Saturday, 27 September 2014 09:07

አፈኛ ሴት፤ የአምስት ዳኛ ሚስት ነኝ፤ ትላለች

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(አዋቄ ሞሽሪያ ተ እቸሹ እራሻ መቾ ገውሱ) - የወላይታ ተረት

አንዳንድ ተረቶች በአንድ ወቅት አልደመጥ ሲሉ በሌላ ወቅት ተደግመው መነገራቸው ግድ ይሆናል፡፡

የሚከተለውም እንደዚያው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሰፊ መስክ ላይ እየጋጡ ሳሉ፤ ሶስት ጅቦች የሚበላ ፍለጋ

ሲዘዋወሩ ያገኙዋቸዋል፡፡
ጅቦቹ ገርሟቸዋል፡፡
አንደኛው ጅብ፤
“እነዚህ አህዮች እንዴት ቢጠግቡ ነው በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት እንደዚህ ተዝናንተው የሚግጡት?”
ሁለተኛው ጅብ
“ዕውነትም የሚገርም ነው፡፡ የተማመኑት ነገር ቢኖር ነው እንጂ እንዲህ ያለ ድፍረት አይፈጽሙም ነበር”
ሦስተኛው ጅብ
“ታዲያ ለምን ችሎት ተቀምጠን አንፈርድባቸውም?” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡
አህዮቹን ከበቡና ተራ በተራ ሊጠይቋቸው ተሰየሙ፡፡
የመጀመሪያዋን አህያ ጠሩና ጠየቋት፡፡ የማህል ዳኛው ነው የሚጠይቃት፡፡
“እሜቴ አህያ፤ ለመሆኑ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት፣ በጠፍ ጨረቃ፣ እንዲህ ዘና ብለሽ የምትግጪው ማንን

ተማምነሽ ነው?”
እሜቴ አህያም፤
“አምላኬን፣ ፈጣሪዬን፣ ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ግፍ የሚሠራን አምላኬ ዝም አይለውም፡፡ መዓት

ያወርድበታል፡፡”
የማህል ጃኛው ጅብም፤
“መልካም ሂጂ፡፡ ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት”
ለሁለተኛዋ አህያም ጥያቄው ቀረበላት:-
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት
ፍንጥዝጥዝ ብለሽ የምትግጪው?”
ሁለተኛይቱ አህያም፤
“ጌታዬን፣ አሳዳሪዬን ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ጥቃት የሚያደርስን ማንንም ቢሆን ጌታዬ ዝም አይለውም፡፡

ይበቀልልኛል ብዬ በማመን ነው” ስትል መለሰች፡፡
ማህል ዳኛው ጅብ፤
“መልካም፡፡ አንቺም ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት” አላት፡፡
ሦስተኛይቱ ቀረበች፡፡
ማህል ዳኛው ጅብም፤
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው ይሄ ሁሉ መዝናናት?” አላት
ሦስተኛይቱ አህያም፤
“እናንተን፣ እናንተን፣ የአካባቢውን ገዢዎች ተማምኜ ነው ጌቶቼ”
ዳኛውም፤
“መልካም፡፡ ሁላችሁም ፍርዳችሁን ጠብቁ” አሉና ሸኟት፡፡
ዳኞቹ መምከር ጀመሩ፡፡
ግራ ቀኝ ዳኞች አስተያየት ከሰጡ በኋላ፤ የመካከል ዳኛው ጅብ እንዲህ አሉ :-
“የመጀመሪያዋን ብንበላት እንዳለችው አምላክ አይለቀንም፡፡ ይበቀልላታል፡፡ ሁለተኛዋን ብንበላት ምናልባት

አሳዳሪ ጌታዋ ተከታትሎ፣ ያጠፋናል፡፡ ይቺን ሶስተኛዋን፣ እኛን የተማመነችውን ብንበላት ማናባቱ ይጠይቀናል?”

ሲል መሪ - ሀሳብ አቀረበ፡፡
ሁለቱ ጅቦች ባንድ ድምጽ፤
“ዕውነት ነው፡፡ እኛን የተማመነችውን እንብላት!” አሉ፡፡
እነሱን የተማመነችው ላይ ሰፈሩባት፡፡
***
የጌቶች አስተሳሰብ ምን እንደሚመስል ተገዢ ወዳጆች ማወቅ አለባቸው፡፡ ሎሌነቱንም በቅጥ በቅጥ አለመያዝ፣

የመጨረሻውን ቀን ከማፋጠን አያልፍም፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ የሚለውን ተረት፤ በአፉ የሚንጣጣ

ሁሉ በጊዜ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ መጨረሻው፤ “ያመኑት ፈረስ፣ ይጥል በደንደስ” ነውና፡፡ “እናቴን ያገባ ሁሉም

አባቴ ነው” ለሚሉ የዋሀን ሁልጊዜ ፋሲካ ሊመስላቸው ቢችልም፤ ለሁሉም ጊዜ አለውና “ምነው ምላሴን

በቆረጠው” የሚያሰኝ የፍርድ ቀን እንደሚኖር አሌ አይባልም፡፡
“እንብላም ካላችሁ እንብላ፤ አንብላም ካላችሁ እንብላ” በሚል ጅባማ ፍልስፍና ውስጥ መበላላት መሪ መርሀ -

ግብር መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡
“ለጋማማ አህያም ጋማ አላት
አያስጥልም እንጂ ጅብ ሲዘነጥላት” ሲባል የከረመው ያለ ነገር አይደለም፡፡
“እነሆ ብዙ ዘመን አለፍን፡፡ ከሁሉም የተረፈን ብዙ ምላሶችና እጅግ ጥቂት ልቦች ናቸው” ይላል ሲ ጆርጅ

የተባለ ፀሐፊ፡፡ በሀገራችን በቅንነት ሃሳብ የሚሰጡና በሎሌነት ሃሳብ የሚሰጡ መለየት አለባቸው፡፡ “ውሸት

አለምን ዞሮ ሊጨርስ ሲቃረብ ዕውነት ገና ቦት ጫማውን እያጠለቀ ነው” መባሉ በምክን እንጂ በአቦ - ሰጡኝ

አይደለም፡፡ በየአገሩ፤ የንጉሥ አጫዋቾች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ የጋራ ባህሪ ግን አላቸው - ንጉሱ ሲያስነጥሱ

ማስነጠስ፡፡ አድር ባይነት፡፡ በመካያው ራሱ አድርባዩ ማንነቱ ይጠፋበትና “የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ” ማለት

እንኳን ይሳነዋል፡፡ “ነገር አንጓች፤ እንኳን ለጌታው ለራሱም አይመች” ነውና ፍፃሜው አጓጉል መሆኑ ዕሙን

ነው፡፡
የትዕዛዝ ሁሉ ጉልላት ለህሊና መታዘዝ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ ህሊናውን ሲክድ
አታላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ብልጥ ለማኝ፤ “ጌታዬ ጌታዬ አምና የሰጡኝን ልብስ አምስት ዓመት ለበስኩት”

እያለ ይኖራል፡፡ በዕውቀት ያልተደገፈ ድፍረት፣ የህሊና ማጣት ምርኩዝ ነው፡፡” ወትሮም፤ “መራዡ ተኳሹ” ሲል

የኖረ፣ “በራዡ ከላሹ” ማለት ከጀመረ ሁለተዜ ጥፋት ነው፡፡ ሀገራችን አያሌ አድር - ባይ አይታለች፡፡ ለሀገራችን

ጐታቿም አጥፊዋም፣ “አሾክሿኪው” ነው፡፡ ከታሪክ መማር ዕርም በሆነባት አገር ቀለሙን እየለዋወጠ አድር -

ባይ ሁሉ እየመጣ፤ “እንቅፋት በመታው ቁጥር ቲዎሪ ድረሽ” (ያውም ዕውነተኛ ቲዎሪ ካለው) እያለ፤ “መንገድ

ባስቸገረው ቁጥር” መመሪያ ማሪኝ” እያለ ህሊናውን እየሸጠ ይኖራል፡፡ ልባም አይደለምና አፍ ያወጣል፡፡ ምላሱ

እየረዘመ፣ አንጐሉ እየጨለመ ይሄዳል፡፡ አበው “ከመሃይም ምላስ ይሰውረን” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ማህታማ

ጋንዲ እንግሊዝን “በመጨረሻ ባዶህን ትወጣታለህ!” ማለቱን አንርሳ፡፡
“ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ አከለበት” እንዲሉ በምላሱ የሚተዳደር ሰው ውሸት ማብዛቱ ግዱ ነው፡፡ ዕውቀተ

- ቢስ መሠረቱ ለዕውነት ረሃብ ያጋልጠዋልና! “አፈኛ ሴት፤ የአምስት ዳኛ ሚስት ነኝ፤ ትላለች” የሚለው

የወላይታ ተረት ኢላማ ይሆናል!!
መልካም የመስቀል በዓል!

Read 4699 times