻ፣ ማቅለሚያ እንዲሁም መቀረሻ ነው፡፡ ግጥሙ ብዕርን ተናጋሪ፤ ሥፍራ የማይገታው በራሪ፤ አሮጌውን ንዶ አዲስ ስርዓትን ተካይ ነው ይለዋል፡፡ በግጥሙ ብዕር የክፉና የጭንቅ ጊዜ አወያይ፣ ቁጭትን መተንፈሻ ነው፡፡ ገጣሚዋ በሶማሊያ ወታደራዊ እስር ቤት ሆና የጻፈችው ይህ ግጥም፣ በእስር ቤቱ ያሳለፈችውን መራራ የመከራ ህይወት በብዕሯ እንዳቀለለችው ይጠቁማል፡፡ ገጣሚዋ በብዕሯ መሸበቧን አምልጣለች፤ በግጥሞቿ ለልቧ እረፍት ለስሜቷም ሀሴትን ሰጥታለች፡፡ ደበበ ሰይፉን በዚህም ዘመን ጭብጡን የግጥሙ ጉዳይ አድርጎ እናገኘዋለን- “ከያኒና ኪነት” በሚለው ግጥሙ፡፡ በግጥሙ የከያኒ እና የኪነት ምንነትና ህላዌ ተብሰልስሎአል፡፡ የግጥሙ ጭብጥ ገጣሚው በወቅቱ ይከተለው የነበረውን ርዕዮተ ዓለም የሚታገግ ይመስላል፡፡ ከያኒ ብሩህ እይታ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ሊኖረው እንጂ ጨለምተኛ ሊሆን እንደማይገባ ያወሳል፡፡ ከያኒው ጨለምተኛ፣ ኮናኝና ምሬተኛ ከሆነ የራሱ የከያኒውም ሆነ የኪነት ሞት እውነት እንደሚሆን ግጥሙ ይሞግታል፡፡ ለደበበ ከያኒ ብሩህ እይታ ያለውና ተስፈኛ፣ ኪነቱም ይህንኑ የሚያሳይ ብርሃንና መሪ ነው፡፡

ይህን ዘመን ተሻግረን ወደ 80ዎቹ ብናልፍም በአሰርቱ ኪነጥበብን ጭብጥ አድርገው የተጻፉ ግጥሞች (በኔ አሰሳ ልክ) አልተገኙም፡፡ በትጋት ልፈልግ ቃል ገብቼ ለዛሬው ወደ ቀጣዩ አሰርት እንለፍ፡፡ በ1990ዎቹ ኪነጥበብን የግጥሞቻቸው ጭብጥ አድርገው የጻፉ በርካታ ገጣሚያንን እናገኛለን፡፡ ከእነዚህ መካከል ነቢይ መኮንን፣ በእውቀቱ ስዩም እና ቸርነት ወልደ ገብርኤልን እናንሳ፡፡ (አላዳላሁም! ግጥሞቻቸው ጭብጡን ይወክላሉ ያልኩትን ነው የመረጥኩት፡፡) ነቢይ “ዕውነት ማነው ጅሉ” በሚለው ግጥሙ የገጣሚን ሰብዕና አግዝፎአል፡፡ ግጥሙ ጠያቂ መስሎ መላሽ ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ሀሳብ ገጣሚ “ጅል” እንዳልሆነ፣ “ጅል” ነው ካልንም “ጅል” ሁሉ ግን ገጣሚ እንዳልሆነ አበክሮ ይገልጻል፡፡ በዚህም ገጣሚ “ጅል” ቢመስልም ጠቢብ፣ ተላላ ቢመስልም ትሁትና ታላቅ ሰብዕና ያለው መሆኑን ይሞግታል፡፡ ከያኒው በግጥሙ ለገጣሚ ያለውን አመለካከት አንጸባርቆአል፡፡ ቀጣዮቹ የግጥሙ የመጨረሻ ስንኞች የግጥሙን ጭብጥ የሚነግሩ ናቸው፡፡ …እያንዳንዱ ጅል ግን፣ ገጣሚ እንዳልሆነ ይሄው ባንተ አየሁት፣ ባንተው ተመዘነ፡፡

የበእውቀቱ ስዩም “ሰው አለ” የተሰኘው ግጥም ሞጋች ነው፡፡ ገጣሚው በዚህ ግጥሙ የፈላስፋው የዲዮጋንን ተጠቃሽ “ሀሳብ” በሀሳብ አፍርሶአል፡፡ ማፍረሻው በአመክንዮ የተመላ ነው፡፡ ፈላስፋው ዲዮጋን “ሰው እፈልጋለሁ” ብሎ፣ በፀሐይ ብርሃን ፋኖስ ይዞ ገበያ መሀል መንከራተቱን ገጣሚው “የምን ሰው ትፈልጋለህ? ሰውን ትፈልግ ዘንድ የያዝከው ፋኖስ እኮ ሰው የሰራው ነው፡፡” በማለት የዲዮጋንን አለማስተዋል ያጋልጣል፡፡ በዚህም ትክክል ነው፤ ሃቅ ነው፤ ብለን በጅምላ የተቀበልነው ሀሳብና እውቀት ሁሉ ከጥያቄ እንደማያመልጥ አሳይቶአል፡፡ የቸርነት ወልደ ገብርኤልን “ጥበብ” የተሰኘ ግጥም አንስተን ዘመኑን እንሰናበት፡፡ ገጣሚው ጥበብ የነበረችና የምትኖር- ዘላለማዊ፤ ህያው፡፡ ስፍራ የማይወስናት “ምልዑ በኩለሄ” ነች ይለናል፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡ ሀሳቡን ጥቅሟ ላይ በማኖር፡ …ሀይልሽን ያልተረዳ- የሁሉነትሽን የሳተ- መለኮታዊነትሽን ያልተገነዘበ፣ እሱ አበደ- እሱ ነተበ- እሱ ጠበበ በማለት የሰው ልጅ ያለ ጥበብ ከንቱና ህልውናውን ያጣ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህም የሰው ልጅ ጥበብን አጥብቆ ሊሻ፣ ሊያሳድድና ገንዘቡ ሊያደርጋት እንደሚገባ ያወሳል፡፡

እነዚህን ግጥሞች ስንመለከት፤ በአሰርቱ በጻፉ ገጣሚያን እይታ ኪነጥበብ እጅጉን ታላቅ ጉዳይ እንደነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ ከ2001 እስከ 2006 ዓ.ም ያሉትን ስድስት ዓመታት ስንቃኝ፤ በእነዚህ ዓመታት ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ በርካታ ግጥሞች ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሰሎሞን ሞገስን “ቋንቋ’ኮ ቁምጣ ነው” የተባለ ግጥም እናስቀድም፡፡ ግጥሙ የስነ ፅሑፍ ዋናው ጉዳይ (መገለጫ/መሳሪያ) የሆነውን የቋንቋን ቀርነት (ምልዑ ያለመሆን) ያወሳ ነው፡፡ ገጣሚው በግጥሙ ቋንቋ ሁሉን ይገልጻል፤ ሁሉን ያስረዳል፤ በማለት ቢያስብም ቋንቋን “ቀር” ሆኖ እንዳገኘው በቁጭት ይገልጻል፡፡ የግጥሙ ጭብጥ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ጥናት ውስጥ የሚታመነውን የመስኩን እይታ የታገገ ነው፡፡ የሰው ልጅ “ታላቅ ሀብት” የሆነው ቋንቋ፣ ምሉዕነቱ በግጥሙ ጥያቄ ወድቆበታል፡፡ የግጥሙ ገዢ ሀሳብ የቋንቋን ቀርነት ማውሳት፣ መግለጽ፣ መንገር ነው፡፡ ሌላው ግጥም የኢሰማዕከ ወርቁ “አራሚ” ነው፡፡ ግጥሙ ሀያሲን በጎ አመለካከት የሌለው፣ ከዲሲፕሊኑ የወጣና ሙያውን ያጎደፈ፤ ነቃፊና አራሚ ነው፤ በማለት ይተቸዋል፡፡ ሀያሲ ከትናንት እስከ አሁን ቢኖርም ያው፣ ያልተሻሻለና ያልተለወጠ፤ ባረም አመካኝቶ ሰብልን የሚነቅል፤ በግድፈት አመካኝቶ መልካሙን ቃልና ሀሳብ የሚነቅፍ እንደሆነ ግጥሙ ይገልጻል፡፡ የሰሎሞን ሽፈራውን “ጥበብ ፈሩን ሲስት” የተሰኘ ግጥም አንስተን ቅኝታችንን እናብቃ፡፡ የሰሎሞን ግጥም ማዕከላዊ ሀሳብ ለጥበብ መቆጨት ነው፡፡ በግጥሙ ጥበብ በዚህ ዘመን ማደፏና መጉደፏ፣ ለመልካም ነገር ከመዋሏ ይልቅ ለክፋት መዋሏ፤ ዘመኑም ጥበብ ያለው ክፋትን፣ ብልጣብልጥነትን እና መሰሪነትን መሆኑን ተወስቶአል፡፡ የግጥሙ ተራኪ ይህንን “እድፈት” በምሬት ሲተች ይስተዋላል፡፡

ይህ ዘመን በርካታ ገጣሚያን ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ ግጥሞችን የጻፉበት ነው፡፡ ገጣሚያኑ በግጥሞቻቸው ያንሸራሸሯቸውን ሀሳቦች ጠቅለን ስንመለከት ኪነጥበቡ “ገበያ ተኮርና ጥልቀት የለሽ” በመሆኑ የተቆጩበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በስድስቱም አሰርት በተጻፉ ግጥሞች ውስጥ ኪነጥበብ እጅግ ክቡር፣ ታላቅ፣ ጠቃሚ እና ገናን ጉዳይ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ገጣሚያኑም ለኪነጥበብ እጅጉን ቀናኢና ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡ “ላለፉት እረፍት፤ ላሉት ህይወት ይስጥልን!” አንባቢዎቼን አንድ ነገር ላሳስብ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት፣ በተጠቀሰው የዘመን ወሰን ውስጥ ኪነጥበብን ጭብጣቸው አድርገው የተጻፉ ግጥሞች እነዚህ ብቻ ናቸው የሚል እምነትም ድፍረትም የለኝም፡፡ በተለያየ ምክንያት በእጄ ያልገቡና ያልተመለከትኳቸው ግጥሞች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ይህንን ቅኝት እየጻፍኩ ውስጤ እጅጉን የተብሰለሰለበትን ሀሳብ ሰንዝሬ ልሰናበት፡፡ ምናልባት ለቀጣይ ውይይት መነሻ ሊሆነን ይችላል፡ ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉት አብዛኞቹ ግጥሞች (በተለይ የቅርቦቹ) ኪነጥበብ ውሉን እንደሳተ፣ ጥልቀቱን እንዳጣ፣ ከራሱ እንደተፋታ… የሚሞግቱ ናቸው፡፡ እናም ጠየቅሁ፡፡ የኪነጥበብ ውሉ ምንድን ነው? ጥልቀቱስ እስከ የት ነው? መልካም ሰንበት!!

Read 15409 times