Saturday, 13 September 2014 13:46

የአረቦች የህክምና ጥበብ አብዮት!

Written by  ኑርሁሴን እንድሪስ
Rate this item
(8 votes)

“ለእያንዳንዱ በሽታ መድኀኒት አለው”

        ጂዎፈሪ ቻውሰር የተባለው ፀሐፊ “General Prologue” በተባለው መፅሀፉ አራት የሙስሊም አረብ ስሞችን ይጠቅሳል - ኢብን ኢሳ፣ ራዚ፣ ኢብን ሲና እና ኢብን ረሽድ ናቸው፡፡ እነኚህ ሰዎች በመጽሃፉ ውስጥ የተጠቀሱት ከረዥም ዓመታት በፊት ለዓለም የህክምና ዘርፍ ባበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ከ8ኛው - 11ኛው ክፍለ ዘመን የአረብ የህክምና ባለሙያዎች ለዛሬው የአውሮፓውያን የሕክምና ጥበብ መሰረት እንደጣሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሮማውያን ግዛት በ15ኛው ክፍለ ዘመን መገርሰሱን ተከትሎ አውሮፓ በብዙ ዘርፍ የነበሯትን የእውቀት ሀብት አጥታለች፡፡ በተለይም የግሪካውያን ሳይንስና የቦይታስ የሒሳብና ሎጂክ ጥበቦች በኢንሳይክሎፒዲያ ውስጥ ከመስፈር ውጭ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው አላገኙም ነበር፡፡ የአውሮፓ የሃይማኖት አዋቂዎች እኒህን ጥበቦች አግኝተው የሚያስፋፉበትና አዲስ ነገር የሚፈጥሩበት እድል አልነበራቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ የአውሮፓ አዲሱ አለም ከህክምና ጥበብ ጋር ተፋታ፡፡
በጊዜው የነበረው የቤተክርስቲያን አመለካከት፣ ከአካላዊ ህክምናዎች ይልቅ መንፈሳዊ ፈውሶች ላይ ያተኩራል፡፡ መድኃኒቶችን መውሰድና አካላዊ ንፅህናን መጠበቅ ተቀባይነት ያልነበራቸው ሲሆን በድን ለሚሆን አካል አለመጨነቅ እንደ ፅድቅ ይቆጠር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መላ አውሮፓውያን በሽታን መግታትም ሆነ መከላከል እንደማይቻል ያስቡ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ በ7ኛው ክፍለ ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቀዶ ጥገና “የሰዎችን መንፈስ ያበላሻል” በሚል ሙሉ ለሙሉ ከለከለች፡፡ የአውሮፓ የቀዶ ጥገና ሳይንስም በዚሁ አከተመ፡፡ በተመሳሳይ ዘመን በምስራቅ በኩል የእስልምና ስልጣኔ ብቅ አለ፡፡ እስልምና ድንበሩን በማስፋፋት ብዙ ሀገሮችን መቆጣጠር ቻለ፡፡ ከዚህ መስፋፋት ጎን ለጎን በብዙ ዘርፎች እውቀቶች እና ትምህርቶች መዳበር ጀመሩ፡፡ እስልምናና የቁርዓን ቋንቋ የሆነው አረብኛ አለማቀፋዊ እየሆኑ መጡ፡፡ ላቲንና ግሪክ በምዕራቡ ዓለም እንደነገሱት ሁሉ የአረብኛ ቋንቋም የምስራቁን ክፍል በሰፊው ተቆጣጠረው፡፡ አረብኛ የሥነ-ፅሁፍ፣ የሳይንስና የምሁራን አንደበት በመሆን እውቅናን አገኘ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር የግሪኮች የሕክምና ሳይንስ በሙስሊም ምሁራን መጠናት የጀመረው፡፡ በ636 ዓ.ም ፐርሺያ በሙስሊሞች እጅ ስር የወደቀች ሲሆን የአረብ አስተዳዳሪዎች ለፐርሺያው ጁንዲሻፑር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የህክምና ምርምር ድጋፍ ማድረግን ሥራዬ ብለው ያዙት፡፡ ሙስሊም ምሁራኖች በዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሒፖክራተስ፣ ጋላንና ሌሎች የግሪክ የህክምና ስራዎች ጋር በቅጡ እየተዋወቁ መጡ፡፡ ከዚህም ባሻገር የባዛንታይን፣ ፐርሺያ፣ ህንድና ቻይና የህክምና እውቀቶችንም መፈልፈል ያዙ፡፡ በዚህ ምክንያት ጁንዲሻፑር ዩኒቨርስቲ ለሙስሊሙ ዓለም ለ200 ዓመት የዘለቀ ታላቅ የህክምና ምርምር ማዕከል ለመሆን በቅቷል፡
በ9ኛው ክፍለ ዘመን በስፋት የተከናወነው የአውሮፓውያንን የህክምና እውቀቶች የመተርጎም ስራ፣ ለአረቦች የህክምና ጥበብ ሁነኛ መሰረት ጥሏል፡፡ ከህክምና መፅሃፍት ትርጉም ጎን ለጎን የሆስፒታሎች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን የመጀመሪያው ሆስፒታልም በ805 በባግዳድ ነበር የተቋቋመው፡፡ በሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥም በመላው የእስልምና ግዛት 34 የሚደርሱ ሌሎች ሆስፒታሎች ተከፈቱ፡፡ ቁጥራቸውም ከዓመት ዓመት እየተበራከተ ሄደ፡፡
ሆስፒታሎች ለበሽተኞች ህክምና ከመስጠት ባሻገር ምርምር የሚካሄድባቸውና የህክምና እውቀቶች የሚስፋፉባቸው ሆኑ፡፡ የህክምና ት/ቤቶችና ቤተ መፃህፍቶችም ጎን ለጎን መቋቋም ጀመሩ፡፡ በ11ኛው ክፍለ ዘመን ላይም ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች ስራ የጀመሩ ሲሆን ፋርማሲዎችም ሊስፋፉ ችለዋል፡፡ ይህም የአረቡን ዓለም የህክምና እድገት እያጠናከረው መጣ፡፡
ነቢዩ መሃመድ (ሰዐወ) “ለእያንዳንዱ በሽታ መድኀኒት አለው” ባሉት መሰረት፣ ሙስሊም የህክምና ተመራማሪዎች፣ እውቀታቸውን ከጥረታቸው ጋር በማጣመር ከፍተኛ የህክምና አብዮት በአረቡ አለም አካሄዱ፡፡ በ9ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መድሀኒቶችን የሚያመርትና የሚያሰራጭ መደብር በባግዳድ የተከፈተ ሲሆን የመጀመሪያው የህክምና ስራም አል-ራዚ በተባለ ባለሙያ ተጀመረ፡፡
አል-ራዚ
አል-ራዚ በምዕራባውያን ዘንድ ራሐዚስ በሚል ስም ይታወቃል፡፡ ከቴህራን አቅራቢያ በምትገኘው ራይ የተባለች የፐርሺያ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ ወጣትነቱን በሙዚቀኛነት፣ በሒሳብና በኬሚስትሪ ሙያ ካሳለፈ በኋላ ወደ ባግዳድ በመሔድ በ40 ዓመቱ ህክምናን ማጥናት ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ራይ ከተማ ተመልሶ፣ በሆስፒታል ውስጥ የአመራር ቦታ ተሰጠው፡፡ ከዚያም ባግዳድ ውስጥ በተገነባው አዲስ ሆስፒታል በዳይሬክተርነት ተሾመ፡፡
አል-ራዚ በአረብ ህክምና ውስጥ በፈርቀዳጅነቱ የሚታወቅ ሲሆን 237 መፃህፍቶችንም ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በህክምና ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ በህፃናት በሽታ ህክምና ላይ የጻፈው መጽሃፉ “የህፃናት ህክምና አባት” አሰኝቶታል፡፡ ንፍጥ የሚያበዛ ጉንፋንና መንስኤውን ተመራምሮ ያገኘ የመጀመሪያው ባለሙያ ነው፡፡ የኩላሊት ጠጠር ላይ ያካሄደው ጥናትም እስካሁን ድረስ ይጠቀስለታል፡፡
አል-ራዚ ከባግዳድ ወደ ትውልድ ቀዬው ራይ በመመለስ፣ በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ የፈውስ ጥበቦችን አስተምሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እውቅናን ያገኘበትን “አል-ኪታብ አል-ማንሱሪ” የተሰኘ መጽሃፍ በ10 ተከታታይ ክፍሎች አቅርቧል፡፡ በዚህ ሥራው የተለያዩ የህክምና ቀመሮችንና ትርጉሞችን እንዲሁም ምግቦችና መድኀኒቶች በሰው ልጅ አካል ውስጥ የሚፈጥሩትን ተፅእኖ አሳይቷል፡፡ በጣም ገናና ስራው ግን “አል-ኪታብ አል-ሀዊ” በሚል በ25 ክፍሎች ያሰናዳው የህክምና ኢንሳይክሎፒዲያ ነው፡፡ አል-ራዚ ህይወቱን ሙሉ ለህክምና የሚሆኑ መረጃዎችን በማሰባሰብ በወቅቱ ለነበረው የህክምና ሙያ ማጠቃለያ መስጠት የቻለ ድንቅ የህክምና ሰው ነው፡፡ ብዙ በሽተኞችን በህክምና ጥበቡ በመፈወስም ስኬት አስመዝግቧል፡፡ ሀኪሞች እንዴት በሽተኞችን በፈጣን ሁኔታ ማከም እንደሚችሉም አሳይቷል፡፡ ከአል-ራዚ ህልፈት በኋላ የተተካው አል-ሁሴይን ኢብን አብደላህ ኢብን ሲና (980-1037) ሲሆን በአውሮፓውያንና በላቲኖች ዘንድ አቪሲና በመባል ይታወቃል፡፡
አቪሲና
አል-ሁሴን ኢብን አብደላ ኢብን ሲና (980-1037) ወይም አቪሲና የተወለደው አሁን ኡዝቤክስታን፣ ቀድሞ ቡካራ በምትባለው ጥንታዊቷ የፐርሺያ ከተማ ነው፡፡ አርስቶትል የግሪካውያን፣ ገተ የጀርመናውያን እንደሆኑት ሁሉ አቪሲናም የአረቦች እንቁ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የአቪሲና እውቀት በህክምና ጥበብ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ በሙዚቃ፣ በግጥምና በእደጥበብ እውቀቱም የመጠቀ ነበር፡፡ በመላው አውሮፓ አሁንም ድረስ “የሐኪሞች ልዑል” በሚል ቅጽል ስሙ ይታወቃል፡፡
ከግብር ሰብሳቢ አባቱ የተወለደው አቪሲና፤ በአስር ዓመቱ ሁሉንም የቁርዓን አንቀፅ ሸምድዶ ሀፊዝ ለመሆን ቻለ፡፡ ከዚያም ህግ፣ ሒሳብ፣ ፊዚክስና ፍልስፍና ተማረ፡፡ በ16 ዓመቱ ወደ ሕክምና ጥናት ገባ፡፡ በ18 ዓመቱም የሳማኒድ ልዑል የነበረውን ኑህ ኢብን መንሱርን በማከም ታዋቂ ዶክተር ሊሆን ቻለ፡፡ ይሄም በቡካራ ታዋቂ በነበረው የንጉሳዊያን ቤተ-መጽሐፍት ገብቶ እውቀት እንዲቀስም እድል ከፍቶለታል፡፡ ኢብን ሲና ከዓመት ዓመት በሥራ የተወጠረ ባተሌ ቢሆንም በተገኘው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ይጽፍ ነበር፡፡ ከነዚህም ውስጥ በሃይማኖት፣ በፊዚክስ፣ በአስትሮኖሚ፣ በቋንቋና ስነ-ግጥም ዙሪያ የጻፋቸው ይጠቀሱለታል፡፡ “ኪታብ-አል-ሺፋ”(The Book of Healing) የተሰኘውን የህክምና መጽሃፉን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል፡፡ እጅግ ታዋቂ ሥራው “ቃኑን ፊ-አል ጢብ” (The Canon of Medicine) የተሰኘው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቃላት የያዘው መጽሃፉ ሲሆን በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ያልተካተተ የህክምና ጥበብ የለም ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ መጽሃፉ በዋነኝነት ምግብና የአየር ንብረት በሰው ልጅ ጤና ላይ ያላቸውን ተጽእኖ በሰፊው ያብራራ ሲሆን የጡት ካንሰር፣ኪንታሮት፣ ምጥና የመመረዝ ፈውሶችንም ይፋ አድርጓል፡፡ እኒህ ብቻ ግን አይደሉም፡፡ ስለ ማጅራት ገትርና ከእሱ ጋር የሚመሳሰሉ በሽታዎች መለያ ባህሪያት፣ ስለ ኩላሊት በሽታ፣ ስለ ሰውነት በድን መሆንና ስለ ጨጓራ ቁስለት ከእነመንስኤያቸው ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ 760 የሚደርሱ የህክምና ዕጽዋትንና መድሃኒቶችንም በመጽሃፉ አስተዋውቋል፡፡
“ቃኑን ፊ-አል ጢብ” (The Canon of Medicine) የተሰኘው መጽሃፉ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በመላው ዓለም የህክምና ማስተማሪያና ማጣቀሻ በመሆንም አገልግሏል፡፡
በ10ኛው ክፍለ ዘመን የአረቦች የምርምር መፅሀፍት በካታሎኒያን ተርጓሚዎች መተርጎምን ተከትሎ አውሮፓውያን የአረቦችን የእውቀት ሀብት መድፈር ጀመሩ፡፡ አረቦች የእነ ሒፖክራተስን የህክምና ጥበቦች አዳብረው የፈጠሯቸው አዳዲስ ግኝቶች ተመልሰው አውሮፓውያን እጅ ገቡ፡፡ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የኢብን ሲና ስራ የሆነው “አል-ጢብ” (The Canon) ኮፒ እየተደረገ የአውሮፓውያን የህክምና ሥራ ማጣቀሻ ሆነ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአል-ራዚ የህክምና መፅሀፍ “አል-ኪታ አልሀዊ” የህትመት ፈጠራ እንደተጀመረ ተተርጉሞ ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኘት ችሏል፡፡ ዘጠነኛው የአል-ኪታብ “አል-መንሱር” መፅሀፍ (ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ ያሉ በሽታዎችን የያዘ ነው) በቱቢንጂን ዩኒቨርሲቲ እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የህክምና ካሪኩለም ሆኖ አገልግሏል፡፡
አውሮፓውያን ዛሬም ድረስ ለኢብን ሲና እና አል-ራዚን የህክምና ስራዎች ትልቅ ቦታ ይሰጧቸዋል፡፡ የእነኝህ ሁለት ተመራማሪዎች ታሪክና ሥራዎች በፓሪስ የህክምና ዩኒቨርሲቲ ተሰንደው ተቀምጠዋል፡፡
በአውሮፓውያን ላይ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉት ኢብን ሲናና አል-ራዚ ብቻ አይደሉም፡፡ ከ400 መፅሃፍት በላይ የተተረጎመላቸው በአይን ህክምና፣ በቀዶ ጥገና፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በህጻናት እንክብካቤና ጤና ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሌሎች አረቦችም አሉ፡፡ እንግዲህ እነኝህ ናቸው የአውሮፓውያንን የህክምና ሳይንስና ዘመናዊውን ጥበብ አድሰው የወለዱት፡፡
ምንጭ (Aramco world, David Tschanz)

 

Read 5103 times