Saturday, 27 September 2014 08:37

የዶ/ር ሃምሊን 90ኛ አመት ልደት ዛሬ በአሜሪካ ይከበራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባና በአምስት ክልሎች ባቋቋሟቸው የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና ማዕከላት ከ40ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታማሚዎች የህክምና እርዳታ በመስጠት የሚታወቁት የዶ/ር ካትሪን ሃምሊን 90ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ሪትዝካርልተን ይከበራል፡፡ የፕሮግራሙን አዘጋጆች በመጥቀስ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ እንደዘገበው፣ ዶ/ር ሃሚሊን በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ልዩ መልዕክት እንደሚያስተላልፉና በወሊድ ምክንያት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን ለማጥፋት ርብርብ እንዲደረግ ያስተላለፉትን ጥሪ ተቀብለው የራሳቸውን ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ዝግጅቱን እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ የዶ/ር ሃምሊን የ90ኛ አመት የልደት በዓል፣ የተከበሩ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ ከአገር ውስጥና ከሌሎች የአለም አገራት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ጥር ወር በአዲስ አበባ መከበሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ዶ/ር ሃምሊን ፌስቱላን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ላለፉት 55 አመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም በአገሪቱ ከፍተኛ የጤና ችግር ሆኖ የቆየውንና ተገቢ ህክምና ያልነበረውን ፌስቱላን ለማጥፋት ይዘው ለተነሱት ታላቅ ራዕይ መሳካት እገዛ የሚያደርገውን የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ተጠቃሽ ሰው መሆናቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ፌስቱላ በአፍሪካ ከአስራ ሁለት ሴቶች በአንዷ ላይ የሚከሰት አሳሳቢ የጤና ችግር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Read 1282 times