Saturday, 27 September 2014 08:57

“ክራውን ፕላዛ ሆቴል” የስያሜ እግድ ተላለፈበት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ሆቴሉ የብድርና የኮንትራት ማናጅመንት ስምምነቶችን ነገ ይፈራረማል

ግንባታው ከ18 ወራት በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል የተባለው የአለማቀፉ ኢንተርኮንቲኔንታል ግሩፕስ አካል የሆነው “ክራውን ፕላዛ ሆቴል”፤ በአዲስ አበባ በአገልግሎት ላይ ከሚገኘው “ክራውን ሆቴል” የስያሜ ኮፒ ራይት መብት ጥያቄ ቀርቦበት ፍ/ቤት የንግድ ስያሜ እግድ አስተላልፎበታል፡፡ “ክራውን” የሚለው ስያሜ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የተመዘገበና በስራ ላይ የሚገኝ እንደሆነ የጠቆመው “ክራውን ሆቴል”፤ ስያሜው ለሌላ አካል መሰጠቱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ለፍ/ቤቱ ይግባኝ ብሏል፡፡ “ክራውን ሆቴል” የሚለው የንግድ ምልክት በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት ተመዝግቦ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ20 አመታት በላይ አስቆጥሯል የሚለው ለይግባኝ ሰሚ ፍ/ብሔር ችሎት የቀረበው የሆቴሉ ማመልከቻ፤ ውሳኔው “ክራውን ሆቴል” በሁለት አስርት ዓመታት ያገኘውን ስምና ዝና እንዲሁም ገበያውን አዲሱ ሆቴል እንዲሻማበት የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት “ክራውን ሆቴልን” ሳያማክር ሚያዚያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ኢንተርኮንቲኔንታል ፕሩፕስ አካል ሆነው ሆቴል “ክራውን ፕላዛ” የሚለውን ስያሜ መፍቀዱ አግባብ አይደለም ሲል ይግባኝ የጠየቀው ክራውን ሆቴል፤ ፍ/ቤቱ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የሰጠው ውሳኔ የይግባኝ ባይን በንግድ ምልክቱ የመጠቀም ህጋዊ መብት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ፍ/ቤቱ ተገንዝቦ የፅ/ቤቱን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመሻር ስሙ በድጋሚ የተሰጠው ሆቴል “ክራውን ፕላዛ” በሚለው የንግድ ምልክት መጠቀም አይችልም የሚል ውሳኔ እንዲሰጥለት በሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም ለፍ/ቤቱ በፅሁፍ አመልክቶ ነበር፡፡ ፍ/ቤቱም መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ይግባኝ ባይ መስከረም 5 ቀን 2007 ዓ.ም በቃለ መሃላ በተደገፈ አቤቱታ እግድ መጠየቃቸውን አስታውቆ በሰጠው ትዕዛዝ፤ ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የሰጠው ውሳኔ አፈፃፀም ታግዷል ብሏል፡፡

የይግባኝ ቅሬታውን ለመስማትም ለጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የንግድ ምልክትና ኢንስፔክሽን ዋና የስራ ሂደት ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ፅጉ፤ የፍ/ቤቱ እግድ ትዕዛዝ እንደደረሳቸው አረጋግጠው፣ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ በመሆኑ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ፣ ነገር ግን ጽ/ቤታቸው የፍ/ቤቱን እግድ እንደሚያስከብር ገልፀዋል፡፡ አለማቀፍ የሆኑ የሆቴልም ሆነ ሌሎች ኩባንያዎች ስያሜና የንግድ አርማ የሃገራችን ኩባንያዎች በምን አግባብ ነው እንዲጠቀሙ የሚደረገው ስንል የጠየቅናቸው ዳይሬክተሩ፤ “ባለ ኩባንያው የንግድ ምልክቱን ያስመዘግባል፤ በንግድ ምልክቱ ዙሪያም ተቃዋሚ ካለ እንዲቀርብ የጋዜጣ ማስታወቂያ ይወጣል፤ ካልቀረበና በምርመራ ከተረጋገጠ ይሰጠዋል፤ በዚህ መንገድ ነው የሚስተናገደው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የስትራክቸር ግንባታ ስራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ የተገለጸው “ክራውን ፕላዛ ሆቴል”ን የሚያስገነባው ፀሜክስ ሆቴሎችና ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ ማህበር ከአለም ባንክ ጋር የ19 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የሚፈራረም ሲሆን በፀሜክስ እና በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ግሩፕ መካከል ደግሞ የሆቴል ማናጅመንት ኮንትራት ውል ስምምነት በነገው ዕለት ይፈራረማል ተብሏል፡፡

Read 2762 times