Saturday, 27 September 2014 09:11

“ገላጋይ መስሎ አጥቂ”

Written by  ሌሊሳ
Rate this item
(0 votes)

ባህላዊው ዘረ-መል

ስለ ሥልጣን በቅርብ ጊዜያት ሳሰላስል ለራሴ የገባኝን እነሆ:-
ለምሳሌ በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ዳኛው ግጥሚያው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በጨዋታውም ላይ ሆነ በተጫዋቾቹ

ላይ ያሻውን የማድረግ ስልጣን አለው፡፡ ግን ስልጣኑ የመነጨው አጨዋወቱን ለመዳኘት የላቀ ብቃት ስላለው

ነው፡፡ ፍትሐዊ ዳኛ ብቃቱን ተጠቅሞ፣ ዘጠና ደቂቃዋ ላይ አዛዥ ናዛዥ ይሆናል፡፡ ፍትሐዊ ዳኛ በእግር ኳሱ

እውነታ ላይ በህግ መሰረት ጨዋታው እንዲካሄድ ማድረግ ያስቻለ ነው፡፡ ከዳኛው በላይ ስልጣን ያለው

የጨዋታው ህግ ነው፡፡ ህጉ የስልጣን ምንጩ ነው፡፡
በዚያው አካሄድ፣ ማህበረሰቡን ወይንም ህዝቡን በህይወት ጨዋታው ላይ የሚያስተዳድረው መንግስት ስልጣንን

ይቆናጠጣል፡፡ ስልጣኑ በህዝቡ ህይወት ላይ ፈላጭ ቆራጭ ቢያደርገውም … የመፍለጥና የመቁረጥ አቅሙ

የመነጨበት የበላይ ህግ መኖሩ የግድ ነው፡፡ ልክ እንደ እግርኳሱ ህግ የመሰለ የሚመራበት የበላይ መተዳደሪያ

ያስፈልገዋል፡፡ ይህን የበላይ መተዳደሪያ ህገ መንግስት ብለው ይጠሩታል፡፡ ግን እስቲ ስለ እውነት እንነጋገር

ከተባለ… በእኛ ተጨባጭ  ሀገራዊ ሁኔታ ከህገ መንግስት በላይ ህገ - ባህል የበለጠ መተዳደሪያ አይመስላችሁም?
ባህል በህዝብ ላይ በተለይም እንደኔ አይነቱ ግለሰብ ላይ ከመንግስትም ሆነ ከህገ መንግስት በላይ ስልጣን

አለው፡፡ በእኛ አገር መሪ በሚያስተዳድረው ህዝብ ላይ መኖር የሚችለው… በባህላዊ ህጉ “ጉልበት” የሚመለክ

እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ባህሉ ነው የስልጣን ምንጭ… ለባህሉ አጥብቆ የተገዛ ዜጋ ሁሉ የስልጣኑ ተጠቃሚ

ነው፡፡ ባህሉ እንዳልኩት “የጉልበትን ርትዕ” የሚቀበል ከሆነ… ጉልበት ያለው የሚያደርሰው ጉዳት ካለ… ጉዳቱ

እንደ አሉታዊ የህግ ጥሰት ሳይሆን እንደ “ቆራጥነት” ወይንም “ቆፍጣናነት” ተወስዶ “አሜን” ይባልለታል፡፡
ስለዚህ፤ መንግስት ህገ መንግስቱን ተከተለ አልተከተለ የሚያወዛግበን አይደለም፡፡ ህገ-ባህሉን ግን መከተል

ችሏል ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ ባይችልም እድሜ ኖሮት ባልዘለቀ፡፡
የባህላችንን አቅም በየምንኖርበት ቀዬ እውነትነቱ ይታየናል፡፡ ለምሳሌ፡- በህገ መንግስቱ ላይ “ጎረቤቶችህን እና

የመንደርህን ሰዎች ጠዋት እና ማታ ስታገኛቸው… “እንደምን አደራችሁ… እንዴት አመሻችሁ”… ማለት

ይጠበቅብሀል” የሚል የስነ-ምግባር አንቀፅ ሰፍሮ አይገኝም፡፡
ባይሰፍርም እኔ ግን አውቃለሁ… ለጎረቤቶቼ የእግዜርን ሰላምታ ሳላቆራርጥ ማቅረብ ካልቻልኩ… እንደምጠላ፡፡

እንደምገለል፡፡ መጥላት እና ማግለል የስልጣን ማሳያ ነው፡፡ እኔ የፈለገ በምክንያታዊነት የማምን ግለሰብ ነኝ

ብልም… የእኔን ግለሰብ ልዕልና ማህበረሰቡ ሊቀጣ ይችላል እንጂ እኔ በተገላቢጦሽ የመቅጣት አቅም የለኝም፡፡

እኔ ብንቃቸው እነሱ አይነኩም… እነሱ ቢንቁኝ ግን እኔ እጎዳለሁ፡፡
የህዝብ ባህል ወይም የትውፊት ዘረ-መል ከአንዳች ሀሳብ የመነጨ መሆኑ አያጠራጥረኝም፡፡ ሀሳቡን ርዕዮተ

ዓለም ብለን መጥራት እንችላለን፡፡ ርዕዮተ አለሙ ኢትዮጵያዊ አመለካከትን፣ አስተሳሰብን፣ አኗኗርን… ወደ ባህል

እና ዘልማድ ህግ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ እንደ አሻራ ውሎ ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራል፡፡ ህገ - መንግስት

ሳይሆን ህገ - ህዝብ ይሆናል፡፡ በወረቀት ላይ የሰፈረው ህግ ሰም፣ በውስጣዊ ማንነት ላይ የታተመው ህግ ወርቅ

ሆኖ … ወርቁ ሰሙን እየፈተነ እና እያቀለጠ ይዘልቃል፡፡
ይኼ የባህላዊ ህጉ ዘረ መል ከሃይማኖት የመነጨ ነው ብዬ ለመደምደም አልደፍርም፡፡ የተለያዩ ሀይማኖቶች

ውስጥ አንድ አይነት ኢትዮጵያዊነት ቀለም ባልተገነባ ነበርና ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የምዕራባዊያንን ባህላዊ ዘረ መል

ወይንም የርዕዮተ አለማቸውን ማዕከል “ምክንያታዊነት” ብዬ ልጠራው እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊ ባህልን

በምዕራባዊያን መለዋወጥ ሙሉ ለሙሉ የሚያቅተን የእኛ ባህል እንደነእርሱ በምክንያታዊነት መሀከለኛ ስበት

የተፀነሰ ባለመሆኑ ነው፡፡
ባለመሆኑም፤ የራስን ትተን የእነሱን ለመቀበል በሞከርንበት ጊዜ ሁሉ ስልጣን እናጣለን፡፡ ስልጣን በራሳችን

የባህል ህግ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ህጉ ደግሞ በእያንዳንዳችን ውስጥ የእድገት ዘመናችንን ያህል በውስጣችን

ሲነቀስ ኖሯል፡፡ አዲስ ንቅሳት የድሮውን አያጠራም፡፡ ምናልባት ሁለቱንም አደብዝዞ ግራ ያጋባቸው ይሆናል

እንጂ፡፡
ሰሎሞን ዴሬሳ፡- “እንዴት አደርክስ የስራ ፈት ጥያቄ አይዶል፤ ሀኪም ካልሆኑ በቀር፡፡ ደርሶ ጤና ይስጥልኝ

ማለትስ ይታዘዝ ይመስል…” ይላል፤ በእሽቅድድም” “የልጅነት” ግጥም መድብሉ መግቢያ ላይ፡፡ በምክንያታዊነት

ከተመለከትነው በእርግጥም “እንዴት አደርክ” የስራ ፈት ጥያቄ ነው፡፡ ባህላዊ ዘረ መላችን ግን በምክንያታዊነት

አይደለም የሚያስበው፡፡ የእኛነታችን መገለጫ ምክንያታዊነታችን ባለመሆኑ “እንዴት አደርክ” ሀኪም

ላልሆንነውም… ለህክምና ባለሞያዎች ብቻ የተፈቀደውን ጥያቄ (ያለቦታው) ስንጠያየቅ እንድንኖር አድርጎናል፡፡

ማድረጉንም ከጉድለት አልቆጠርነውም፡፡ ደግሞ አይደለም፡፡
በምክንያታዊነት መመልከት… ለምእራባውያኖቹ ሳይንስን እንደ ባህል ሰጥቷቸዋል፡፡ በምክንያታዊነት

ባለመመልከት ለአበሾች ደግሞ ቅኔን እንደ ባህል አግኝተዋል፡፡ ቅኔ በሳይንስ ሊሰራ አይችልም፡፡ ሳይንስም በቅኔ

እንደዚሁ፡፡
ምክንያቱም አንደኛው (ሳይንስ) ምክንያታዊ ተፈጥሮው፣ የተደበቀውን ነገር መግለፅ፣ መተንተን ሲሆን  ሌላው

(ቅኔ) ደግሞ ግልፁን መደበቅ ነው ስሪቱ፡፡ ህገ-መንግስታችን ወይም መንግስታችን ራሱ ከሳይንሳዊ

ምክንያታዊነት የተመሰረተ ቢሆን እንኳን፣ ለባህላዊ አብሮነታችን (social compact) ፈተና ነው የሚሆንብን፡፡

ባህላዊ አብሮነታችን በሳይንሳዊ ምክንያታዊነት የመነጨ ዘረ-መል፣ ሲቀጥልም ርዕዮት አለም የለውም፡፡

ከሳይንሳዊነት ይልቅ ሃይማኖታዊነት ለማንነታችን ይቀርበናል፡፡ በሃይማኖታዊ ማንነት ወደ ሳይንሳዊ ገነት

(ልማታዊነት) ለመግባት አይቻልም፡፡ እስካሁንም ሳንገባ የቆየንበት ምክንያቱ ይሄ ነው፡፡ ወደፊት ከገባንም…

አገባባችን የሰም እና ወርቅ ፍቺ ያሻዋል፡፡
ቶማስ ሆብስን ወይንም ዣን ዣክ ሩሶን በምክንያታዊ አንደበት ብናነበንብም… ልባችን እና ተግባራችን ግን

በባህላዊው ዘረ-መላችን ስልጣን ስር የተቀፈደደ ነው፡፡ ባህላዊው ማንነታችን ራሱ ከቅኔ የታነፁ ቶማስ ሆብስ

እና ሩሶ አሉት፡፡ ማንም ሲመጣ የማይለውጠው፡፡
ቅርፅ ይዘትን አይለውጥም፡፡ ተጫዋች ወይንም ዳኛ ቢለዋወጥ የእግር ኳስ ጨዋታ ይዘት አይለወጥም፡፡ የኢትዮ

ቴሌኮም ሞባይል እና ኢንተርኔት አገልግሎት የኢትዮጵያዊ ባህላዊ ዘረ-መልን ይዘት አይቀይርም፡፡ ህገ-መንግስት

መሻሻል ካለበት፣ ባህላችንን መስሎ ካልሆነ ለመሰረታዊው ይዘታችን አይረባውም፡፡ ፕሮፌሰሩ በሬዲዮ ላይ

ቀርበው፤ “የስልጣን ፍላጎት የጉልበት ፍላጎታችንን/ የመጨቆን ፍላጎታችንን የማርኪያ መንገድ ነው” ብለው

እንደተናገሩት ነው ነገሩ፡፡ መጨቆን መፈለግ፣ ባህላዊ ይዘታችን ከሆነ ጭቆናንን መቀበልም በዚያው ሳንቲም ላይ

የሚገኝ የግልባጭ ገፅታ መሆኑን ማመን ይገባናል፡፡ አመንንም አላመንንም አንዳንድ ነገሮች እውነት ናቸው፡፡
ይህ ከላይ ያሰፈርኩት ፅሁፍም ለእኔ እውነቴ ነው፡፡ የግለሰብ እውነቴ፡፡ የግለሰብ እውነት ለባህላዊው እውነት

ጠላቱ ነው፡፡ የፕፌሰሩ እውነት ለማህበረሰቡ ንቀት ተብሎ እንደተተረጎመው ማለቴ ነው፡፡ እና እኔም የፃፍኩት

የግለሰብ እይታዬን ቢሆንም ከማህበረሰብ እይታ ጋር እንዳይጋጭ ሰም እና ወርቅ አቀራረብ ተጠቅሜአለሁ፡፡

አቀራረቡን ምናልባት ከኢትዮጵያዊነት ዘረ መል ያገኘሁት ሳይሆን አይቀርም፡፡ መቀየር እፈልጋለሁ ብል እንኳን

“አበሻ አበሽነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም” በሚለው ህገ መንግስት ላይ ባልሰፈረ ህግ ታስሬአለሁ፡፡

ዥንጉርጉርነቱ ላይ ነው ቁምነገሩ ያለው፡፡ ዥንጉርጉርነቱ ነው ደጋፊው ከተቃዋሚው በተጨባጭ አይሎ

በሚገኝበት ሁኔታ ኢህአዴግ እንቅልፍ እንዳይተኛ ያደረገው፡፡ ዥንጉርጉርነቱ ነው ህዝብን በአፉ ግለሰብነቱን፣

በተግባሩ ግን ማህበረሰባዊነቱን እንዲንከባከብ ያደረገው፡፡ ዥንጉርጉርነቱ ነው የገላጋይ ማሊያ አስለብሶ የአጥቂ

ጨዋታ የሚያጫውተው፡፡ ዥንጉርጉርነቱ ነው ቅኔው፡፡ ምናልባትም ዥንጉርጉርነቱ ነው የባህላዊ ዘረ መሉ

እውነተኛ ማንነት!!  

Read 2733 times