Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 31 December 2011 11:08

አዲሱ የ”አዲካ” የጥበብ መንገድ የት ያደርሰዋል?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሦስት የሙዚቃ አልበሞችን አሳትሟል

ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ፊቱን አዙሯል

ከአውቶቢስ ተራ - ወደ ሒልተን ክብር ለአዲካ (ጥቂት አርቲስቶች)

ኪነ - ጥበብ የሚባለው የሥነ ጥበብ ባህሪ በሙዚቃ፣ በድርሰት፣ በቅኔ፣ በቅርፃቅርጽ እና በመሳሰሉት የሰው ልጅ በእጁ ከሚሠራው እና ከመንፈሱ በሚያፈልቀው የፈጠራ ሥራ ይገለጣል፡፡ ውጤቱ ደግሞ የፈጣሪው ወይም የሠሪው የአዕምሮ ንብረት ይሆናል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት የኪነ ጥበብ መገለጫዎች አንዱ የሆነው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በዋናነት የፈጣሪው ወይም የሠሪው የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት በኢትዮጵያ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ የተነሳ ኢንዱስትሪውን ከሚገባው በላይ ጉዳት ላይ መጣሉ ያፈጠጠ ሃቅ ሆኗል፡፡

የሙዚቃ ባለሞያዎቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰጧቸው አስተያየቶች እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የቅጂ መብት ሕግ በሚገባ ባለመከበሩ አንድ አሣታሚ የአንድን ድምፃዊ አልበም ገዝቶ ገበያ ላይ በሚያውልበት ጊዜ አልበሙ በቅጂ ስለሚዳረስ እንኳን ትርፍ ሊያመጣለት ይቅርና ወጪውን በአግባቡ ሊመልስ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በቀጣይ የሌሎች ባለሞያዎችን ሥራ ከመግዛት እጁን ይሰበስባል፡፡ ድምፃዊው በበኩሉ የመጀመሪያ ሥራውን ሸጦ ትርፍ ማግኘት ካልቻለ ወይም አስቀድሞ የሚያወጣውን ወጪ መመለስ ካልቻለ በቀጣይ የሚያሳትመው አልበም በግጥም፣ በዜማ እና በቅንብር ደረጃውን የጠበቀ ሥራ እንዳይሠራ ያግደዋል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው በተጠቀሰው የአንድ መንገድ ዙሪያ ጥምጥም ስለሚሽከረከር የሞያው ባለቤቶች ሞያውን ጥለው እንዲወጡ፤ የቀሩትም ተስፋ እንዲቆርጡ፣ አዲሶችም ወደ ሞያው እንዳይገቡ ማነቆ ሆኖባቸዋል፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም በጣም ጥቂት ከሚባሉ የቀድሞ እና አዲስ ባለሞያዎች በስተቀር ሙሉ የሙዚቃ አልበምን አሳትሞ ወደ ገበያ ማውጣት እየነደደ ባለ እሳት ውስጥ እንደ መማገድ ያክል ከዳር ቆሞ የሚሆነውን የሚጠባበቅ ተመልካች ባለሞያን እንዲያፈራ አስገድዶታል፡፡

የ”አዲካ” ድንገት መምጣት

“አዲካን የማውቀው በጣም ገበያዊ ያልሆኑ ነገር ግን ጥበባዊ የሆኑ ትልልቅ ኮንሰርቶችን በድፍረት ሲሠራ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በድፍረት ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል “ጂጂ”ን ብንወስድ እሷን እንኳን ሰው ስለሚወዳት ተመልካች አለው ብንል እንኳን ከሌሎች ባለሞያዎች ጋር በመሆን ለሁለት ቀናት የሠራው “አኬዥያ የጃዝ ፌስቲቫል” እጅግ የሚያስመሰግነው ሥራው ነው፡፡ የጃዝ ኮንሰርት ሥራ ምንም ዓይነት ገበያ የሌለው ተመልካችን እያዝናና የጃዝ ሙዚቃን ብቻ ለማስተዋወቅ ተብሎ የተሠራ በመሆኑ ያን ኮንሰርት ባየሁ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አርቱን የሚያከብር ፕሮዲዩሰር ሙዚቃ ወደ ማሣተሙ ሥራ ቢገባ እንዴት ጥሩ ይሆን ነበር? ብዬ ተመኘሁ በማለት ከወራት በኋላ ምኞቱ እውን ሆኖ ድርጅቱ በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብቶ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሙዚቃ አልበም የማሳተሙ ሥራ ውስጥ መግባቱን ሲያይ እጅግ መደሰቱን የገለፀልን የሙዚቃ ባለሞያው እና የኢትዮጵያን አይደል ዳኛ ሰርፀ ፍሬስብሃት ነበር፡፡

“አዲካ ቱር እና ትራቭል” ወጣቱ አዋድ መሐመድ በመኪና ኪራይ ንግድ ከ10 ዓመት በፊት የጀመረው ድርጅት ነበር፡፡ ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ እና እያደገ የሄደ ሲሆን አቶ አዋድ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ለመግባት ካለው ፍላጐት የተነሳ ከዛሬ አምስት ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ፊልሞችን ስፖንሰር በማድረግ፣ ከሌሎች የፕሮሞሽን ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በዋናነት የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር በማዘጋጀት እንዲሁም የታዋቂዋን ድምፃዊ አስቴር አወቀ፣ ጐሳዬ ተስፋዬ፣ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ሌሎች አርቲስቶችን ከውጪ ደግሞ ባባዓል የተሰኘ የማሊ ዘፋኝ፣ ኤኬዥያ ጃዝ ፌስቲቫል እና ሌሎች የሙዚቃ ዝግጅቶችን ሲያከናውን የቆየ ድርጅት ነው፡፡ በቅርቡም ዋና ባለድርሻ አቶ አዋድ መሐመድ የያዘበት፣ አቶ አሸናፊ ዘለቀ እና ወ/ሮ ሜሮን ተሰማ ሼር ሆልደሮች የሆኑበት “አዲካ ኮሙየኒኬሽን ኤንድ ኢቨንት ፒ ኤል ሲ” በማቋቋም በሙዚቃ እና በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ራሱን ማስገባቱን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ዘለቀ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አስረድቷል፡፡ በመጀመሪያ በሬጌ ስልቱ የተወደደውን “ቺጌ” የተሰኘ የኃይሌ ሩትስ (ኃይለሚካኤል ጌትነትን) አልበም አሳተመ፡፡ በመቀጠልም “ኮበለይ” በሚለው የትግረኛ ዘፈኗ ታዋቂነትን ያተረፈችው አርቲስት ትርሃስ ታረቀኝ “አዳነይ” የተሰኘ አልበም በመግዛት የማስተዋወቅ ሥራውን እየሠራ ሲሆን በመጪው ገና ገበያ ላይ ያውለዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ የኢትዮጵያን አይዶል ዳኛ የሆነችው የሙዚቃ ባለሙያ የሺ ደምመላሽ “ቅኔ” የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ገበያ ላይ ሊያውል ነው፡፡ የኪነጥበብ ኢንቨስትመንት ወዲያውኑ ወይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ የሚያደርግ አሊያም ወጪውን የሚመልስ ዘርፍ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ገበያዊ ያልሆኑ ኪነጥበባዊ ዋጋ ያላቸው ሥራዎች ከሆኑ የሚለው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት፤ ኪነጥበባዊ ዋጋ ያላቸውንም ሥራዎች ሠርቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚወስን ሰው ለከፈለው መስዋትነት ምላሹን ሊያገኝ የሚችለው ምናልባት ከ50 ዓመታት በኋላ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል፡፡አብዛኞቹ አሣታሚዎች የሚሉትን በመጥቀስ የሚናገረው ሰርፀ፤ በሕገወጥ ቅጂ ምክኒያት ብዙዎቹ አሣታሚዎች ተዳከመዋል፡፡ ሁኔታው ለማሠራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ስላልፈጠረላቸው ማስተር የያዙ ድምፃዊያኖችን አልበም ሊገዙ አልቻሉም፡፡ አስተያየቶቹ እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ደግሞ ጀማሪ ድምፃውያን ብቻ ሳይሆኑ ገዥ አጥተው ይንከራተታሉ ተብለው የማይታሰቡት አንጋፋ ድምፃውያን በገዢ እጦት ምክኒያት ማስተራቸውን ይዘው መቀመጣቸውን ያስረዳል፡፡ “እናም በዚህ አስቸጋሪ እና ለባለሞያዎቹ ፈታኝ የሆነ ወቅት ላይ “አዲካ” በእነዚህ ሦስት የሙዚቃ አልበሞች ኢንዱስትሪውን እየተቀላቀለ መሆኑ እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው” በማለት ሰርፀ አስተያየቱን ይደመድማል፡፡“አዲካ እቅዱ ብዙ ነው፡፡ ሥራውንም በሁለት ከፍሎታል፡፡ የሙዚቃ አልበሞቹን የማሳተም ሥራ የሚሠራው በጥናት ላይ ተመሥርቶ እና በባለሞያዎች የተደራጀ ቡድን አቋቁሞ አልበሞቹን በመገምገም ነው፡፡ ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ በመሆኑ ገበያው ለአጭር ጊዜ የሚፈልጋቸው የ”ገበያ” ሥራዎችን ይሠራል፤ የሙዚቃ ሥራ ዘመን ተሻግሮ እንዲሄድ የሚያስችሉትን ኪነጥበባዊ ዋጋ ያላቸውንም የሙዚቃ አልበሞች በማሳተም ለኢንዱስትሪው ድጋፍ ያደርጋል” የሚለው አቶ አሸናፊ፤ የድርጅቱን ቀጣይ ተግባሮች ሲያስረዳ፤ “በድርድር ላይ ያሉ ሦስት የሙዚቃ አልበሞች ተራቸውን በመጠበቅ ላይ ናቸው፤ ቀደም ሲል የፊልም ሥራዎችን በገንዘብ በመደገፍ ሲያከናውን የቆየውን ሥራውን አሳድጐም ስክሪፕቶችን በመግዛት ፕሮዲዩስ የማድረግ ሥራውን ይገፋበታል፤ በተጨማሪም የሰይፉ ፋንታሁንን “ይፈለጋል ቁጥር ሁለት” ፊልም ለመሥራትም በዝግጅት ላይ ነው፡፡የሙዚቃ አልበሞቹን ከማሣተም ጀምሮ ደረጃውን ከጠበቀ የማስተዋወቅ ሥራ እስከ ኮንሠርት ድረስ ለመሥራት ስምምነት ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ድርጅት መሆኑን የገለፀው አቶ አሸናፊ፤ በቀጣይ የሲዲ ማተሚያ ፋብሪካ በመገንባት በራሱ ድርጅት ሲዲውን በማሳተም የኦርጅናሉን ዋጋ ለመቀነስ እና አድማጩ በአነስተኛ ወጪ አልበም ለመግዛት የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፆልናል፡፡አዲካ ወደዚህ ሥራ ውስጥ የገባው በሞኖፖሊ ሥራውን በሙሉ ጠቅልሎ ለመያዝ ሳይሆን፤ አርቲስቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ የሙዚቃ ኢንዱስቱሪውን ለማሳደግ እና ሌሎች ተወዳዳሪ ድርጅቶችም ዘርፉን ተቀላቅለው እንዲሠሩ በማድረግ ኪነ-ጥበቡን የበለጠ ለማሳደግ፤ ከዚያም ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እንዲያመጣ ለማብቃት መሆኑን አቶ አሸናፊ አስረድቷል፡፡በቀጣይም አዳዲስ ተሰጥኦ ያላቸውን ድምፃዊያን የመደገፍ እና የማበረታታት፣ ተሰጥኦ ኖሯቸው በአቅም ማነስ ምክኒያት መሥራት ላልቻሉት ዕድል ለመስጠት እንዲሁም በዋናነት በሞያው ውስጥ ያሉትን የሙዚቃ ባለሞያዎች ሞያዊ በሆነ መንገድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መርዳት የድርጅቱ ዓላማ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግሯል፡፡አዲካ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተመው “ቺጌ” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም ድምፃዊ ኃይሌ ሩትስ ስለ አዲካ ለአዲስ አድማስ ሲገልፅ፤ “በመጀመሪያ ደረጃ እኔ የሙዚቃ አልበሜን ሠርቼ ጨርሼ በቶሎ ወደ ሕዝብ ያለማድረሴ ዋና ምክኒያት የአሣታሚ ማጣት ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም አሣታሚዎቹ ሲሠሩበት ከነበረው አሠራር የተለየ እና ሞያዊ የሆነ መንገድ ይዞ የመጣ ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው አንደኛ ለአዲስ የሙዚቃ አልበም ማስታወቂያ ያለውን ፋይዳ በሚገባ የተገነዘበ በመሆኑ ለጥሩ ማስታወቂያ ክብር የሰጠነው፣ በሁለተኛነት ደግሞ የኦርጅናል ሲዲ እና የኮፒ ሲዲን ልዩነት በሚገባ ያሳየ፤ ነው ኦርጅናሉ ሲዲ ከፎቶ ባሻገር ለዲዛይኑ የተጨነቀ በውስጡ አስፈላጊ እና በርካታ መረጃዎችን እንዲያካትት ተደርጐ የተሠራ ነው” በማለት አዲካ በዚህ ወቅት ወደዚህ ሥራ መምጣቱ የሚሠጠው ጥቅም የላቀ ነው ብሎታል፡፡“ከበለይ” በተሰኘው ነጠላ ዜማዋ ታዋቂነትን ያተረፈችው አርቲስት፤ “አዳነይ” የተሰኘ የሙዚቃ አልበም በመጪው ገና ለገበያ ለማቅረብ አዲካ የገዛት ሲሆን፤ አርቲስት ትርሃስ ታረቀ ስለ አዲካ ስትገልፅ፤ “በቅጂ መብት ጥሰት የተነሳ ሙዚቃ ቤቶች በሙሉ ተዘግተው ገዥ በታጣበት በዚህ ወቅት አዲካ ወደ ኢንዱስትሪው ገብቶ አልበም መግዛቱ እና፤ ከአልበሙ መውጣት ባሻገር የማስተዋወቅ ሥራ ኃላፊነቱን በሙሉ ወስዶ በመሥራቱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ያደረገልኝ፡፡ ከዛም በላይ ደግሞ ይህን ሥራ በመጀመሩ ተስፋ ቆርጦ ላለው አርቲስት አዲስ ተስፋን የሚሰጥ ሥራ ሆኖ አግኝቻለሁ፡፡” በማለት አዲካ የጀመረው መንገድ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪውን ከሞት የመታደግ ያህል ነው ብላዋለች፡፡ የሙዚቃ ባለሞያዋ እና የኢትዮጵያን አይዶል ዳኛ የሺ ደመላሽ አዲካ በቅርቡ ገበያ ላይ ከሚያውላቸው አልበሞች አንዱ የሆነውን “ቅኔ” የተሰኘ አልበም ሠርታ ጨርሳለች፡፡ አርቲስቷ ባሳለፍነው ሳምንት የሠራችውን የሙዚቃ አልበም ባስገመገመችበት ወቅት እስካሁን ከተለመዱት ስታይሎች ወጣ ያለ እና በአዳዲስ ቅኝቶች እና ቅኝቶችን በማዋሃድ የተሠሩ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎችን አቅርባለች፡፡ የሙዚቃ ባለሙያዋ የሺ፤ “በሕገወጥ ቅጂ ምክንያት አሳታሚው ሁሉ ወደኋላ እየሸሸ ባለበት በዚህ ወቅት አዲካ ወደ ኢንዱስትሪው የመግባቱ ጥሩነት ምን ጥያቄ አለው?” በማለት አዲካ ክፍተቱን በመሙላት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የተነሳ ድርጅት በመሆኑ ሊደገፍ እንደሚገባ ተናግራለች፡፡ ሒልተን በተከናወነው የየሺ አዲስ የሙዚቃ አልበም ግምገማ ላይ ተጋብዘው የተገኙ አንዳንድ አርቲስቶች “ከአውቶብስ ተራ አውጥቶ ሒልተን ላመጣን አዲካ ክብር ይገባዋል” ብለዋል፡፡የአዲካ አዲስ መንገድ ኢንዱስትሪውን የሚያሳድግ እንዲሆን እና የቀደሙት አሳታሚዎች ተጉዘው የተሸነፉበት የቀድሞ መንገድ ለአዲካ እክል ሆኖ ጉዞውን እንዳያደናቅፈው፤ የፈጠራ ሥራውን ጥራት መጠበቅ ከአርቲስቶች የሚጠበቅ ብርቱ ተግባር ነው፡፡ የወጡት ሕጐች በሚገባ እንዲተገበሩ፤ የአዕምሮ ንብረት የፈጠራ ባለቤትነትን መብት በሚገባ እንዲከበር እና ሞያውን ለመደገፍ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ብርቱ ተግባር ነው፡፡ የሙዚቃ አድማጭ ማኅበረሰብ ደግሞ እንደ አዲካ ያሉ ድርጅቶች የሚያሳትሟቸውን ሥራዎች ኦርጅናል በመግዛት የሚያደርገው ትብብር ለኢንዱስትሪው ማደግ የሚሰጠው ጥቅም ዋናውን ቦታ ይይዛል፡፡ እነዚህ ነገሮች ካልተተገበሩ ግን አዲሱ መንገድ “አዲካ”ን ወደ አዲስ ቦታ ሳይሆን ወደቀደሙት አሳታሚዎች ይመልሰዋል፡፡

 

 

Read 9262 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 16:11

Latest from