Monday, 22 September 2014 14:18

“የኩረጃና የግልበጣ ዘመን ማብቃት አለበት”

Written by  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና ምሁር)
Rate this item
(8 votes)

ያለፈውን ዓመት ከሁለት አኳያ ነው የምመለከተው፡፡ አንደኛው ከግል አኳያ ሲሆን ሁለተኛው ከሃገራችን ሁኔታ በተለይም ከፖለቲካው አኳያ ነው፡፡ በግል ደረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያስተማርኩ ነው የከረምኩት፡፡ ቤተሰቦቼ ቦስተን አሜሪካን ይኖራሉ፤ እነሱ ናፍቀውኛል፤ ሄጄ ማየት እፈልጋለሁ፡፡
በሃገር ደረጃ የዲሞክራሲ ሂደቱ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፉ በኋላ ትንሽ የመደናበር፣ የመደናገጥ ሁኔታ አለ፡፡ በአንድ በኩል በአቶ መለስ አለመኖር፣ በሌላ በኩል በምርጫው መቃረብ የተነሳ እቺን ጨቅላና ሙከራ ላይ ያለች ዲሞክራሲ ገዥው ፓርቲ መሸከም ያቃተው ይመስላል፡፡ አሁን ደግሞ ወጣት ጦማሪያንን፣ ፀሃፊዎችን ማዋከብ ይዟል፡፡ ከ3 ወር በፊት ጦማሪያን ሲታሰሩ በጋዜጠኞች ላይም ሊቀጥል ይችላል ብዬ ነበር፡፡ ይሄም እየሆነ ነው፡፡
አሁን የተፈለገው አንድ ዓይነት ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሃገር ጥሩ አይደለም፡፡ ኢህአዴጐች ከ20 ዓመት በላይ ሃገሪቱን ካስተዳደሩ በኋላም ራሳቸውን የመተቸት ልማድ አላካበቱም፡፡ አንድ አመራር ደግሞ ራሱን የመተቸትና ሌሎችም እንዲተቹት የመፍቀድ ባህሉን ካላጠናከረ ችግር አለው ማለት ነው፡፡
የአዲስ ዓመት ምኞት ሲባል ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ የሚባለው ሰላም ብልፅግና … ነው፡፡ ሰላምና ብልፅግናማ ዘመን በተቀያየረ ቁጥር ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ እኔ በአዲሱ ዓመት ወደ ራሳችን ቀልብ እንድንመለስ፣ ኢትዮጵያ ኮራጅና ገልባጭ መሆኗን እንድታቆም ነው የምመኘው፡፡ አሁን ምን ማለት ነው “EBC” ማለት? የአማርኛ፣ የኦሮምኛ ወይም ሌላ የአገራችን ቋንቋ ቃል ጠፍቶ ነው? አማርኛውን ጠላነው ካሉ ለምን መናገሩን አይተዉትም?! ይሄ የግልበጣና በራስ ያለመተማመን ችግራችንን ፈትሸን ነው ዘመን እንድንሻገር የምፈልገው፡፡ ቲያትሩ፣ ሲኒማው፣ ሬዲዮ ፕሮግራሙ ኩረጃ ነው፡፡ ይህ የግልበጣ ዘመን ይቁምና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ትሁን ነው የምለው፡፡ እንግዳ ተቀባይ ነን፣ እንደኛ የሚያምር የለም… ወዘተ እያልን ለራሳችን የተለየ ግምት የምንሰጥባቸውን አባባሎች ማቆም አለብን፡፡ የትኛውም ሃገር እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡ ጥሩ ሃገር፣ ትልቅ ሃገር አለን፤ በዚህ ደረጃ እናስብ፡፡

Read 2666 times