Saturday, 30 August 2014 11:13

የጆሲ የአዲስ ዓመት ስጦታ -“መቼ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

         አልበም ሰርቶ ማጠናቀቅ አምጦ ልጅ የመውለድ ያህል ከባድ ነው ይባላል፡፡ የዚህ አልበም ምጥና ውልደት እንዴት ነበር? እውነት ነው፤ በጣም አስቸጋሪ ሂደትን ማለፍ ይጠይቃል፡፡ እኔም ይህን አልበም እዚህ ለማድረስ ላለፉት ስድስት ዓመታት ስለፋ ቆይቻለሁ፡፡ አሜሪካ ለኮንሰርት በቆየሁበትም ሆነ ለሌላ ስራ ውጭ በነበርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ከአልበም ስራው ላይ አልተለየሁም፡፡

የተለያዩ የአሜሪካ ስቱዲዮዎች ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ለምሳሌ እንደ ሳንዲያጎ፣ ዲሲና ኒውዮርክ በሚገኙ ስቱዲዮዎች ገብቼ ነበር፡፡ የአልበሙ ስራ የተጀመረው አሜሪካ ነው፤ እዚያው እያለሁ ዜማዎችን እሰራ ነበር፡፡ እናም የሙዚቃው ሂደት ውስጥ እጅግ ከባድ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን አልፌያለሁ፡፡ ብዙ ወጪ፣ ብዙ ድካምና ጊዜ ፈጅቷል፡፡ እስቲ በጣም ፈታኝ የሆኑብህን ነገሮች ግለፅልኝ? እኛ አገር የድምፃዊያን ፈተና በአብዛኛው የሙዚቀኞች ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭውን አገር ልምድ ብነግርሽ፣ አንድ አልበም ለመስራት ከኩባንያ ጋር ነው ስምምነት የምታደርጊው፡፡ የምትከፍይውም በሰዓት ስለሆነ ጉዳዩን ዋና ስራ አድርገው ነው የሚይዙት፡፡ እዚህ አገር ያሉ ሙዚቀኞችን ስትመለከቺ፣ አንቺ ዛሬ ይህንን ስራ እሰራለሁ፤በዚህ ሰዓት ይሄኛውን እጨርሳለሁ ብለሽ እነሱ ጋር ስትሄጂ “ዛሬ ሙዴ አልመጣም” ይሉሻል፡፡ ሙዳቸው ካልመጣ አይሰሩልሽም፡፡ እዚህ አገር “ሙድ” የሚባል እንደ ባህል የተያዘ ጉዳይ አለ፡፡

በዚህ የተነሳ ያሰብሽውን ሳታሳኪ፣ ያቀድሽውንም ሰዓት ሳትጠቀሚበት ብክነት ውስጥ ትገቢያለሽ፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ድምፃዊያን ከፍተኛ ፈተናና ራስ ምታት ነው፡፡ ድምፃዊያንን ብታነጋግሪ ይህንኑ ይነግሩሻል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲያማርሩ ሰምተሽም ይሆናል፡፡ ይሄ ግን በሁሉም ሙዚቀኞች ዘንድ የሚስተዋል ነው ማለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ይሄ “ሙድ” የሚሉት ጉዳይ፣ አንዳንዴ ትክክል ነው ትያለሽ፡፡ በጣም አሪፍ ስራ የሚሰሩልሽ “ሙዳቸው” በመጣ ሰዓት ነው፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃ መዝናኛ እንደመሆኑ መጠን የሙዚቀኞቹ ስሜት ወሳኝ ነው፤ ነገር ግን ለድምፃውያኑ ፈታኝ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ያነሳሁት ሲበዛ ስለሚከብድ ነው እንጂ ከ“ሙድ” ውጭ ሆነው ይስሩ ማለቴ አይደለም፡፡ በገንዘብ ረገድ እግዚአብሔር ይመስገን ተቸግሬ አላውቅም፤ በተጓዳኝ ሌሎች ስራዎችንና ኮንሰርቶችን ስለምሰራ፣በገንዘብ እጥረት የአልበሙ ስራ ተስተጓግሎብኝ አያውቅም፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈሽ ስራውን ካጠናቀቅሽ በኋላ ፕሮዱዩሰሮች (አሳታሚዎች) ጋ ሌላ እንቅፋት ይገጥምሻል፡፡ ምን አይነት እንቅፋት? እዚህ አገር በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ለረጅም ጊዜ የቆዩና ትልልቅ የምትያቸው ፕሮዱዩሰሮች የልምድ ስራ እንጂ ፕሮፌሽናል ስራ አይሰሩም፡፡

ስም መጥቀስ ባልፈልግም ትልልቅ የምንላቸው ሙዚቃ ቤቶች፣ አንድ ድምፃዊ ደክሞ ለፍቶ ጥሩ ሚክሲንግ አሰርቶ፣ ማስተሪንጉን ጨርሶ ሊያሰማቸው ሲሄድ በጣም ትንሽ በሆነች ቴሌቪዥንና በአንድ ስፒከር ብቻ ይሰሙታል፡፡ ይሄ ለእኔ ፕሮፌሽናል አሰራር አይደለም፡፡ እንግዲህ እንዲህ የሚያደርጉት አሉ የሚባሉና ትልልቅ የምትያቸው ሙዚቃ ቤቶች ናቸው፡፡ የዚህ አገር የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በብዙ መልኩ በችግር የተከበበ ነው፡፡ እነሱ የሚከፍሉት ገንዘብ ብዙ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አልበምሽ አድማጭ ጋ እንዲደርስ ጓጉተሸ ወደእነሱ ስትሄጂ እንደዚህ አይነት ችግሮች ይገጥሙሻል፡፡ አንድም የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ የገደሉት እነዚህ በልምድ ብቻ የሚሰሩ ሙዚቃ ቤቶች ናቸው፡፡ በአሜሪካ የተለያዩ ስቱዲዮዎች ገብተህ አሰራራቸውን አይተሃል፡፡ እስኪ የታዘብከውን አካፍለን--- የሌላውን አገር ልምድ ስንመለከት፤ ሙዚቃ የሚያቀናብረው ሌላ ሰው ነው፣ ድምፁን የሚቀዳው ሌላ ሰው ነው፣ ማስተሪንግ የሚሰራውም እንዲሁ ሌላ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ዘርፍ ውስጥ ስፔሻላይዝ አድርገው ነው የሚሰሩት፡፡

ወደ እኛ አገር ስትመጪ፣ ከሙያተኞች እጥረት የተነሳ እነዚህን ስራዎች የሚሰራቸው አንድ ሰው ነው፡፡ በአሳታሚ ደረጃ ያየሽ እንደሆነ፣ ከአንድ ኩባንያ ጋር ለአምስት ዓመት ይፈራረማሉ፡፡ በአምስት ዓመቱ ውስጥ ማግኘት የሚገባቸውን ነገር ሁሉ ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ኮንሰርት ይዘጋጃል፣ መኪና ካስፈለገው ሁለት ሶስት መኪና ይዘጋጅለታል፣ በቃ የዚያን ሰው ስራ ኩባንያው ፕሮፌሽናል በሆኑ ሰራተኞቹ ያከናውነዋል፡፡ ሰራተኞቹ በየሙዚቃው ዘርፍ የተማሩና በቂ እውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ እዚህ አገር አብዛኛው በልምድ ነው የሚሰራው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢንዱስትሪውን ገድሎታል፡፡ ግን እኮ አብዛኛው አድማጭና በሙዚቃው ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ሰዎች፣ ለሙዚቃው መዳከም ድምፃውያንን ተጠያቂ ያደርጋሉ… በምን መልኩ? በአሁኑ ወቅት ያሉ አብዛኞቹ ድምፃዊያን አዳዲስ ፈጠራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በቀደምት ድምፃዊያን በቅጡ የተዘፈኑትን መልሶ በመዝፈንና የበፊት ይዞታቸውን በማበላሸት ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው መውደቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል በሚል ይወቅሳሉ፡፡ በዚህ ትስማማለህ? በመሰረቱ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ መውደቅ ተጠያቂዎቹ ሙዚቃ ቤቶች ብቻ ናቸው አላልኩም፡፡ በሙዚቃ ሥራ ውስጥ ስለሚገጥሙ ፈተናዎች ስናወራ፣ ከችግሮቹ መካከል አንዱ መሆናቸውን ለማሳየት ነው የሞከርኩት፡፡ እንዳልሽው እኛም ጋ ችግር ሊኖር ይችላል፡፡

አሁን ላነሳሽው ጥያቄ ግን እንደምታውቂው እኔ ድምፃዊ ብቻ አይደለሁም፤ ጋዜጠኛም ነኝ፡፡ በጋዜጠኝነቴ ከተለያዩ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር ቃለ-ምልልስ በማደርግበት ጊዜ እንደሚነግሩኝ፣ የቆዩ ሙዚቃዎችን አድሶ መዝፈን አሁን የመጣ ፋሽን ሳይሆን ቀደም ሲልም የነበረ ነው፡፡ ለምሳሌ እነ ሙሉቀን መለሰ ሲመጡ፣ የራሳቸውን ዘፈን ከማውጣታቸው በፊት የቀደምት ዘፋኞችን ሙዚቃዎች ነበር የሚጫወቱት፡፡ የሆነ ትውልድ ወደ ሙዚቃው ሲመጣ፣ የቀደሙትን ዘፈኖች እየተጨዋተ ወደ አዲስ ስራ ይገባል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን የመጣ ሳይሆን ድሮም የነበረ ነው ልልሽ ፈልጌ ነው፡፡ ሆኖም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው የሚታየው ችግር የአርቲስቱ ነው፣ የሙዚቃ ቤቱ ነው፣ የአቀናባሪው ነው ብለሽ ልታልፊው የምትችይው አይደለም፡፡ እጅግ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ በዚህ የተነሳ የሙዚቃ ባለሙያዎችንም ህይወት አዳክሟል፡፡ ሙዚቃው እየተደጎመ ባለመሆኑ፣ ለምሳሌ ድሮ አንድ ብር ትገዢው የነበረው ሻማ አራት ብር ሲገባ፣ ሲዲ በድሮው ዋጋው እየተሸጠ እንኳን ጥበቡን አድንቆ የሚገዛ በመጥፋቱ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ገንዘብ እያገኙ አይደለም፡፡

የቤት ኪራይ የሚከፍሉት፣ የሚለብሱትና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ገንዘብ እያጡ ባሉበት ሁኔታ፣ ነፃ ጥበብ መፍጠርና በፈጠራ የነጠሩ እንዲሆኑ መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡ ይሄም ለኢንዱስትሪው ማደግ ማነቆ ከሆኑት አንዱ ነው ማለት ይቻላል? አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛውም ነው፡፡ ሙዚቃ አትራፊ እየሆነ ዘርፉ እያደገ ሲመጣ፣ ሙዚቀኛውም ለአዲስ ስራና ለፈጠራ ይነቃቃል፡፡ ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ባለሀብቶችም ይበዛሉ፡፡ አሁን ግን ደክመሽ ሰርተሽ በህገ-ወጥ መንገድ ሌሎች ሲጠቀሙበት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የፊልሙን ኢንዱስትሪ ተመልከቺ፤ አትራፊ ነው ስለሚባል ብዙ ባለሀብቶች እየተሳተፉበት ነው፡፡ ወደ ሙዚቃው ስትመጪ ግን ብዙ ውስብስብ ችግሮች ስላሉት፣ነባሮቹና በደንብ ይሰራሉ የሚባሉትም ከዘርፉ ወጥተዋል፡፡ አዲስ ሰው እንዳይገባ አትራፊ አይደለም፤ ይሄ ነው የእኛ አገር የሙዚቃ ጉዳይ፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት አንተ እንዴት ደፍረህ ገባህ? አንደኛ ሙዚቃ ለእኔ ህይወቴ ነው! ሳትዘፍን ኑር ብትይኝ የማይሆን ነገር ነው፤ ምክንያቱም የምወደው ሙያ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ መሆን የምፈልገውን ነው የሆንኩት፡፡ እኔ ለምሳሌ የተለያዩ ስራዎች እሞክራለሁ፡- ሙዚቃው አለ፣ ጋዜጠኝነቱም አለ፤ የቴሌቪዥን ሾው አለኝ፡፡

አንዱ አንዱን እየደጎመ እጓዛለሁ፡፡ ነፍሴን ግን ለሙዚቃው ታደላለች፡፡ ሌላ ስራም ባልሰራ፣ የሚደጉመኝ ባይኖርም ከሙዚቃው እጅ ሰጥቼ አልወጣም፡፡ የነፍስ ጥሪሽ ከሆነ፣ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ደከመ ብለሽ ከዘርፉ አትወጪም፡፡ በቃ ሙዚቃ ልክፍት ነው፡፡ የሰው ዘፈን ይዘፍናሉ የምትያቸው እንኳን ከከበባቸው ችግር አኳያ ለአዲስ ፈጠራ ይቸገሩ ይሆናል እንጂ ከሙዚቃው አይወጡም፡፡ እንደነገርኩሽ በተለያዩ ፈታኝ ችግሮች ውስጥ አልፌ፣ከስድስት ዓመት በኋላ አልበሜን ዳር አድርሻለሁ፡፡ እዚህ እስክደርስ ድረስ ግን “ይሄ ይለቅ እንጂ ሁለተኛ አልበም የሚባል ልሰራ?” ስል ነው የቆየሁት፡፡ ያ ሁሉ አልፎ አልበሜን ስለቅ ግን፣ ቀጣዩን አልበም በምን መልኩ መስራት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ “መቼ ነው” በሚል ስያሜ ስለወጣው አዲስ አልበምህ ንገረኝ… አብዛኛው የአልበሙ ይዘት ፍቅር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ፍቅር የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ አንድነትን የሚያቀነቅን ዘፈንም አለ፡፡

ጉራጊኛ ዘፈኑን ብትወስጂ አንድ መሆንን፣ ህብረት መፍጠርን፣ በጋራ ማደግን የሚሰብክ ነው፡፡ በሰል ብሎ የተሰራውና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “መቼ ነው” የሚለውን የፍቅር ዘፈን ደግሞ ለእናቴ ነው የዘፈንኩት፤ ለእህቶቼም ጭምር፡፡ እህቶቼ ለእኔ ፊት ለፊት ገንዘብ መስጠት ባይችሉ እንኳን ችግር እንዳይገጥመኝ የሚያስፈልገኝን ነገር ከጓደኞቼ በመጠየቅ እየደጎሙኝ ነው ያደግሁት፡፡ እናቴም እኔን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን እዚህ ለማድረስ ብዙ ደክማለች፡፡ ሴቶች ማለትም እናቶች፣ እህቶች፣ ሚስቶችና ፍቅረኞች በእኔ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ለምን መሰለሽ--- ሴት ልጅ ሄዳ ሄዳ እናትነት ጋ ነው የምትደርሰው፡፡ እናት ደግሞ ደሃም ትሁን ሀብታም፤ የተማረችም ትሁን ያልተማረች---ምንግዜም ፍቅሯ አይቀዘቅዝም፤ ማጣት አይለውጣትም፡፡ ሚስቶችን ተመልከቺ፤ ከራሳቸው በላይ ለባሎቻቸው ይኖራሉ፡፡ ለዚህ የተዘፈነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለወጣቶችና ለአድናቂዎቼ ሊያዝናናቸውና ፈታ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ሞቅ ያሉ ዘፈኖችም አሉበት፡፡ በተጨማሪም ለየት የሚያደርገው ጉራጊኛ፣ ትግሪኛ፣ ጎንደርኛ እና የወሎንም ባህላዊ ዘፈኖች ማካተቴ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ላይም የዘፈንኩት አለ፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም እንደየምርጫውና እንደየስሜቱ እንዲያዳምጠኝ በሚል 15 ጥሩ ጥሩ ዘፈኖችን በብፌ መልክ ደርድሬአለሁ፡፡ በግጥምና ዜማ ማን ተሳተፈ? ቅንብሩስ የእነማን ውጤት ነው? በዚህ አልበም ላይ የሚገርምሽ ነገር እኔ ራሴ አልበሙን ከጨረስኩኝ በኋላ ቁጭ ብዬ ስፅፍ ነው ሰባት አቀናባሪዎች መሳተፋቸውን ልብ ያልኩት፡፡ አብይ ኢርካ፣ ካሙዙ ካሳ፤ ትግርኛውን ያቀናበረው ሳምሶን ገ/አሊፍ ይባላል፡፡ እንዲሁም አሌክ ይለፍ፣ መኮንን ለማ እና ሚካኤል ሃይሉ አቀናብረውታል፡፡

ላይቭ ሙዚቃ የተጫወቱ፣ ፊቸሪንግ የገቡ፣ በድምፅ ያጀቡኝን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 25 ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ወደ ግጥምና ዜማ ስንመጣ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ጌትሽ ማሞ፣ ጃሉድ አወልና ሌሎችም አሉበት፡፡ “መቼ ነው” ሁለተኛ አልበምህ ነው፡፡ ከበፊቱ ስራህ ጋር እንዴት ታነጻጽረዋለህ? … ምን መሰለሽ---የመጀመሪያው ስራዬ በወቅቱ እንከን የለሽ ነበር ለእኔ፡፡ ያኔ የነበረኝን አቅምና የምችለውን ሁሉ አድርጌ ነው የሰራሁት፡፡ እንግዲህ የዛሬ 7 ዓመት ነው አልበሙ የወጣው፡፡ ለሁለተኛ ስራህ በጣም የዘገየህ አልመሰለህም? ዘግይቻለሁ፡፡ በነገርኩሽ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት… ለኮንሰርት የተለያዩ አገራት መዞር አለ፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ነው የዘገየሁት፡፡ የአሁኑን አልበሜን ስመለከተው ከበፊቱ የተለየ ስራ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ ምክንያቱም በእድሜም በልምድም እየበሰልሽ ነው የምትሄጂው፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ሆነሽ ስትዘፍኚና በ32 ዓመትሽ ስትዘፍኚ እኩል አይሆንም፡፡ ለምን? ከወጣትነት ወደ ጉልምስና ስትሄጂ፤ እየሰከንሽ፣ እያስተዋልሽና ኃላፊነት እየተሰማሽ ነው የምትመጪው፡፡ እንዳልኩሽ ያን ጊዜ ለእድሜዬና ለአቅሜ የሚመጥነውን ሰርቻለሁ፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላ አይደለም ከአንድ ዓመት በኋላ የምሰራውም ልዩነት ማምጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህ ጥሩና የበሰሉ ስራዎችን ይዤ መጥቻለሁ፡፡ የተገናኘነው ዛሬ አልበሙ ገበያ ላይ በዋለበት ቀን ነው (ማክሰኞ ከሰዓት ነበር) የዛሬ የገበያው ምን ይመስላል? በጣም ከጠበቅነው በላይ እየሸጥን ነው፡፡ በዚህም ደስተኞች ነን፡፡

ዛሬ እጅግ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ አይቻለሁ፡፡ አሳታሚው ማን ነው? የሚያከፋፍለውስ? እራሴ ነኝ ያሳተምኩት፤ የማከፋፈሉን ስራ “ፍሉት ኢንተርቴይመንት” እያከናወነው ይገኛል፡፡ ስፖንሰርን በተመለከተ ከፍተኛ እገዛ ያደረገልኝ ዳሽን ቢራ ነው፡ በዚህ አጋጣሚ በጣም ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው በተዳከመበት በአሁኑ ወቅት ከምጠብቀው በላይ እንደውም አልበም በማሳተም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን እገዛ አድርገውልኛል፡፡ ዳሽን ቢራ በቲቪ ሾው የበዓል ዝግጅቴ ላይ ተባባሪዎቼ ናቸው፡፡ ማሳተሚያው ምን ያህል ፈጀ? በተለያዩ ምክንያቶች የገንዘቡን መጠን መጥቀስ አልፈልግም፡፡ ብቻ ዳሽኖች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል፡፡ በዚህ ምክንያት አልበሙን በምፈልገው ጥራትና ሁኔታ ለማሳተም ችያለሁ፡፡ ለማስተዋወቅም የገንዘብ እጥረት ገጥሞኝ አልሰስትም፤ ይሄ ሁሉ በእነርሱ ነው የሆነው፡፡ በኢቢኤስ በምታዘጋጀው “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ” ቲቪ ፕሮግራም ላይ በምታከናውናቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘትህ ይታወቃል፡፡ በተለይ ለድምፃዊ ማንአልሞሽ ዲቦ ልጆች ያደረግኸው ነገር የብዙዎችን ልብ ነክቷል፤ ሆኖም ከዚያን ጊዜ በኋላ ጆሲ ከመዝናኛ ፕሮግራሙ ይልቅ ወደ በጎ አድራጎቱ አዘንብሏል የሚሉ አስተያቶች ይሰነዘራሉ… እስቲ እኔ ደግሞ ጥያቄሽን በጥያቄ ልመልስ፡፡ እኔ እንግዲህ ከአንድ ዓመት በፊት በፋሲካ ነው ፕሮግራሙን የጀመርኩት፡፡ በዓመቱ ለማንአልሞሽ ልጆች ያንን ካደረግሁ በኋላ፣ የትኛው ፕሮግራም ነው ከመዝናኛነት ወጥቶ መደ በጎ አድራጎት ስራ የሄደው? ከማንአልሞሽ ዲቦ ልጆች በኋላ አንድም የበጎ አድራጎት ፕሮግራም አልሰራሁም! በቃ መልሱ ይሄ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ፋሲካ ጀምሬ በዓመቱ የልጆቹን ሾው እስክሰራ ድረስ 52 ሳምንታት አሉ፡፡ በተለያዩ ችግሮች ሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት ፕሮግራሙ ከመቋረጡ ውጭ 50 ያህሉ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ይህን አይነት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ ብዬ አላምንም፤ ካሉም ግን ከሌሎች ሰዎች ሃሳብ በተቃራኒው ለመቆም የሚፈልጉና የሃሳብ ልዩነት ማንሳት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በእነዚያ 52 ሳምንታት ከተሰሩት ውስጥ በጣም ጥቂት ፕሮግራሞች በእርዳታ ላይ ሳይሆን ሰውን የማስታወስ ስራ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ከዚያ ውጭ ፕሮግራሙን የጀመርንበትን አንደኛ ዓመት ስናከብር፣ ከሜሪጆይ ጋር ነው ያሳለፍነው፡፡ እንግዲህ ለአዲስ ዓመት፣ ለገና፣ ለፋሲካ እና ለአንደኛ ዓመታችን ያካሄድናቸው ፕሮግራሞችን ጨምሮ አምስቱ ብቻ ናቸው የበጎ አድራጎት ሥራ የተሰራባቸው፡፡ ሌላው 50 ሳምንት የመዝናኛ ፕሮራሞች ናቸው የተሰሩት፡፡

ከፋሲካ በኋላ ሌላ ፕሮግራም አልሰራንም፤ ምክንያቱም አዲሱን ሲዝን ለመጀመር የተለያዩ ድርጅቱን የማሳደግ፣ የመገንባትና የማስፋፋት ሥራ ላይ ነው የተጠመድነው፡፡ ስለዚህ ያነሳሽው ጥያቄ ትክክል አይደለም!! እኔ ለቴሌቪዥን ፕሮፖዛል ሳቀርብ የመዝናኛ ፕሮግራም ብዬ ነው፡፡ ሌላ ልስራ ብትይም አይፈቀድልሽም፡፡ ነገር ግን የመዝናኛ ፕሮግራሙ እየተወደደና ተመልካቹ እየበዛ ሲሄድ፣ በዚህ አጋጣሚ ሰዎች የተቸገሩ ወገኖቻቸውን እንዲረዱ፣ የተረሱትን እንዲያስታውሱ ትምህርት ለመስጠት ታስቦ ነው እነዚያ አምስት ልዩ ፕሮግራሞች የተዘጋጁት፡፡ ሌሎች የበዓል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ተመልከቺ፡- የሞላላቸው፣ የደላቸው ወይም በአንድ ነገር ላይ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ቤት ተዘጋጅቶ ሲዘፈን፣ ሲጨፈር ነው የምትመለከቺው፡፡ እኔ ጋ ስትመጪ ይሄንን ስራ ብሎ የመከረኝ ሰው የለም፤ የውስጤ ሃሳብ ነው የገፋፋኝ፡፡ እሺ እነዚህ ሰዎች ደከሙ፤ ለአገራቸው ብዙ ለፉ፤ መስዋዕትነት ከፈሉና ተረሱ፤ ብናስታውሳቸው ምንድነው ችግሩ? በጎ አድራጎት ቢሆንስ ምንድነው ክፋቱ? በቅን ልቦና ካሰብነው፣ የእርዳታ ስራ ቢመስልስ ምን ችግር አለው ነው የእኔ ጥያቄ? እንደውም ኖሮኝ መርዳት ብችል ደስታውን አልችለውም፡፡ የሚደርሱኝ አስተያየቶች “እባክህ የተረሱ ወገኖችን ፈልግና እኛም የአቅማችንን እናድርግ” የሚሉ ናቸው፡፡ አልበም ከወጣ በኋላ ኮንሰርት ማዘጋጀት የተለመደ ነው፡፡ ምን አስበሃል? እንግዲህ ቅድሚያ ትኩረት የሰጠነው የአልበሙ ጉዳይ ላይ ነው፡፡

አሁን አልበሙ ተለቋል፡፡ ወደ አምስትና ስድስት ያህል ዘፈኖች ክሊፕ ሰርተንላቸው፣ መስከረም ላይ ከበፊቶቹ ጋር ቀላቅለን ለተመልካች ለማድረስ እየተጋን እንገኛለን፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የቴሌቪዥን ዝግጅቱን ከበፊቱ በተሻለ መልክ ለማቅረብ ከፍተኛ ዝግጀት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ያሉን ስራዎች እነዚህ ናቸው፡፡ የኮንሰርቱን ሁኔታ ለጊዜው አላሰብነውም፤ ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ባይሆን የአልበም ምርቃት በቅርቡ ይኖረናል፡፡ የመዝጊያ መልዕክት ወይም ምስጋና አለህ ? አልበሙ ላይ የተሳተፉትን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ዳሽን ቢራ ፋብሪካንም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ቤተሰቦቼን፣ ወዳጆቼንና አድናቂዎቼንም እንዲሁ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ ሳልረሳው አንድ ቁም ነገር ልንገርሽ፡፡ የማንአልሞሽን ልጆች ፕሮግራም ለመስራት ለፋሲካ ወደ ደብረዘይት እየሄድን ነበር፡፡ ለዳሽን ቢራ የስፖንሰር ጥያቄ ካቀረብኩ ቆይቻለሁ፡፡ አልበሙንም ለፋሲካ ለማውጣት ነበር ያሰብኩት፡፡

የስፖንሰር ጥያቄው የብዙ ሰዎችን ውሳኔ የሚፈልግ ስለሆነ እየተነጋገሩበት ነበር ማለት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ረስቼው ስራዬን እየሰራሁ ነበር፤ እናም የማናልሞሽን ልጆች ከቤት ወስጄ ደብረዘይት አድርሼያቸው አብረን በሚኒባስ ተመልሰን ቤታቸውን ላስረክባቸው ዱከም ስደርስ፣ ከዳሽን ቢራ ተደወለልኝ፡፡ ከጠየቅኳቸው በላይ በጣም ትልቅ የሚባል ብር ፈቀዱልኝ፤ በጣም ገረመኝ፡፡ በዚያን ሰዓት ምን አልኩኝ? “አንተ የሰውን ቤት ስትሰራ፣ እግዚአብሔር ያንተን ቤት ይሰራል” ብዬ አሰብኩኝ፡፡ በዚያው ቅፅበት ምን አሰብኩ? “እግዚአብሔር ለእኔ ብር ሰጥቶኛል፤ አልበሙ ተሸጦ ከሚገኘው ትርፍ 50 በመቶው ለማስታወቂያ፣ 50 በመቶውን ደግሞ ለእርዳታ ድርጅት እሰጣለሁ” ብዬ ቃል ገብቻለሁ፤ ቃሌንም እጠብቃለሁ፡፡ ለማን ነው የምሰጠው? የሚለውን ለመወሰን በእጄ ላይ ያሉ የተለያዩ ፕሮፖዛሎችን ማየት አለብኝ፡፡ እነሱን ገምግሜ ቅድሚያ ለሚሰጠው ድርጅት ግልፅነት በተመላበት መልኩ እሰጣለሁ፡፡ በተረፈ “መቼ ነው” የሚለውን ዘፈኔን ለፍቅር መስዋዕትነት ለሚከፍሉ ሚስቶች፣ እናቶች፣ እህቶችና ፍቅረኞች ጋብዣለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ በይልኝ፤ አመሰግናለሁ!!

Read 3872 times