Saturday, 13 September 2014 12:55

ለ“ቻይነታችን” ዓለም አቀፍ ሽልማት ይገባናል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(6 votes)

*የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት የተራዘመው “ለበጎ” ነው

 

       የአዲስ አበባ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርቱን ችግርና የታክሲውን ወረፋ በትዕግስት ችሎ መቆየቱን በማድነቅ፣ይቅርታና ምስጋና በአንድ ላይ ማቅረባቸውን ሰማሁ፡፡ (ኧረ ሽልማትም ይገባን ነበር!) በዚህ አጋጣሚ ግን ኢህአዴጎች የትም ዓለም ላይ ቢሄዱ እንደዚህ ያለ “ቻይ ህዝብ” እንደማያገኙ ልጠቁማቸው እወዳለሁ (“አያውቁንም” አለ ዘፋኙ?!) በነገራችሁ ላይ ይቅርታ መጠየቅና ማመስገን እንደሽንፈት በሚቆጠርባት አገር፣ከንቲባው ላሳዩት ድፍረት ምስጋና ይገባቸዋል (አድናቂያቸው ነኝ!) ሌሎች የመንግስት ባለሥልጣናትና የተቃዋሚ አመራሮችም ከሳቸው እንደሚማሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ (“ተስፋ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው” እንዳትሉኝ!)
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ--- ነዋሪው እኮ ያልቻለው ነገር የለም! የመልካም አስተዳደር ችግር (ራሱ ኢህአዴግ ያመነው እኮ ነው!) የመብራት፣ የኔትዎርክ፣ የኢንተርኔትና የውሃ መጥፋት--- ሌላም ሌላም ችሎ ነው የሚኖረው፡፡(“ዓለም አቀፍ የቻይነት አዋርድ” የለም እንዴ?) ለቻይነታችን እኮ ዓለም አቀፍ ሽልማት ይገባናል፡፡ እኔ የምለው ግን---የከንቲባው “ይቅርታና ምስጋና” ላለፈው ብቻ ነው ወይስ ለመጪውም ጊዜ ነው? (የ“ይቅርታ” ቀብድ የለውም ብዬ እኮ ነው!) ወደ ሌላ ወቅታዊ አጀንዳ ደግሞ እንለፍ፡
በዓመቱ ማብቂያ (ጳጉሜ 5 ላይ) ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ሊሰጥ ታስቦ የነበረው ሽልማት ምን ደረሰ? (በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የተዘጋጀውን ማለቴ ነው!) ተራዘመ ሲባል ሰማሁ ልበል፡፡ (ኧረ በደንብ ይራዘም!) መራዘም ብቻ ሳይሆን መክረም ያለበት ጉዳይ እኮ ነው፡፡ በተለያዩ የኪነጥበብ ዘርፎች (በተለይ በሥነጽሁፍ) የተመረጡትን እጩ ተሸላሚዎች ስመለከት ግርም ነው ያለኝ፡፡ (እጣ የወጣላቸው እኮ ነው የሚመስሉት?) እንዴ --- ጊዜ ወስዶና የዘርፉን ባለሙያዎች አማክሮ እጩዎችን በቅጡ መምረጥ ማንን ገደለ? (“እርሟን ብታፈላ…” አሉ!) እስቲ አስቡት… ስለአገሪቱ ደራሲያን እያወራችሁ እነ አዳም ረታን (የአጭር ልብወለድ ቁንጮ እኮ ነው!) ይስማዕከ ወርቁን (“ዴርቶጋዳ” የተባለ ልብወለዱ ከ150ሺ ኮፒ በላይ ተቸብችቦለታል!) አለማካተት ምን ይባላል? (“ወይ እቺ አገር” አሉ አቦይ!)
አንጋፋዎቹን እነሃዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አቤ ጉበኛ … ተዋቸው፡፡ ያስታወሳቸው የለም፡፡ ለነገሩ እንኳን በህይወት የሌሉት በህይወት ያሉትስ መች በወጉ ታወሱ?! እውነቴን ነው--- የእጩዎቹን ዝርዝር ስታዩ እኮ መለኪያው ግራ ይገባችኋል (በኮታ ይሆን እንዴ?) ግን እኮ ኮታውንም ቢሆን በወጉ ማድረግ ይቻል ነበር - በካታጎሪ (በዘርፍ በዘርፉ) በመከፋፈል፡፡ (“ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንዳትሉኝ!) ከምሬ እኮ ነው … “ምርጥ ወጣት ደራሲ”፣ “ምርጥ የህይወት ዘመን ደራሲ”፣ “ምርጥ ፈርቀዳጅ ደራሲ”፣ “ምርጥ የኦሮሞኛ ልብወለድ ደራሲ” … ኧረ ቀላል ነው (ሮኬት ሳይንስ እኮ አይደለም!)
ሌላው ያስገረመኝን ደግሞ ልንገራችሁ (ላላያችሁት ነው ታዲያ!) በስነጥበብ ዘርፍ ከአስሩ እጩ ተሸላሚዎች (ሰዓሊዎች ማለት ነው) ውስጥ አንደኛው የስእል ጋለሪ ነው፡፡ ይታያችሁ---ሰዓሊዎችና የስዕል ጋለሪ በአንድ ዘርፍ ሲወዳደሩ? (እንዳይሆን እንዳይሆን ነው ልበል!) ለማንኛውም ግን አዘጋጆቹ ይሄን ተሞክሮ ከየትኛው አገር እንደቀዱት ቢነግሩን ሸጋ ነው (ከስህተት ለመማር እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን የመሸለም ኃላፊነት የባህልና ቱሪዝም መሆኑን ያወቅሁት ዘንድሮ ነው፡፡ መቼም በአዋጅ የተሰጠው ሥራው ከሆነ እስከዛሬ የት ሄዶ ነው ያስብላል፡፡
(ብዙ ሽልማቶች አምልጠውናል ማለት ነው!) ዕድላችን ሆኖ ነው መሰለኝ ይሄ የሽልማት ነገር ብዙ ጊዜ አይዋጣልንም (“ምን ተዋጥቶልን ያውቃል?” ብትሉኝ መልስ የለኝም!)
ከዚህ ቀደም ስንቶቹ የሆሊውድ ዓይነት “ኦስካር” እንጀምራለን ብለው የውሃ ሽታ እንደሆኑ አልነግራችሁም፡፡ (ስፖንሰር አድራጊዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ ይመስላል!) በሥነጽሑፍም----በተለይ በአጭር ልብወለድ ዘርፍ ለአንድ ዙር እንቁልልጬ ብለውን የውሃ ሽታ የሆኑ አሉ፡፡ (በምን ኃጢያታችን ይሆን?) እኔ የምለው ግን … ሰው ሁሉ “ገጣሚ” በሆነባት አገር፣ እንዴት ገጣሚያንን የሚሸልም ጠፋ? (የግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክሾፕ የግድ ነው!)
በነገራችሁ ላይ በባህልና ቱሪዝም የእጩ ተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ እነ ግጥም፣ አጭር ልብወለድና ቲያትር .. ከእነመኖራቸውም ተዘንግተዋል (በ“ኪራይ ሰብሳቢነት” ተፈርጀው ነው አልልም!) ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ በእድሜ አንጋፋ የሆነው ትያትር ተዘንግቶ ፊልም መታጨቱ ነው (“ከኋላ የመጣ አይን አወጣ” አሉ!) ሌላው ቢቀር ጥቂት ትያትሮችን ከአንድ ትያትር ቤት ጋር ማጨት እንዴት ተሳናቸው? (ሰዓሊያኑና ጋለሪው በአንድ ዘርፍ እንደታጩት ማለቴ ነው!)
እኔ የምለው ግን … አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዚህ በዚህ ወሳኝ ጊዜ የት ነው የሚጠፋው? የሥነ-ፅሁፍ ሥራዎችን የመሸለም ወግና ማዕረግ የሚያገኘውስ መቼ ነው? ትላንት የተጀመረው “ፔን ኢትዮጵያ” እንኳን የእንግሊዝኛ ልብወለዶችን በሦስት ዙር ሸለመ እኮ! (“ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” ለማለት ነው!) እናላችሁ--- አርአያ መሆን ቢያቅት አርአያ መከተል ይቻላል እኮ!
የሆኖ ሆኖ ግን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የ2006 የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት የተራዘመው ለበጎ ነው ብዬአለሁ፡፡ (እውነት ተራዝሞ ከሆነ ማለቴ ነው!) ለምን መሰላችሁ? በያዛቸው እጩ ተሸላሚዎች ዝርዝር ቢቀጥል እኮ “ሽልማቱ ተጭበርብሯል፤ይደገም!” የሚል ቅሬታ አይቀርም ነበር፡፡ (ከመጭበርበርና ከማጭበርበር ያውጣን!!)

Read 3267 times