Saturday, 20 September 2014 10:43

የሚዲያ ጥቅም ያልገባት ሀገር!

Written by  መድሃኔ ግደይ (በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር)
Rate this item
(2 votes)

የማስተካከያ መልዕክት ለተወዛገበውና ላወዛገበው ኢቴቪ

       ውድ አንባብያን፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ እነሆ በዚሁ ነጻ አስተያየት ዓምድ ዛሬ ተገናኘን፡፡ እንኳን አደረሰን! ሰሞኑን የመነጋገርያ አጀንዳ በሆነውና በኢቴቪ በተላለፈው “ያልተገሩ ብዕሮች” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ዙርያ አንዳንድ ጉዳዮች በመመዘዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በርካታ የሙያ ክፍተት ባስተናገደው ዘጋቢ ፊልም ላይ በእንግድነት ተጋብዤ ቃለ መጠይቅ መስጠቴን ባለፈው ጊዜ መግለጼ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢቴቪ (ኢብኮ) የጋዜጠኝነት ሙያ ከሚጠይቀው አግባብ ውጪ በሆነ መልኩ በርካታ ነገሮች ተቆራርጠው ጣቢያው የሚፈልገውን መልዕክት ማስተላለፍ እንደቻለ ማስረጃዎችን በማካተት በዝርዝር አቅርቤ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ አቶ ታምራት ደጀኔ የተባሉ ወዳጄ፣ በዚሁ ዓምድ “አድርባይነት የተጠናወተው የምሁሩ አስተያየት” በሚል ርዕስ፣ ከዕውቀት የጸዳ ምላሻቸውን አስፍረዋል፡፡ ምንም እንኳን ላቀረቡት ያልሰለጠነ ሂሳቸው ሙሉ አክብሮት ቢኖረኝም፤ አስተያየታቸው ከዘጋቢው ፊልም ያልተናነሰ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት ግን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡

በመሆኑም ኢቴቪን “ገለልተኛ” ነው ለማለት የደፈሩት እኝህ አስተያየት ሰጪ፤ የማስተካከያ ምላሽ ካልተሰጣቸው በተሳሳተ መንገድ ህዝቡን ማሳሳታቸው እንደማይቀር ግልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያ ስህተታቸውን ለማረም ዝግጁ ከሆኑ አንዳንድ ማስተካከያ ባጭሩ ልስጥ፡፡ አቶ ታምራት፤ ለመሆኑ ኢቴቪ ገለልተኛ ነው ለማለት ያስደፈራቸው ምን ይሆን? ለነገሩ የኢቴቪን ገለልተኛነት ደግፎ ለመከራከር በዕውቀት የተመሰረተ ምክንያት ማጣታቸውን ምክንያት አልባው ምላሻቸው ይናገራል፡፡ ወዳጄ፤ ገለልተኝነት በጋዜጠኝነት መነጽር ሲታይ፣ ከሌሎች ዘርፎች ለየት የሚያደርጉት አንዳንድ ነጥቦች አሉ፡፡ እርስዎ እንዳሉት፤ የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን፤ ከማንኛውም ዓይነት ተፅዕኖ ነጻ መሆን (distance from faction) ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ጋዜጠኛ መረጃውን አሰባስቦ ካበቃ በኋላ ሙያዊ ስነምግባሩን ተከትሎ ህዝቡ ዘንድ መድረስ ያለበትን በነጻነት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የጋዜጠኝነት መርህ ደግሞ የተገኘውን መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ (verification) ነው፡፡ ይህ መርህ ጋዜጠኝነት ከልቦለድ፣ ፕሮፓጋንዳና ማስታወቂያ የመሳሰሉት የጥበብ ስራዎች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ይህን መርህ አንዳንድ ምሁራን ሲያብራሩ፤ ማንኛውም ጋዜጠኛ እናቱ እንኳን እወድሃለው ብትለው ማረጋገጥ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

የእናት ፍቅር በመጠራጠራቸው ሳይሆን ደጋግሞ ማጣራትና ማረጋገጥ ትልቁ የጋዜጠኝነት መርህ መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡ ስለ ሁለቱም ተያያዥ መርሆች ይህን ያህል ካነሳሁ፣ አሁን ወደ ኢቴቪ ልመለስ፡፡ ኢቴቪ በብቸኛ የዜና ምንጭነት ጋዜጣዊ መግለጫ (press release) ወይም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚያዘጋጁትን ዜና በስፋት እንደሚጠቀም የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በየትኛውም ሚዲያ እነዚህን የዜና ምንጮች እንደብቸኛ የዜና ምንጭ አድርጐ መጠቀም አይመከርም፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ግንኙነት ለሚሰራበት ድርጅት በጐ ገጽታ ግንባታ የሚተጋ ሲሆን ጋዜጠኝነት ግን ከዚህ በተለየ መልኩ እውነታውን ለህዝቡ ለማሳወቅ የሚታትር በመሆኑ ነው፡፡ እና ታዲያ የቱ ጋ ነው ገልተኝነቱ? በተዘዋዋሪ ኢቴቪ የተለያዩ ድርጅቶችን (ገዢውን ፓርቲ ይጨምራል) በጐ ገጽታ በመገንባት የራሱ ሚና ይጫወታል ማለት ነው፡፡ ሌላው አቶ ታምራት አንስተውት በተሳሳተ መንገድ ካቀረቡት መርህ አንዱ ሚዛናዊነት ነው፡፡ ሚዛናዊነት የሚባለው አንድ ፕሮግራም የተለያዩ አመለካከቶችን ተገቢ (fair) በሆነ መልኩ ሲያቀርብ ነው፡፡ ይህም ማለት በኢቴቪ ዶክመንታሪ ላይ የግል ሚዲያውን በመደገፍ፣አሳማኝ ምክንያቶችን ማቅረብ የሚችል ማንኛውም ሰው በዚሁ ሚዛናዊ ያልሆነው ዘጋቢ ፊልም ላይ መቅረብ ነበረበት፡፡ እነዚህ የተለያዩ አመለካከቶች ተመጣጣኝ የሆነ የአየር ሰዓት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ይህም ተመልካቹ በጉዳዩ ዙርያ የተሟላ ምስል እንዲኖረው ያስችላል፡፡ የሚያሳዝን የሙያ ግድፈቶችን ያስተናገደው ዘጋቢ ፊልሙ፤ተመሳሳይ መልዕክት ከማስተላለፉ በተጨማሪ ሚዛናዊ አለመሆኑ ለመረዳት እኔ ያቀረብኩት ሐሳብ መቆረጡ ማሳያ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው፣ ይህን ዘጋቢ ፊልም ለማድነቅ ምን ይሆን የገፋፋዎት? አንድ ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ ታሳቢ መሆን ካለባቸው ነገሮች አንዱና ትልቁ ነገር ጥናት (research) ነው፡፡ ይህንን እንዳለመታደል ሆኖ በኢቴቪ በሚሰሩት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ አንመለከተውም፡፡ እንደ ምሳሌ ቢቢሲና ሲኤንኤንን በመሳሰሉት ትልልቅ የመገናኛ ብዙሃን፣ በበቂ ጥናት ላይ ታግዘው የሚሰሩ ሚዛናዊ የሆኑ ዶክመንተሪዎቻቸውን ማየት በቂ ነው፡፡ ምንም እንኳን የቴክኖሎጂና ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሩም ሙያው የሚጠይቀውን ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ግን ህዝብን በቅንነት የማገልገል ፍላጎት በቂ ይመስለኛል፡፡ አስተያየት ሰጪው እኔ ባቀረብኩት ሐሳብ ላይ ትኩረት በማድረግ፣አስተያየታቸውን በምክንያት በማስደገፍ ማቅረብ ሲገባዎ፣ “አድርባይነት፣ ያዙኝ ልቀቁኝ…” በመሳሰሉት ቃላት እኔን ለመግለፅ ሞክረዋል፡፡ ቁምነገሩ እኔ የሰጠሁት አስተያየት መቆረጡ ብቻ ሳይሆን ኢቴቪ ሚዛናዊ ባልሆነው ዘገባው ህዝቡን የማሳሳት ዘመቻውን መቀጠሉ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ባለ አንድ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት መሆናችን ነው እንጂ ይህ ጣቢያ እንደዚህ ሰፋ ያለ ትኩረት ስለማግኘቱ እጠራጠራለሁ፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለመጠይቅ መስጠት ነውር ነው የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ግን አልፈልግም፡፡ ምናልባት በመለፍለፍ ላይ ብቻ የተጠመደው ይህ ድርጅት፤ መስማት ከጀመረ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ እንዲለወጥ የሁላችንም ምኞት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ታምራት፤ “ፅንፈኛ” ያሉትን የግሉን ሚዲያ መተቸትን እንደ ጦር መፍራቴን በአስተያየታቸው አንስተው ነበር፡፡ የግል ሚዲያው በተለይ ጋዜጦች የግል አስተያየቶች መጠራቀምያ እየሆኑ መምጣታቸው በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ሐሳብን የመግልፅ መብት መበረታታት ቢኖርበትም እነዚህ የግል ሚዲያዎች ሙያው የሚጠይቀውን አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች መዘንጋታቸው ግልፅ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ የግል ጋዜጣ መካተት ያለበትና ትልቁ የጋዜጠኝነት ስራ የሆነውን የዜና እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህ የግሉንና የመንግስት ሚዲያን ለመተቸት የሚያስችል ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን ስፈልገናል፡፡ የህዝቡ የማወቅ መብቱ መገደቡና አማራጭ የመረጃ ምንጭ (alternative source of information) እየጠበበ መምጣቱ በጣም አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው የግል ሚዲያውን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ማንኛውም ዘመቻ መገደብ የሚኖርበት፡፡ ከሌላው በተለየ መልኩ በሚዲያ ላይ የሚደረገው ማንኛውም አስተያየት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ በጨቅላነት እድሜው ላይ የሚገኘው የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንዳይጠፋ እሰጋለሁ፡፡ የጥርስ ሀኪም ዓይን እንደማያክም እየታወቀ፣ ለምን ሙያውን ለባለሙያ እንደማንሰጥ ግልጽ አይደለም፡፡ በ1930ዎቹ የአሜሪካ ቀዳሚ እመቤት የነበሩት ኤልኖር ሩስቬልት፤ ሰዎችን በሚወያዩበት ርዕስ ዙሪያ ለሶስት ይከፍሏቸዋል፡፡ የመጀመሪዎቹ ያልሰለጠነ አስተሳሰብ (small minds) ያላቸው ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች በግለሰቦች ዙርያ መወያየት ይቀናቸዋል፡፡ ሌሎቹ መካከለኛ አስተሳሰብ (Average minds) ያላቸውና በክስተቶች (events) ዙሪያ የሚነጋገሩ ናቸው፡፡ ከነዚህ በተለየ መልኩ የሰለጠነ አስተሳሰብ (great minds) ያላቸው ሰዎች በበኩላቸው፤ በሀሳብ (idea) ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡

ወዳጄ! የቱ ላይ ራስዎትን አገኙት? የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዕውን ለማድረግ ከተፈለገ፣ መንግስት በቂ የመጫወቻ ሜዳ መፍቀድ አለበት፡፡ ይህ ሜዳ ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት የጸዳና ጋዜጠኞች በነጻነት የሚሯሯጡበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ጋዜጠኞችም ፕሮፌሽናል መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ጋዜጠኝነት ሀብትን ለመሰብሰብ አልያም ዝናን ፍለጋ የሚገቡበት ሳይሆን ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ተረድተው፣ ህዝብን ለማገልገል ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገለልተኛ የሆነ ዳኛ ያሻዋል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች የሙያ ክፍተት ሲኖርባቸው፣ መንግስት ሳይሆን ይህ ገለልተኛ ዳኛ ሙያዊ አስተያየት የሚሰጥበት ሊሆን ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች በበኩላቸው፤ ሚዲያ የግል ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት ሳይሆን ትልቅ የልማትና የዴሞክራሲ መሳርያ መሆኑን አውቀው፣ ሚዲያውና ህዝቡ እንዲቀራረቡ የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው፡፡ በህመም ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን መታከም ይኖርበታል፡፡ በርቀት ከመሰዳደብ ተቀራርቦ መወያየት ይበጃል፡፡ መፈቃቀር ባይጠበቅብንም በሰለጠነ መልኩ መነጋገር የግድ ነው፡፡

Read 3853 times