Saturday, 13 September 2014 13:23

አዲስ አመት ሲመጣ ከአሮጌ ማንነት እንውጣ!

Written by  ዘመላክ ስለሺ
Rate this item
(5 votes)

(እስቲ እውነት እውነቱን እናውራ)

   ሰው መሬት መንገሻው ሰማይ መናፈሻው ተደርገው የታነፁለት ንጉስ ነው፡፡ ስለሆነም ልቡን ስሎ፣ አዕምሮውን አብስሎ ሲተጋና ጥበብን ሲሻ በመሬት የተተከሉ፣ በሰማይ የተሰቀሉ እንዲሁም መሀል ላይ የሚንቀዋለሉ ፍጥረታት ሁሉ ያለማመንታት ይገዙለታል፡፡ እሱም ለስጋው ድሎት፣ ለነፍሱ ችሎትና ለመንፈሱ አገልግሎት ያስገብራቸዋል፡፡ ይሄኔም ልኩ ታውቆ፣ ቦታው ተጠብቆ በፀጋ ስያሜው የፍጥረት ራስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰው አስተሳሰቡን ማበጠር አካባቢውን መቆጣጠር ሲሳነው ግን የፍጥረት ራስ መሆኑ ቀርቶ ትራስ ይሆናል፡፡ ትራስ የሚሆን ራስ ደግሞ የመስመጥ እንጂ የማበጥ፣ የመልፋት እንጂ የመፋፋት፣ የማለቅ እንጂ የመዝለቅ ህልውና የለውም፡፡ ሰብዕናው መታሸት፣ እድሉ መበላሸት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ውስጡ ተንፍሶ፣ ውጪው ተበጣጥሶ እስከሚወረወር ድረስ የሌሎች መሞላቀቂያ፣ የእንቅልፋቸው ማድመቂያ፣ የድካማቸው ማስለቀቂያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ትራስ የሚሆን ራስ በልማዱ ከስር የመርመጥመጥ እንጂ ከላይ የመቀመጥ ጠባይ ስለሌለው አምላኩም ፈለኩም የተጫነበት ተራራ፣ የወደቀበት መከራ ነው፡፡ በመሆኑም ጭነቱን ገፎ፣ ሸክሙን አራግፎ ለመለወጥ አይባጅም፡፡ ይልቁንም ባለበት አምኖ፣ በኖረበት ተከድኖ ያለመገረም፣ ያለማጉረምረም ይቀጥላል፡፡ ትራስ የሚሆን ራስ ከታሰረበት ከተማ፣ ከተወረወረበት ጨለማ ለመውጣት ፀጋውን መርምሮ፣ ተሰጥኦውን በርብሮ ስለማይንቀሳቀስ ብርሃን ቤቱን ጥበብ ህይወቱን አያውቁትም፡፡
ይህ የእኔና የአንተ እውነት ነው፡፡ በቤታችን መሬት መታሻ፣ ሰማይ ማልቀሻ ሆነው ሰው ራስ በሆነ ማንነት ሳይሆን ትራስ በሆነ መናኛነት ይመላለሳል፡፡ የአዕምሮ ጥቅሙ፣ የጥበብ ቀለሙ አይታወቅም፡፡ የፍጥረት አቻዎቻችን በየወቅቱ እየተነሱ ምድርን በግኝት ብርሃናቸው ሲያጠምቋት፣ በፍላጐት ክንዳቸው ሲያመጥቋትና በአስተሳሰብ ሃይላቸው ሲያደምቋት እኔና አንተ በፍርሃት ተከበን፣ በጨለማ ተሸብበን እንገኛለን፡፡ ወደ ብርሃን መውጣት ለውጥ ማምጣት አይታየንም፡፡ ጥበብ መካፈል ግኝት መፈልፈል አይቃጣንም፡፡ ድካምን ማድከም እረፍትን ማከም አንሻም፡፡ ችግርን መርሳት ተድላን ማውሳት፣ ህሊናን ማደስ ኑሮን ማወደስ ወደ ሀሳባችን አይመጣም፡፡ ልዩነት በድህነት መዝለቅ፣ በዕጦት ወረርሽኝ ማለቅ ይመስለናል፡፡ ልዩ መሆን፣ ልዩ ነኝ እያሉ ማውራት፣ የዋሻና የሀውልት ስም መጥራት ሆኖብናል፡፡
ዛሬም ድረስ በአዳም በሬ፣ ጅራፍ በያዘ ገበሬ እናርሳለን፡፡ ውሃ እና መብራት፣ ቁርስና ራት ይርበናል፡፡ በልቶ ማደር ፀሎታችን፣ ለብሶ ማጌጥ ህልማችን ነው፡፡ የቤት ዕቃ መቀየር ብርቃችን፣ ጐጆ መቀለስ ድንቃችን ነው፡፡ ዘመናችን ሁሉ መሰረታዊ ፍላጐታችንን ለማሟላት ለማናውቀው አዚም የተከፈለ ቀብድ ነው፡፡ መኖር ፈጽሞ ሌላ አላማ የሌለው እስኪመስለን ድረስ ዕለት በዕለት፣ ከልጅነት እስከ እውቀት የሰቀቀን ተላላኪ፣ የግዞት ህላዌ አምላኪ፣ የሲኦል ፍዳ ተራኪ ሆነን፣ አካላችን ተበዝብዞ፣ ህሊናችን ተመርዞ መቆም ታክቶን፣ ሳቅ ተረስቶን ከምሬት ወደ መሬት፣ ከሞት ወደ ሞት እንሸጋገራለን፡፡ በጨለማ ውስጥ ተወልደን፣ በጨለማ ውስጥ አርፍደን ወደጨለማ እንመለሳለን፡፡ የዚህ ምድር አባል ለመሆን ቀደም ሲል መወለዳችን ሳይወሳ የቀብራችን ጡሩንባ ይነፋል፤ የዘመዶቻችን እንባ ይጐርፋል፡፡ አቶ ሀበሻ ወደዚህ ምድር ሳይመጡ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል ይባላል፡፡
ሰው ለመታከት ለምን ይፈጠራል! ህይወታችን ጉልበት እንጂ ሽበት፣ ክበብ እንጂ ጥበብ የለበትም፡፡ ጥጃ ከእናቷ ወተትን፣ እኛ ከእናታችን መዋተትን እንቀበላለን፡፡ አንበሳ ከአባቱ ጋማ፣ እኛ ከአባታችን የድህነት አርማ እንወርሳለን፡፡ ውጣ ውረድ የኛ ውርስ፣ የልጆቻችን ቅርስ ነው፡፡ ምኞታችን የኋሊት፣ መንገዳችን በሌሊት ነው፡፡ ለሚቀለው በር፣ ለሚከብደው ድንበር የለንም፡፡ ከለበስነው የተሻለ ማቅ፣ ከምናውቀው የበለጠ ሀቅ ያለ አይመስለንም፡፡ ከለመድነው ያለመድነው እንደሚበዛ፣ ከምናየው የማናየው እንደሚገዛ አናስተውልም፡፡ ጨረቃ ልጅ ሆና ትወለዳለች፡፡ ከዛም በአካል ጐርምሳ በብርሃን ጐልምሳ ትጠፋለች፡፡ እኛ ልጅ ሆነን እንወለዳለን፡፡ ሆኖም በአካል ዳጉሰን በብርሃን አንሰን እንጠፋለን፡፡ በአሰራርም በአኗኗርም አንጐለምስም፡፡
ስልጣኔ ተመኝተን፣ ከተማ ሰርተን፣ ስርአት አበጅተን ያው ነን፡፡ በጣት ከመቁጠር ደን ከመመንጠር፣ ጌሾ ከመውቀጥ፣ ቲማቲም ከመቀጥቀጥ አልወጣንም፡፡ ምስር በሰፌድ ከመልቀም ሳፋን ለገላ መታጠቢያነት ከመጠቀም፣ ሌት ፖፖ ላይ፣ ቀንም መንገድ ላይ ከመሽናት አልተላቀቅንም፡፡ መኖሪያችን ጭቃ፣ መጥረጊያችን ጨፈቃ ነው፡፡ ወለላችን እበት፣ ማገዷችን ኩበት ነው፡፡ መኝታችን ኬሻ፣ ሸክማችንም በትከሻ ነው፡፡ በታሪክ እግር በዘመን ሽግግር የኖረ ልምዳችንን ለውጠን፣ ከነባር ድህነታችን አፈንግጠን አልተራመድንም፡፡ አሁንም ወተት በእንስራ፣ አቀበት በከዘራ እንገፋለን፡፡ በመጅ ፈጭተን፣ በእጅ አቡክተን እናድራለን፡፡ መቀመጫችን አጐዛ፣ አንቡላንሳችን ቃሬዛ፤ መፋቂያችን እንጨት፣ መኮፈሻችን ፉጨት ነው፡፡ በየጉዟችን ምዕራፍ ደም አፍሰን፣ አጥንት ከስክሰን ስለጠበቅነው በር፣ ስላፀናነው ድንበር ብናቅራራም ከአድዋ የገበየነው ቅዋ፣ ከመቅደላም የተጐናፀፍነው ተድላ የለም፡፡ ትርፋችን እንቶ ፈንቶ፣ ጡረታችን ቀረርቶ ነው፡፡
ኮንጐ ዘምተን፣ ኮንጐ ጫማ ሰፍተን እናደርጋለን፡፡ ኮሪያ ዘምተን፣ ኮሌታ አብክተን እንለብሳለን፡፡ ሁልጊዜ ዕቅድ ነድፈን፣ ህልም ጽፈን ብንነሳም ከዘፈን አልፈን፣ ቁርን አርግፈን፣ መረቅ ጨልፈን አናውቅም፡፡ የምንማረው ተመራምረን ሳይሆን ተማረን ለመኖር ነው፡፡ ዲግሪ ጭነን፣ ፈተና ተጭነን እንዞራለን፡፡ ሰብሮ ከመውጣት ታግሶ መቀጣት፣ ሃሳብ ከማመንጨት ፀጉር መንጨት ይቀለናል፡፡ በወረቀት እንጂ በዕውቀት፣ በዝናብ እንጂ በምናብ አንተማመንም፡፡ በዚህም ከንስሮቻችን ዶሮዎቻችን እየገዙን፣ ከአራዶቻችን ወራዶቻችን እያዘዙን እና ከመሪዎቻችን ፈሪዎቻችን እየገረዙን ወባ እና ሌባ የሚያምሱን ልሞች፣ ጨፌ እና እጥፌ የሚጐለስሱን ደካሞች ሆነናል፡፡ ሁኔታችን ልቦናውን እንደጣለ ሰው ነው፡፡ ግልፁ ድብቅ፣ ፍሬው እብቅ፣ ጥንቡ ዘረፋ፣ ኦናው ወረፋ፣ ቀኙ ግራ፣ ሰላምታውም አተካራ ይሆንብናል፡፡ ጐፈሬውን ከልጩ፣ ምንጩን ከፍንጩ አንለይም፡፡ ቀጂ ሆነን ጥም ያንቀናል፡፡ አራጅ ሆነን ቅልጥም ይናፍቀናል፡፡
ለመለወጥ ባለን መሻት ውስጣችን ያመነ፣ አቋማችን የሰከነ፣ እርምጃችን የተካነ አይደለም፡፡ ነፍሳችን በሃሳዊ ኩራት የረጋች፣ በግለኝነት የተዘጋች፣ በምንቸገረኝነት የተወጋች ቁስለኛ ናት፡፡ ስለ ሀገራችን ከከንፈር ያለፈ ትኩረት፣ ከልብ የገዘፈ ህብረት የለንም፡፡ አንድነታችን የዕድር፣ በጀታችን የብድር ነው፡፡ ይህም አብሮ ከመተለቅ አብሮ ማለቅን ስውር ግብ ባደረገው ህይወታችን ለሽሚያ እንጂ ለቅድሚያ፣ ለመኳተን እንጂ ለመተንተን ልግመኞች በመሆናችን ውስጥ ይሰበካል፡፡ እርስበርሳችን በጋራ የምንኖር ባለጋራዎች ነንና አቋራጫችን የረዘመ፣ መፍትሔያችን የቆዘመ ነው፡፡ ከመተላለፍ መቆላለፍ ያፈጥነናል፡፡ ከመደናነቅ መተናነቅ ያከባብረናል፡፡ በዘመናችን ተመሳስሎ ማደር እንጂ ተለያይቶ መደራደር ሲያሳጣ እንጂ ሲያዋጣ ተመልክተን ስለማናውቅ፣ የብሔር እንጂ የሀሳብ ልዩነት አይገባንም፡፡ በአንድ አቅጣጫ ፈጠን፣ በአንድ ሩጫ ተመስጠን ቀርተናል፡፡ ንግግራችን የፍራቻ ምግባራችን የዘመቻ ነው፡፡ ከመወያየት መተያየት፣ ከመኮረጅ መፈረጅ ይቀለናል፡፡ ለመውደድ አደብ፣ ለመጥላት ሰበብ የለንም፡፡ ውንጀላችን ያለቦታው፣ ውዳሴያችን ያለጌታው ነው፡፡
ቅድመ አያቶቻችን ሲያልፉ፣ ምንጅላቶቻችን ሲጠፉ የተረከብነው መሪነት፣ የከረከምነው ኋላቀርነትም ሆነ ያበለፀግነው ማንነት የለም፡፡ እንዲያውም ወኔያችንን ሰልበን፣ ጠኔያችንን አራግበንና ልቦናችንን አጥብበን ቀጥለናል፡፡ ከትችት ርችት፣ ከክርክር ዝክር፣ ከንባብ የመሸታ ቤት ድባብ ደስ ይለናል፡፡ ዝንባሌዎቻችን ችግርን መልመድ፣ እርስበርስ መጠማመድ፣ ዛር ማብላት፣ ባለጉዳይ ማጉላላት፣ ወሬ ማቃጠር፣ ፀጉር መቆጣጠር የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለችርቻሮ የሚቀርበው መብታችንም ሆነ በቀጠሮ የሚቀረው ኑሯችን አያስጨንቀንም፡፡ መሬቶቻችን የአበባ፣ መስሪያ ቤቶቻችን የስብሰባ እርሻዎች ናቸው፡፡ የቢራ ፋብሪካ እንጂ የማንበቢያ ዋርካ የለንም፡፡ እስካሁን ካነበብነው ህልዮት፣ ከተከተልነው ርዕዮትም ሆነ ካፈነዳነው አብዮት የቀዳነው ትምህርት፤ ስንኖር እንባ፣ ስንሞት ሰካራም የሚነፋው ጡሩንባ ብቻ ነው፡፡ በወሬ ጠግበን በፍሬ ተርበን ግን እስከመቼ? እስከመቼ ማለትስ እስከመቼ ነው? ትራስ ከመሆን ራስ መሆን ይሻላል፡፡
እስኪ በአዲስ አመት አዲስ ማንነት እንቀምር፤ አዲስ ህይወት እንጀምር፡፡ ከአቧራ ምኞት ከአቧራ ህይወት እንውጣ፡፡ የቤታችን ሰላምታ፣ የስራ ቦታችንም እንቢልታ ይሁን፡፡ እስኪ ወደ ብርሃን እንውጣ. ፤ውጦች እናምጣ፡፡ ጥበብ እንካፈል፣ ግኝት እንፈልፍል፡፡ ህሊናን እናድስ፣ ኑሮን እናወድስ፡፡ እስኪ በአዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ እንደ ግለሰብ መቋሚያ የሚያሲዝ እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ መቋቋሚያ የሚሆን እውነት እንጨብጥ፡፡ ፓርላማ ውስጥ የሚያዛጉ ብቻ ሳይሆን የሚተጉም ይለመዱ፡፡ በርቀት መነቋቆር ሳይን በቅርበት መነጋገር ባህል ይሁን፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ ከአሮጌ ማንነት እንውጣ!!

 

Read 3611 times