Saturday, 27 September 2014 08:55

እንዋሻለን! እናስመስላለን!

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(4 votes)

             ይህቺን ሀገርና ህዝቦቿን በቅጡ ላስተዋለ እንደ ህዝብ በርካታ በሽታዎች እንደተጣቡን ለመገንዘብ ብዙ መድከም አያስፈልገውም፡፡ ሌላውን ለሌላ ጊዜ አሳድረን ለዛሬ ሁለቱን ተያያዥ በሽታዎቻችንን እናውሳ፡፡ ውሸት እና ማስመሰል!! እንደ ህዝብ ከምንታወቅበት ምስጉን ሞራልና ስነ ምግባር ተፋተን፣ ፍጹም ሌላ እና ኢ-ተገቢ የሆነን ሰብእና ከተላበስን ጊዜያት አለፉ፡፡ ምንም እንኳን ድሆችና ችግረኞች ሆነን መኖራችን እርግጥ ቢሆንም ስነ ምግባር እና ታላቅ ሞራል የነበረን ህዝቦች ነን፡፡ ብዙ የመከራና የችግር ዘመናትን ብናሳልፍም፣ (በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በቀር) እንደ ህዝብ ራሳችንን ዝቅ ያደረግንበትና ባህላችንን ክደን ዋሾና አስመሳይ የሆንበት ጊዜ አልነበረም፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ይሄ ሁሉ ተለውጦ ታሪክ ሊሆን እየተንደረደረ ይመስላል፡፡ እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ህዝብ ነባር የሆነውን ቅቡል ስነ ምግባራችንን እየገደፍን ነው፡፡ ሞራላችንን አሽቀንጥረን ጥለናል፡፡ ህጻናት ልጆቻችንን “ውሸት ጥሩ አይደለም፤ አትዋሹ!” በማለት አንዴ ከቅዱስ መጽሐፍ እየጠቀስን፣ ሌላ ጊዜ ተረት እየተረትን ብንመክርም እኛ አዋቂዎቹ እንዋሻለን፡፡ የውሸታችን ሰንሰለት ደግሞ የተያያዘና ማብቂያ የሌለው ነው፡፡ ይህም ግለሰብን ከመዋሸትና ከመጉዳት አልፎ ሀገርን(እኛኑ) እስከ መዋሸትና መጉዳት ደርሶአል፡፡ ጥቂት ማሳያዎችን ላንሳ፡፡ አንድ መንግስታዊ በሉት የግል ድርጅት የሳምንት በሉት የዓመት እቅድ አቅዶአል፡፡ ይህንን እቅድ የሚፈጽሙ እና የሚያስፈጽሙ ሰዎች ከላይ እስከ ታች ተቀምጠዋል፡፡ በጊዜ ገደቡ መጨረሻ ሪፖርት እየቀረበ ነው፡፡

ምንአልባት ከታቀደው ውስጥ እጅግ ጥቂቱ ወይንም አብዛኛው በተለያዩ ተግዳሮቶችም በሉት በእኛ ስንፍና አልተሰራም እንበል፡፡ ሆኖም ለአለቃችን ሪፖርት ስናቀርብ ስላልተሰራው ስራ አንናገርም፡፡ እቅዱ መቶ በመቶ እንደተሰራ ነው ሪፖርት የምናደርገው፡፡ ለምን መሰላችሁ? አንድም አለቃ ሁሌም አልተሰራም የሚባል ቃል መስማት ስለማይፈልግ፤ አንድም እኛ ድክመታችንን ማመን ስለማንፈልግ ነው፡፡ እናም የአለቃችንን ግልምጫና ቁጣ ፈርተንና ሸሽተን ያልተፈጸመውን “ተፈጽሞአል!” ብለን እንዋሻለን፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የሀገራችን ኃላፊዎች “አልተሰራም” የሚባል ቃል መስማት አይፈልጉም፡፡ ግን እኮ ስራው ያልተሰራበት አሳማኝ ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ይህንን ለመስማት ትዕግስቱም ሆነ ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ ሪፖርቱ ልክ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ለማረጋገጥ መጣርማ አይሞከርም፡፡ እኛም አለመሰራቱን እና ያልተሰራበትን ምክንያት ለማቅረብ አንሞክርም፡፡

ያልተደረገውን “ተደርጎአል!”፣ ያልተፈጸመውን “ተፈጽሞአል!” በማለት ዋሽተን የአለቃችንን በጎ ምላሽና አድናቆት እናገኛለን- “ምን አስጠቆረን” በማለት፡፡ በዚህም ለችግሩ መፍትሔ በመሻት፣ እንቅፋቱን ለማስወገድ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ እንደሌለ ቆጥረን ይዘነው እንቀጥላለን፡፡ የውሸታችን ጥፋት በዚህ አይቆምም፡፡ ሰንሰለቱን ይዞ ይሰፋል፤ ያድጋል፡፡ ይህንን የውሸት ሪፖርት ከእኛ የተቀበለው አለቃም በእኛ ሪፖርት ላይ በእሱም ደረጃ ሊሰራ ሲገባው ያልተሰራውን “ተሰርቶአል፤ ተፈጽሞአል” ብሎ ጨማምሮና ዋሽቶ ለአለቃው ያቀርባል፡፡ እሱም ከአለቃው ግልምጫና ወቀሳ ለማምለጥ፡፡ ደግሞም ያውቀዋል፤ የእሱም አለቃ “አልተሰራም” የሚባል ቃል መስማት እንደማይፈልግ፡፡

የእሱም አለቃ እርግጡን ፈትሾ ለማረጋገጥ አይሞክርም፡፡ ለማን ብሎ! እንዲህ እንዲህ እያለ ውሸቱ በየመስኩና በየግለሰቡ ከዴስክ ኃላፊ ወደ ቢሮ ኃላፊ፣ ከቢሮ ኃላፊ ወደ ዳይሬክተር፣ ከዳይሬክተር ወደ ሚንስትር፣ ከሚንስትር ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ወይንም ፕሬዚዳንት ይደርሳል፡፡ በመጨረሻም ያልተሰራው ከተሰራው ጋር ተደባልቆ እና “ተሰርቶአል” በሚል ቃል ታስሮ ይታወጃል- እውነትነቱ ሳይፈተሽ፡፡ በዚህም ያልሆነው “ሆኖአል፡፡” በሚል “ሀገራችን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሳለች” ተብሎ ይነገረናል፡፡ እናም እኛው የዋሸነው ውሸት ሰፍቶና አድጎ የሀገር ሪፖርት ሆኖ ይነገረናል፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሀገር መዋቅርም ሆነ ተቋም የለንም፡፡ ይልቁንም እርግጡን ለማረጋገጥ ከመሞከር ይልቅ ሪፖርቱን አጽድቀን፣ ለፕሮፓጋንዳ እና የማይገባ ድጋፍና ጥቅም ለማግኘት እንጠቀምበታለን፡፡ ይህንን እንደ ማሳያ አነሳሁ እንጂ በየመስኩ እንዲሁ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የምንዋሸውማ ስፋቱና ጥልቀቱ ያህላል የለውም፡፡

ውሸት ተጣብቶናል፡፡ የትም ይዋሻል፡፡ “እንዲህ ተደርጎአል”፣ “እንዲህ ተፈጽሞአል”፣ “የሕዝቡ ገቢ አድጎአል”፣ “ህዝቡ ጠግቦ ማደር ችሎአል”፣ “ህዝቡ ደስታውንና ድጋፉን ገለጸ”፣ “ይሄን ማሳካት ተቻለ”… ሌላም ሌላም በጥልቀት ያልተፈተሸ በርካታ ሪፖርት!! እነዚህ ሁሉ ዜናዎች ገና ቀደም ከታች ሲነሱ ሞራላችንን በማጣታችን ኃላፊነት ሳይሰማን ቀርቶና “ተዉ” ባይ ጠፍቶ ያደጉ እና የሰፉ ናቸው፡፡ እናም የመጨረሻው አካል ጋ ደርሰው ተመልሰው ለራሳችን ይነገሩናል፡፡ እውነታው ሌላ ሪፖርቱ ሌላ፡፡ ኑሮአችን ሌላ “ሆናችኋል!” የሚሉን ሌላ፡፡ ውሸታችን የሚያመጣብንን ክስረትና ጥፋት ልብ ባንለውም እንደግለሰብ ያመጣውን ጉዳት ትተን እንደ ሀገር እያከሰረን ነው፡፡ ውሸት! ያም ሆኖ የጎረበጠን አይመስልም፡፡ አዙሪቱ ተመችቶናል፡፡ እውነቱን ደፍረን በመጋፈጥ የተሻለ ቀንን ከመፍጠር ይልቅ እዚያው እንሽከረከራለን፡፡ ሀገርን ያህል ህዝብን ያህል ክቡር ነገር መዋሸት አልጎረበጠንም፡፡ ለምን መሰላችሁ? እውነቱን መድፈር ስላቃተን ሳይሆን ስለማንፈልግ ነው፡፡ ወደ ሁለተኛው በሽታችን እንለፍ፡፡ ማስመሰል!! ይህንንም ማመን ባንፈልግም እንደ ህዝብ እጅጉን አስመሳዮች ነን፡፡ ያልሆነውን፣ የማንወደውን፣ የማናደርገውን መስለን እንታያለን፡፡ እስቲ በርካታ ባለስልጣናትን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የተለያዩ ሙያ ባለቤቶችን… ተመልከቱ፡፡ በአደባባይ የሚናገሩትና ከጀርባ የሚፈጽሙት ፍጹም የተለያየ ነው፡፡ ሚስቱን የሚበድለውና የሚደበድበው ባል፤ ስለ ሴቶች መብት ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት ትሰማላችሁ፡፡

በመንግስት(በህዝብ) ንብረት ራሱን እና ዘመድ ወዳጁን ሠርክ የሚጠቅመው ባለስልጣን ስለ “ኪራይ ሰብሳቢነት” ጉዳት ይሰብካችኋል፡፡ ብሔሩን በመብራት እየፈለገ ከጎኑ የሚያሰልፈው ሰው ስለ ጎጠኝነት የሀገር ነቀርሳነት እና ስለ አንድነት ታላቅነት ሲሰብከን ቅንጣት ማመንታት አይታይበትም፡፡ የመንግስትን ድክመቶች አንድ ሁለት እያለ የሚቆጥርላችሁ ተቃዋሚ፣ ራሱ እዚያው ውስጥ የሚዳክር ነው፡፡ ሙስናን የሚፈጽምና ግብርን የሚያጭበረብር ባለሀብት ስለሙስና ጉዳትና ስለግብር ተገቢነት ሲደሰኩር ትሰማላችሁ፡፡ ባለጉዳዮቹን የሚያመናጭቅና የማያከብር ባለስልጣን ስለመልካም አስተዳደር አስፈላጊነት ያወራላችኋል፡፡ ያልሆነውን ሆነን ህዝብን እናታልላለን፡፡ እኛ ግን ፍጹም ያንን አይደለንም፡፡ በርካታ ማስመሰሎቻችንን ማንሳት ይቻላል፡፡ ስለ ትምህርት ጥራት ተገቢነት ጠበቆች ሆነን ብንሞግትም በተማሪዎቻችን እድሜ ላይ የምንቀልደውና ኃላፊነታችንን በቅጡ የማንወጣው እኛው ነን፡፡ ስለ እናቶችና ህጻናት ሞት፣ በገጠር ህክምና አጥተው ስለሚሞቱ ዜጎች ወዘተ ብዙ እንደሰኩራለን፡፡ ሆኖም ግን እዚያ ሄደን በሙያችን ለማገዝና መከራውን ለማቃለል ፈቃደኞች አይደለንም፡፡ ተቆርቋሪ መስለን ስንቀርብ ግን ተወዳዳሪ የለንም፡፡ የማንፈጽመውን የምናወራው ወይም የምናወራውን የማንፈጽመው ለምን መሰላችሁ? ስንዋሽና ስናስመስል ነው እንጂ ለጉዳዩ ጭራሽ ግድ የለንም፡፡

ሆኖም ያልሆነውን ነን ብለን ክብርና ሞገስ ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ከዚያም ኃላፊነቱን ተረክበን ዘመቻውን እንመራለን፡፡ መንግስትን ወይንም አንድን እንቅስቃሴ ወክለን ግድ ስለማይሰጠን ነገር ተቆርቋሪና ጠበቃ ሆነን እንሞግታለን፡፡ አስመሳዮች ነን! እንደግለሰብ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ያለን ማስመሰልማ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ምንም ግድ የማይሰጠንና ትዝ ብሎን እንኳን የማያውቀውን ሰው ስናገኘው ያለብን ማስመሰል ልክ የለውም፡፡ እጅጉን እንደናፈቀን፣ ብዙ ስናስበው እንደነበረ … እንነግረዋለን፡፡ ሰው ስናይና ብቻችንን ስንሆን ለየቅል ነን፡፡ ምን እንዳስገደደን ባናውቅም (ይሄ ይሉኝታ አይደለም) ማስመሰላችን ልክና ወሰን አጥቶአል፡፡ይህ ህዝብ እንደ ህዝብ ታላቅና አኩሪ ባህል በዚህም ውስጥ ክቡር የሆነ ሞራልና ስነ ምግባር የነበረው ህዝብ ነው፡፡ “እውነቱን ተናግሮ የመሸበት የሚያድር”፣ የሆነውን “ሆኖአል” ያልሆነውን “አልሆነም” የሚል ህዝብ ነበር፡፡ ምንም ያህል ቢቸገርና ቢያጣም ሞራሉን አሽቀንጥሮ የጣለበትና የወረደበት ጊዜ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ያ ሰብእናው አለ ብሎ ማለት ራስን ከማታለል ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ፍጹም ወርደናል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ብቻ የቆመ አይደለም፡፡ ሀገርንና ህዝብን የጎዳ በሽታ፣ ጽኑዕ ሰንኮፍ ሆኖአል፡፡ ህልውናችን ላይ የተጋረጠ አደጋ! የጥቂት ግለሰቦች ሞራልና ስነ ምግባር ማጣት የሀገርን ጉዞ ላያደናቅፍ ይችላል፡፡ እንደ ህዝብ ይህንን ታላቅ እሴት ማጣት ግን ባይመስለንም ጉዳቱ ታላቅ ነው፡፡ በሂደት ሀገርን ያጠፋል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው?! መልካም ሰንበት!!

Read 3267 times