Saturday, 06 September 2014 11:21

አማካይ የወሊድ መጠን እቅድ ..4.4 .. ---እስከ 2015...

Written by 
Rate this item
(38 votes)

       በኢትዮጵያ እናቶች በአማካይ በሕይወት ዘመናቸው የሚወልዱት ልጅ መጠን በ2005 /5.4/ በ2011 /4.8/ (DHS)› ሲሆን በ2015 ይህን ቁጥር ወደ /4.4/ ዝቅ የማድረግ እቅድ ተይዞአል ፡፡ በዚህ ዙሪያ በተለይም ቋሚና የረዥም ጊዜን የመከላከያ ዘዴዎች ጠቀሜታን እና የጎንዮሽ ጉዳታቸውን ዶ/ር ነጋ ተስፋው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ነጋ  በአሁኑ ወቅት በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጥራትና የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው ይሰራሉ፡፡
ጥ/ የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያዎች ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/ የእርግዝና መከላከያዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ በተወሰነ የጊዜ እርቀት ወይንም በየእለቱ ከሚወሰዱት በኪኒን መልክ እና በመርፌ ከተዘጋጁት ውጪ ለረዥም ጊዜ እንዲሁም በቋሚነት እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች አሉ፡፡ የረጅም ጊዜ የሚባሉት በማህጸን ውስጥ እስከ 12/ አመት ድረስ መቀመጥ የሚችል (IUD) ወይንም ሉፕ እና በክንድ ቆዳ ስር እስከ አምስት አመት ድረስ በመቆየት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል የሚችያስችል የህክምና ዘዴ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም መከላከያዎች 99 % ያህል አስተማማኝ የእርግዝና መከላከያዎች ሲሆኑ ሕክምናው የሚሰጠውም ለሴቶች ነው፡፡
ጥ/ (IUD)  ሉፕ የተባለው የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያ በማህጸን ውስጥ ለ12/አመት ያህል ሲቆይ ችግር አያመጣም?
መ/ (IUD)  ሉፕ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውል በመሆኑ እንደመርፌ ወይንም እንክብል በየጊዜው ውሰዱኝ የማይል እና ጊዜውን በትክክል ባለመጠበቅ ምክንያት ችግር የሚያስከትል አይደለም፡፡ ምናልባትም ሕክምናው በተሰጠ ለመጀመሪያዎቹ የሶስት ወራት የወር አበባ መዛባት ሊያስከትል ቢችልም ይህም ጊዜ ሳይፈጅ የሚስተካከል በመሆኑ ምንም አያሳስብም፡፡ በማህጸን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወይንም እስከ 12/አመት ድረስ በመቆየቱም የመመረዝ ወይንም የመቆሸሽ እድል የማይገጥመው ሲሆን በየመሀሉ ማውጣት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ተጠቃሚዋ በፈለገችው ጊዜ እንዲወጣ ከማድረግ በስተቀር እስከ12/ አመት ድረስ ካለምንም ችግር ሊቆይ የሚችል አስተማማኝ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ..ህ.... ሉፕ ቀላል የሆነ የመከላከያ ዘዴ ሲሆን ለተጠቃሚዎችም ምቹ የሆነ እና ከባድ የጤና ችግር የማያስከትል ተስማሚ የሆነ የህክምና ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ (IUD)   ሉፕ የተባለው የእርግዝና መከላከያ አንዳንዴ እርግዝናን ሳይከላከል ከልጅ ጋር አብሮ ይወለዳል?
መ/ በመጀመሪያ ደረጃ የረጅም ጊዜ የእርግዝና መከላያ (IUD)   ሉፕ 99 % ያህል እርግዝናን የመከላከል አቅም ያለው ስለሆነ እርግዝናው ይከሰታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ከኑሮ ሁኔታ ወይንም የግብረስጋ ግንኙነቱ ባህርይ በሚፈጥረው ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ እርግዝናው ቢከሰት እርግዝናው ጊዜው ሳይገፋ ክሩ የሚታይ ከሆነ ሉፑን በቀላሉ ስቦ ማውጣት ይቻላል፡፡ምናልባት ትኩሳት ወይንም የደም መፍሰስ ቢያጋጥም ግን ወደሐኪም በመሔድ መታየት ያስፈልጋል፡፡  ሳይታወቅ እርግዝናው የገፋ እና (IUD)    ሉፑም ክሩ የማይታይ ከሆነ ግን ከልጁ ጋር አብሮ ቢወለድ ምንም ጉዳት አያስከትልም፡፡ በአጠቃላይ ግን (IUD)    ሉፕ በማህጸን ውስጥ በሚቀመጥበት ጊዜ የሚሰጥ የህክምና ባለሙያዎች ምክር ስለሚኖር ያንን በትክክል ተግባራዊ ማድረግ ከተጠቃሚዎች ይጠበቃል፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያዎች ምን አይነት ናቸው?
መ/ ቋሚ የሚባለው የእርግዝና መከላከያ  በቀዶ ሕክምና ለሴቷም ሆነ ለወንዱ የሚሰጥ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡  ቋሚ የሚባለው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ በተለያየ የጋብቻ ሁኔታ ፣የስራ መስክ ፣የእድሜ ክልልና የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ተጨማሪ ልጅ ለመውለድ የማይፈልጉ ሴቶችና ወንዶች የሚመርጡት ዘመናዊ ዘዴ ነው፡፡ ይህ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በቀላል የቀዶ ሕክምና የሚሰጥ ፣ ለሕይወት ዘመን በቋሚነት እርግዝናን የሚከላከል አስተማማኝና በጤና ላይ ምንም ጉዳት የማያስከትል ነው፡፡ ለሴቷ የሚደረገው ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የዘር መተላለፊያውን ቱቦ በመቋጠር ሲሆን የወንዱ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የወንዱ የዘር ፈሳሽ መተላለፊያን በመቋጠር እርግዝናን በቋሚነት መከላከል የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ ተጠቃሚዎች ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል?
መ/ ቀዶ ሕክምናው በጣም ቀላል በመሆኑ ምክንያት ከጥቂት ቆይታ በሁዋላ አገልግሎቱን ያገኙ ሁሉ ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በተለይም ሴቶች ከሆኑ ለሁለት ቀናት ያህል በቤታቸው ከባድ ስራን ከመስራት እንዲቆጠቡ እና በቂ እረፍት እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ሴቶች ለአንድ ሳምንት ወይንም ቁስሉ እስኪድን ድረስ ከግብረስጋ ግንኙነት መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወንዶችን በሚመለከት ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ እንደሴቶቹ ለሁለት ቀናት ያህል በቂ እረፍት ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን የግብረስጋ ግንኙነትን በሚመለከት ግን ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ ለሶስት ወራት ያህል የማስረገዝ እድል ስለሚኖር  መታ ቀብ፣ ሚስትየዋ ሌላ ዘዴ እንድትጠቀም ማድረግ ወይንም ኮንዶም ሁልጊዜና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ጥ/    አገልግሎቱን ያገኙ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ተመልሰው ወደጤና ድርጅት መሄድ ያስፈልጋቸዋልን?  
ሴቶች
* ከፍተኛ ትኩሳት፣
* በታችኛው የሆድ ክፍል ከባድ ሕመም፣
* የቁስሉ እብጠት ቅላትና መመርቀዝ.. መምገልና መድማት..  የሚያዩ ከሆነ በፍጥነት ወደሕክምናው ተቋም መሄድ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ወንዶች
* ቀዶ ሕክምናውን ካደረጉ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ በቀዶ ሕክምናው ቦታ ላይ እብጠት ከተፈጠረ፣
* ቁስሉ ከመድረቅ ይልቅ የማመርቀዝ ፣የመድማት ወይም የመምገል ምልክት ካሳየ ወደ ሕክምና ተቋም መሔድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ምን ያህል ተጠቃሚ አለው?
መ/በአለም አቀፍ ደረጃ ሁለቱም ማለትም ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ  ሆነው ይታያሉ፡፡ በአገራችን ግን እስከአሁን በአለው ልምድ ተጠቃሚው በአብዛኛው መርፌውን የሚመርጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ግንቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴው ከውሳኔ በደረሱ ሰዎች ዘንድ በስፋት እየተለመደ እና በስራ ላይ እየዋለ ያለ ነው፡፡ ይህ ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ሁለቱ ጥንዶች ተስማምተው ወይንም በግልም ቢሆን በእርግጠኝነት በቂ ልጅ ስለአለኝ ወደፊት ልጅ መውለድ አልፈልግም ከሚል ውሳኔ ላይ እስከደረሱ ድረስ ደስተኛ የሆነ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ጉዳት አለውን?
 መ/ በሕክምናው ዘዴ የሚደርስ ምንም አይነት ጉዳት የለም፡፡ ወንድም ሆነ ሴት የቋሚ የእርግዝና መከላከያ እንዲወስዱ በሚወስኑበት ጊዜ ግን መጠንቀቅ ያለባቸው ነገር አለ፡፡
* በጊዜያዊ የኑሮ ሁኔታዎች ተገፋፍቶ፣
* በትዳር ጉዋደኛ አሳማኝነት ወይንም ግፊት ብቻ ተመርቶ፣
* ስሜትን ወይንም የእራስን ፍላጎት በደንብ ሳያዳምጡ፣
* ከሚመለከተው ቅርብ ከሆነው የትዳር ጉዋደኛ ጋር በትክክል ተወያይተው ሳይወስኑ፣
* በአጠቃላይም ሁኔታዎችን በትክክል ሳያመዛዝኑ ...ወዘተ
በዚህ መልክ እርምጃ በአካልዎ ላይ ከወሰዱ በእርግጥ ውጤቱ የሚጸጽት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በሁኔታው አምነው እርምጃ ከወሰዱ ሕክምናው ቀላል እና ከማንኛውም አይነት የኑሮ ሁኔታ ወይንም ከፍቅር ግንኙነት የማያግድ መሆኑን ባለሙያዎችም ሆኑ ተጠቃሚዎች የሚመሰክሩት ነው፡፡ ቋሚና የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያዎች አስተማማኝ እና ለተጠ ቃሚዎች ተስማሚ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ  እንዲጠ ቀምበት ይመከራል፡፡

Read 62727 times