Saturday, 27 September 2014 08:49

የኩዌት አሚር “የሰብአዊ ሥራዎች መሪ” ተብለው ተሸለሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

                  የ4.5ቢ. ዶላር ድጋፍ አድርገዋል የኩዌት አሚር የተከበሩ ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-አልጃበር አል-ሳባህ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለዩ ለዓለም ህዝብ ባደረጉት የተለያዩ ድጋፎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ “የሰብአዊ በጎ አድራጎት ስራዎች መሪ” በማለት እንደሸለማቸው የኩዌት አምባሳደር አስታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በዩጋንዳ የኩዌት አምባሳደር ሺድ አልሃጅሪ፣ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሚሩ ሊሸለሙ የቻሉት፣ ባላቸው መልካም አመለካከትና ቅን አስተሳሰብ የህዝቦችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ለመርዳት ያደረጉትን ሰብአዊ ስራ ለማጉላትና እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሚሩ ያደረጉት ሰብአዊ ድጋፍ 4.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰው፣ 2.5 ቢሊዮን ዶላሩ የአፍሪካ ድርሻ ነው ብለዋል፡፡ ጥቃቅንና መካከለኛ ቢዝነሶች ለመደገፍና ለማበረታታት 500 ሚሊዮን ዶላር፣ ምስራቃዊ ሱዳንን እንደገና ለመገንባት 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ድጋፍ 34 ሚሊዮን ዶላር፣ ለአፍሪካ ህብረት የጤና ክሊኒክ ማስፋፊያ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች 1 ቢሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ ለ13 የሰብአዊ በጎ አገልግሎት ሥራዎች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ስለኢትዮጵያና ኩዌት ግንኙነት የተጠየቁት አምባሳደሩ፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ግንኙነቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሱት በማስታወስ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ባደረጉት ጥረት፣ ሁለቱ አገራት 14 የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ገልፀዋል፡፡ በኩዌት ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ መንግስታቸው ምን እርምጃ እንደወሰደ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “ኩዌት በህግ ተቋም የምትተዳደር አገር ስለሆነች፣ ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ህጉን ለማስከበር በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራሉ፤ የኩዌት ህግ ለማንም አያደላም፤ የአገሩም ሆነ የውጭ ዜጎች እኩል ነው የሚዳኙት፡፡” ብለዋል አምባሳደር ራሺድ አልዛድሪ፡፡ በኩዌት 80ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

Read 2020 times